>

የካባ ድረባ  እና የካፖርት ፖለቲካው... (ታምሩ ገዳ)

የካባ ድረባ  እና የካፖርት ፖለቲካው…

ታምሩ ገዳ

የአገራችን ፖለቲካ  እንደ አለማችን የከባቢ አየር  ሙቀት መጨመር(global warming) ሁሉ በቀላሉ ቅድመ ግምት ሊሰጠው ከማይቻልበት  ደረጃ  ለመድረሱ  የአደባባይ  ምስጢር ሆኗል።
በአንድ ወቅት ” ከእኛ በላይ  ስለ ኢትዮጵያ መናገር ፣ለአሳር ነው፣ ኢትዮጵያዊነት ለእኛ ከማር፣ከሱስ በላይ ነው፣ እመኑን ኢትዮጵያን እኛ ብቻ ነን አሻጋሪዎቿ ያሉን ሹማምንቶች ባለተጠበቀ ፍጥነት ከመንደር ፖለቲካ ውስጥ ሲሸጎጡ ስንመለከት ብዙዎችን  መደናገጣችን፣ማዘናችን አይቀርም።
በአንድ ወቅት  አንዱን ብሔርን ከሰማይ  ጥግ  ያሳቀሉ፣ሌላኛውን ያንኳሰሱ ወይም ከመፈጠሩን የዘነጉ ፣በሺህ የሚቆጠር ዜጋን ያስለቀሱ  ሹማምንት ተብዮዎች  ሀጢያታቸውን መናዘዝ ፣በጠባቧ ክፍል ሆነው በህግ ተጠያቂ መሆን  ሲገባቸው  “የእለቱ የክብር እንግዳ ” ተብለው እጅግ ውድ የሆነ ካባ ተደርቦላቸው፣ በቀይ ምንጣፍ ላይ  ሲንጎራደዱ በቴሌቭዥን መስኮት የተመለከቱ የአራዳ ልጆች ” የዘንድሮ ካባ ምንኛ ረከሰ፣ አቶ አገሌ  እንኳን ደረበው ደም  አያፋሰሰ” የሚል ቅኝት ተቀኝተው አንብቤያለሁ።እኔም በበኩሌ “እማማ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ  የሞተልሽ ቀርቶ… ” ማለቴ አይቀርም ።
የዚህ የካባ እና ካፖርት ደረባ ፖለቲካ  ጉዳይ ሲነሳ  አንድ ቀልድ አዋቂ  የቀድሞው  ሚኒሰተር በአዲስ አበባው ጊዮን ሆቴል  ውስጥ  በአንድ ወቅት በተካሄደ ስብሰባ ላይ ያካፈሉን ገጠመኛቸው ዛሬም ትዝ ይለኛል።ቦታው በምስራቅ ኢትዮጵያ  ውስጥ ነበር። እንደዛሬው ሁሉ በርካታ አታራማሾች፣ ካባ  ደርቡልን ባዮች ፣ካፖርት ደራቢዎች  የበዙበት ወቅት  ነበር።
ችግሩን ለመቅረፍ በስፍራው  የተገኙት  የቀድሞው ባለስልጣኑ  ቀኑን ሙሉ ቢዳክሩ ችግሩን ሊፈቱት ፣ተጠያቂዎችን አንጥረው ማውጣት እንዳልቻሉ የተረዱ የአካባቢው ሽማግሌዎች ጠጋ ብለው”መዳፈር ካልሆነብን ይህንን ችግር እርሶ ሊቀርፉት ስለ ማይችሉ እስቲ ጉዳዩን ለእኛ ይተውት እና እርሶ ወደ ሆቴሎት ሄደው ይረፉ።ውጤቱን በሁዋላ እናሳውቆታለን”በማለት ጥያቄ አቀረቡ።
የቀድሞው  ባለስልጣኑም ውጤት አልባ መሆናቸውን በመረዳት ወደ ሆቴላቸው በመመለስ  አጭር እረፍት በማድረግ ላይ ሳሉ  የአገር ሽማግሌዎቹ አስጠሯቸው እና ችግሩ እልባት መገኘቱ ተነገራቸው።
በሁኔታው የተገረሙት ባለስልጣኑም”እንዴት ብታከናውኑ ነው በአጭር ጊዜ እልባት ያገኛችሁት ?”ሲሉ ጠየቁ ።የአገር ሽማግሌዎችም “እገሌ ይህንን ግድፈት ሰርተሃል ውጣ!፣እገሌ እሰራለሁ ብለሀን  ጉራህን  ነፍተህብን ባለመስራትህ ውጣ!  እያልን ካባ እና  ካፖርት ለባሾችን በሙሉ  አንገዋለል ናቸው”ሱሉ መለሱ። ሚኒስትሩም  የአገር ሽማግሌዎችን በማድነቅ ተሞክሯቸውን  በመግለጽ ” ዛሬም ቢሆን የዚህች አገር ዋንኛ ችግሮች   ካባ እና ካፖርት ደራቢዎች ናቸው “ማለታቸው በወቅቱ ታዳሚውን  በሙሉ  ፈገግ ማድረጋቸው  ትዝ ይለኛል።
ጎበዝ ነገሩ ታሪክ እራሱን ደገመ እንዳይሆንብን ካባ ደራቢዎች ሆናችሁ ፣ካባ አስደራቢዎች የምንተፍረትን(ሼምነትን) ጣጣን ከቀደሙ ጓዶቻችሁ አወዳደቅ  ትንሽ ተማሩ።የያኔዎቹ የአገር ሽማግሌዎች  በጥቂቱም ቢሆን ዛሬም አይጠፉም።
Filed in: Amharic