>

የአጎት ለቅሶ...!!! (ልደቱ አያሌው)

የአጎት ለቅሶ…!!!

ልደቱ አያሌው 

♦ [ አርቲስት ሃጫሉ በተገደለ በሶስተኛው ቀን (ወደ አዲስ አበባ መንገዱ ከመከፈቱ በፊት) የፌደራል ፖሊስ የእኔን ደህንነት በተመለከተ አስጊ የሆነ መረጃ ደርሶኛል በማለት ቤቴ ድረስ ፖሊሶች በመላክ ወደ አዲስ አበባ ታጅቤ እንድገባ አደረገ ]
የዚህን መፅሃፍ ረቂቅ ፅፌ ጨርሼ ወደ ማተሚያ ቤት ለማስገባት በዝግጅት ላይ እያለሁ ከአንድ አጎቴ፣ አንድ ምሽት ላይ የስልክ ጥሪ ደረሰኝ፡፡ ይህንን የስልክ ጥሪ ላለፉት ሁለት ወራት ከነበርኩበት የስሜት ውጣ-ውረድ ጋር ተዛማጅ ሆኖ ስላገኘሁት በቀላሉ ልረሳው አልቻልኩም፡፡ ስለ አጎቴ የስልክ ጥሪ ይዘት ከማውራቴ በፊት በቅድሚያ ባለፉት ወራቶች ስለአጋጠሙኝ ስሜት አዋኪ ሁኔታዎች ትንሽ ለማለት ልሞክር፡፡ ²
ከአቶ ጀዋር መሐመድ ጋር በኦ.ኤም.ኤን ቴሌቪዥን ለቃለ መጠይቅ ተጋብዤ ከቀረብኩ በኋላ ከዓመት በፊት መቀሌ ሄጄ በአንድ ስብሰባ ላይ በተገኘሁበት ወቅት ሲሆን እንደታየው ከፍተኛ የአሉባልታ ዘመቻ ተከፈተብኝ፡፡ በዚያ የአሉባልታ ዘመቻ ላይ ከመንግስት ባለስልጣናት ጀምሮ በርካታ ታዋቂ የሚባሉ ሰዎች ሲረባረቡብኝ አየሁ፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያምን የመሰሉ ትልቅ የሃገር ምሁርና አዛውንት ሳይቀሩ በእኔና ጀዋር ላይ መንግስት ሰይፉን እንዲመዝብን በአደባባይ ሲመክሩ ሰማሁ፡፡ አንዳንድ ማንነታቸው የማይታወቁ ሰዎችም በስልኬ ላይ እየደወሉ እንደሚገሉኝ ሲዝቱብኝ ሰነበቱ፡፡ አንዳንድ ከእኔ ጋር ከረዥም ጊዜ ጀምሮ የቢዝነስ ግንኙነት የነበራቸው ሰዎችም ማንነቱን የማያውቁት ሰው ስልክ እየደወለ ከእኔ ጋር ስላላቸው ግንኙነት እንደጠየቃቸው ነገሩኝ፡፡
የኖቤል ሽልማት ተሸላሚው ዶ/ር ዐቢይም ከመስከረም 30፣ 2013 በኋላ መንግንስት እንደማይኖር የደነገገው ህገ-መንግስቱ መሆኑንና ኮሮና ቫይረስ ወደ ሃገራችን ከመግባቱ በፊት – “ከመስከረም 30፣ 2013 በኋላ በሃገራችን ህጋዊ መንግስት ስለማይኖር የምርጫው ቀን በፍፁም አይተላለፍም” በማለት ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ እንዳልነበር፣ “ከመስከረም 30 በኋላ መንግስት አይኖርም በማለት ሃገር በሚበጠብጡ ሰዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ እየተዘጋጀን ነው” በማለት መግለጫ ሰጡ፡፡
