>

እንደ ትምህርት መሰጠት ያለበት ገዳ ወይስ ፍተሐ ነገሥት?   (አቻምየለህ ታምሩ)

እንደ ትምህርት መሰጠት ያለበት ገዳ ወይስ ፍተሐ ነገሥት?  

አቻምየለህ ታምሩ

ገዳ እድሜያቸው ከአርባ እስከ አርባ ስምንት የሆኑ ብዙ መግደላቸውን የተቆረጠ አንገትና የወንድ ብልት እንደ ማስረጃ በማቅረብ ሉባ መሆናቸውን  ማስመስከር የሚችሉ ነውጠኛ ወንዶች ከነሱ በፊት ያሉ ትውልዶች ያልወረሩትን  የሌላ መሬት ደም ከጠጡ በኋላ ዘመቻ እያካሄዱ ማንነትን፣ ቋንቋን፣ ባሕልንና ሥልጣኔን በተሳካ ሁኔታ የሚያጠፉበት፤  መሬቱን ብቻ ሳይሆን ሰውንም በመውረር ገርባ [ባርያ] አድርገው የሚይዙበት ሥርዓተ ማኅበር ነው።
ፍትሐ ነገሥት ስፋቱና ጥልቀቱ ወደር የሌለው፤ በጽሑፍ የሰፈረ ጥንታዊ የኢትዮጵያ የሥነ መንግሥት መመሪያ ነው። የኢትዮጵያ ፍትሐ ነገሥት ፍትሕ ሥጋዊና ፍትሕ መንፈሳዊ በመባል በሁለት ዓበይት ክፍሎች የተከፈለ ሲሆን ፍትሕ ሥጋዊ ፍርድ፣ አስተዳደርና ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር የሚስተናገድበት ክፍል ነው።
የገዳ ሥርዓት የአንድ ኅብረተሰብ ግማሽ ክፍሎች የሆኑትን ሴቶችን ከማናቸውም የፖለቲካ  ተሳትፎ ብቻ ሳይሆን  የንብረት ባለቤት እንዳይሆኑ ሙሉ በሙሉ ያገደ ሥርዓት ነው። በገዳ ሥርዓት ሴት ልጅ መሪ መሆን ብቻ ሳይሆን የንብረት ባለቤት የመሆን መብት የላትም። በፍትሐ ነገሥት ግን የአንድ ኅብረተሰብ ግማሽ ክፍሎች የሆኑት ሴቶች  ከወንድ እኩል የንብረት ባለቤት የመሆን፣ ከወንድ እኩል ንብረት የመካፈልና  የአገርና የመንግሥት መሪዎች የመሆን መብት አላቸው።
የገዳ  ድርጅት  ሉባዎች ውኃና ለም መሬት ፍለጋ እንዲሁም ባርያ ለመፈንገል በየስምስት ዓመቱ ወረራና ሰፈራ የሚያደርጉበት ሥርዓት ነው።  የሰውን ልጅ ገርባ [ባርያ፤ ሙሉ ሰው ያልሆነ] እና ቦረና [ ሙሉ ሰው የሆነ] ብሎ የሚከፍለው የገዳ ሥርዓተ ማኅበር  ሉባዎች በየስምንት ዓመቱ ወረራ ሲያካሂዱ ማርከው በርስታቸው ላይ ገርባ የሚያደርጓቸውን ነባር ነገዶች  ከነቤተሰቦቻቸው ባርያ አድርጎ የመሸጥ ያልተገደበ  መብትን ለአባገዳው ሲሰጥ፤ ሰው ሁሉ በጥንተ መሰረቱ እኩል ነው በሚለው እሳቤ የቆመው  ፍትሐ ነገሥት ግን ባርያ ነጻ የሚወጣበትን ሥርዓትና ሁኔታ የሚደነግግ ሕግ ነው።
ስለዚህ በዚህ ዘመን ላሉ ልጆች እንደ ትምህርት መሰጠት ያለበት ሰውን ገርባ [ባርያ፤ ሙሉ ሰው ያልሆነ] እና ቦረና [ሙሉ ሰው] ብሎ የሚከፍለው፤ የአንድ ኅብረተሰብ ግማሽ ክፍሎች የሆኑት ሴቶችን ከማናቸውም የፖለቲካ ተሳትፎ ብቻ ሳይሆን  የንብረት ባለቤት የመሆን መብታቸውን በተሳካ ሁኔታ የደፈጠጠው፤ ከ28 በላይ ነባር ማንነቶችን በተሳካ ሁኔታ ያጠፋውና ሰው ከነ ርስቱ  እንዲወረርና በገዛ ርስቱ  ባርያ እንዲሆንና እንደማናቸውም እቃ አባ ገዳው ባሻው ጊዜ ከነቤተሰቡ ገበያ አውጥቶ እንዲሸጠው የሚፈቅደው ገዳ ወይስ  ሴቶች  ከወንድ እኩል የንብረት ባለቤት የመሆን፣ ከወንድ እኩል ንብረት የመካፈል፣ የአገርና የመንግሥት መሪዎች የመሆን መብት የሚሰጠውን፤   ሰው ሁሉ በጥንተ መሰረቱ እኩል ነው በሚል እሳቤ ላይ በመመስረት ባርያ ነጻ የሚወጣበትን ሥርዓትና ሁኔታ የሚደነግገው ፍትሐ ነገሥት?
በኔ እምነት በዚህ ዘመን ያሉ የኢትዮጵያ ልጆች አገር በቀል  የሆነ የሥነ መንግሥት እሳቤ መማር ካለባቸው ከዘመኑ የቀደመውን የሰውን መብት የሚያስጠብቀውን ፍትሐ ነገሥትን  እንጂ ለዚህ ዘመን ብቻ  ለድንጋይ ዘመን እንኳን  የማይመጥነውን፤ የወንድ ልጅ ብልትና አንገት የሚቆረጥበትን፣ ለሰው ልጅ ደረጃ የሚያበጀውን፣ ከ28  በላይ የኢትዮጵያ ነገዶች ቋንቋ፣ ባሕል፣ ሥልጣኔና ማንነት በተሳካ ሁኔታ የጠፋበትን ገዳ የሚባለውን  አውዳሚ የወረራ ሥርዓት መሆን የለበትም።
Filed in: Amharic