>

አማራው መስከረም 30  በሚባል የእሳት ፖለቲካ አይጫወትም!!! (ጌታቸው ሽፈራው)

አማራው መስከረም 30  በሚባል የእሳት ፖለቲካ አይጫወትም!!!

ጌታቸው ሽፈራው

 ትህነግ/ሕወሓት ምርጫ ለማድረግ እየተጣደፈ ያለው ከመስከረም 30 በፊት ምርጫ አድርጎ “መከላከያና ፖሊስ ለመንግስት መታዘዝ የለበትም” ብሎ ለመጮህ ነው።  የኦሮሞ ፅንፈኞችን ይዞ የስልጣን ሽኩቻ ውስጥ የገባው የለማ ቡድንም ይህን ጩኸት  ይፈልገዋል!
መስከረም 30 ትህነግና የኦነግ ቡድን “መንግስት የለም” ብለው ወደ ስልጣን ለመምጣት ያስቀመጡት ቀጠሮ  ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ አማራው ቁርጥ ያለ አቋም መያዝ አለበት። የመስከረም 30 ኢላማዎች ለአማራውም እጅግ አደገኛዎች ናቸው!
1) መስከረም 30 በኋላ የሚጮሁ ጩኸቶች በዋነኝነት ሁለቱን የአማራ ጠላቶች የሚያፋፉ ናቸው። የፌደራል መንግስት እንደ ስሙ ለአማራ ሕዝብ መብት የማይቆምና ሲጠቃ ፈጥኖ የማይደርስ ቢሆንም ትህነግና ኦነግ ከእሱ የባሱ ናቸው። አማራው ስለመስከረም 30 እየጮኸ የበለጡ ጠላቶች ወደ ቤተ መንግስት እንዲመጡ ሊሰራ አይችልም።
2)  የፀጥታ ኃይሉን መንግስት እያዘዝኩት ነው እያለ እንኳ አማራ ከመጠቃት አልዳነም። ጭራሽ “የፀጥታ ኃይሉ ከአሁን በኋላ በመንግስት አይታዘዝም” ቢባል  አማራ ይበልጡን ነው የሚጎዳው። እንበልና ከመስከረም 30 በኋላ የፀጥታ ኃይሉ ለመንግስት አይታዘዝም ቢባል እስካሁን ከተፈጠረው ትርምስ የባሰ ነው የሚፈጠረው። በዚህ ትርምስ ውስጥ ደግሞ ትህነግና ኦነጋዊያን እንደፈለጉ የሚፈነጩበት እድል ይፈጠርላቸዋል። ዋናው ኢላማቸው የሚሆነው ደግሞ አማራው ነው።
መታወቅ ያለበት  ትህነግ ኃይሉን ወደመቀሌ ሰብስቧል። መሃል ሀገር ያሉት አባላቱ እንዳይጎዱበት ለጊዜው የትግራይ ብልፅግና ውስጥ ተሰግስገው ደሕንነታቸውንና ጥቅማቸውን አስጠብቀው መረጃ ይመግቡታል። በስልታዊና በለመደው  መንገድም ቢሆን የራሱን ሰዎች ይጠብቃል።
የአማራ ሕዝብ ግን አሁንም እንደተበተነ ነው። ሌላው ቀርቶ ከትግራይ ሕዝብ በብዙ እጥፍ የሚበልጥ አማራ በየክልሉ ይኖራል። ይህ ሕዝብ ውጥንቅጥ ሲፈጠር ቀዳሚ ተጠቂ ነው። እስካሁን መንግስት እመራዋለሁ የሚለው ኃይል ለአማራ ባይደርስም፣ ጩከታችን እያሰማን ያለነው መከላከያ፣ ፖሊስ ስርዓት እንዲያስከብር ነው።
ከመስከረም 30 በኋላ የፀጥታ ኃይሉ ለመንግስት አይታዘዝም እያልን ችግር ሲፈጠር “መንግስት ለምን አይደርስም?” ብለን መጮህም፣ መወትወትም አንችልም። ትህነግና ኦነግ ደግሞ የበለጠ ይገድላሉ እንጅ ፀጥታ ሊያስከብሩ አይችሉም። በመሆኑም አማራው መስከረም 30 በሚባል የእሳት ፖለቲካ ሊጫወት አይችልም።
3) የአማራ ሕዝብ ከአሁን መንግስትንም ሆነ ሕገ መንግስቱን ሕጋዊ ናቸው ብሎ አያውቅም። እስካሁን የቀጠለው መንግስት ሕጋዊ ነው ያላለ ሕዝብ ደርሶ መስከረም 30 ላይ ሕገወጥ ነው ሊል አይችልም።
