>

«እብዱ እና ጠሹ፣ እስክንድር ነጋ...!» (ዶ/ር መክብብ ፈቀደ)

«እብዱ እና ጠሹ፣ እስክንድር ነጋ…!»

ዶ/ር መክብብ ፈቀደ
* …ለአንዳንዱ «እብድና ንክ፣ ጠሽም» ነው፣ ለሌላው በአዲስ አበባ የአብን ተወካይ የሆነ «አማራ»ና «የደንበጫ ፖለቲካ» አራማጅ ነው፣ ለሌላው «አዲስ አበቤ» ነው፣ ለአንዳንዱ «የኦርቶዶክስ አክራሪ» ነው፣ ለሌላው «ጋዜጠኛና የሰብአዊ መብት ተሟጋች» ነው፣ ለአንዳንዱ የፖለቲካ ድርጅት «መሪ» ነው፣ ለሌላው ኩርቱ ፌስታል የሚይዝ፣ አለባበስ የማይችል፣ «ፋራ፣ ኋላቀርና ሰገጤ» ነው፣ ለአንዳንዱ ሙስሊምና ኦሮሞን የሚጠላ «ዘውጌ» ነው፣ ለተቀረው ተራ ኢትዮጵያዊ፣ ባለትዳርና የአንድ ልጅ «አባት» ነው ሌላም…. ሌላም….!!!
 
የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ጨርሰን ከቢሮ እየወጣን «ሰውየው ነገ እኮ የዓመቱ ቅዳሜ ነው፣ ይለፍልህ እስቲ ምሳ ጋብዘኝ» አልኩት። ፈገግ ብሎ «አግኝቼ ነው? በደስታ» አለኝ። በቃ በአንድ አፍ፣ ነገ አራት ኪሎ በተለመደው ቦታ፣ ሰባት ሰዓት እንገናኝ፣ በዛውም የማወራህ ቁም ነገር ይኖራል» ብዬው ተለያየን።
በማግስቱ ከተባባልነው ሰዓት ትንሽ ቀደም ብዬ ደረስኩና ቅዳሜ ቅዳሜ የምትወጣውን የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ «ፍትህ መፅሔት»ን እያጣጣምኩ ጠበኩት። በንባብ መሀል ድንገት ቀና ስል፣ በሩቁ አንድ ሰው ወደ አለሁበት ሬስቶራንት ሲገባ ተመለከትኩ። በሩ አካባቢ ቆሞ፣ ፊቱን ወዲህና ወዲያ ያማትራል። የግለሰቡ ሁኔታ አንድ ወዳጁን እየፈለገ እንደሆነ ያሳብቅበታል። ሰውየው ሸንቀጥ ብሎ ረዘም ያለና ቁመተ ሎጋ ነው። በሙሉ ጥቁር ሱፍ ላይ ነጭ ሸሚዝ አክሎበት፣ በጥቁር ጫማና መነፅር ተውቦ፣ በቀላሉ ዐይነ ግቡ እንዲሆን አድርጎታል። Nike የምትል ፅሁፍ ከነምልክቱ ያለባት ሰማያዊ Brand ኮፊያም አጥልቋል። ባጠቃላይ High Class የሚባል ገፅታን ተላብሷል። ይህ ወደ ሬስቶራንቱ የገባው ሰው ማነው? ትልቁ ጥያቄ ይህ ነው!!!
