>
5:13 pm - Wednesday April 19, 4851

የቀዳማይ ወያኔ ታሪክና  ሊላይ ኃይለ ማርያም እያስተጋባው ያለው የፈጠራ ታሪክ ሲፈተሽ [ክፍል ፪] (አቻምየለህ ታምሩ)

የቀዳማይ ወያኔ ታሪክና  ሊላይ ኃይለ ማርያም እያስተጋባው ያለው የፈጠራ ታሪክ ሲፈተሽ [ክፍል ፪]

አቻምየለህ ታምሩ

በክፍል ፩ ባቀረብሁት ጽሑፍ ሊላይ ኃይለ ማርያም  አርበኛ  አድርጎ ያቀረባቸውና  የ[ቀ]ዳማይ ወያኔ መሪ እንደሆኑ የሚነገርላቸው  አባቱ “ብላታ”  ኃይለ ማርያም ረዳ ፋሽስት ጣሊያንን አምስት ዓመታት ሙሉ ያገለገሉ ባንዳ ስለመሆናቸው፤ የትግራይ አርበኞች ጸር እንደነበሩና “ብላታ” የሚለው ማዕረግም የተሰጣቸውም በፋሽስት ጣሊያን መሆኑን አውስቻለሁ። የኢትዮጵያ አርበኞች ፋሽስትን አቧራ አስገስተው ድል ከነሱ በኋላ ደግሞ  ባንዳ ሆነው ያገለገሉበት ኀጢያታቸው ተሰርዮላቸው ፋሽስት ጣሊያን የሰጣቸው የብላታነት ማዕረግ እንዲጸላቸውና በፋሽስት ጣሊያን ዘመን የተሰጣቸው ሹመት እንዲከበርላቸው ለግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና ለልዑል ራስ ሥዩም  መንገሻ አመልክተው ጥያቄቸው ተቀባይነት በማጣቱ ኢትዮጵያ በፋሽስት ጥሊያን ነጻነቷ ሲገፈፍ፣ ክብሯ ሲደፈርና ሰንደቅ አላማዋ ሲታጠፍ ባንዳ ሆነው ፋሽስት ጣሊያንን እስመጨረሻው ሰዓት ድረስ በማገልገል ላይ ተጠምደው ያልሸፈቱት ሰው  ፋሽስት ሲባረር ጥቅማቸው ስለተነካ ኢትዮጵያ ነጻነቷን ስትቀዳጅ በአርበኞች ላይ መሸፈታቸውን ታሪካቸውን ከነምንጩ አቅርቤያለሁ።
በዚህ ክፍል  “ብላታ” ኃይለ ማርያም ረዳ ለሁለተኛ ጊዜ ሸፍተው የመሩት “ቀዳማይ ወያኔ” የሚባለው የሽፍትነት እንቅስቃሴ እንዴት እንደተፈጠረ  እውነተኛውን  ታሪክ ከምንጩ አቀርባለሁ።
የታሪኩ ዋነኛ ምንጭ የቀዳማይ ወያኔን እንቅስቃሴ ያከሸፉትና የቀዳማይ ወያኔ እንቅስቃሴ በተነሳበት ወቅት የትግራይ ጠቅላይ ግዛት የጦር አበጋዝ የነበሩት የዓድዋ ተወላጁ ጸረ ፋሽስት አርበኛ የደጃዝማች ዓባይ ካሳ ልጅ የሆኑት ኮሎኔል ቃለ ክርስቶስ ዓባይ የአባታቸውን የደጃዝማች ዓባይ ካሳን ቃል፣ የጀግናውን ጸረ ፋሽስት አርበኛና በወቅቱ የአድዋ አውራጃ አስተዳዳሪ የነበሩትን የአድዋ ተወላጁን የደጃዝማች ገብረ ሕይዎት መሸሻ ትዝታንና በቀዳማዊ ወያኔ ዘመን የወቅቱ የእንደርታ አውራጃ አሰተዳዳሪ የነበሩት የእንደርታ ተወላጁ አርበኛ የቀኛዝማች ይኩኖ አምላክ ደስታ ማስታወሻን ዋቢ በማድረግ በዋናነት ሶስቱ አርበኞች ስላከሸፉት የቀዳማይ ወያኔ እንቅስቃሴ የጻፉት የታሪክ መጽሐፍ ነው።
