>

በዓለ ደብረ ታቦር !!   (ቡሄ)  - ሀብታሙ አያሌው

በዓለ ደብረ ታቦር !!   (ቡሄ) 

ብታሙ አያሌው

ደብረ ታቦር ከገሊላ ባሕር በምዕራባዊ በኩል 10 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ተራራ ሲሆን፤ ከፍታው ከባሕር ወለል በላይ 572 ሜትር ይሆናል፡፡ በዚህ ተራራ ላይ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን እንደሚገልጽ ምሳሌና ትንቢት ተነግሯል፡፡ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በትንቢቱ “ታቦርና አርሞንኤም በስም ደስ ይላቸዋል” ብሎ የተናገረው ትንቢት እንዲፈጸም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተአምራቱን በዚህ ተራራ ላይ ገልጧል /መዝ. 88፥12/፡፡ በዘመነ መሳፍንት ባርቅ ሲሣራን ከነሠራዊቱ ድል ያደረገው በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ነው፡፡ ምሳሌነቱም ባርቅ የጌታችን ሲሣራ ደግሞ የአጋንንት ነው፡፡ ጌታችን በደብረ ታቦር ክብሩን በመግለጥ በአይሁድ እያደረ አምላክነቱን እንዲጠራጠሩ ያደረጋቸውን አጋንንት ድል የማድረጉ ምሳሌ ነው /መሳ. 4፥6/፡፡
     ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን በቂሳርያ “የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?” ብሎ ከጠየቃቸው ከስድስት ቀን በኋላ አዕማድ ተብለው የሚጠሩ ሦስቱን ሐዋርያት ይዞ ወደ ረጅም ታቦር ተራራ ወጣ፡፡ በፊታቸውም ተለወጠ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ፡፡ እነሆም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ መልሶ ጌታችን ኢየሱስን ጌታ ሆይ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፡፡ ብትወድስ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱን ለሙሴ አንዱን ለኤልያስ በዚህ እንሥራ አለ፡፡ በዚህ ጊዜ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፡፡ ከደመናውም በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፡፡ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ ተሰማ፡፡ ሐዋርያት ይህንን ሰምተው የጌታችንን መለኮታዊ ክብር አይተው በፊታቸው ወደቁ እጅግ ፈርተው ነበር፡፡ ጌታችንንም ተነሡ አትፍሩም አላቸው፡፡ በዚህ መልኩ አምላክነቱን ገለጠላቸው /ማቴ. 17፥1-10/፡፡
አዕማደ (የምስጢር) ሐዋርያት ለምን ተመረጡ?
     አዕማደ ሐዋርያት ተብለው የተጠሩት ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ናቸው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ያዕቆብን “አዕማድ ሐዋርያት” እያለ ጠርቷቸዋል /ገላ. 2፥9/፡፡ ስያሜውን ያገኙበት ዋናው ምክንያት የኢየሩሳሌምን ቤተ ክርስቲያን በሓላፊነት ያስተባብሩ ስለነበረ ነው፡፡ ከዚህን በተጨማሪ ጌታችን በኢያኢሮስ ቤት ልጁን ሲፈውስ፣ በጌቴ ሴማኒ ሲጸልይና በደብረ ታቦር ምስጢረ መለኮቱን ሲገልጥ ከእሱ ስላልተለዩና ይዟቸው ስለሔደ ነው /ማር.5፥37-43/፡፡
ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሦስቱ ደቀ መዛሙርት የተመረጡበትን ምክንያት ሲያትቱ እንዲህ ብለዋል፡፡ ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ሹመት፣ ሽልማትና ክብር ፈላጊዎች ነበሩ፡፡ ከዚህ ሃሳብ እንዲወጡ ከብልየታቸው እንዲታደሱ ለይቶ አውጥቷቸዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ለድኅነተ ዓለም የመጣው በሕማማቱ በሞቱ ቤዛ የሚሆነን አምላክ “ልሰቀል ነው” ባላቸው ጊዜ “አይሁንብህ” ብሎት ነበር፡፡ እንዲህ ያለው ሃሳብ የጠላት እንጂ የሰው ልጆች ሊሆን አይችልም ከሞቱ በቀር ድኀነት ሊያስገኝልን የሚችል የለምና፡፡ ደቀ መዝሙሩ ግን ከሞተ ክብሬ ምንድን ነው ብሏልና “አይሁንብህ” አለ፡፡ /ማቴ. 16/ በሌላም ስፍራ እንዲሁ “ሁሉን ትተን ተከተልንህ እንግዲያስ ምን እናገኝ ይሆን?” በማለት ይጠይቃል፡፡ /ማቴ.19/፡፡ ጌታ ግን ዋጋችሁ ሰማያዊ ክብራችሁ ዘላለማዊ ነው ሲል እስከ ፍጹማን መዓርግ /ነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ/ አድርሶ ብርሃነ መለኮትን ገልጦ ተስፋውን ነገራቸው፡፡
    “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም” እንዲል /ሚል 3፥6/ በእርሱ ዘንድ ወረት የለም፡፡ አስቀድሞ ከተዓምራቱ ከምሥጢሩ አይለያቸውም ነበርና ብርሃነ መለኮትን ለማየት አበቃቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ለማወቅ፣ ለመማር፣ ለመጠየቅ ያሳዩት ትጋት ምስጢር ተገልጦላቸዋል፡፡ ይህ ምስጢር ለሦስቱ ደቀ መዛሙርት ተገልጦ የሚቀር አይደለም፡፡ እስከ ዓለም ፍፃሜ እግዚአብሔር ለመረጣቸው ሲገለጥ፣ በመረጣቸውም ሲነገር የሚኖር ነው፡፡
 ደቀ መዝሙሩ ጴጥሮስ “አልክድህም አልተውህም” የሚለው /ማቴ. 26፥35/ ቢወድደው አይደለምን? ፍቅሩን መግለጡ ለክብር አብቅቶታል፡፡ ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም “ጽዋዬን ልትጠጡ አትችሉም” ቢላቸውም /ማቴ. 20፥22/ አንዳችን በቀኝ ሌላችን በግራ ሆነን አብረንህ እንሞታለን ሲሉ በምስጢር ለምነዋል፡፡ ሞታቸውን ከሞቱ ጋር መደመራቸው ፍቅራቸውን መግለጣቸው ነው፡፡
             ከተራራው ግርጌ
ከቅዱሱ ተራራ ግርጌ ዘጠኙ ደቀ መዛሙርት ተቀምጠዋል፡፡ ነቢዩ “አቤቱ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰውስ ተራራህ ማን ይኖራል” /መዝ.14፥1/ በማለት ጠይቆ ወደ ተቀደሰው ተራራ የሚወጡ ሰዎች ምን ዓይነት ሕይወት ያላቸው ሊሆን እንደሚገባ ሲገልጥ “… በአንደበቱ የማይሸነግል፤ በባልንጀራው ላይ ክፉትን የማያደርግ … በንፁሑ ላይ መማለጃን የማይቀበል ….” በማለት የጠቀሳቸው ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ /መዝ. 14፥1-5/ ወደ ቅድስናው ስፍራ ወጥቶ ምስጢር ለማየት ብቃት ያልነበረው ይሁዳን ለመለየት አምላክ ባወቀ ዘጠኙን ከተራራው ግርጌ አቆይቷቸዋል፡፡
“የኃጥእ ዳፋ ጻድቁን ያዳፋ” የሚል ብሂል አለ፡፡ ይህ አባባል ግን ከተራራዉ ግርጌ ለቀሩት ደቀ መዛሙርት አይሆንም፡፡ ይሁዳን በጥበብ ከምስጢር ለየው እንጂ ጌታ ስምንቱ ደቀ መዛሙርቱን የምስጢሩ ተካፋይ አድርጓቸዋል፡፡ ለጥፋቱ ምክንያት እንዳያገኝ ከምስጢሩ ቢለየኝ ከሞቱ ገባሁበት እንዳይል በጥበብ ይህን አደረገ፡፡ ስምንቱ ደቀ መዛሙርት ግን በንጹሕ ልቡና ከተራራው ግርጌ ተቀምጠውም ምስጢር አልተከለከላቸውም፡፡ ምክንያቱም “ልበ ንጹሐን ብፁዓን ናቸው እግዚአብሔርን ያዩታልና” /ማቴ.5/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ እግዚአብሔርን ለማየት ለሚወዱ “ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚቻለው የለምና” እንዲል፡፡ /ዕብ.11/፡፡
  ሙሴና ኤልያስ ለምን ተመረጡ?
