>

«አብይ አህመድ የወያኔ ዘመኑን የፍርድ ቤት ድራማ አጠናክሮ ቀጥሎበታል ...!!! (አሳፍ ሀይሉ)

«አብይ አህመድ የወያኔ ዘመኑን የፍርድ ቤት ድራማ አጠናክሮ ቀጥሎበታል …!!!

አሳፍ ሀይሉ

* … አቡነ ጴጥሮስ በመትረየስ ሲረሸኑ፣ በላይ ዘለቀ በአደባባይ ሲሰቀል፣ እነ ጄነራል አማን አንዶም ቤታቸው በታንክ ሲጨፈለቅ፣ እነ ፋንታ በላይ በተሸሸጉበት በጥይት ሲቆሉ፣ እነ እስክንድር ሲታሰሩ፣ ሲፈቱ፣ ሲወቀጡ፣ ዝም ብሎ ከሩቅ ባሻጋሪ እየተመለከተ የተቀመጠ ህዝብ – አሁንም ገና ብዙ ግፍ እጁን አፉ ላይ ጭኖ ‹‹ጉድ›› እያለ ያሳልፋል፡፡ ግፍን የሚጠላ ማኅበረሰብ እስካልተፈጠረ ድረስ ግፍና ግፈኞች ይቀጥላሉ!!!
*   *   *
«በእነ እስክንድር ላይ ከመጋረጃ ጀርባ የቀረቡት የማይታውቁ ምስክሮች በመጋረጃ ውስጥ ተደብቀው በድምፅ ማጉያ መስክረዋል። ሁሉም ምስክሮች የሚሉት እነ እስክንድር ቄሮ አብያተክርስቲያናትን ሊያጠቃ ነውና ቤተክርስቲያንን ጠብቁ ተከላከሉ ብለዋል የሚል ነው:: በቤተ ክርስቲያን ላይ ቄሮ ጥቃት ሊፈጽም ነውና ቤተክርስቲያናችሁን ተከላከሉ ብሎ እስክንድር 500,000 ብር በጀት ይዞ እንደነበር እስክንድር ራሱ ነግሮናል የሚል ውሸት መስክረዋል። ሰዎቹ ግን ከእነ እስክንድር ጋር ተገናኝተው አያውቁም:: ነገም ደግሞ ሌሎች የውሸት ምሰከሮች እንደሚመሰከሩባቸዉ ታውቋል:: እነ አስክንድር የፍርድ ቤት ድራማውን ዝም ብለው ከማዳመጥ ውጭ የሚናገሩት የለም። ጠበቃም የለም መናገርም የለም።»
ይህ መረጃና አስተያየት ዛሬ ዶ/ር ሰማኸኝ ጋሹ አበበ በፌስቡክ ገፁ ያካፈለው ነው፡፡
            —
ይሄን ነገር ሳስብ የግድ ጥቂት እንድል ገፋፋኝ፡፡ በነገራችን ላይ ቄሮም ሆነ ማን ቤተክርስትያንን ሊያጠቃ ሲመጣ መከላከል መብት አይደለም ወይ? ሌላ ቀርቶ አንድ ሰው ወይም ቡድን በወንጀል ድርጊት ላይ መሰማራቱን እያየ እያወቀ ዝም ብሎ መተው፣ እንዳላየ ማለፍ፣ ለማስቆም አለመሞከር፣ አለመጠቆም፣ ንብረትን ወይም ህይወትን ከፍ ካለ አደጋ ለመከላከል አለመሞከር ራሱ እኮ ወንጀል ነው፡፡ በተለይ በኦሮሚያ እንደታየው የሙያ ኃላፊነት ያለባቸው ሰዎች እንደ ፖሊስ ወይ ሀኪም ወይም ሌሎች የህግ አስከባሪ አካላት – ወንጀል እየተፈፀመ እያዩ እንዳላየ ሆነው በማለፋቸው – እንዲያውም ከሌላው ሰው በተለየ ከፍ ያለ ወንጀል እንደሠሩ ነው የሚቆጠረው፡፡ እና ቄሮ ቤተክርስትያንን ሊያጠቃ ሲመጣ መከላከልማ መብት ብቻ ሳይሆን የዜግነት ግዴታም ጭምር ነውኮ! እና ምኑ ነው ይሄ ወንጀሉ!? እነ ነውር አያውቁ፣ እነ ይሉኝታ አያውቁ! ንብረታችሁን ጠብቁ፣ ቤተክርስትያንን ጠብቁ – ማለት ወንጀል የሆነበት ዘመን! የጉድ ሀገር!