የመጽሐፉ ርዕስ “የ1953ቱ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራና ከ1908-1966 ዓ/ም የኢትዮጵያ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ሂደት” የሚል ሲሆን የታተመው በ1997 ዓ.ም. ነው። በነገራችን ላይ ኮሎኔል ቃለ ክርስቶስ ዓባይ በጀኔራል መንግሥቱ ነዋይ አቀናባሪነት በ1953 ዓ.ም. የተካሄደውን ስዒረ መንግሥት ከመሩት ሰዎች መካከል አንዱ ሲሆኑ ስዒረ መንግሥቱን በመምራቱ ረገድ ከንዋይ ወንድማማቾች ቀጥሎ በ4ተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጡ ናቸው። በወቅቱ ሻለቃ የነበሩት ኮሎኔል ቃለ ክርስቶስ ስዒረ መንግሥቱ ሲካሄድ የክቡር ዘበኛ መድፈኛ አዛዥ ነበሩ። በመፈንቅለ መንግሥቱ የነበራቸውን ተሳትፎ በተረኩበት  የመጸሐፋቸው ክፍል  ራስ እምሩን ጠቅላይ ሚኒስቴር፤ መርድ አዝማች አስፋው ወሰንን ደግሞ በአባታቸው ቦታ ንጉሠ ነገሥት ሆነው እንዲሾሙ  ለነ መንግሥቱ ነዋይ ሀሳቡን ያቀረቡት እሳቸው መሆናቸውን ነግረውናል።
የባንዳው የ “ብላታ” ኃይለ ማርያም ረዳ ልጅ ሊላይ ኃይለ ማርያም በፋና ቴለቭዥን ቀርቦ የባጡንና የቆጡን ሲዘባርቅ ስማቸውን ካጠፋቸው የትግራይ አርበኞች መካከል የአድዋ ተወላጆቹ  ደጃዝማች ዓባይ ካሳና ደጃዝማች ገብረ ሕይዎት መሸሻ  ዋናዎቹ ናቸው። ሊላይ የጀግኖቹን የደጃዝማች ዓባይ ካሳንና የደጃዝማች ገብረ ሕይዎት መሸሻን ስም እየደጋገመ ለማጉደፍ የሞከረው የፋሽስት ሹም የነበሩት  አባቱ “ብላታ” ኃይለ ማርያም ረዳ መሩት ያለውን የሽፍትነት እንቅስቃሴ ጸረ ፋሽስት የነበሩት ሁለቱ ጀግኖች ስላከሸፉት ነው። በነገራችን ላይ ደጃዝማች ገብረ ሕይዎት መሸሻ ማለት ሐዲስ አለማየሁ “ትዝታ” በሚል በጻፈው የጸረ ፋሽስት የተጋድሎ ዘመን ታሪኩ ውስጥ ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ  መልዕክት አስይዘው ተከዜ አፋፍ  ሰፍረው ወደነበሩት ወደ ደጃዝማች አያሌው ብሩ ሰፈር በላኩት ወቅት ድንኳን ውስጥ ከደጃዝማች አያሌው ብሩ ጎን ለጎን በተነጠፉ ድልዳሎች ላይ ተቀምጠው ያገኛቸውና  “ከትግራይ የመጡ የልዑል ራስ ሥዩም ታላቅ መኮንን” ሲል የሚገልጻፈው አርበኛ ናቸው[1]።
ሊላይ  ኃይለ ማርያም የፋሽስት ጣሊያን ሹም የነበሩት አባቱ የመሩትን የሽፍትነት እንቅስቃሴ ስላከሸፉበት በፋና ቴለቭዥን ከሁሉ በላይ አብዝቶ የዘለፋቸው የአድዋው አርበኛ ደጃዝማች ገብረ ሕይዎት መሸሻ  የሱ አባት “ብላታ” የሚል  የባንዳነት ማዕረግ ከፋሽስት አግኝተው እንደርታ በመሾም ጠላትን አምስት ዓመታት ሙሉ  እስኪያልባቸው ሲያገለግሉ ደጃዝማች ገብረ ሕይዎት መሸሻ  ግን  ገራኣልታ መሽገው  በዱር በገደሉ እየተንከራተቱ  አምስት ዓመታት ሙሉ ጠላትን በመድፍና መትረየስ ድባቅ ይመቱ ነበር[2]።