    ሙሴንና ኤልያስን ወደ ደብረ ታቦር እንዲመጡ ያደረገበት ምክንያት የባሕርይ አምላክ መሆኑን እንዲመሰክሩ ነው፡፡ ሙሴን ከመቃብር ተነሥቶ ስለጌታችን እንዲህ የሚል ምስክርነት ሰጥቷል፡- “እኔ ባሕር ብከፍልም፤ ጠላት ብገድልም፤ ደመና ብጋርድም፤ መና ባወርድም እስራኤልን ከክፋታቸው መልሼ ማዳን ያልተቻለኝ ደካማ ነኝ፤ የእኔን ፈጣሪ እንዴት ሙሴ ይሉሃል? የሙሴ ፈጣሪ እግዚአብሔር ይበሉህ እንጂ!” ኤልያስም ደግሞ ከብሔረ ሕያዋን መጥቶ “እኔ ሰማይ ዝናብ እንዳይሰጥ ብለጉም፣ እሳት ባዘንብም፣ እስራኤልን ከክፋታቸው ማዳን የማይቻለን ነኝ እንዴት የእኔን ፈጣሪ ኤልያስ ነህ ይሉሃል? የኤልያስ ፈጣሪ እግዚአብሔር ይበሉህ እንጂ!” ብለው የባሕርይ አምላክነቱን በደብረ ታቦር ላይ መስክረዋል፡፡ በማቴ.16፡14 ላይ “አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት።” ይላልና፡፡
ሙሴና ኤልያስ የተመረጡበት ሌላው ምክንያት ሙሴ “ጀርባዬንም ታያለህ፤ ፊቴ ግን አይታይም”  ተብሎ ስለተነገረለት /ዘጸ.33፡23/ ኤልያስ “በኋለኛው ዘመን ምስክሬ ትሆናለህ” ስለተባለ ያንን ለመፈጸም ነው፤ ካገቡት ሙሴን ከደናግል ኤልያስ ያመጣቸው መንግሥተ ሰማያት በሕግ የተጋቡ ሕጋውያንና ሥርዐት ጠብቀው የሚኖሩ ደናግላን እንደሚወርሷት ለማስተማር ሁለቱን መርጧቸዋል፡፡
 የደብረ ታቦር ምሳሌነት
  የወንጌል ምሳሌ ነው፡፡ ተራራ ሲወጡ በጣም ያስቸግራል፤ ከብዙ ድካምና ውጣ ውረድ በኋላ ተራራውን ጨርሰው ከላይ ሲወጡ ግን አባጣ ጎባጣውን ሜዳና ገደሉን ያሳያል፡፡ ወንጌልንም በሚገባ ከተማሯት ጽድቅን ከኃጢአት ለይተን እንድናውቅ ታደርገናለች፡፡
ለቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡ በደብረ ታቦር ምስጢረ ሥላሴ እንደተገለጠ በቤተ ክርስቲያንም የቅድስት ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ይነገርባታል፡፡ ተራራ መሠረቱ ከመሬት አናቱ ከሰማይ እንደሆነ ሁሉ፤ ቤተ ክርስቲያንም መሠረቷ በምድር ሲሆን ራሷ በሰማይ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮቿ የተጠሩት ከምድር (ከዓለም) ሲሆን ክብራቸው ግን በሰማይ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እኛስ ሀገራችን በሰማይ ነውና›› እንዲል /ፊልጵ. 3፥20/፡፡
 የደብረ ታቦር ተራራ ይህን ሁሉ ምስጢር የያዘ በመሆኑ በክርስትና ታሪክ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ደብረ ታቦር ምሥጢረ መለኮት የተገለጠበት፣ ከዘጠኙ የጌታችን ዐበይት በዓላትም አንዱ ነው፤ በምእመናንም ዘንድ ቡሔ ይባላል፡፡ የቡሔ በዓል ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ የያዘ በመሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት ልናከብረው ይገባናል፡፡