ለአንዳንዱ «እብድና ንክ፣ ጠሽም» ነው፣ ለሌላው በአዲስ አበባ የአብን ተወካይ የሆነ «አማራ»ና «የደንበጫ ፖለቲካ» አራማጅ ነው፣ ለሌላው «አዲስ አበቤ» ነው፣ ለአንዳንዱ «የኦርቶዶክስ አክራሪ» ነው፣ ለሌላው «ጋዜጠኛና የሰብአዊ መብት ተሟጋች» ነው፣ ለአንዳንዱ የፖለቲካ ድርጅት «መሪ» ነው፣ ለሌላው ኩርቱ ፌስታል የሚይዝ፣ አለባበስ የማይችል፣ «ፋራ፣ ኋላቀርና ሰገጤ» ነው፣ ለአንዳንዱ ሙስሊምና ኦሮሞን የሚጠላ «ዘውጌ» ነው፣ ለተቀረው ተራ ኢትዮጵያዊ፣ ባለትዳርና የአንድ ልጅ «አባት» ነው።
 እንደ እይታህ አንግል እና ቀርበህ ሰውየውን እንዳወከው ግንዛቤህም እንደዛው ይለያያል። አፈር ያቅልልለትና ጋሽ ስብሀት ገ/እግዚአብሔር በአንድ ቃለ መጠይቁ «የኔ ቤት፣ እኔ ቤት ላለችው አይጥ ዓለሟ ሲሆን፣ ለኔ ግን እውነታው፣ ቤት ማለት አድሬ የምወጣበት በጣም ትንሽዬ የዓለም ክፍል ማለት ነው» ብሎ ነበር።
አይጥነት ነገርን በራስ እውቀት ብቻ መዝኖ ወደ አላግባብ ድምዳሜ (Hasty Generalization) መድረስ ነው። ስለዚህ አይጣዊ አመለካከትን በማስወገድ ሰፊና እውነተኛ ዕይታ ይኖር ዘንድ ይህ ተፃፈ። አይጧ በጊዜ ቤቱ፣ ቤት እንጂ ዓለም አይደለም ካልተባለች፣ በአይጥ ላይ አይጥ እየፈለፈለች፣ አይጣዊ አመለካከትን እያስፋፋች በሂደት «ለምጣዱ ሲባል፣ አይጧ ትለፍ» የሚያስብል በምንፈልገው ምጣድ በደካማ ጎናችን ስም Bargaining Power ልታዳብር ትችላለችና።
በእርግጥ ወደ ሬስቶራንቱ የገባው ይህ ሰው ማነው? 
«ሩትጋር ዩንቨርሲቲ» ከሚሰራው አባቱና «የአሜሪካን ዩንቨርሲቲ ኦፍ ቤሩት» አስተማሪ ከሆነችው እናቱ ምሁርና classic ከሆነ ቤተሰብ በ1960 ዓ.ም ተወለደ ሸገር ውስጥ ተወለደ ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው ብዙዎች እዛ በመማራቸው በሚጎርሩበት በሳንፎርድ ት/ቤት ሲሆን፣ ወደ አሜሪካ በማቅናት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እዛው ጨርሶ፣ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው «አሜሪካን ዩንቨርሲቲ» ተቀላቀሎ፣ ፖለቲካል ሳይንስን ከኢኮኖሚክስ ጋር አዋህዶ እንደ ውሀ ጠጣው።
ለሀገሩ ትልቅ ፍቅር ያለው ይህ አሁን እኔ ባለሁበት ሬስቶራንት በር ላይ የቆመ ግለሰብ፣ የላመ የጣመውን ህይወት ትቶ፣ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ። ለኢትዮጵያ ሲል፣ ወደ ኢትዮጵያ መነነ። የመጀመሪያ ጋዜጣውን «ኢትዮጲስን» በ1985ዓ.ም «ሀ» ብሎ ማሳተም ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ታገደበት። የሰርካለም አሳታሚ ዋና ስራ አስኪያጅ በመሆን «አስኳል»፣ «ሳተናው» እና
 «ምኒሊክ» የተባሉ ጋዜጦች ያሳትም የነበረ ቢሆንም፣ ሁሉም በመንግሥት ታግደውበት ነበር። የአፍሪካ ችሎታ ማገድ ነው።
 የ1997 ዓ.ም ምርጫ ውጤትን ተከትሎ ብዙ ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች ሲታሰሩ፣ ከነዛ ውስጥ እሱና ባለቤቱ ሰርካለም ይገኙበታል። ሰርካለም ያለ ጊዜዋ እስር ቤት ናፍቆት የሚባለው ብቸኛ ልጇን ተገላገለች። ሰውየው ለሰብዓዊ መብት መከበር ባደረገው ትግል ባጠቃላይ ዘጠኝ ጊዜ ለእስር ተዳርጓል። መናኝ ነውና በኢትዮጵያ ምድር ፈተና ፀናበት። «ይቅርታ ጠይቀህ ውጣ» ሲባል እምቢ በማለቱ፣ ከሰባት ዓመታት እስር በኋላ፤ «ለውጡ¡ ሲመጣ» የፖለቲካ እስረኞችና ጋዜጠኞች በመፈታታቸው ከእስር ሊወጣ ችሏል። የእድሜውን እኩሌታ ለታገለለት ሰብአዊ መብት እና የመናገር ነፃነት ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ፣ እውቅናና ክብር አግኝቷል።
….