በአሁኑ ወቅት ከአዲስ አበባ ሆነው ሕወሓትን ለመጣል እየታገልን ነው የሚሉ ሰዎች እያከሄድነው ነው የሚሉትን እንቅስቃሴ “ፈንቅል” የሚል ስም ሰጥተው የፈንቅልን ታሪክ ሲያብራሩ  የሕወሓት ታጋይ የነበረው የሓየሎም አርአያ መጠሪያ እንደነበር ሲናገሩ ይሰማል። ይህ ግን ከታሪክ አኳያ የተሳሳተ ነው። ፈንቅል የሚለው ስም የጀግናው ጸረ ፋሽስት አርበኛና የቀዳማይ ወያኔን የሽፍትነት እንቅስቃሴ የደመሰሱት የደጃዝማች ገብረ ሕይዎት መሸሻ የፈረስ ስም እንጂ የቀዳማይ ወያኔ የመንፈስ ልጆች ነን ብለው ጫካ ከገቡት ዋነኞች መካከል ቀዳሚ ለሆነው ለሕወሓቱ ሓየሎም አርኣያ የወጣ ስም አይደለም። ሌላው ቀርቶ ሓየሎም አርአያ  የፈንቅል ስም ታሪካዊ  ወራሽ እንኳን  ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም  በፈረስ ስማቸው ፈንቅል በመባል የሚታወቁት  የአድዋው አርበኛ  ደጃዝማች ገብረ ሕይዎት መሸሻ የቀዳማይ ወያኔን እንቅስቃሴ ከደመሰሱት መካከል ሲሆኑ ሓየሎም አርአያ ደግሞ ጫካ የገባው ደጃዝማች ገብረ ሕይዎት መሸሻ የደመሰሱትን የቀዳማይ ወያኔን እንቅስቃሴ ወራሾት ነን ብለው  “ካላአይ ወያኔ”  ከሆኑት  “ወንበዴዎች” መካከል አንዱ በመሆኑ ነው።
ለማንኛውም በፈረስ ስማቸው ፈንቅል  በመባል ለሚታወቁትና ጠላትን አምስት ዓመታት ሙሉ በመድፍና በመትረየው ሲነቅሉ ለባጁት  ለደጃዝማች ገብረ ሕይዎት መሸሻ  ጀግንነታቸውን የሚያውቀው ተከታያቸው እንዲህ ሲል አሞግሷቸው ነበር[3]፤
ስሙ ገብረ ሕይዎት ፈረሱ ፈንቅል፣
በመድፍ በመትረየስ ጠላት የሚነቅል፤
ቀዳማይ ወያኔን ስለደመሰሱት የትግራይ አርበኞች ታሪክ ይህንን ያህል ካልሁ አሁን ቀዳማይ ወያኔ እየተባለ የሚነገርለት አመጽ እንዴት እንደተመሰረተ ታሪኩን ከምንጩ ወደማቅረቡ ልሸጋገር።
ቀዳማይ ወያኔ እንዴት ተመሰረተ?
ፋሽስት ጥሊያን በኢትዮጵያ አርበኞች ተጋድሎ በአማዲዮ ዲ አኮስታ የሚመራው ብርጌድ በአምባላጌው ጦርነት ድል ከሆነ በኋላ በአካባቢው የነበረው ሁኔታ ሌላ መልክ እየያዘ መምጣት ጀምሮ ነበር። ከተማረኩ የፋሽስት ጣሊያንና የባንዳ ወታደሮች የተገኘው የነፍስ ወከፍ የጦር መሣርያ በግዥም በዘረፋም በአካባቢው ገበሬዎች እጅ ገባ። አንዳንድ አርበኞችም የማረኩትን ቀላል የጦር መሣሪያ በርካሽ ዋጋ ቸበቸቡት። በዚያን ጊዜ በእንደርታ የዘመናዊ የነፍስ ወከፍ የጦር መሣሪያ ባለቤት መሆን የማይገኝ እድል ነበር። የእንደርታ ገበሬ ከብቱን እየሸጠ መሣሪያ መሸመት ጀመረ። ወቅቱ በተለይም በእንደርታ አውራጃ በዋጅራት ለሚኖረው ገበሬ ሰርግና ምላሽ ሆነለት[4]። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ እንዲህ ነው።
