>

ሹም ማቅበጥ፤ ሹም መፍራት፤ ሹም ማባለግ፤ ከዛ ደግሞ ማልቀስ...?!? (ያሬድ ሀይለማርያም)

ሹም ማቅበጥ፤ ሹም መፍራት፤ ሹም ማባለግ፤ ከዛ ደግሞ ማልቀስ…?!?

ያሬድ ሀይለማርያም

ሹም ማቅበጥ፣ ማሞሰን፣ ማባለግ፣ ሕዝብ አናት ላይ ወጥተው ፊጢጥ እንዲሉ፣ ከሕግ እና ከሀገር በላይ እራሳቸውን እንዲቆጥሩ እና ቶሎ እንዲታበዩ ማድረግ፣ ትክክለኛውን መስመር ማሳት እናውቅበታለን። የኢትዬጲያ ሕዝብ በዚህ ሁሉ የረዥም ዘመን ታሪኩ ከተሳኑት ነገሮች አንዱ ሥልጣንን መግራትና ማረቅ ነው። ሥልጣንን እና ባለሥልጣናትን መግራት አልቻልንም። በተቃራኒው ባለሥልጣናትን የማባለግ ችሎታችን እና ሥልጣን የፈለጉትን የማድረጊያ መሣሪያ እንዲሆን ሁኔታዎችን የማመቻቸት አቅማችን የሚደንቅ ነው።
ከዛ ደግሞ የሚደንቀው ያባለጋቸውን፣ ያሞሰናቸውን፣ ያቀበጥናቸውን እና አናታችን ላይ ፊጢጥ እንዲሉ የፈቀድንላቸውን ሹሞች እጅግ መፍራታችን ነው። ሕዝባችን ባለሥልጣናት ቋንጃውን ቢቆርጡት፣ አገሩን ቢነጥቁት፣ ከቅዬው ቢነቅሉት፣ ንብረቱን ቢዘርፋት፣ ልጆቹን ቢነጥቁት አዮ ጉድ፣ አዮ ጉድ እያለ እንባውን ወደሰማይ እየረጨ ከፈረደበት ከፈጣሪው ጋር ‘ወይ ፍረድ ወይ ውረድ ‘ የሚል ሙግት ይገጥማል እንጂ ቶሎ ወደ ሹሞቹ ፉቱን አያዞርም። አይጠይቅም፣ አይሟገትም። በሆዱ ሁሉን ችሎ፣ ችሎ በዘመናት አንዴ ያመቀው ብሶት ሲፈነዳ እንደ ሱናሜ ሁሉንም ይጠራርግና አዳዲስ ሹመኛች ተቀብሎ በዛው በለመደው መንገድ እነሱንም ያባልጋል፣ ያሞስናል፣ ያቀብጣል፣ ይፈራል። ብዙም ሳይቆይ ወደ እዬዬው ይገባል።
አዮ ጉድ አዮ ይላል ያገሬ ሰው
ትዝብቱ ታምቆ ሆዱን ሲያላውሰው።
ይቺ ግጥም ማህበረሰባችንን በደንብ ትገልጸዋለች። በዚህ ሁለት አመት ካባ ያልተደረበለት፣ ጃኖ ትከሻው ላይ ጣል ያልተደረከለት፣ ወርቅ አንገቱ ላይ ያልተጠለቀለት፣ ቲሸርት ያልተለበሰለት፣ ሲሾም እልል ያልተባለለት፣ ለፍሬ ፈርስኪ ንግግሩ ሁሉ ያልተጨበጨበለት ከካድሬ እስከ ትልቅ ሹም ብንቆጥር ብዙ አናገኝም። ታዲያ በጉልበት ሥልጣን ላይ የመጡትን አርቀን ከአናታችን በላይ የሰቀልናቸውን ሹሞች ማውረድ እያቃተን የሹሞች ምርኮኛ ሆነን ዘመናትን አስቆጠርን። ሹሞቹ ይቀያየራሉ እንጂ የእኛ የምርኮኝነት ኑሮ ሳይቀየር ዘመን ተቀብለን፣ ዘመን እየሸኘን እንዳለን አለን።
የኢትዬጲያ ሕዝብ ያልሾማቸውን ሹምች ለምን እንደሚያቀብጥ አይገባኝም።  ይህ ለረዥም ጊዜ አብሮን የቆየ እና ክፉኛ የተጠናወተን የማስመሰል፣ የአድረ ባይነት ባሕሪ ሥልጣን ከሕግ ልጓም ውጭ እንዲወጣ እና ባለሥልጣናትም ቶሎ መረን እንዲወጡ ያደርጋል።
ትላንት በገንቦ ማር እና ቅቤ አየሞሉ ተንበርክከው መብታቸው ለመጠየቅ፣ ብሶታቸው ለመናገር ደጅ ይጠኑ የነበሩ ቀደምቶቻችን ታሪክ ዛሬም እንደጥላ እየተከተለን ነው። ሠልጥነናል ብንልም ገና የሥልጣን ባለቤት አልሆንም። የሥልጣን ባለቤት ያልሆነ ሕዝብ ከሥልጣኔ እሩቅ መሆኑንም የገባን አልመሰለኝም። ሥልጣኔ የሚጀምረው ሥልጣንን ከመግራት እንጂ ሌላው አለም አምጦ የፈጠረው ቴክኖሎጂ ከመጠቀም አይደለም። ሌላው አለም የሥልጣኔ ማማ ላይ ለመውጣት የመጀመሪያ እርምጃው ሥልጣንን መግራት ነበር። የእንግሊዙን የማግና ካርታ ታሪክ ልብ ይለዋል። ምእራባዊያን ሥልጣንን መግራት ተስኗቸው ቢሆን ኖሮ ዘመናቸውን ሁሉ እንደኛ በጨለማ ውስጥ ሲደናበሩ ይኖሩ ነበር። እኛም ሞባይል እና ሌሎች የቴክኖሎጂ ትሩፋቶችን እንኳን ሊኖረን በአይናችን የማየት እድል አይኖረንም ነበር።
እና ባጭሩ ያልመረጥናቸውን ካድሬና ተሻሚዎች ካባና ጃኖ እያለበስን ከምናቀብጥ እና ከምናሞስን ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት የሚሆንበትን፣ ያሻውን በምርጫ የሚሾምበትን፣ ያልወደደውን የሚሽርበትን መንግሥታዊ ሥርዓት ለመፍጠር ብንረባረብና እና የሚከፈለውን ዋጋ ብንከፍል እራሳችንንም፤ ቀጣዩ ትውልድንም ነጻ እናወጣለን።። ከዚያ መልስ ያለው እዳው ገብስ ነው።
ቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic