>

ጌታቸዉ ተካ፤ ቀልድና ቁምነገር ገንዘቡ። (ሮማን ካሣዬ፤ ከካናዳ)

ጌታቸዉ ተካ፤ ቀልድና ቁምነገር ገንዘቡ።

                                 በርካቶች- በጨዋታ ለዛዉና በፈገግታዉ፣በዉብ ድምጹና በትህትናዉ ያዉቁታል                                  

                               እኔ በሰዉ አማኝነቱና በቁምነገረኝነቱ ጭምር አዉቀዋለሁ።ጌታቸዉ ተካ ዋሴ ነበር።

 ሮማን ካሣዬ፤ ከካናዳ


በቀዳሚት ሰንበት የጌታቸዉ ተካን ህልፈተ-ህይወት የያዘዉን ጽሁፍ ሳነብ የተሰማኝ ሀዘን ጥልቅ ነበር። እስካሁንም ጠሊቅ ነዉ። ከወጣትነት ዘመኔ ጀምሮ የማዉቀዉ ፤እንደታላቅ ወንድሜ የምቆጥረዉ ጌታቸዉ ተካ ያ ፤ተወዳጅ ሳቁ ዳግም ላይሰማ ወደ ዘላለማዊዉ እረፍት ማሸለቡን ስሰማ ጉንጮቼ በትኩስ እምባ ረጠቡ።

የሰዉ ልጅ፣ በኑሮ ማእበል ሲላጋ ኖሮ የጉልምስና ዘመኑን ሲያገባድድ የወደፊት ቀሪ እድሜዉን ከማሰብ ይልቅ በልጅነት ወይንም በወጣትነት ዘመኑ ትውስታ ለምን ሃሳቡ ተሸብቦ እንደሚያዝ ይገርመኛል። ምናልባትም፤ መጪዉ ጊዜ እንግዳ ሰለሆነና ምን አይነት ነገር በህይወታችን ላይ እንደሚያመጣልን ወይንም እንደሚያመጣብን ስለማናዉቀዉ ሊሆን ይችላል። በአንጻሩ ፤ ያለፈዉ ዘመን ግን እንዲህና እንዲህ ሆኖ ነበር የምንለዉ፤ ያለፍንበት፣ያየነዉና የዳሰስነዉ ፤ኖረንበት አሻራዉን በዉስጣችን አትመን የያዝነዉ ስለሆነ ስለሚቀጥለዉ አንድ አመት ከማሰብ ይልቅ ስላለፉት ሰላሳና አርባ አመታት ማሰብና ማሰላሰል ይቀለናል። በትናንትናዉ እለት በመንፈሴ ዉስጥ እንደ ጥጥ ሲባዘት የነበረዉም ይህ እሳቤ ነበር።

ታሪኩ የሆነዉ ከብዙ አመታት በፊት ቢሆንም፤ በህይወት እስካለሁ ድረስ cherish የማደርገዉ ትዝታዬ ነዉ።

በመንግስት መስሪያ ቤት በገንዘብ ያዥነት ለመቀጠር የሚያምንብኝ ሁነኛ ዋስ ያስፈልገኝ ነበር።  ገና አፍላ ወጣት በመሆኔ ደግሞ፤ «ገንዘብ ብታጎድል እኔ እከፍልላታለሁ» ብሎ የሚወራረድብኝ ዘመድ ማግኘት ቀላል አልነበረም። ለጌትሽ ነገርኩት።

« ሮማን ካሣዬ! እኔ እያለሁ ምን ችግር አለ» አለኝ። ጌትሽ፣ ያባቴን ስም ሳይጨምር ጠርቶኝ አያዉቅም።  እኔም ደስ እያለኝ፣ ተያዤን ይዤ በማግስቱ እንደምመጣ ለማሳወቅና ተጨማሪ መመሪያ ለመቀበል ወደ መስርያ ቤቱ ስሄድ የሚያስደነግጥ ነገር ሰማሁ። ለሶስት ክፍላተ-ሀገራት ለመቀጠር ፈተናዉን ካለፍነዉ  መካከል አንደኛዋ ልጅ መቀጠር ሳትችል እንደቀረች ሰማሁ። ምክንያቱ ደግሞ ፤ለሌላ ስራ ቢሆን ችግር እንደሌለበት ሆኖም ግን ለገንዘብ ያዥነት ወንድምዋ ተያዥ ሊሆናት እንደማይፈልግ በመግለጹ ነበር። ጌትሽ ሃሳቡን ከቀየረ እኔም መቅረቴ ነዉ ብዬ አሰብኩ። ሆኖም ከልቡ እርግጠኛ ሳይሆን ተያዥ እንዲሆነኝ ስላልፈለግሁ እቤት እንዲመጣ መልእክት ላኩበትና ጌትሽ ሲመጣ ለምን እንደጠራሁት ነገርኩት። 

