>
5:13 pm - Wednesday April 20, 5188

የኢያሪኮ መንገደኛ...!!! (በዲያቆን ብርሃኑ አድማስ)፤   

የኢያሪኮ መንገደኛ…!!!

(በዲያቆን ብርሃኑ አድማስ)፤   

    አቤቱ በእኔ በኵል እለፍ…!     
  ጌታዬ ሆይ አቤቱ በአዲስ ዘመን ዋዜማ በአጠገቤ እለፍና አንሣኝ፡፡ ዘይትና ወይን ባልካቸው የመሥዋዕት ደምህ ቁስሌን ጥረግልኝ፡፡ ጨርቅ በተባለ ፍቅርህም ግጥም አድረገህ እሰርለኝና ከጥላቻ፣ ከከንቱነት፣ ከግብዝነት፣ ከለፍላፊነት፣ ከኩራትና ከትዕቢት፣ ከዝሙትና ከርኩሰት ቁስሌ ማገገምን ስጠኝ፡፡ በአገልጋይህ በኩል ስበህ የእንግዶች ማደሪያ ወዳልካት ቤትህ አስጠጋኝ፡፡ ጌታዬ ሆይ እባክህን ለእኔ ለምስኪኑ ዛሬም ዲናርህን ክፈልልኝ፤ አቤቱ ሁለቱ ዲናሮችህ በተባሉ በብሉይና በሐዲስ እጅግ የደከመች ቁስለኛ ነፍሴን መግበህ አድንልኝ፡፡ የነፍሴ እረኛ ሆይ በአንተ ዘንድ ዝለት መሰልቸት የለምና የእኔ መቅበዝበዝ አይተህ ቸል አትበለኝ፤ ጠባቂዬ ሆይ በኃጢአቴ ምክንያት ካገኘኝ ደዌ ሥጋ ደዌ ነፈስ ፈውሰህ ሰው አድርገህ አቁመኝ፡፡
ስለእኔ የእሾህ አክሊል የደፋኸው ጌታ ሆይ የአንተ ራስ ስለእኔ ተወግቷልና ኅሊናዬን ከሚወጋኝ የሀሳብና የኃጢአት እሾህ አድነኝ፡፡ በውኑ አንተ ለእኛ ብለህ ካልሆነ በከንቱ ተወግተሃልን? ስለዚህ ጌታ ሆይ ቤተ መቅደስ ውስጥ ቆሜ እየጸለይኩ እያስቀደስኩ ሳይቀር እሾህ ነገር እያሰወጋ ከሚያቆስለኝ ክፉ ሀሳብ ስለደፋህልኝ የእሾህ አክሊል ብለህ እኔን አድን፡፡ አቤቴ እረኛዬ ሆይ በዘመነ ሥጋዌህ ኃጢአትህ ተተወልህ፣ ኃጢአትሽ ተተወልሽ እንዳልካቸው ኃጢአትህ ተትቶልሃል የሚለውን ድምጽህን አዲሱ ዘመን ከመግባቱ በፊት አሰማኝ፡፡ የልጆችን ለውሾች መስጠት አይገባም እንዳልካት ሴት  ፈውስ ባይገባኝ እንኳ  ጌታ ሆይ ውሾችም ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ ስትለህ እምነቷን አይተህ እንደፈወስክላት እኔንም በእምነት ፍጹማን ከሆኑት የተረፈውን የፈውስ ፍርፋሪ አቅምሰኝ፡፡ ቤዛዬ ሆይ ስለእኔ ተገርፈሃልና በመገረፍህ ቁስል ፈውሰኝ፡፡ በሙሴ ፊት ብርሃን በሳልከበት በአንተ ፊት ላይ አይሁድ የረከሰ ምራቃቸውን ሲተፉብህ የተጋሰከው ቤዛዬ ሆይ ዛሬም እኔ በየቀኑ በአንተ ፍጡር ላይ የምተፋውን አይተህ አላጠፋኸኝም፣ ነገር ግን ርኩሱን ምራቅ በብርሃናዊ ፊትህ ላይ ስለመቀበልህ እኔን ከርኩሰቴ አንጻኝ፡፡