ትህነግ ያለፈው መንግስት አካል ስለሆነ “ሕጋዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ አሳታፊ” ብሎ የቀለደበት የ2007 ዓ/ም ምርጫ በኋላ የቀጠለውን መንግስት ሕጋዊ ነው ብሎ ስለሚያስብ ይህ ጊዜ ሲያልፍ “ሕገወጥ ነው” ቢል ያለፈውን ስርዓት ዋና አንጓ ስለሆነ ነው። ለአማራ ሕዝብ ግን ያለፈው ስርዓትም ሕጋዊ አይደለም። መስከረም 30 ላይ ደርሶ ሕገወጥ ነው ቢል እስካሁን በሰነድ ሲያጠቃው የኖረውን ስርዓት ሕጋዊ እውቅና እንደመስጠት ነው።
4) የአማራ ሕዝብ ከተበደለባቸው ጉዳዮች አንደኛው የኢኮኖሚው መስክ ነው። ባለፉት ዘመናት የአማራ ባለሀብቶች ከዋና ዋና አማራ ከተሞች ሳይቀር ተገፍቷል። ትህነግ በሆነ ባልሆነው አሳቅቆ የአማራው ባለሀብት ሕዝቡን እንዳያገለግል አድርጓል። የአማራ ሕዝብ በኢኮኖሚ እንዲደቅ አድርጓል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአማራና ሌሎች ባለሀብቶች ወደ አማራው ምድር እየተመለሱ ነው። ፖለቲካው ያለ ኢኮኖሚ ባዶ ነው። ገዥዎቹ በኢመደበኛው ኃይላቸው በኩል ሳይቀር ፖለቲካውን የተቆጣጠሩት ገንዘብ ስላላቸው ነው።
አደረጃጀት የሚፈጥሩት፣ በሚዲያ የሚያደነቁሩን፣ ጠላት የሚልኩብን ገንዘብ ስላላቸው ነው። የራሳችን ሰው የሚያሰለፉብን ገንዘብ ስላላቸው ነው። ያለ የሌለውን ጠላት የሚያደራጁት ባለፉት 30 አመታት ኢኮኖሚው  ላይም ስለሰሩ ጭምር ነው። መስከረም 30 በሚባለው ቀጠሮ ትህነግ የራሱን ክልል አጥሮ ነው ሌሎች ላይ እሳት ማንደድ የሚፈልገው።
በዚህ ውጥንቅጥ የራሱን እድል  ሲስገበገብ ቀርጥፎ የበላው ትህነግ የሌሎችንም ለማጨለም ነው የሚሰራው። አማራው ደግሞ ተስፋው የጨለመበት ትህነግና ከስልጣን የተገፋው የኦነግ ቡድን ያቀደውን መስከረም 30 ጩኸት እያሰማ የራሱን ብሩህ ተስፋ አያጨልምም።
5) ደርግ በነበረበት ችግር የአማራ ሕዝብ ለባለፈው ሶስት አስርት አመታት ሲያደሙት ከኖሩት ጋር ሆኖ ወደአራት ኪሎ አስገብቷቸዋል። “የለውጥ ኃይል ነን” ያሉትን እውነት መስሎት ለጊዜው ደግፏቸዋል።
 በእነዚህ ሁለት ሂደቶች የአማራ ሕዝብ ሀገሩን አስቀድሞ የራሱን ስሌት አላሰላም። አሁን ማንም ጥቅሙ የተነካበት ተነስቶ መንግስትን ስላዋከበ የአማራ ሕዝብ ከጎኑ ሊሆን አይችልም።   ከሁሉም በቅርብ ርቀት ሆኖ የሚያሰላው፣ የሚያስጠብቀው የራሱ ጥቅም አለው። ትህነግ ጋር ሆኖ ደርግን እንዳባረረው፣ ዛሬ ትህነግና ኦነግ ቤተ መንግስት እንዲገቡ ሊያግዝ አይችልም።
የራሱን ጥቅምና ደሕንነት ማስጠበቅ የሚችልበትን መንገድም ማሰብ አለበት።  አማራ በዚህ ወቅት በምንም ተአምር ትህነግና ኦነግ ጋር ሆኖ ጥቅሙን ማስከበር አይቻለውም።
መስከረም 30 በተባለው የሁለቱ ቀጠሮም የአማራ ጥቅም ሊከበር አይችልም።
ከዚህ ይልቅ ቀርፋፋውን፣ ከፅንፈኞች ጋር እያበረ አማራን የሚያስጠቃውን የመንግስት መዋቅር  ለራሱ በሚጠቅመው መልኩ እያጋለጠና እየታገለ  በፖለቲካውና በኢኮኖሚው እየተደራጀ ደሕንነቱን መጠበቅ፣ የቀጣይ ፖለቲካ ጉዞውን ማስተካከል ነው ያለበት።
የአማራ  ሕዝብ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ በዚህ ጉዳይ ላይ ቁርጥ ያለ አቋም መያዝ አለባቸው!”
Filed in: Amharic