>

ሳይቃጠል በቅጠል...!!! (የትነበርክ ታደለ)

ሳይቃጠል በቅጠል…!!!

የትነበርክ ታደለ
ትምህርት ትውልድ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በአዲስ አስተሳሰብና በኑሮ ዘይቤ የሚቀረጽበት፣ ችግር ፈቺ ሆኖ ያለውን እሴት ይበልጥ የሚያዘምንበት መሳርያ ነው። ይህ ታላቅ የጥበብ መሳሪያ ደግሞ በሳይንሳዊ ዘዴ ሊቀመርና ሊመራ ይገባዋል።
ይህ ባለመሆኑ ምክኒያትና ፖለቲካው እጁንና እግሩን ሳይታጠብ ስላንቦራጨቀው የኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት አንድም አመርቂ ለውጥ ሳያመጣ፣ ትውልድን ችግር ፈቺ ከማድረግ ይልቅ ይበልጥ ለሀገር ችግር ፈጣሪ እየሆነ የፖለቲከኞች ምኞት ማስፈጸሚያ ሆኖ እነሆ ዘንድሮ ደግሞ ጆሮ አይሰማው የለ “የገዳ ስርዓት እንደ አንድ የትምህር አይነት ሊሰጥ” መሆኑ አዳነች አቤቤ (ወ/ሮ) ገልጸዋል።
ምን ችግር አለው?
የገዳ ስርዓትን ኢትዮጵያውያን ሁሉ ቢማሩት ምን ችግር አለው? ምንም! ማንኛውንም ነገር መማር ምንም ጉዳት የለውም። እንድያውም የእስከዛሬው ችግራችን ያሉንን ሀብቶቻችንን ሁሉ ያለማወቃችን በመሆኑ ይህ አይን ከፋች ሊሆን ይችላል።
ይሁን እንጂ “እንዴት?” የሚለው ጥያቄ አንገብጋቢና አሳሳቢ ነው። ከላይ እንደገለጽኩት የትምህርት ስርዓት በሳይንሳዊ ዘዴ ምርምር እና ጥናት ተደርጎበት ተመዝኖ ተፈትሾ በምሁራን ውይይትና ክርክር ተደርጎበት አሳማኝ መለኪያዎችን ሲያልፍ ወደ ስርዓቱ እንዲገባ ማድረግ ይቻላል። ይሁንና ብልጽግናዎች (ልክ እንደ ቀድሞ አባታቸው ኢህአዴግ) ምንም ውይይትና ምክክር አላስፈለጋቸውም። በጨፌያቸው የወሰኑትን በብርሀን ፍጥነት ተግባራዊ ለማድረግ ተንቀሳቅሰዋል።
ይህ ደግሞ ልክ ብዙዎችን መስዋዕት ካደረገ በኋላ እንደ ከሸፈው እንደ ቀድሞው የትምህርት ስርዓት አሁንም ተመሳሳይ ኪሳራ አድርሶ መፍረጡ አይቀሬ መሆኑን ያሳያል። በፖለቲከኞች የሚሰራ እንኳን የትምህርት ፖሊሲ የመንገድ ግንባታም ብዙ አመት የማገልገል አቅም አይኖረውም።
ሌላውና ዋነኝው ጥያቄ ደግሞ የገዳ ስርዓትን እና አጠቃላይ የኦሮሞን ባህላዊ እና መንፈሳዊ እሴቶች ለኢትዮጵያውያን ማስተማር ተገቢ ሆኖ ሳለ ልክ እንደ አንድ ራሱን የቻለ የትምህርት አይነት የሚሰጠው እንዴት ባለ አግባብ ነው? ይህ በራሱ ትርጓሜው ምንድነው? ኢትዮጵያ ካሏት 90 እና ከዝያ በላይ ብሄረሰብ የራሱ የሆነ ባህል አለው። እነዚህን ባህሎች በማህበረሰብ ትምህርቶች ማስተማር ይቻላል ግን እንዴት ሆኖ ነው ራሳቸውን የቻሉ የትምህርት አይነቶች የሚሆኑት? የይዘትና የምዘና እንዲሁም የብያኔው ጉዳይ ወደ ጎን ይቀመጥና ምን ያህል ተጨባጭ ይሆናል? ከዚህ የትምህርት አይነትስ የምንጠብቀው ውጤት ምንድነው? ኦሮሟዊነት?…
የገዳን ስርዓት እንደ አንድ የትምህርት አይነት ማስተማር ከተቻለ የሌሎቹንስ ማስተማር ይቻላል? ካልተቻለ ሊፈጠር የሚችለው የፖለቲካ ተቃርኖ እንዴት ይታያል?
በኦሮሚያ ክልል ያልተሰጠ የገዳ ስርዓት የትምህርት አይነት ለአዲስ አበባ ተማሪዎች መሰጠቱስ ምን ማለት ነው?
ተጨማሪው ጥያቄ ደግሞ “የገዳ ስርዓት” ካለው መንፈስዊና ባህላዊ እሴቱ አንጻር መመዝገብ ያለበት ከሀይማኖት ተርታ ሆኖ ሳለ በሳይንሳዊ መንገድ ትምህርት ሆኖ የሚቀረጸው በምን መረጃ ነው። የገዳ ስርዓት አማኝ (አምላኪ) ያልሆኑ ዜጎችስ እንዲማሩ እንዴት ይገደዳሉ?
እዚህ ላይ በርካታ የስነ – ትምህርት እንዲሁም የፖለቲካ ጥያቄዎች ማንሳት ይቻላል። ይሁን እንጂ ግን፦
የአብይ አህመድ አስተዳደር በአንድ በኩል ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን በጋራ ለማሻገር የሚያቀርበው ትንታኔ በሌላ በኩል ደግሞ በተለይም አዲስ አበባን ተመርኩዞ የሚያራምደው የኦሮሚያዊነት እንቅስቃሴ ዛሬ በአጣብቂኝ ውስጥ ያለችው ሀገር ነዋሪዎች ይህቺ ተስፋ እንዳትጠፋ በማለት በተሟጠጠ ተስፋ እየደገፉት ወደ ፊት እንዲሄድ ያላቸውን አቋም እየገለጹ በተቃራኒው እንዲህ ያሉ የእጅ አዙር ከፋፋይ እና ግጭት ቆስቋሽ ፖሊሲዎቹን ለማስፈጸም መንቀሳቀሱ እጅግ አስፈሪ ነው።
በዚህ ጉዳይ ብዙ ማለት የሚቻል ቢሆንም እሱ ራሱ ገና ህዝባዊ ቅቡልነት በሌለው ስልጣኑ ሀገርን አረጋግቶ የተረጋጋ ስርዓት ፈጥሮ ምርጫ ማካሄድ ሲገባ ልክ እንደ ስዩመ እግዚአብሄር በልቦናው ያሰበውን ሁሉ ወደ ተግባር እየለወጠ የህዝብን (ጊዚያዊ) ቅቡልነት እያጣ ተመልሶ አጣብቂኝ ውስጥ በመግባት ሀገርን ለበለጠ ችግር ላለመዳረግ እንዲህ ካሉ የብዙሀን ጥያቄዎች ላይ እጁን መሰብሰብ አለበት እላታለሁ።
Filed in: Amharic