>

"በኢትዮጵያ ውስጥ ወራሪ ማለት ተገቢ ባይሆንም ወራሪ የሚሉ ከሆነ ግን ወራሪ ኦሮሞ ብቻ ነው!" (ዶ/ር ላጲሶ ጌ ዴሌቦ)

“በኢትዮጵያ ውስጥ ወራሪ ማለት ተገቢ ባይሆንም ወራሪ የሚሉ ከሆነ ግን ወራሪ ኦሮሞ ብቻ ነው!”

ዶ/ር ላጲሶ ጌ ዴሌቦ

 ዶ /ር ላጲሶ የ16ተኛውን ክፍለ ዘመን የኦሮሞ ወረራ እንቅስቃሴ እንዲህ አስቀምጠውታል።
በግምት ከ1520ዎቹ እስከ 1620ዎቹ ባለው በአንድ ምዕተ-ዓመት ጊዜ ውስጥ በደቡብ ምስራቅ ከቦረና በፍለሳ (migration) ስምሪት በመንቀሳቀስ የበሩማ ኦሮሞ ጎሳዎች በምስራቅና በሰሜን በጥንቱ የባሌ፣ የደዋሮ፣ የአዳል፣ የአርጎባ፣ የፈጠጋር፣ የይፋት፣ የአንጎትና የላስታ አገሮች እስከ ትግራይ ወሰን ድረስ እንደ አካባቢው ሁኔታ በሙሉ ወይንም በከፊል ሰፈሩ።
የቦረና ጎሳዎች ደግሞ በተመሳሳይ እንቅስቃሴ በመሀል እና በመሀል-ምዕራብ በጥንቱ የሀዲያ፣ የሻርካ፣ የማያ፣ የዋጅ፣ የገበርጌ፣ የወረባ፣ የሸዋ፣ የበጌምድር፣ የደንቢያ፣ የጎጃም፣ የዳሞት፣ የጋፋት፣ በጊቤ-አባይ-ደዴሳ በነባሩ የሄናሮ (እናሪያ)፣ የአንፊሎ፣ የቦሻ፣ የዲማ፣ የቢዛሞ ወዘተ ላይ ተመሳሳይ የፍለሳና የሰፈራ እንቅስቃሴዎች አካሄዱ።
በዚህ የፍለሳና የሰፈራ (invasion and settling) የተለያዩ የኦሮሞ ጎሳዎች ከ1522 – 1530 ከቦረና አካባቢ የገላን ወንዝ ተሻግረው ከምዕራብ በኩል ወደ ባሌ አገር ደረሱ። ቀጥሎም ከ1530 -1538 የዋቢን ወንዝ ተሻግረው ሰፈሩ።
ወደፊት በመቀጠል ከ1538-1546 ባሌን አልፈው ወደ ደዋሮ ማለትም ወደ ሰሜናዊ ሐርረጌና አዋሽ ሸለቆ አካባቢ ደረሱ። ከ1546-1554 ከደዋሮ ወደ
ፈጠጋር ማለትም ወደ ዛሬው አሩሲ፣ የረርና ከረዩ አካባቢ ደረሱ።
ከ1554-1562 በአዋሽ ወንዝና በዝዋይ ሐይቅ ክልል ወደ ዋጅ ወይንም ገበርጌ ወደ ወረባ አገሮች ደረሱ። በዚህ ዘመን የኦሮሞ ሰዎች የበቅሎና የፈረስ አጠቃቀም በመማር በጦር ዝግጅትና ስልት በፍለሳ እንቅስቃሴያቸው የእድገት ለውጥ አመጡ። በደረሱበት አካባቢ ሁሉ በነዋሪነት መስፈርም ጀመሩ።
የቦረና ኦሮሞ ጎሳዎች ከ1562 – 1570 በሰሜኑ ደጋ በዛሬው ወሎና ጎንደር የዘረፋ ጦርነት አካሄዱ። ከ1570-1578 በሰሜናዊ ሸዋና በምስራቃዊ ጎጃም ዘረፋ አካሄዱ። በዚሁ ዘመን በምስራቅ የኦሮሞ # ሰፋሪዎች በሐረር አካባቢ በመቶ የሚቆጠሩ የአዳል ማለትም የሀርላ መንደሮችን አጠፉ። በሐረር ከተማም ላይ ከበባ አካሄዱ። የአዳልን መንግሥት በሐረርና በአውሳ ከፍለው መሀሉን ያዙ። ከ1578 – 1586 አመራር በሰሜናዊ ምዕራብ ወደ ደንቢያ በመሀል ምዕራብ ደግሞ ወደ ዳሞትና ጋፋት አገሮች ደረሱ።
በመጨረሻም ከ1586 -1594 ኦሮሞዎች በሸዋና በጎጃም ላይ ዘመቱ። ጦረኛው አፄ ሠርፀ-ድንግል (1563 -1597) የፍለሳውን ስምሪት ከትግራይ፣ ከበጌምድርና ከጎጃም ወደኋላ ስለመለሰው የማኅበረሰቡ (የኦሮሞ) የተለያዩ ጎሳዎች በደረሱበት አካባቢ ሁሉ በነዋሪነት የሰፈራ ሂደትና ልምድ ጀመሩ።
በተለማመዱት የሰፈራ ኑሮና በአዲስ  የእርሻ ሥራ ምክንያት በራሱ በኦሮሞ ኅብረተሰብ ዘንድ ውስጣዊ የገዳ ሥርዓት ለውጥና የገባር ሥርዓት ጥንስስ ቀስ በቀስ መታየት ጀመረ። በኢትዮጵያ ውስጥ ወራሪ ማለት ተገቢ ባይሆንም ወራሪ የሚሉ ከሆነ ግን ወራሪ ኦሮሞ ብቻ ነው!
Filed in: Amharic