ይህ በተባለ ማግስት ማንነታቸውን የማላውቃቸው ሰዎች ጠዋት ከቤቴ ስወጣ ጀምሮ በሶስት መኪናዎች ውስጥ ሆነው ይከታተሉኝ ጀመር፡፡ ጉዳዩን ለመንግስት የደህንነት ባለስልጣናትና ለመገናኛ ብዙሃን አሳውቄ ይፋ ከሆነ በኋላ የሚከታተሉኝ መኪኖች ከዕይታዬ ተሰወሩ፡፡ በወቅቱ በእኔ በኩል የነበረኝ ጥርጣሬ እንዲህ አይነት ክትትል ሊያደርግብኝ የሚችለው “መንግስት ነው” የሚል ቢሆንም በመንግስት በኩል ግን “እጄ የለበትም” የሚል ማስተባበያ ተሰጠኝ፡፡ የተሰጠኝን ማስተባበያ ለጊዜው አምኜ በመቀበል ነገር ግን ይከታተሉኝ የነበሩትን መኪኖች ታርጋ ቁጥር ለደህንነት ባለስልጣናት በመስጠት ጉዳዩ እንዲጣራልኝ ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ ላቀረብኩት ጥያቄ ግን እስካሁን ድረስ የተሰጠኝ ምንም አይነት ማብራሪያም ሆነ መልስ የለም፡፡
በመኪና ክትትል በተደረገብኝ ሰሞን ከውጪ ወደ ሃገር ውስጥ በሚተላለፍ አንድ መገናኛ ብዙሃን የሻዕቢያ ነፍሰ-ገዳይ ስኳዶች አዲስ አበባ እንደገቡና ሊገድሉ ካሰቧቸው ሰዎች ውስጥም አንዱ እኔ ልሆን እንደምችል ፍንጭ የሚሰጥ መረጃ መናገራቸውን ሰማሁ፡፡ ከአቶ ጀዋር መሐመድ ጋር አንድ ላይ በመታየቴ ምክንያት ያን ያህል የስም ማጥፋት ዘመቻ በእኔ ላይ በመካሄዱም ሆነ የማላውቃቸው ሰዎች በእኔ ላይ ክትትል ማድረጋቸው ድርጊቱ ቢያሳዝነኝም ያን ያህል ግን አላስደነቀኝም፡፡ የስም ማጥፋቱን ዘመቻ ቢያንስ ለ17 ዓመት ያህል፣ የመኪና ክትትሉን ደግሞ ለተከታታይ 120 ቀናት ያህል ለምጄዋለሁና፡፡ እኔን አብዝቶ ያስደነቀኝ ብቻ ሳይሆን ያስደነገጠኝ ግን፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት በመላ ሃገሪቱ ስለ ለውጥ፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ አንድነትና ሰላም ሲሰበክ ከከረመም በኋላ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ እንጂ ወደፊት ለመራመድ አለመሞከሩ ነበር፡፡ ___________________________
² ፅሁፌን በዚህ የግል ጉዳይ መቋጨት ያስፈለገኝ የሃገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታና መጣ የተባለው “ለውጥ” በተግባር ምን እንደሚመስል ጥሩ ማሳያ ይሆናል ብዬ ስላመንኩ ነው፡፡
ይህ ሁኔታ – “እንዲህ እያደር ጥሬ በሚሆነው የሃገራችን ፖለቲካ ውስጥ መቀጠል የምችለው እስከመቼ ነው?” የሚል ያልተለመደ እና የማልወደውን ጥያቄ በአዕምሮዬ ውስጥ አብዝቶ እንዲመላለስ አደረገ፡፡ ለዚህ ትግል ጉልበቴን፣ ጊዜዬን፣ ገንዘቤን፣ ዕውቀቴን፣ አካሌን፣ በአጠቃላይም የ28 ዓመታት የወጣትነት ህይወቴን ያለስስት ገበርኩለት፡፡ ውጤቱ ግን እንኳንስ ለሃገርና ለህዝብ ሊተርፍ ለራሴም መብትና ህልውና ዋስትና የሚያሳጣኝ ሆነ፡፡