 ቡሄ
 ቡሄ ማለት ብራ፣ ብርሃን፣ ደማቅ ማለት ነው፡፡ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት በዓል የሚዘከርበት እና ለበዓሉም ችቦ ስለሚበራ የብርሃን በዓል በማለት የቡሄ በዓል እንላለን፡፡
ወቅቱ የክረምት ጨለማ አልፎ የብርሃን ወቅት፤ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚለወጥበት፤ የመሸጋገሪያ ወቅት ነው፡፡ “ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት” እንዲሉ፡፡ በሌላ በኩልም “ቡኮ/ሊጥ” ተቦክቶ ዳቦ የሚጋገርበት “ሙልሙል” የሚታደልበት በዓል በመሆኑ ቡሄ ተብሏል፡፡
    ጅራፍ
  በደብረ ታቦር በዓል በትውፊታዊ መልኩ የሚታየው ምስጢር በኢየሩሳሌም ስለሚሆነው የጌታችን ምስጢራዊ ሞቱ ነው፡፡ ጅራፍ መገመድ እና ጅራፍ ማጮኽ ሁለት ዓይነት ምስጢር ይዞ የሚከወን ትውፊታዊ ተግባር ነው፡፡ የመጀመሪያው ግርፋቱንና ሞቱን እናስብበታለን፡፡ እንዲሁም ድምፁን ስንሰማ የባሕርይ አባቱን የአብን ምስክርነት ቃል፣ እንደ ነጎድጓድ ድምፅ ያስታውሰናል፡፡
የጅራፍ ትውፊታዊነት /ውርስ/፣ መጽሐፋዊ ትምህርትና ምስጢር ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ጨዋታውን በተራራማ አካባቢ፣ ከመኖሪያ ቤት ርቆና፣ በሜዳ ማድረጉ ጠቃሚ ነው፡፡ ጅራፍን በርችት መቀየር የሚያመጣውን የምስጢር ተፋልሶ ብቻ መመልከት ከማኅበራዊ ጎጂ ገጽታው በላይ እንድናስወግደው ያስገድደናል፡፡
 ችቦ
  ችቦ የጌታችንን ብርሃነ መለኮት መገለጥ የሚያመለክት ነው፡፡ በመሆኑም ችቦ ለኩሰን በዓሉን እናከብራለን፡፡ የዚህ ትውፊታዊ የት መጣ ግን በብርሃኑ ድምቀት የቀኑን መምሸት ያልተረዱ እረኞች በሜዳ ቀርተዋልና ወላጆች ከመንደር ችቦ ለኩሰው ልጆቻቸውን ፍለጋ ሔደዋልና ታሪኩን እያዘከርን በዓሉት እናከብራለን፡፡ የችቦው መንደድም ሌላ ትርጉም አለው፡፡ አንድ ምእመን ለሌላው ምእመን መካሪ አስተማሪ መሆኑን፣ መከራ እየተቀበለም አርአያ ምሳሌ ብርሃን መሆኑን ያሳያል፡፡ በሃይማኖትም አርአያ ምሳሌ ይሆንላቸዋል፡፡
 ሙልሙል
   በችቦ ብርሃን ልጆቻቸውን ፍለጋ የወጡ ወላጆች ዳቦ ጋግረው ይዘውላቸው ወጥተዋል፡፡ ስጦታው ቤተሰባዊነትን፣ ፍቅርንና መተሳሰብን መግለጫ ነው፡፡ ወደ ቤታችን “ቡሄ” እያሉ ለሚመጡ አዳጊዎችም ዘምረው እንዳበቁ የሚሰጥ “ሙልሙል” ዳቦ አለ፡፡ ሕፃናቱም ሊዘምሩ ሲመጡ ዳቦ መስጠት ልማዳዊ ብቻ አይደለም፡፡ ሕፃናቱ የደቀመዛሙርት ምሳሌ ናቸው፡፡ መዝሙራቸው ደግሞ ሐዋርያት “የምሥራች” ይዘው የመምጣታቸው ምሳሌ ነው፡፡ ሐዋርያት በገቡበት አገር አስተምረው አጥምቀው የጸጋ ልጅነትን አሰጥተው በረከት አድለው እንደሚሔዱም፣ ልጆችም ዘምረው፣ አመስግነው፣ መርቀው “ውለዱ ክበዱ፣ ሀብት አግኙ፣ የመንግሥተ ሰማያት ወራሾች ያድርጋችሁ ….” ይላሉ፡፡
     መልካም : በዓል : ያድርግልን
Filed in: Amharic