>
5:13 pm - Saturday April 18, 3942

ታሪክን በተመለከተ "ብሔራዊ ንግግር" ማድረግ ከሚቸግርባቸው ምክንያቶች ውስጥ አምስቱ..!!! (በፍቃዱ ሀይሉ)

ታሪክን በተመለከተ “ብሔራዊ ንግግር” ማድረግ ከሚቸግርባቸው ምክንያቶች ውስጥ አምስቱ..!!!

በፍቃዱ ሀይሉ

ተግዳሮት ፩፣ ባለታሪክና ትውልድን መቀላቀል
1.1. የጥንት ሰዎች ጥፋት (ልማት) ሲነገር፣ በብሔር/ቋንቋ የሚመስሏቸው በሙሉ እኛ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት (ውዳሴ) ብለው ማሰባቸው። ጥፋታቸው ሲጠቀስ “እኛ ተወቀስን”፣ ልማታቸው ሲነገር “እኛ እኮ ነን” የማለት ባልነበሩበት ታሪክ በግል መሸማቀቅ እና መኩራራት። (ይህ መጥፎውን ሁሉ እንዳልተከሰተ ለመካድ ይዳርጋል።)
1.2. የጥንት ሰዎች ጥፋት የዛሬ ዘመን ሰዎች በብሔር/ቋንቋ ይዛመዷቸዋል ብሎ በማሰብ የዛሬ ዘመን ሰዎችን ተወቃሽ ማድረግ። (ይህ ለቂም በቀል እርምጃ ይዳርጋል፤ ተጠቃሚም ሆኑ ተጎጂ ትውልዶች ወላጆቻቸውን አልመረጡም።)
ተግዳሮት ፪፣ የታሪክን ውጤት ማቃለል
1.1. የታሪክ ትሩፋት – ታሪክ የራሱን ትሩፋት ትቶ ነው የሚያልፈው። አንዳንዱ ትሩፋቱ ለተወሰኑ የማኀበረሰብ ክፍሎች ከሌሎች የተሻለ ተጠቃሚነት ጥሎ ያልፋል። የተጠቃሚነቱ ትሩፋት አንዳንዴ አጭር፣ ሌላ ጊዜ ረዥም ዘመን ይዘልቃል። (ብዙዎች የትሩፋት ተጠቃሚነታቸውን ከፍትሐዊነት ጋር ይቀላቅሉታል። ለሆነ ታሪክና ባለ ታሪክ ቀና ምልከታ ይኖራቸዋል።)
1.2. የታሪክ ጠባሳ – ታሪክ ትሩፋት ብቻ ሳይሆን ጠባሳም አለው። ጠባሳውም ልክ እንደትሩፋቱ ሁሉ ለአጭር ጊዜ ወይም ለረዥም ጊዜ ሊቆይ ይችላል። (ይህ ጠባሳ በወራሾቹ ትውልዶች ላይ የአቅም ማጣት እና አለመወከል ስሜት ያዳብራል። ስለዚህ ለሆነ ታሪክ እና ባለታሪኮች ጥላቻ ያዳብራሉ።)
ተግዳሮት ፫፣ ታሪክ እና ትርክትን ቀላቅሎ መመልከት
3.1. በታሪክ ሐቆች ላይ የጎሉ ልዩነቶች የሉም። ልዩነቶች ቢኖሩም በእውነተኛ ምርምር፣ ውይይት እና ትምህርት ይቀረፋል። የጎላ ልዩነት ያለው እነዚህ የታሪክ ሁነቶችን የምንመለከትበት መንገድ ነው። የታሪክ ሁነቶች ፍቺ ከላይ በጠቀስናቸው የትሩፋቱ እና የጠባሳው ወራሾች በተለያየ መንገድ ነው የሚረዱት። ይህንን አረዳድ አንዳቸው ሌላኛቸውን አስገድደው ለመጫን መሞከራቸው አግባብ አይደለም። ታሪክ ለእያንዳንዳችን የሚሰጠን ትርጉም ሊለያይ ይችላል የሚል አቋም እና አንድ ዓይነት ትርክት ላይ ለመድረስ መሞከር ውይይቱን ፍሬ አልባ ያደርገዋል።
3.2. የታሪክ ፍቺ እና የፖለቲካ ትርክቶች ላይ የሚደረጉ ክርክሮች ከትሩፋትና ጠባሳ ወራሾች አንጻር፣ ግባቸው ቀጣዩን ስርዓት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍትሕ እንዴት እናስፍን በሚል ግብ መሆን ይኖርበታል።