ከእነዚህም :-
1. 2004ዓ.ም (2012) PEN/Barbara Goldsmith Freedom to Write Award 

2. 2006ዓ.ም (2014 ) World Association of Newspapers’ Golden Pen of Freedom Award
3. 2009ዓ.ም (2017) International Press Institute World Press Freedom Hero
4. 2010 (2018) Oxfam Novib/PEN Award ይገኙበታል
እጄን አውለበለብኩለት። ሲያየኝ ፈገግ ብሎ ወደኔ መምጣት ጀመረ። ገና ቁጭ ሳይል። «የቀጠርከኝ ምሳ ልታጋብዘኝ እንጂ፣ ልታሳጣኝ ነውንዴ?» ስለው ከትከት ብሎ ስቆ «እኮ እንዴት አለቃ?» አለኝ። «አለቃ» ብዙ ጊዜ ከአፉ የማትጠፋ ቃል ነች። «እሺ አለቃ፣ ቻው አለቃ፣ አትጥፋ አለቃ፣ በርታ አለቃ….» የተለመዱ ንግግሮቹ ናቸው። «እንዴ ምንድነው እንደዚህ መዘነጥ?» አልኩት። «አይ አለቃ፣ አሁን ይቺም አለባበስ ሆና? ኧረ ተው!» አለ መነፅሩንና ኮፊያውን አውልቆ ወንበር ስቦ እየተቀመጠ።
«የምሬንኮነው እስኬው ለምንድነው ግን ሁሌም እንደዚህ የማትለብሰው? አንዳንድ ቦታ ስትሄድ፣ ኢንተርቪው ሲኖርህ፣ ሰዎችን ስታገኝ ፀዳ ማለትኮ አሪፍ ነው። በዛ ላይ ደሞ Public Figure ነህ። እንደዛሬ ዘንጠህ አይቼህ አላውቅም» ብዬ መለስኩለት። ቀጥሎ የተናገረው ነጥብ ግን ያስረዳኝ እስከዛች ቀን በነበረን ትውውቅ የእስክንድር ነጋን የስነ ልቡና ልዕልና ገና እንዳለገባኝ እና የአይጧ አመለካከት እኔም ጋር እንደነበረ ነው። «በዓይነት ዓይነቱ በጣም ብዙ ልብስኮ አለኝ፣ ካለኝ ልብስ ሩቡን እንኳ አለብሰውም፣ ይህም የማደርገው ቢሮ ውስጥ የስራ ባለደረቦቼ ላይ ተፅዕኖ እንዳልፈጥርና ተናንሶ ዝቅ ብሎ ከድሀው ማህበረሰባችን ጋር ተመሳስሎ መኖር በተለይ አሁን ለያዝነው መንገድ እጅግ ወሳኝ ነው። በየቀኑ ዝንጥ ማለት ለኔ ቀላል ነገር ነው። አብረውህ ለሚሰሩ ይህንን ማድረግ ለማይችሉ ሰዎች ግን የስነ ልቦና ቀውስ አስከትሎ ከአንተ እንዲርቁ ያደርጋል። የህዝባችን ኑሮ ደሞ እንደምታውቀው ነው። እንኳን አማርጦ በየቀኑ ሊለብስ፣ ያለችውን ልብስ አስር