«ልጅትዋ ስራዉ ያመለጣት የእናትዋ ልጅ ወንድምዋ ለገንዘብ ያዥነት ተያዥ ሊሆናት ባለመፈለጉ ነዉ እና ጌትሽ አንተን ተያዥ ማድረግ ከበደኝ አልኩት። በዚያም ላይ ገና ትዳር መመስረቱ ነበርና ሃላፊነት ላበዛበት ጠላሁ።  ከትከት ብሎ ሳቀና «በይ አትቀልጂ፣ ይልቁን ጉርድ ፎቶ ያልሽዉን አምጥቻለሁ ነገ ኬላ እንገናኝና አብረን ሄደን ፈርሜልሽ በዚያዉ ወደ ሥራዬ እገባለሁ» ብሎኝ ተሰነባበትን። እኔም ከዋስትናዉ ፎርም ጋር የሚያያዘዉን በዉትድርና የማእረግ ልብሱ የተነሳዉን ጉርድ ፎቶ በጥንቃቄ ከቦርሳዬ ዉስጥ አስቀመጥኩት። ጌታቸዉ ተካ፣ ደስ እያለዉ፤ ለአስራ አምስት ሺህ ብር ዋስ ሆኖ የመጀመርያ ቁዋሚ ስራዬን አስቀጠረኝ።

ኢሉባቦር፤ ኢሉባቦር መቱ፣

ይማርካል የደንሽ ዉበቱ፤

 እያልኩ ጅማን ሰንጥቄ ኢሉባቦር ገባሁ። ከዚያ በፊትም ሆነ ከዚያ በሁዋላ በርካታ የሳቅና የደስታ ጊዜያት በቤተሰብ ፍቅር አሳልፈናል። ለብዙ አመታት ካናዳ ቆይቼ ቤተሰብ ለመጎብኘት አዲስ አበባ ስሄድ ከጌትሽ ጋር ያለፈዉን እያነሳን  ተጨዋዉተናል። ኑሮ የሚሉት ሽንፍላ ባንድ ወገን ሲያጥቡት በሌላዉ አልጠራ እያለ ልቤ እንዳሰበዉ ሞልቶልኝ ጌትሽን ዳግመኛ ሳላገኘዉ ጊዜያት ቢያልፉም በሚቀጥለዉ አዲስ አበባ ስገባ  አግኝቼዉ ያን የማይጠገብ ሳቅና ጨዋታዉን ልታደም ጓጉቼ ነበር። አንድ ጊዜም ያባቴን ስም ሳይጨምር ጠርቶኝ የማያዉቀዉ ዉድ ወንድሜ ፤ዋሴ፤ ቀልድና ቁምነገር ገንዘቡ፤ ጌታቸዉ ተካ ከዚህ አለም በመለየቱ የተሰማኝ ሀዘን ጥልቅ ነዉ። ፈረንሳይ ለጋሲዮን አንድ ባንድ የቀድሞ ዉበትዋ መርገፉንና በሳቅዋ ላይ ጀምበር ማዘቅዘቅዋን ሳይ ዉስጤ ተረበሸ። የእድሜ ልክ ወዳጁንና የሙያ አጋሩን በማጣቱ ለጋሽ አየለ ማሞም አዘንኩለት።

 ወይ ሰፈሬ፤)

   በርካቶች፤ በጨዋታ ለዛዉ፤ ፣በዉብ ድምጹና በትህትናዉ የሚያዉቁት ጌታቸዉ ተካ እኔ በሰዉ አማኝነቱና በቁምነገረኝነቱ ጭምር የማዉቀዉ አኩሪ ወንድሜና ዋሴም ነበር። ጌታቸዉ ሲበዛ ትሁት በመሆኑ ይህን ታሪክ ስናገር ቢሰማ ምቾት እንደማይሰጠዉ አዉቃለሁ። « አይ ሮማን ካሣዬ፤ ይህ እኮ ቀላል ነዉ» እንደሚል አልጠራጠርም። አንዳንድ ወንድሞች ለእህቶቻቸዉ ማድረግ የሚከብዳቸዉን ዉለታ በፍጹም የወንድምነት ስሜት ጌታቸዉ ተካ ለእኔ አደረገልኝ። ምንም ምላሽ ሳይጠብቅ ለሰዉ በጎነት የሚያደርግ ሰዉ በህያዋን ልቡና ዉስጥ ህያዉ ሆኖ እንደሚኖር ምስክር እሆን ዘንድ መልካምነቱን ተናገርኩ።

የጊዜን ምስጢር ቀርቃሪነት ሳስብ በሌላ አጋጣሚ ከጻፍኩዋትና ለህትመት በመዘጋጀት ላይ ካለችው የግጥም መድብሌ ቀንጨብ አድርጌ ጌትሽን ልሰናበተው።

 

                                                እስክንጠይቃቸዉ እኛን ተመችቶን፤

                                                መች ይጠብቁናል በሽተኞቻችን፤

                                                ያሸልባሉ እንጂ ጠሪያቸዉ ሲመጣ፤

                                                እነርሱ ከማለፍ፤ እኛም ከመጸጸት

                                                ምን ጊዜም ላንወጣ።

                                                ይህ ይሆናል ብለን እንዳንጠረጥረዉ፤

                                                ምስጢሩን ይቀብራል ጊዜ ሸረኛ ነዉ።

 እግዚአብሄር የጌትሽን ነፍስ በገነት ያኑርልን። ለባለቤቱ ለተዋበች፤ለልጆቹና ለዘመድ ወዳጁቹ መጽናናትን በእጅጉ እመኛለሁ።

Filed in: Amharic