ተግዳሮት ፬፣ የጥንትን ታሪክ በዛሬ ዘመን ዓይን መመልከት፣
የታሪክ ወራሾች ጉዳይ (የትሩፋት እና ጠባሳው ወራሾች ጉዳይ) ነጭና ጥቁር አይደለም። የትኛውም ሕዝብ ወጥ ማንነት አልነበረውም፣ የለውም፣ አይኖረውምም። ስለዚህ ዛሬ በብሔር እየደረደርን የምንመለከታቸው ቡድናዊ አመለካከቶች ታሪካዊ ሐቆችን ሊገድፉ ይችላሉ። ታሪክ አንድ ቦታ የረጋ ሳይሆን ጊዜን እየስገበረ የሚጓዝ ወንዝ ነው። ዛሬ ስለታሪክ የሚያነታርኩን እና የሚያኩራሩን ጉዳዮች የዛሬ መቶ እና ሺሕ ዓመት ፍፁም የተለዩ ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ እርግጠኝነትን መቀነስ፣ ባለሙያዎን ማሳተፍ እና ከተለያዩ አንግሎች መመልከት ይጠቅማል።
ተግዳሮት ፭፣ ታሪክን በነገሥታት ዓይን መቃኘት
5.1. ታሪክ የነገሥታት የሥልጣን እና የግዛት ማስፋፋት ተጋድሎን ብቻ ሳይሆን ተገዢዎች ላይ የሚያሳድረውንም ተፅዕኖ ያካትታል። ከዚህም ባሻገር ድርቅና ቸነፈር፣ ወረርሽኞች፣ ንግድ እና ቴክኖሎጂ፣ ፍልሰት፣ ወዘተ… የታሪክን እውነተኛ ገጽታ አመላካቾች ናቸው። እነዚህን የገደፈ የታሪክ አረዳድ እና ትርክት ለእውነታው የቀረበ አረዳድ አይኖረውም።
5.2. ታሪክን በአሸናፊ ጦረኞች ዓይን ብቻ ሳይሆን በተሸናፊና ገባሪዎችም ዓይን መተረክ እና መመልከት ያስፈልጋል። ታሪክ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የግንኙነት ውጤት እንጂ የአንድ ወገን ቀጥተኛ ግስጋሴ አይደለም። ይህንን አለመገንዘብ የታሪክ ውጤት ላይም ሊኖር የሚችለውን ልዩነት መገንዘብ እንዳይቻል ያደርጋል።
መደምደሚያ
እንኳን በትላንት ታሪክ በዛሬ ዜና ላይ እንኳን እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ታሪክ እና ትርክት ከፖለቲካ ተዋስኦ የማይወገዱ በመሆኑ አረዳድን ስለማስተካከል እንጂ “መግባባት” ላይ ስለመድረስ መወያየት ይቻላል ወይም የግድ ያስፈልጋል ማለት አይደለም። ይልቁንም መግባባት ላይ መድረስ የሚቻለው የወል ችግሮች የሆኑ ድህነት እና ኋላ ቀርነት እንዴት ይቀረፉ በሚለው ላይ ነው።
የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች በሐቀኝነት መነጋገር ያለባቸው «ሁሉም የሚገዙለት የጫወታ ሕግ ምን ይሁን?» በሚለው ጉዳይ ነው። ቀሪው በምሁራን የተመራ ጫፍ አልባ ንግግር የሚፈልግ፣ እያደገ እና እየታደሰ የሚሔድ ነገር ነው። አንድ ቀን፣ አንድ አዳራሽ ውስጥ፣ በጥቂት ታዋቂ ሰዎች የሚደረጉ ውይይቶች መጀመሪያው እንጂ መጨረሻው መሆን የለበትም።
Filed in: Amharic