ጊዜ የሚያስጠቅም (የሚያሰፋ) ምስኪን ህዝብ ነው። ወጣ ያለ አለባበስ ለብሼ ለድሆች ድምፅ ለመሆን ወደ ድሆች ስሄድ ምን ይሰማቸዋል? እና ከዚህ ከዚህ አንፃር ነው በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ልብሶች የምለብሰውና ለፕሮቶኮል ግድ የሌለኝ።» አለ! ምን እንደምመልስለት ቃል አጠረኝ። ለእያንዳንዱ እንቅስቃሴው ምን ያህል ኃላፊነት የሚሰማው ትሁት ሰው እንደሆነ በማወቄ ተደመምኩ። አይጣዊ አመለካከቴም አሳፈረኝ።
ስለዚህ እስክንድር በዓለማችን ውስጥ ለወንዶች ምርጥ ከሚባሉት እንደ AER TECH PACK ቦርሳ መያዝ እየቻለ ልብሱን በኩርቱ ፌስታል ይዞ ካየኸው፣ መንገድ ላይ ዝንጥ ያለ ሱፍ ሳይሆን ድክም ያለች ልብስ ለብሶ ከተመለከትከው፣ በRVA4 ሲሄድ ሳይሆን የታክሲ ሰልፍ ላይ ካገኘኸው የስነ ልቡናው የከፍታ ሚስጥር ይህ ስለሆነ ነው። ለድሀ ሲጮህ መስማት ከሰለቸህ፣ የሚጮኸው «እብድ» ወይም «ንክ» ወይም «ጠሽ» ስለሆነ ሳይሆን ወይም እንደምትለው PTSD (post traumatic stress disorder) ከእስር በኃላ develop አድርጎ ሳይሆን የድሀ ድምፅ አቅም ስለሌለው፣ ስለማይሰማ ድማፃቸውን ለማጉላት ነው። Otherwise በብዙ እብዶች መሀል የሚኖር ጤነኛ ነው።
መቼም አንተ የምትመኘውን ህይወት ኑሮ የጨረሰ፣ ሸገር ተወልዶ፣ ሳንፎርድ ተምሮ፣ ገና በልጅነቱ አሜሪካን ሀገር ሄዶ፣ እዛው ሀገር በዩኒቨርስቲ ደረጃ በፖለቲካል ሳይንስ እና ኢኮኖሚክስ ዲግሪውን ይዞ «ፋራ፣ ኃላቀር፣ ሰገጤ» ልትለው አትችልም። አቅሙ የለህም። ልቅም ያለ የአራዳ ልጅ ነው። ለሰብአዊ መብት መከበር ስለታገለ አያሌ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን የተቀናጀን ሰው «አክራሪ አማራና ኦርቶዶክስ ነው፣ ኦሮሞና እስላም ጠል ነው።» ብለህ ያለ ግብሩ ሰውየውን ካጠበብከው እራስህ የዘር በሽታ ተጠቂ ስለሆንክ አመለካከትህ የአይጥ ነው ማለት ነው። Sorry for the collateral damage! The burdon of proof is on your shoulder, actually!
የዚህ ፅሁፍ ዋና ዓላማ እስክንድር ነጋን መልዐክ አድርጎ ማቅረብ አይደለም። በፍፁም። የህሊና ዳኝነት ስለመስጠት ነው። «ሰው ይሳሳታል፣ እስክንድር ነጋ ሰው ነው፣ ስለዚህ እስክንድር ነጋ ይሳሳታል!» ከዚህ የPsychology Deductive Logic እና Transitive Relation-Rule Of Maths እስክንድር ሊያመልጥ አይችልም። አሁን ፓርቲው ውስጥ የሚገኙ የስራ አስፈፃሚ አባላት ሊመሰክሩ እንደሚችሉት በተለይ Activismን ከProfessionalism ጋር አመጣጥኖ ከመሄድ አንፃር በየስብሰባችን እንደኔ የሚተቸው ሰው አልነበረም። «የፓርቲ ፕሮቶኮል ያንሰናል፣ ፓርቲው «የዓላማ» ሳይሆን «የአካሄድ» ህፀፁ እየበዛ መጥቷል፣ ለዚህም ዋናው ተጠያቂው አንተ ነህ» እስከማለት ደርሼ ሁላ ነበር። እውነት ነው ብዙ ጉዳዮች ላይ በአንድም ይሁን በሌላ፣ አንድ ሁለት ብለን ልንዘረዝር የምንችላቸውን ግድፈቶችን ፈፅሟል። የሚፈፅማቸው ስህተቶች ግን «እብድ» ወይም «አክራሪ» ወይም «ዘውገኛ» ወይም «ፋራ» ስለሆነ ሳይሆን በከፍተኛ ወኔ «ስለሚሰራ» ብቻ ነው። የሚሰራ ሰው ደሞ ይሳሳታል። ሲገሰፅ ይመለሳል። ይታረማል። የስህተቱ ምክንያት ከዚህ አንፃር ማየት ተገቢ ነው። እሱን አለመውደድ፣ ፓለቲካ አይችልም ማለት የቆመለትን ዓላማ መሞገት መብት ነው። ያልሆነ ስብዕና መስጠት ግን ነውር ነው።
«አይ ምክንያትህ አሳማኝ ነው፣ ግን ደሞ አልፎ አልፎም ቢሆን መልበስማ ግድ ይልሀል» ብዬው ተሳስቀን፣ ምሳችንን አዘን፣ በልተን፣ ስንጨርስ የዛን ቀን የቀጠርኩት ለምን እንደሆነ ነገርኩት። «እስኬው በዚህ በዚህ [ዝርዝሩ እዚህ ጋር መግለፅ ስለማይጠቅም] ምክንያት ገና እየገባሁበት ከነበረው ፖለቲካ ልወጣ ነው» አልኩት። ባመነባቸው ጉዳዮች ላይ ይበልጥ አዳብረን ስንወያይ፣ ጥቂት ባላመነባቸው ጉዳዮች ደሞ እንደ ታላቅና ታናሽ ወንድም ተከራከርን። ሀሳቦች ተፋጩ። በመጨረሻም ስምምነት ላይ ደርሰን፣ ያሰብኳቸው ነገሮች እንዲሳኩልኝ መልካም ምኞት ተመኝቶ፣ ከሬስቶራንቱ ልንወጣ ስንል። «እስኬው፣ ባንተ ዙርያም ጥቂት ብናገር ደስ ይለኛ ነበር» አልኩት። «እንዴ አለቃ፣ ምን ችግር አለው? ንገረኛ» አለ። «መቼ ነው ለራስህ ለሚስተህ እና ለልጅህ መኖር የምትጀምረው?» አልኩት። አተኩሮ እየተመለከተኝ፣ በመሀላችን ዝምታ ሰፈነ። «የምሬን ነው እስኬው ሚስትህ እንዳባወራ፣ ልጅህ ደሞ እንዳባት ይፈልጉሀልኮ!» ብዬ ዝምታውን ለመስበር ሞከርኩ።
