>

እውነታውን በማድበስበስ ከተጠያቂነት ማምለጥ አይቻልም!!! (ኢዜማ)

እውነታውን በማድበስበስ ከተጠያቂነት ማምለጥ አይቻልም!!!
ኢዜማ

የ ኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (#ኢዜማ) በአዲስ አበባ ከተማ መሬት ወረራን እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢፍትሃዊ ዕደላን በተመለከተ የሚደርሱትን ጥቆማዎች በመቀበል ጉዳዮን የሚመረምር ከብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የተወጣጣ ኮሚቴ አቋቁሞ ጥናት ሲያደርግ ቆይቷል። የጥናቱን ውጤት ለሕዝብ እና ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ ለማድረግ ዛሬ አርብ ነሐሴ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ጋዜጣዊ መግለጫ ተዘጋጅቶ ነበር።
ይህ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲዘጋጅ ከዚህ ቀደም ጋዜጣዊ መግለጫ ስንሰጥ እንደምናደርገው ሁሉ ጋዜጣዊ መግለጫው ለሚደረግበት ራስ ሆቴል እንዲሁም በደብዳቤ ቁጥር ኢዜማ/695/12 ለኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስቴር አስቀድመን አሳውቀናል።
ፓርቲያችን ሊሰጥ የነበረውን መግለጫ ለመከታተል እና ለሕዝብ ለማድረስ የተጠሩ ጋዜጠኞች ከተባሉት ሰዓት ቀድመው በአዳራሹ ውስጥ የተገኙ ሲሆን ብዙዎቹም የቀረጻ መሣሪዎቻቸውን አሰናድተው  የመግለጫውን መሰጠት በመጠባበቅ ላይ እያሉ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አባል መሆናቸውን የገለፁ የፖሊስ አባላት መግለጫው መሰጠት እንደማይቻል በማሳወቅ ጋዜጠኞቹ አዳራሹን ለቀው እንዲወጡ አድርገዋል። ፖሊሶቹ ጋዜጣዊ መግለጫውን ለማስቆም የሰጡት ምክንያት ጋዜጣዊ መግለጫው እንዲካሄድ ትዕዛዝ አልተሰጠንም የሚል ነበር።
በስፍራው የተገኙት የኢዜማ አመራሮች ሙሉ ትብብር ያደረጉ ሲሆን ስለመግለጫው ለሰላም ሚኒሰቴር በደብዳቤ ማሳወቃቸውን ለፖሊስ አባላቱ አስረድተዋል። ወደ ሰላም ሚኒስቴር በመደውልም የተፈጠረውን ለሚንስትር መስሪያ ቤቱ ያሳወቁ ሲሆን የፖሊስ አባላቱን ከሰላም ሚኒስቴር ጋርም በስልክ የማገናኘት ሥራ ተሠርቷል። ነገር ግን የፖሊስ አባላቱ መልሰው «የሰላም ሚኒስቴር ሊፈቅድ የሚችለው ስብሰባዎችን እንጂ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን አይደለም። የመግለጫ ጉዳይ የሚመለከተው ፖሊስን ነው።» በሚል መግለጫውን በመከልከል ጸንተዋል:: ይህንንም ተከትሎ የኢትዮያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በአዲስ አበባ ከተማ እየተፈፀመ ያለውን የመሬት ወረራ እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢፍትሃዊ ዕደላን አስመልክቶ የሠራውን ጥናት ውጤት ለሕዝብ ለማሳወቅ ያዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ተስተጓጉሏል።
ትላንት የአዲስ አበባ መሬት በሕገወጥ መንገድ እየታጠረ ሲወረር እና ሲዘረፍ ማቆም ያልቻሉ የሕግ አስከባሪዎች በሕጋዊ መንገድ የተጠራ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳይሰጥ አጥር ሆነዋል። የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነትን እና የሕግ የበላይነትን የሚያረጋግጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ እንደዛሬው ዓይነት እክል ትላንትናም አላስቆመንም፤ ዛሬም አያስቆመንም! የተፈጸመ ስህተት ካለ አዳምጦ ለማረም ከመዘጋጀት ይልቅ የዜጎችን እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት በማፈን እና እውነቱን በማድበስበስ ከተጠያቂነት ለመራቅ መሞከር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንቅፋት እንደሆነ ግልጽ ሊሆን ይገባል። ዛሬ በተከሰተው መግለጫውን የማስተጓጎል ተግባር እውነታውን ማድበስበስ እና ከተጠያቂነት ማምለጥ አይቻልም።
ከዚህ ቀደም የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣ የመሬት ልማት ቢሮ እና የቤቶች ልማት ኤጀንሲ በጥናታችን የደረስንበትን ውጤት አያይዘን የነሱን ምልከታ በጥናት ውጤታችን ውስጥ ለማካተት ምላሽ እንዲሰጡን ጠይቀን የነበረ ቢሆንም ሁሉም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ካለመሆናቸው በተጨማሪ የመሬት ልማት ቢሮ እና የቤቶች ልማት ኤጀንሲ የላክንላቸውን ደብዳቤም ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በጥናቱ የደረሰበትን ሕገ ወጥነት እና ኢፍትሃዊነት ሰኞ ነሐሴ 25 ቀን 2012 ዓ.ም ከሰዓት 8 ሰዓት ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል። ሀሳባችንን የመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብታችንን ለማስከበር ወደኃላ እንደማንል እና ያገኘነውን ውጤት ሕዝብ ጋር እንደምናደርስ እንዲያውቁት በድጋሚ ለኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስትር እና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ደብዳቤ ልከናል።
የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት
Filed in: Amharic