ኦ.ኤም.ኤን ላይ እኔና ጀዋር መሐመድ ቃለ-መጠይቅ በመስጠታችን ሰፊ ዘመቻ በእኔ ላይ የተከፈተው በቃለ-መጠይቁ ወቅት የተናገርኩት የተሳሳተ ወይም ተቺዎችን የሚያስከፋ ንግግር ተገኝቶ አይደም፡፡ ይልቁንም የአብዛኛዎቹ ዘመቻ አድራጊዎች ትችት – “ልደቱ እንዴት ‘ነፍሰ-ገዳይ’ ከሆነው ከጀዋር መሐመድ ጋር አንድ ላይ ይቀርባል” የሚል ነበር፡፡ የሚገርመው እንዲህ በማለት ዘመቻ የከፈቱብኝ አብዛኛዎቹ ሰዎች ትናንት ከመሬት ተነስተው እኔንም በነፍሰ-ገዳይነት ሲወነጅሉኝ የነበሩት የኢሳት እና የግንቦት 7 ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ግብዝ አሉባልተኞች “እንዴት ከነፍሰ-ገዳይ ጋር አብረህ ትቀመጣለህ” በማለት ከትናንት የራሳቸው ክስ እኔን ነፃ ሲያወጡኝ ስሰማ ምን ያህል በጭፍን ጥላቻ ታውረው እንዲህ አይነቱን የሃሳብ ቅራኔ እንኳን ለመገንዘብ እንደተሳናቸው በማወቅ አዘንኩላቸው፡፡ እነዚህ የእኔ የፖለቲካ ባላንጣዎች በሃገሪቱ ፖለቲካ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆነው ከአቶ ጀዋር ጋር መወያየቴን እንደ ወንጀል ቆጥረው በእኔ ላይ ዘመቻ መክፈታቸው መቼም ቢሆን የማያድግ የፖለቲካ ስብዕና ያላቸው መሆኑን ዳግም ከማረጋገጥ ያለፈ ትርጉም አልሰጠኝም፡፡
ይልቁንስ እኔን ያስገረመኝ አንዳንድ የእኔ ጠንካራ ደጋፊ ሆነው የኖሩ ሰዎች ጭምር በእኔና በአቶ ጀዋር መገናኘት ሲደናገጡ በማየቴ ነበር፡፡ አንድነት ተኮር የሆነው የፖለቲካ ኃይል ለአቶ ጀዋር ምን ያህል የመረረ ጥላቻ እንዳለው የማውቅ ቢሆንም – በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከሚያገባው ከማንኛውም ሰው ጋር ለመወያየት ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ የሌለኝ መሆኑን፣ ሰዎች ቢጠሉትም ቢወዱትም ያመንኩበትን ከመናገር ወይም ከመፈፀም ወደኋላ እንደማልል፣ የሃገራችን የፖለቲካ ችግር መፈታት ያለበት በውይይትና በድርድር ሂደት ብቻ ነው የሚል ፅኑ አቋም ያለኝ መሆኑን፣ እነዚህን የፖለቲካ መርሆዎቼን ዳግም ለድርድር የማላቀርብ ሰው እንደሆንኩ ቢያንስ ከ1997 ምርጫ ጀምሮ ደጋግመው በተግባር ሲያዩ የኖሩ አንዳንድ አድናቂዎቼ እንዲህ ዓይነት ብዥታ ውስጥ ድንገት ገብተው ሳገኛቸው ትንሽ የሞራል ስብራት ተሰማኝ፡፡ እናም አንዳንድ ጥያቄዎች አዕምሮዬ ውስጥ መመላለስ ጀመሩ፡፡
ፈጣሪ በሰጠኝ ነፃ አዕምሮዬ አስቤ የደረስኩበትን የራሴን ነፃ አስተሳሰብ በማራመዴ ሰዎች ለምን የአሉባልታ ዘመቻ አጀንዳቸው ያደርጉኛል? የፖለቲካ ባላንጣዎቼ ‘ራስህን መሆን ትተህ እኛን ምሰል’ በማለት በእኔ ላይ የሚያካሄዱትን ዘመቻ የሚያቆሙት መቼ ነው? በእኔነቴ እንዲወዱኝ ወይም እንዲጠሉኝ ሳይሆን በእኔነቴ እንዲያውቁኝ ለማድረግስ ከዚህ በላይ በስንት