አንተ ስለእኛ ስለሁላችን ተከሰህ በጲላጦስ ፊትህ ቀርበህልናልና አቤቱ ጌታ ሆይ እኛ ስለኃጢአታችን አንከሰስ አንወቀስ፤ በአንተ መከሰስ እኛ እንፈወስ እንጂ፡፡ ጌታ ሆይ ስለአንተ መንገላታታ የምእመናን መንገላታት ይበቃ፡፡ ስለአንተ መናቅ እኛ በድነቁርናና ባለማሰብ፤ ባለማቀድና ባለመሥራት የገጠመን መናቅና መገፋት በአዲሱ ዐመት ይከልከልልን፡፡ ጌታ ሆይ ስለእኛ መስቀል ተሸክመህ ሦስት ጊዜ ወድቀሃልና፣ በግል በሠራነው ኃጢአት ከወደቅንበት ውድቀት፣ እንደተቋምም ተሰነካክለን ከወደቅንበት አዘቅት፣ የአባቶችን ገድልና ትሩፋት ይዘን ስለወደቅንበትም ታሪካዊ ውደቀት የአንተ መውደቅ ቤዛ ሆኖን እንነሣ፤ አቤቱ አንሣን፣ ቀጥ አድርገህም አቁመን፡፡ ተነሣ አልጋህን ተሸክመህ ተመላለስ እንዳልከው፤ ተነሡ ወንጌል እውነት ይዛችሁ፣ የተኛችሁበትን የታሪክ፣ የገድልና የፍቅር አልጋ ይዛችሁ በአገልግሎት ተመላለሱ ብለህ በኃጢአትና በድከመት የሰለሉ እግሮቻችንን አጽና፡፡ ጌታ ሆይ ስለእኛ ተቸንከረሃልና ከተቸነከርንባቸው የጎሰኝነት፣ የድንቁርና የጥቅመኝነትና የአድሎ ችንካሮች አልላቀን፡፡ አቤቱ ጌታ ሆይ ስለእኛ የሆምጣጤውን መራራ ጽዋ ቀምሰሃልና  በምትኩ ከፍቅርና ከይቅርታ፣ ከዕወቀትና ከምሕረት ጽዋ እኛን አቅምሰን፡፡ ሳይገባህ ስለእኛ ተገንዘህ ተቀብረሃልና አቤቱ ከድንዛዜ መግነዝ ፍታን፣ ከጥልቅ የድንቁርና መቃብርም አውጣን፡፡ ስለ ልዩ ትንሣኤህ ትንሣኤ ልቡና ወኅሊና አድለን፡፡ ስለ ቅድስት ዕረገትህም ዕርገተ ኅሊናና አልዕሎ ልቡናን አሳድርብን፡፡ ስለ ዳግም ምጽአትህም በቀኝህ የሚቆሙ ወዳጆችህ የሚሠሩትን ምግባረ ሃይማኖት ለመሥራት አብቃን፡፡
ጌታ ሆይ በዚህች በዿግሜ ኢዮብን በዮርዳኖስ ወንዘህ አጥበህ እንደፈወስነው እኛን ኢትዮጵያውያንን ከሚያጸይፍ ቁስለ ነፍሳችን ፈውሰን፡፡ እጠበን እንጠራለን፤ አንጻንም እንነጻለን፡፡ ጌታ ሆይ ስለእኛ አይደለም መምጣትህን አስቀድመው ይነግሩ ዘንድ ስለነገርሃቸው አርእሰተ አበውና ነቢያት፣ መርጠህ አስተምረህ ሾመህ ዐለምን ወደአንተ ይመልሱ ዘንድ መስቀል መከራ ሞትን አሸክመህ ስለላክሃቸው ሐዋርያት፣ ኑፋቄ ዘርቶ መንጋውን ከአንተ ለመለየት የተጋውን የዲያብሎስን ሽንገላ ተቃውመው ሃይማኖትን በንጽህ ስለጠበቁ ሊቃውንት፣ ፍትወታትን ድል ነሥተው በተጋድሏቸው ያለደም መፍሰስ ሰማዕትነትን ስለተቀበሉ ጻድቃን፣ የነገሥታትን ማስፈራራትና የሚያደርሱባቸውን መከራ ሳይሰቀቁ ነገሥታተ አሕዛብን ድል ስለነሡ ሰማዕታት፣ በንጽሕ እና በትጋት ሆነው ያለመታከት አንተን ስለሚያገለግሉ ሊቃነ መላእከትና ሠራዊተ መላእክት ብለህ ይልቁንም ደግሞ ከሁሉም በላይ ስለሆነች ከእርሷ ሰው ትሆን ዘንድ ስለመርጥካት የንጽሕና መሠረት የባሕርየ አዳም መመኪያ ስለሆነች ስለንጽሕተ ንጹሐን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል እናትህ ብለህ ጌታ ሆይ በወደቅሁበት አዘቅት እለፍና እኔን ምስኪኑን ቁስለኛ የዲያብሎስ ምርኮኛ ከወደቅሁበት አንሣኝ፤ በሚቀጥለው ዐመትና በመጪዎቹ ዘመናትም አንተን በመከተል ሕግህን በመጠበቅና ፈቃድህን በመፈጸም አንሣኝ፡፡ ለፈቃዴ አሳልፈህ አትሰጠኝ፣ ይልቁንም ለፈቃድህ የምገዛበትን ልቡና ሥጠኝ፡፡ አቤቱ አትተወኝ አትጣለኝም፣ አሜን፡፡
Filed in: Amharic