>

የቀድሞው የአዲስ አበባ ም/ከንቲባ  ለኢዜማ ጥናት ምላሽ ሰጡ...!!! (ኢትዮጵያ ኢንተርሴፕት)

የቀድሞው የአዲስ አበባ ም/ከንቲባ  ለኢዜማ ጥናት ምላሽ ሰጡ…!!!

ኢትዮጵያ ኢንተርሴፕት

* …በሃሰተኛ እና በተጋነነ መረጃ ጠንካራ መምሰል እንጂ መሆን አይቻልም፤ በሀሰተኛ መረጃ ድካማችንና ስራችንን ለማጠልሸት ቢሞከርም ስራችን ይናገራል…

* …በራሳቸው መሬት ላይ በተሰራ ህንጻ ዘበኛ እና ተሸካሚ ሆነው ከቀሩ 67 ሺህ አባወራዎች መሃል  20 ሺህ ኮንዶሚንየም መሰጠቱ ቢያንስ እንጂ አይበዛም!!!

በሀሰተኛ መረጃ ሀገር ማፍረስ ይቻል ይሆናል እንጂ ሀገር አይገነባም የፖለቲካ ትርፍም የለውም ለዚህ ምላሽ ለመስጠት ተገቢው ቦታ ላይ ባልገኝም ከዚህየመጓተት ፖለቲካ አስተሳሰብ መውጣት አለመቻል ግን ትልቅ ህመም እንደሆነ ይሰማኛል። የመሬት ወረራን በተመለከተ ከመጀመሪያዋ ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻዋ እለት ድረስ ጠንካራ የሆነ እርምጃ ስንወስድበት የቆየንበት ጉዳይ ነው።

በተለያዩ ጊዜዎች የወሰድናቸው እርምጃዎችም ህያው ምስክሮች ናቸው። እኛ ህገወጥ የመሬት ወረራንለመከላከል እርምጃ ስንወስድ የዛሬ ተቺዎች የሰብአዊ መብት ተነካ፣ ዜጎች ተፈናቀሉ ብለው ዘመቻ ከከፈቱብን ውስጥ ነበሩ።

ለ20ሺህ አርሶአደሮች የተሰጡ የኮንዶሚኒየም ቤቶች በተመለከተም ከአንድ አመት ተኩል በፊት በካቢኔ የተወሰነና የተተገበረ ነው። በድብቅ የተተገበረም ሳይሆን በመን ግስት ሚዲያም በይፋ የተገለፀ ነበር። ከመሬታቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ ከወደቁ በራሳቸው መሬት ላይ በተሰራ ህንጻ ዘበኛ እና ተሸካሚ ሆነው ከቀሩ 67 ሺህ አባወራዎች መሃል የከፋ ችግር ላይ ለወደቁት 20 ሺህ ኮንዶሚንየም ቢያንስ እንጂ የሚበዛ አይደለም።

ከዚህ ውጭ በህገወጥ መንገድ የተሰጠ ምንም አይነት ቤት የለም። ይህ ሥራችን በተደጋጋሚ በይፋ ስንናገር እንደነበረው የምናፍርበት ሳይሆን የምንኮራበት ነው።በግፍ የተገፋን፣ በግፍ ከመሬቱ የተፈናቀለን አርሶ አደር መካስ ያኮራናል።

በዙሪያዋ ካሉት አርሶ አደሮች ጋር በፍቅር ተሳስባ የምትኖር የተሰናሰለች ከተማ እንጂ በዙሪያዋ ካሉት ህዝቦች ጋር የተቀያየመች ከተማ እንድትኖር አንሻም ነበርና። ይህ ደግሞ የከተማዋ ነዋሪዎች ፍላጎት መሆኑንም እንገነዘባለን።

አንድም ቀን በግፍ ለተፈናቀሉ አርሶአደሮች የመቆርቆር ስሜት አሳይቶ የማያውቅ ቡድን ዛሬ የአርሶአደሮችን ጉዳት ለተቀባይነት ማግኛ መጠቀሚያ ሲያደርገው ማየት ያሳዝናል። ነገር ግን በሃሰተኛ እና በተጋነነ መረጃ ጠንካራ መምሰል እንጂ መሆን አይቻልም። በሀሰተኛ መረጃ ድካማችንና ስራችንን ለማጠልሸት ቢሞከርም ስራችን ይናገራልና ፍርድ የህዝብ ነው።

Filed in: Amharic