ተጨማሪ የአሉባልታ ዘመቻ ውስጥ ማለፍ አለብኝ? እስካሁን በማስታወሻዬ ላይ ከመዘገብኳቸው ከ10 ደርዘን ያላነሱ በእኔ ላይ ከተወሩ የፈጠራ አሉባልታዎች በላይስ ስንት ተጨማሪ አሉባልታዎችን ወደፊት መመዝገብ አለብኝ? የሚወራብኝን አሉባልታ ለማስተባበል እስካሁን ካደረግሁት በላይ ስንት ቃለ-መጠይቅ መስጠት፣ ስንት መጣጥፍና መፅሃፍት መፃፍና በስንት ተጨማሪ የትግል ዓመታት ማለፍስ አለብኝ? እነዚህን ጥያቄዎች ደጋግሜ ብጠይቅም የረባ መልስ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ መልስ ያለው ‘ድንጋይ ጣይም’ የት እንዳለም አላውቅም፡፡
የመኪና ክትትል እንደተደረገብኝ ከተሰማ በኋላ ከመቼውም ጊዜ በላይ በባሰ መጠን በቅርብም በሩቅም የሚገኙ ወዳጅ ዘመዶች የደህንነቴ ጉዳይ አብዝቶ ስላሳሰባቸው ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ገቡ፡፡ “ምነው ከሰው ባልተፈጠርኩ” ብዬ እስክመኝና እስክማረር ድረስ ለጊዜው ከሃገሩም ሆነ ከትግሉ ገለል እንድል ሲነዘንዙኝ ከረሙ፡፡ እስካሁን ሳላገባና ልጅ ሳልወልድ የኖርኩት ከዚህ ዓይነቱ ቤተሰባዊ ጫና እና ተፅዕኖ ለመዳን ብዬ
ቢሆንም የፈራሁትን ነገር ላመልጠው ግን አልቻልኩም፡፡ ለዚህን ያህል ዓመት በእኔ ጉዳይ ወዳጆቼ፣ ጓደኞቼና ቤተሰቦቼ እንዲህ በመረረ ስቃይ ውስጥ መኖራቸው ከወትሮው በተለየ ከፍተኛ የጥፋተኝነት ስሜት ውስጥ አስገባኝና ለእነሱ ከልቤ አዘንኩ፡፡ ስልክ ሲደውሉልኝም አንስቼ ለማውራት ተሳቀቅሁ፡፡
በዚህ አይነት ጫና ውስጥ እያለሁ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ በድንገት ተገደለ፡፡ እሱ በተገደለ ማግስትም በመላው ኦሮሚያ እና አዲስ አበባ ከፍተኛ ብጥብጥ ተፈጠረ፡፡ በዚያ ወቅት የነበርኩት ቢሾፍቱ በሚገኘው መኖሪያ ቤቴ ስለነበርና በቢሾፍቱ ከተማም ተመሳሳይ ብጥብጥ በመፈጠሩ ወደ አዲስ አበባ መሄድ አልቻልኩም፡፡ በዚህ ምክንያት ወዳጅ ዘመዶች የበለጠ ጭንቀት ውስጥ ገቡ፡፡ በአርቲስቱ ድንገተኛ ሞት የተበሳጩ፣ ወይም ለራሳቸው የፖለቲካ አጀንዳ መጠቀሚያ ሊያደርጉት የሚፈልጉ ኃይሎች አጋጣሚውን ተጠቅመው ሊገሉት ይችላሉ የሚል ከፍተኛ ስጋት አደረባቸው፡፡ በእርግጥም ይህ የወዳጅ ዘመዶች ስጋት ምክንያታዊ የሆነና እኔም የምጋራው ስጋት ነበር፡፡
አርቲስት ሃጫሉ በተገደለ በሶስተኛው ቀን (ወደ አዲስ አበባ መንገዱ ከመከፈቱ በፊት) የፌደራል ፖሊስ የእኔን ደህንነት በተመለከተ አስጊ የሆነ መረጃ ደርሶኛል በማለት ቤቴ ድረስ ፖሊሶች በመላክ ወደ አዲስ አበባ ታጅቤ እንድገባ አደረገ፡፡ ነገር ግን በወቅቱ የፌደራል ፖሊሶች ቤቴ ድረስ መጥተው ሲወስዱኝ በትዕዛዝ አሰጣጥ ወይም በትዕዛዝ አቀባበል ስህተት ምክንያት ይመስለኛል እጄን በካቴና አስረውና ሰፈሬ ውስጥ ከፍተኛ ግርግር ፈጥረው ስለነበርና ይህንንም የአካባቢው ሰው ያይ ስለነበር “ልደቱ ታሰረ” ተብሎ በሰፊው ተወራ፡፡ እኔም ዝርዝሩ ውስጥ ሳልገባ ያልታሰርኩ መሆኔን ብቻ ለአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ገለፅኩ፡፡
በወቅቱ ፌደራል ፖሊስ ስለ ደህንነቴ የራሴን ጥንቃቄ እንዳደርግ በጥብቅ አሳስቦኝ ስለነበር ሁኔታዎች እስኪረጋጉ ድረስ አዲስ አበባ ከመቆየት ይሻላል ብዬ በማሰብ ወደ ላሊበላ ለመሄድ ወሰንኩ፡፡ በወቅቱ ከኮቪድ 19 ስርጭት ጋር በተያያዘ ቱሪስቶች መምጣት ስላቆሙ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ላሊበላ የሚያደርገውን በረራ አቁሞ ስለነበር ከአዲስ አበባ ባህር-ዳር በአውሮፕላን ሄጄ ከዚያም ከባህር-ዳር ወደ ላሊበላ በመኪና መሄድ ነበረብኝ፡፡ ባህር-ዳር ደርሼ የማርፍበት ሆቴል በገባሁ ግማሽ ሰዐት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የደህንነት ሰዎች ያረፍኩበት ሆቴል ድረስ መጥተው ከእኔ ደህንነት ጋር በተያያዘ አንዳንድ አሳሳቢ ጉዳዮች ስላሉ እኔ ወዳለሁበት ክፍል ሰዎች እንዳይገቡ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስበውና ችግር ካለ እንዲደወልላቸው ለሆቴሉ እንግዳ ተቀባይ ኃላፊ ስልክ ቁጥር ትተው መሄዳቸውን የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ ክፍሌ ድረስ መጥቶ ነገረኝ፡፡ እኔም ከክፍሌ ሳልወጣ እዚያው አምሽቼ እዚያው አደርኩ፡፡
ጠዋት 12፡00 ሰዐት ላይ ከእንቅልፌ ተነስቼ መጋረጃ ስከፍት አንድ መሳሪያ የታጠቀ ሰው የመኝታ ክፍሌ አካባቢ ተቀምጦ ሲጠብቀኝ እንዳደረ አየሁ፡፡ ከቁርስ በኋላ ወደ ላሊበላ ጉዞ ለመጀመር ሻንጣዬን ወደ መኪና እየጫንኩ እያለ የእንግዳ ተቀባይ ክፍል ኃላፊው ወደኔ ሲመጣ አየሁት፡፡ ቀረብ አለኝና – “ጋሽ ልደቱ ከደህንነት ቢሮ አሁን ደውለው፣ አቶ ልደቱ ለጉዞው አጃቢ የሚፈልግ ከሆነ ጠይቀውና ደውልልኝ ብለውኝ ነበር” አለኝ፡፡ እኔም ዛሬ ወደ ላሊበላ እንደምጓዝ እንዴት ሊያውቁ እንደቻሉ ገርሞኝ – “ስለ ትብብራችሁ ከልብ አመሰግናለሁ፣ አጃቢ ግን አያስፈልገኝም በላቸው” አልኩትና ተሰናብቼው መኪና ውስጥ ገባሁ፡፡ ከሆቴሉ ግቢ ስወጣ ዙሪያ ገባውን እያየሁ ራሴን አንድ ጥያቄ ጠየቅኩ፡፡ “ለደህንነቴ በሚጨነቅ አካል ጥበቃ ውስጥ ነኝ? ወይስ ሊያጠቁኝ በሚፈልጉ ሰዎች ክትትል ስር?”፤ በዚህ በቀላሉ መልስ የማላገኝነት ጥያቄ መባዘኔን አቁሜ ጉዞዬን ከጠዋቱ 2፡00 ሰዐት አካባቢ በአንድ ጓደኛዬ መኪና ከባህር ዳር ጀምሬ ከግማሽ ቀን ጉዞ በኋላ ላሊበላ በሰላም ገባሁ፡፡