በክፍል ፩  እንዳቀረብሁት ዋጅራት አንድ ለየት ያለ መጥፎ ልማድ ነበረው። ይህም ልማዱ በየዓመቱ እየዘመተና እየወረረ የመዝረፍ ባሕሉ ነው። ይህ የመዝረፍ ባሕል የወንዶች ጉብዝና መለኪያ ተደርጎም ይቆጠር ነበር። ይህ ዘመቻ ወይንም ዘረፋ «ጋዝ» ተብሎ ይጠራል። በተጠጋጋ አባባል ዘመቻው ባሕላዊ  የወረራ ዘመቻ ሊባል ይችላል[5][6]።
እንግዲህ! ፋሽስት ጣሊያን ሲጠቀምበት የነበረውን ዘመናዊ የነፍስ ወከፍ መሣሪያ እንደልብ መታጠቅ ለጋዝ ወይንም ለወረራ ዘመቻ ምን ያህል ኃይል እንደሚሰጥና አስፈላጊ እንደሆነ መገመት ይቻላል። ዋጅራት ከአፋር ጋር ላለበት የጋዝ ዘመቻ የታጠቀው አውሮፓ ሰራሽ መሣሪያ በወረራው ብልጫ እንደሚያመጣ ዋና ጉዳይ ሆነ።[7]
የፋሽስት ጥሊያን ከኢትዮጵያ መደምሰስ እየወረረ ያሻውን ይዘርፍ ለነበረው የጋዝ ጦረኛ መንግሥት ዘረፋውን ለማስቆም የሚያደርገው አስተዳደራዊ አርምጃ አልተመቸውም ነበር። ከፋሽስት ጥሊያን ጋር በነበረው የመጨረሻው ከአሜዲዮ ዲ አኮስታ ጋር በተደረገው የአምባላጌ ጦርነት መጨረሻ ላይ የተማረከው የጦር መሳሪያ ዋጅራት በያመቱ ወደ አፋር የሚያደርገውን የጋዝ ወረራ ከበፊቱ በከረረና በተባባሰ ሁኔታ እንዲያካሂድ አድርጎታል። በወቅቱ በአንድ አመት ብቻ አይሙት ኪዶ በሚባል የወረራ አለቃ መሪነት ዋጅራት ሰባተኛ ወረራውን ወደ አፋር አካሂዷል[8]።
በአይሙት ኪዱ መሪነት የተካሄደው የጋዝ ወረራ በአፋር ላይ ባደረገው ዘረፋና ግድያ ድል እየተጎናጸፈ በመሄዱ የዘረፋው ጠቃሚነት በወራሪው በኩል ጥቅሙ እየጎላ መሄዱን  የተገነዘበው የአገሬው አቀንቃኝ  በወቅቱ እንዲህ ብሎ ሕዝቡን ቀስቅሶ ነበር [9]፤
ሶሞ አይሙት ኪዱ፣
ዝሞተ ይሙት፣
አይሙት ኪዱ፣ አይሙት ኪዱ፣
ኮርቻ እርዱ፣
ሕሩስ መንገዱ፣
ቀኝ መንገዱ ጎራ መንገዱ፤
ይህ የዘረፋ ዘፈን ትርጉሙ ወደ አማርኛ ሲመለስ እንደሚከተለው ነው፤
ከአይሙት ኪዱ ጋር ዝመት፣
የሞተው ይሙት፤
አይሙት ኪዶ፣ አይሙት ኩዶ
ኮርቻ ምሽጉ፣
መንገዱ ይታረስልህ፣
ቀኝ ይሁልህ ግራው ይቅናልህ፤
ይህ ዘፈን በሚዘፈንበት ጊዜ ጎረምሳውና ጎልማሳው የጥይት ባሩድ ለማሽተትና ሾተሉን ደም ለማቅመስ ጥማትና ወልፍ እየያዘው ስለተነሳ ዋጅራት በአፋር ላይ የሚያካሂደውን የግድያና የዝርፊያ ወረራ ከቀድሞው በበለጠ የከረረና ውጊያውንም በባሰ ሁኔታ እንዲካሄድ ሊያደርገው ችሏል። በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥት ወረራውን የፈጸሙትና በአፋር ሕዝብ ላይ ጭፍጨፋ፣ ሰለባና ዘረፋ ያካሄዱት ለሕግ እንዲቀርቡ የጠቅላይ ግዛቱ ዋና ዴሬክተር የነበሩት ደጃዝማች ክፍሌ ዳዲ ታዘዙ። ደጃዝማች ክፍሌ ዳዲም ትዕዛዙን በተዋረድ በወቅቱ የጠቅላይ ግዛቱ የጦር አበጋዝ ለነበሩት ለአድዋው ተወላጅና ለጀግናው  ጸረ ፋሽስት አርበኛ ለደጃዝማች ዓባይ ካሳ አስተላለፉ[10]።
በጦር አበጋዙ በደጃዝማች ዓባይ ካሣ የአካባቢው የአውራጃና የወረዳ ገዢዎች የአገሬውን ነጭ ለባሽ አስከትለው ከዋጅራት በሚያዋስነው አካባቢ ግንቦት ሁለትና ሶስት ቀን 1935 ዓ.ም. ተሰበሰቡ። በሌላ በኩል ደግሞ የዋጅራት ሕዝብ የጎበዝ አለቆች ሕዝቡን በየአምባው አሰልፈው ከመንግሥት ጋር ለሚያደርጉት ውጊያ ቦታ ከአስያዙ በኋላ በነደጃዝማች ዓባይ ካሳ አማካኝነት ከመንግሥት የተላከውን ልዑክ በሚያነጋግርበት ወቅት ሁለት ዘዴ ይዞ በመነሳት ግባቸውን ለመጨበጥ አቀዱ[11]፤
ሀ/ አንደኛው አነስተኛ ጉዳት በመቀበል ጉዳዩ በሰላም እንዲያልቅ በማለት ከካህናት፣ ከወንድና ከሴት ሽማግሌዎችና ባልቴቶች የተውጣጣ የጥምር የሽምግልና ቡድን ወይንም በአካባቢው አጠራር «ዱበርቲ» የሚባለውን መርጠው በማውጣት ወደ አበጋዙ ወደ ደጃዝማች ዓባይ ካሳ ለልመና ሲልኩ የጠየቁትም «ሕዝቡ ጥቂት ጀብደኞች እንዳሉ ስለሚያምን እነሱን መርጦ እስከነመሳሪያቸው ለመንግሥት እንዲያስረክብ፣ መንግሥት ደግሞ በበኩሉ አስተያየት አድርጎ ቅጣቱን እንዲያቀልላቸው» የሚል ነበር።
ለ/ ሁለተኛው የዋጅራት ዕቅድ ደግሞ የመንግሥት ባለሥልጣኖች የተላኩትን የአገር ሽማግሌዎች ልመናና ያስቀመጡትን ቅድመ ሁኔታ ባይቀበሉ ወደ አካባቢው የተላከውን የከተት ጦር ለመውጋት ጦሩን በየአምባውና በየጎበዝ አለቃው አማካኝነት ለውጊያ ማሰለፍ ነበር።
በመንግሥት ባለሥልጣኖች በኩል የተፈለገው ደግሞ የዋጅራት ጋዝ የሚለውን የወረራ ልማድ እንዲያቆምና አጥፊዎችም ለሕግ እንዲቀርቡ ስለነበረ ሕዝቡ ራሱ ለማመልከት በላካቸው ሽማግሌዎች ይህንን ለማድረግ ከጠየቀ ከዚህ የተሻለ መፍትሔ እንደሌለ በመገመት እስከነመሣሪያቸው ይዞ እንዲያስረክብ ለልመና ከመጡ ሽማግሌዎች ጋር ስምምነት ተደርጎ ለማመልከት የመጡትም ሽማግሌዎች የቁርስና የቡና ግብዣ ግራዝማች ኃይሌ ተድላ በሚባሉ ሰው ግቢ ተደርጎላቸው ሲመለሱ ለክተት በመጣው ጦር በኩልም ከእንደርታ የመጣው ብቻ አገሩ ቅርብ በመሆኑ በየሰፈረበት ሲቀር ሌላው አርሶ አደር ወደ እርሻው እንዲመለስ ተደረገ።[12]
ሁኔታው በመንግሥት ባለሥልጣናት በኩል ከልብ እንደሚከበር ታምኖበት ሳለ ቀድሞውንም የዋጅራት የጎበዝ አለቆች ጥፋተኞቹን ለፍርድ እናቀርባለን በሚል ያቀረቡት የእርቅ ሀሳብ ጊዜ መግዣ ስለነበር ከጋዝ ዘማቾች መካከል ፊታውራሪ ኪሮስ አምባዬ የሚባሉ ሽፍታ እርቁን ተቀብሎ በፋንታው ወደ አምባው ሲለመስ በነበረ ደጃዝማች አለማየሁ በሚባሉ አርበኛ ይመራ በነበረው ተመላሽ የክተት ጦር ላይ ግንቦት 11 ቀን 1935 ዓ.ም. ሙጃ የሚባል ቦታ ሲደርሱ የዋጅራት ጦር በእሪታና በጡሩምባ ጥሪ ዳር እስከዳር ተቀስቅሶ እንደ ድንገተኛ ደራሽ ጎርፍ ወደየአገሩ እየተመለሰ ባለና በመንግሥት ጥሪ ለሰላም ማስከበር በከተተ ጦር ላይ ውጊያ ከፍቶ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ማርኮ ወደተለያዩ አካባቢዎች ወስዶ በማሰር ጥፋተኞችን ለመንግሥት ላለማቅረብ ፍቃደኛ አለመሆኑን አሳየ።[13]
በዚህ ድንገት በተከፈተ ውጊያ ከመንግሥት ባለ ሥልጣናት ጋር ለእርቅ ተቀምጠው የነበሩ የሕዝብ ሽማግሌዎች ጭምር ተቀላቅለው የተፋፋመ የእጅ በእጅ ውጊያ በመደረጉ የመንግሥት አስተዳዳሪዎች፣ የጦር መሪዎችና ለክተት የተሰበሰበው ለጦርነት ያልተዘጋጀ አርሶ አደር አለቀ። ከዚህ በኋላ ዋጅራት ከመንግሥት ጋር ለመደራደር እንዲያመቸው ምርኮኞችን በእስር ይዞ በከባድ ቁጥጥር እያስጠበቀ ከአምባ ወደ አምባ እያዘዋወረ በማስቀመጥ ጥበቃውን ቀጠለ። በመቀጠልም ዋጅራት በሙሉ በየጎበዝ አለቃው ለውጊያ ተደራጅቶ በምርኮ የተወሰዱትን እነ ደጃዝማች ዓባይ ካሣና ሌሎችን የመንግሥት ምርኮኞች ለማስለቀቅ ከሚመጣው የመንግሥት ጦር ጋር ውጊያ ለመግጠም መዘጋጀት ጀመረ።[14]
ልዑል ራስ ሥዩምንና  ንጉሠ ነገሥቱን ደጅ ጠንተው የፈለጉትን ባለማግኘታቸው ቅር ተሰኝተው እንደርታ ውስጥ በግላቸው  ሸፍተው የነበሩት ባንዳው የሊላይ አባት “ብላታ” ኃይለ ማርያም ረዳ  የዋጅራትን  የጋዝ ዘመቻ ተከትሎ ለሽምግልና የተላኩትን የመንግሥት ባለሥልጣናት እነ ደጃዝማች ዓባይ ካሳን ዋጅራት የድንገቴ ጦርነት ከፍቶ መማረኩን ከሸፈቱበት ሰሙ።  በዚህ ጊዜ በሁኔታው የጎመዡት “ብላታ” ኃይለ ማርያም ረዳ ደጅ ጠንተው ያጡትን ሹመት በግርግሩ ለመንጠቅ በሸፈቱበት አካባቢ በድድባ ደርገአጀን ሸጎዳ በተባለ ሥፍራ ይኖር የነበረውን ባላገር ሰብስበው፤
– “ዐፄ ኃይለ ሥላሴ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን እምነት ከልብ የማይከተሉ ላይ ላዩን የዚች ቤተክርስቲያን ታማኝ መስለው ለሥልጣናቸው መጠናከሪያ ብቻ ሲጠቀሙባት በተዘዋዋሪ መንገድ እንድትዳከም በማድረግ ላይ የሚገኙ ናቸው”፤
– “ንጉሠ ነገሥቱ ካቶሊክ ሆነዋል፤ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የካቶሉክ ሃይማኖት ታቦት እንዲገባ አድርገዋ”፤ ወዘተ የሚል ቅስቀሳ አደረጉ፤
ከዚህ በተጨማሪ አጎዛና ቆዳ የለበሱ፣ ብረት ሰንሰለት በወገባቸው የታጠቁ አስመሳዮችንም ባሕታውያን ናቸው በማለት ካሰማሩ በኋላ  “ንጉሠ ነገሥቱ እውነተኛ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይ አይደሉም”  የሚለውን  ክሳቸውን በሕዝቡ ዘንድ እንዲስፋፋና በመንግሥት ላይ እንዲነሳሳ አደረጉ[15][16]።