«ኢትዮጵያስ? ለማን ትቻት?» አለ ቁጭት በተሞላው ገፀ-ፊት። «ስንት ዋጋ የተከፈለባት ይቺ ሀገር እንደ ቀልድ መጫወቻ ስትሆን፣ እንደ ሀገር መቀጠሏ ጥያቄ ውስጥ መግባቱን እያየሁ፣ ለማን ትቻት የራሴን ኑሮ ልኑር? » ብሎ በጥያቄ አፋጠጠኝ። «እንዴ በቃቃቃአ! ሀገር እንጂ ግለሰብ አይደለችምኮ፣ ባንተ ጫንቃ እስከመቼ ታነክሳለች? ሌላ ልጅ ይነሳላታ እንግድያው! አንተስ ማን አለህ? ሁለቴ አትኖር ነገር፣ ቤተሰብህስ ማን አለው ካንተ ውጪ? ተረጋግተህ ከቤተሰብህ ጋር ቀሪውን እድሜህ ማሳለፍ አለብህ» አልኩት እኔም ኮምጨጭ ብዬ። እግዚአብሔር በሚያውቀው ሁሌም ልፋቱ ስለሚያሳዝነኝ አጋጣሚውን ልጠቀም ብዬ ነው። ብቻ ሲበዛ ብኩን ነው፣ ቁርስ በልቶ ምሳ የማይደግም ባተሌ።
«እውነት ብለሀል ቤተሰቦቼ ያስፈልጉኛል፣ እኔም አስፈልጋቸዋለሁ። ልጄ ናፍቆት አሁንኮ ብታየው በስመአብ ትልቅ ሆኗል። ከኔ ጋር ስልክ ላይ ለማውራት ያለው ፍላጎት እምብዛም ነው።እንደ አባት የሚያየኝ አይመስለኝም፣ ታውቀላህ? በሚገባ አባት አልሆንኩትም። እርቄዋለሁ። የባለቤቴ ጥንካሬ ባያግዘኝ ኖሮ እስከዛሬም መጓዝ ለኔ ከባድ ነበር። ነገር ግን አሁን አልችልም። ለህዝብ ቃል ገብቻለሁ። እንደ ባህላችን ቃሌ ከሚጠፋ ደሞ ልጄ የመሰዋዕት በግ መሆኑ ግድ ነው። ስለዚህ እስከምርጫው መታገልና መታገስ አለብኝ። ይህ ምርጫ የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣፈንታ የሚወስን ወሳኝ ምዕራፍ ነው። ድል ካደረግን በኃላ ወይ እነሱ መጥተው እዚህ አብረን እንኖራለን ወይ ደሞ የህዝብ ይሁንታ ካገኘሁ እኔ ስልጣን ስለማልፈልግ አደራዬን አስረክቤ፣ እኔ ወደዛው አሜሪካ እሄዳለሁ። ከተሸነፍን ግን እንዳልከው ለነሱም ጊዜ መስጠት ስላለብኝ ወደዛው አቅንቼ ቀሪ ኑሬዬን ከነሱ ጋር አደርጋለሁ።» ብሎኝ በውሳኔው ደስ በሎኝ ከሬስቶራንቱ ወጣን። «ሰላም ሁን አለቃ….» የመጨረሻ ንግግሩ ነበረች።
እንዲህ ከተባባልን እኔም ከፓርቲው ከወጣሁ ወር እንኳ ሳይሞላ፣ ወደ ፍጥሞ ደሴት ተጋዘ!
እስኬው፣ እውነተኛ እንደሆንክ ልቤ ያውቃልና እውነት ነፃ ታውጣህ! ነፃ የሚያወጣ ፍርዱ ፍፁም የሆነ እግዚአብሔር ብቻ ነውና፣ ፈጣሪ ነፃ ያውጣህ። ወደ ፍጥሞ ደሴት የተጋዘው የዋሁ ዮሐንስ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ነፃ መውጣቱ አይቀርም። ከቤተሰብህ ጋር ተገናኝተህ የተመኘኸውን ኑሮ ለመኖር ያብቃህ! ሰላም ሁን አለቃ!
Filed in: Amharic