ላሊበላ ሆኜ በተረጋጋ መንፈስ በዙሪያዬ እያንዣበበ ስላለው አደጋ ለማሰላሰል ስሞክር የወቅቱ የሃገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታ ለእኔ አይነት ሰው እጅግ አስጊና አሳሳቢ ሆኖ ታየኝ፡፡ ከወዳጄ ከኢንጂነር ስመኘው ሞት ጀምሮ እስከ ቅርቡ የአርቲስት ሃጫሉ ሞት ድረስ እየሆኑ ያሉትን ክስተቶች ገጣጥሜ ለማየት ስሞክር የሆነ አይነት ስውር እጅ (Invisible hand) እያመሰን እንደሆነ ተሰማኝ፡፡ በዚህ ሁሉ የህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ሳልፍ አሟሟትን እንጂ ሞትን ፈርቼው አላውቅም፡፡ የምፈራው አጉል አሟሟት በዙሪያዬ እንዣንበበ እንደሆነ ተሰማኝና ስጋት ቢጤ አደረብኝ፡፡ ማለትም – መንግስት ብቻ ሳይሆን በማንኛውም የማይታወቅ የፖለቲካ ኃይል፤ አምኜበት በምታገልለት ዓላማ ምክንያት ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያነት ሲባል ህይወቴን በድንገት ላጣ እንደምችል ገመትኩ፡፡ “በእንዲህ አይነት ሁኔታ ደመ-ከልብ ሆኜ መሞት አለብኝ?” በማለትም ራሴን ደጋግሜ ጠየቅኩ፡፡ ለራስ ሳይሆን ለሌሎች አጀንዳ ማስፈፀሚያ ሆኖ መሞትም ድርብ ሞት ሆኖ ተሰማኝ፡፡
እዚያው ላሊበላ እያለሁ “ልደቱ ታስሯል” የሚል ወሬ እንደገና በመገናኛ ብዙሃን ሳይቀር በሰፊው ናኘ፡፡ አሁንም ወዳጅ ዘመዶቼ ከባድ ጭንቀት ውስጥ ገቡ፡፡ አንዳንዶቹ ስልኬ ላይ ደውለው እያነጋገሩኝ እያለም በስልክ እያዋራኋቸው ያለሁት እኔ መሆኔን ጭምር እስከመጠራጠር ደረሱ፡፡ የሚሰሙት ድምፅ የኔ መሆኑን የተጠራጠሩ አንዳንድ ጓደኞቼም በሌሎች ጓደኞቼ ስልክ እየደወሉ አግኝተው አዋሩኝ፡፡ በዚህ ወቅት በመግቢያዬ ላይ እንደገለፅኩት ከአንድ አጎቴ የስልክ ጥሪ ደረሰኝ፡፡
ይህ አጎቴ ዕድሜው ከ65 ዓመት በላይ የሆነ፣ የራሱ የፖለቲካ የህይወት ተሞክሮ ያለውና የሃገሪቱን ፖለቲካም በቅርበት የሚከታተል ሰው ነው፡፡ ነገር ግን በእኔ የፖለቲካ ተሳትፎ ገና ከጅምሩ ደስተኛ ስላልነበረ ከፖለቲካ ትግሉ ራሴን እንዳርቅ ብዙ ጊዜ ሲጨቀጭቀኝ ኖሯል፡፡ አልሳካለት ሲል ግን ተስፋ ቆርጦ ትቶኛል፡፡ በዚህም ምክንያት ምናልባት ላለፉት ዘጠኝ ወይም አስር ዓመታት እኔና አጎቴ ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ምንም ነገር አውርተን አናውቅም፡፡
በዚያ ምሽት አጎቴ ደውሎልኝ ሰላምታ ከተቀያየርን በኋላ “ታስሯል” መባሌን ሰምቶ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ እንደደወለልኝ ነገረኝ፡፡ ከዚያም ቀጠለና- “ታዬ ቦጋለ የሚባለው ሰው የማያውቀውን የአባትህን ስም እየጠራ ያካሄደብህን የስም ማጥፋት ዘመቻ ሰማኸው?” አለኝ የንዴት ስሜት በተጫነው ድምፀት፡፡