በመጨረሻም  “ብላታ” ኃይለ ማርያም ያደራጁት የባላገር የጎበዝ አለቃ «አረና ሐረና» በማለት በእንጣሎ ዋጅራት ውስጥ ልዩ ስሙ ማይደርሁ በተባለ ሥፍራ ተማምሎ ሃይማኖታቸውን ቀይረዋል በተባሉት ነጉሠ ነገሥት ላይ አመጹ[ወየኑ]።  “ብላታ” ኃይለ ማርያም  በዚህ አኳኋን  ያሳመጹትን ባላገር እየመሩ “የእንደርታ ሕዝብ ወኪል ነኝ” በማለት  ጳግሜ 2 ቀን 1935 ዓ.ም. ኩያ ከተባለው ቦታ ላይ ሰፍሮ በሰላም ከተቀመጠው የጦር ሠራዊት ላይ  ሳይታሰብ አደጋ ጥለው ብዙ የጦር ሠራዊት ከማረኩ በኋላ  የጦሩ አዛዥ የነበሩትን ሜጀር ጀኔራል ኢሳያስ ገብረ ሥላሴን ማረኩ[17]። ይህ አመጽ ነው እንግዲህ “ቀዳማይ ወያኔ”  እየተባለ ሲጠራና “ብላታ” ኃይለ ማርያም ረዳ መሩት ስየተባለ ሲተረክ የኖረው።
ይቀጥላል. .
በቀጣይ ክፍል  ቀዳማይ ወያኔዎች «ንጉሠ ነገሥቱ እውነተኛ የኦሮቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይ አይደሉም» በማለት የእንደርታን ሕዝብ ለማሳመጽ ይጠቀሙበት ከነበረው ስልት በተጨማሪ የትግራይን ሕዝብ ለማሳመጽና ትግራይን ከኤርትራ ጋር አንድ አድርጎ ትግራይ ትግርኝን ለመፍጠር ይሰራ የነበረው እንግሊዝ  ያካሂደው ስለነበረው ቅስቀሳና  የቀዳማይ ወያኔን አመጽ ቀሪ ታሪክ አቀርባለሁ።
ምንጮች
[1]ሐዲስ አለማየሁ (1985). ትዝታ፣ አዲስ አበባ፣ ኩራዝ አሳታዊ ድርጅት፣ ገጽ 50-59.
[2] ተድላ ዘዮሐንስ(2004). የኢትዮጵያ ታሪክ: ኢጣሊያ በኢትዮጵያ: ክወልወል እስከ ጎንደር ግንቦት 1927-ኅዳር 1934 ዓ.ም. ፣ አዲስ አበባ፣ ማንኩሳ አሳታሚ ኃላ.የተ.የግ.ማኅበር፣ ገጽ 57-61.
[3] ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል(1961). ቼ፡ በለው፣ አዲስ አበባ፣ ንግድ ማተሚያ ቤት፣ ገጽ 84.
[4] ቃለ ክርስቶስ ዓባይ(1997).  የ1953ቱ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራና ከ1908-1966 ዓ/ም የኢትዮጵያ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ሂደት፣ አዲስ አበባ; ገጽ 66.
[5] Berhe, Fesseha(2011). Studies on the Biography of Blatta Hayle Maryam Redda (1909-1995);  Page 80.
[6] Tarekegn Gebreyesus, “Gaz”, in Siegbert Uhlig(ed): Encyclopedia Aethiopica, vol.2 (D-H), Wiesbaden, 2005.
[7] ቃለ ክርስቶስ ዓባይ(1997); ገጽ 66.
[8] Ibid; Page 72.
[9] Ibid.
[10] Ibid.
[11] Ibid.
[12] Ibid;ገጽ 74.
[13] Ibid.
[14] Ibid.
[15] Ibid; ገጽ 86-87.
[16] በሪሁን ከበደ(1993). የአፄ ኃይለሥላሴ ታሪክ፣ አዲስ አበባ፣ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፣ ገጽ 701 & 708.
[17] Ibid; ገጽ 701.
Filed in: Amharic