“እኔ አልሰማሁትም፤ ሰዎች ግን ነግረውኛል” አልኩት፡፡
አጎቴ ስለ ፖለቲካ ከኔ ጋር ማውራት ካቆመ ከብዙ ዓመታት በኋላ ይህ ጉዳይ ለምን ስሜቱን ሊነካው እንደቻለ ለማወቅ ስለፈለግሁ – “ስለ አባቴ ምን አለ?” አልኩት፡፡
አጎቴ ለዚህ ጥያቄ ምንም አይነት መልስ ሊሰጠኝ ሳይሞክር- “ይህ የተግማማ ፖለቲካ ውስጥ መኖር አይበቃህም? አንተ ግን በኢትዮጵያ ተስፋ የምትቆርጠው መቼ ነው?” አለኝ፡፡
እኔም ያለኝን ነገር ሰምቼ እንዳልሰማሁ ዝም አልኩት፡፡  ያ- እጅግ መንፈሰ ጠንካራ መሆኑን የማውቀው አጎቴ ስልኩን እንደያዘ ተንሰቅስቆ ሲያለቅስ ሰማሁት፡፡ እኔም ዝም እንዳልኩ የሲቃ ለቅሶውን ለደቂቃ ያህል አዳመጥኩትና ምንም ተጨማሪ ነገር ሳናወራ ስልኩ ተዘጋ፡፡ ስልኩን የዘጋው እሱ ይሁን እኔ በውል አላስታውስም፡፡
ከአጎቴ ጋር እንደዚያ በስልክ ያወራሁት መኝታ ቤት ውስጥ አንደኛውን የግድግዳ ማዕዘን ተደግፌ ቆሜ ነበር፡፡ የተዘጋውን ስልክ ከጆሮዬ ሳላነሳው፣ ከቆምኩበትም ቦታ ሳልንቀሳቀስ ደንዝዤ ለተወሰነ ጊዜ ቆየሁ፡፡ ምናልባት ከ15 ደቂቃዎች በኋላ ሊሆን ይችላል ከድንዛዜዬ ነቃሁና አልጋዬ ጠርዝ ላይ ቁጭ ብዬ በረዥሙ ተነፈስኩ፡፡ የአጎቴ ሁኔታ ስሜቴን አብዝቶ ስለረበሸው ስልኩ ሲደወልልኝ ያቋረጥኩትን የፅሁፍ ስራ ከዚያ በኋላ መቀጠል አልቻልኩም፡፡ የተለመደው የመኝታ ሰዐቴ ገና ያልደረሰ ቢሆንም ያለወትሮዬ ቀድሜ ለመተኛት አልጋዬ ውስጥ ገባሁ፡፡
ያ-  የአጎቴ የስልክ ንግግር ሙሉ ሌሊት እንቅልፍ ነስቶኝ አደረ፡፡ “አንተ ግን በኢትዮጵያ ተስፋ የምትቆርጠው መቼ ነው?” የሚለውን የአጎቴን ጥያቄና የሲቃ ለቅሶ ጆሮዬ ላይ መስማት ማቆም አልቻልኩም፡፡ ከስልክ ጥሪው ማግስት በነበሩት ቀናቶች ሁሉ፤ እየበላሁም፣ ከሰዎች ጋር እያወራሁም፣ እያነበብኩም፣ እየፃፍኩም ሆነ ሌላ ስራ በምሰራበት ወቅት የአጎቴ ድምፅ ከቁጥጥሬ ውጪ ደጋግሞ ጆሮዬ ላይ እየጮኸ በጠበጠኝ፡፡ የአጎቴን ጥያቄ በቀላሉ መመለስ አልቻልኩም፡፡ ግን መቼ ነው እኔ በኢትዮጵያ ተስፋ የምቆርጠው?
ከእኔ በላይ ስለ እኔ ደህንነት ለዚህ ሁሉ ዓመታት በስጋትና በጭንቀት ነፍሳችሁ ስትሰቃይ የኖራችሁ፣ በእኔ ጉዳይ መጨነቅና መቸገርን ሰልችታችሁ የማታውቁ፣ ስማችሁን ዘርዝሬና ውለታችሁን ቆጥሬ ልጨርሰው የማልችል ወዳጆቼ፣ ጓደኞቼና ዘመዶቼ በሙሉ፤ በዋጋ ለማይተመነውና በእኔ አቅም ሊከፈል ለማይችለው ውለታችሁ በትህትና ጎንበስ ብዬ አመሰግናለሁ፡፡ ስቃያችሁ መቋጫ የሌለው እንዲሆን በማድረግም አብዝቼ በድያችኋለሁና ይቅር በሉኝ።
ምንጭ:- ህብር ራድዮ
Filed in: Amharic