ነገሩ – መረገጥንና መዋረድን የመረጠና የለመደ ህዝብ ገና ከዚህም በላይ ብዙ የሚሆነውና የሚሰማው ነገር አለ! አንዳንዴ እንደ እነ እስክንድር ዓይነቱ የሚደርስባቸውን እንግልትና ግፍ – እና የሚታገሉለትንና የቆሙለትን ህዝብ ምንቸገረኝነትና ራስወዳድነት ላስተዋለ – ለየትኛው ህዝብ ነው የምታገለው? ብሎ ራሱን ደጋግሞ ለመጠየቅ መገደዱ እንደማይቀር ይሰማኛል! እስክንድር ለራሱ ጥቅም ቆሞ አይደለም የታሰረው፡፡ ለህዝቡ፣ በተለይም ለአዲሳባ ህዝብ ጥቅምና መብት በመቆሙ ነው፡፡ የቆምክለት ሰው ለአንድ ቀን እንኳ ለአንተ ለመቆም ፈቃደኛ ያልሆነ ሰው ከሆነ – ለማን ነው መስዋዕትነት የሚያስፈልገው? ሰዉ ለመብቱ እንዲቆም ገና ብዙ ይቀረዋል! ብዙ ግፍ! እስከዚያ እነ እስክንድር የህዝቡን መስቀል ተሸክመው ያለአመስጋኝና አይዞህ ባይ ብቻቸውን ይሰቃያሉ!
ሰዉ ራሱን ከሰው በታች አውሎታል! እና ያን ለምዶታል! መቃብርም ይሞቃል! ምን ይደረጋል? – ቁጭትና ብስጭት ብቻ ነው የተረፈን! ፈጣሪ አዕምሮ፣ ልቦናና ክብር ያለው ዜጋ ያምጣልን – ብሎ ከመመኘት በቀር – ግፍን የመረጠና የወደደ ማኅበረሰብ ውስጥ እየኖሩ – የሚደረግ አንዳች ነገር ያለ አይመስለኝም! አንዳንዴ – እንደ እነ ዶ/ር ብርሃኑ ዓይነት ስንት ነገር ህዝቡ ተስፋ የጣለባቸው ሰዎች – ሁሉን ነገር እርግፍ አድርገው የገዢው ተለጣፊ ሆነው እጃቸውን አጣጥፈው ሲቀመጡ ስናይ ብዙዎች እጅግ ይገርመን ነበር፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ – ህዝቡ እንዲህ ቢሆንባቸውኮ ነው! ህዝቡ ሙት መሆኑን አውቀው – ከዚህ ህዝብ ጋር መታገልም፣ ይህን በልቦናው የሞተ ህዝብ ይዞ መነሳትም፣ ለውጥ ማምጣትም እንደማይቻል እውነታውን ተረድተውት ከሆነስ?? በህዝቡ ተስፋ ቆርጠው ከሆነስ? ህዝቡን በተግባር ፈትነው – ከብዙዎቻችን በላይ – በትክክል አውቀውት ገብቷቸው ከሆነስ? ያስብላል፡፡
በማንም አልፈርድም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ምን እንደነካው ፈጣሪ ብቻ ይወቅልን! ፋሺስቱ ግራዚያኒ በዚህ ወቅት ደግሞ አዲስ አበባ ጦሩን አስከትቶ ቢመጣ – ህዝቡ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ ዘንባባ እየጎዘጎዘ እንደማይቀበለው ምንም ማረጋገጫ የለንም! በእነ እስክንድር ላይ እየሆነ ያለው ሁሉ እጅግ ያሳዝናል፣ ያንገበግባል፡፡ ልክ ወገን እንደሌላቸው ነው የሆኑት፡፡ ዛሬ ወጥቶ መጮህ ያቃተው ህዝብ፣ ነገ ወጥቶ ሌላ ትግል ያደርጋል ብሎ ተስፋ ማድረግ – ‹‹የሞተውን አባባ ይሉታል›› እንደተባለው ነው የሚሆነው፡፡ ፈጣሪ የጠፋብንን ኢትዮጵያዊ ነፍስ ይመልስልን ከማለት ሌላ ምንም የምለው የለኝም!
መቼም አንድ ቀን ግፉ በዝቶ ሞልቶ መፍሰሱና – ለግፈኛውም መድረሱ አይቀርም! እስከዚያው እንደለመድነው የሚሆነውን ሁሉ ባሻጋሪ ቆሞ መመልከት ነው፡፡ አቡነ ጴጥሮስ በመትረየስ ሲረሸኑ፣ በላይ ዘለቀ በአደባባይ ሲሰቀል፣ እነ ጄነራል አማን አንዶም ቤታቸው በታንክ ሲጨፈለቅ፣ እነ ፋንታ በላይ በተሸሸጉበት በጥይት ሲቆሉ፣ እነ እስክንድር ሲታሰሩ፣ ሲፈቱ፣ ሲወቀጡ፣ ዝም ብሎ ከሩቅ ባሻጋሪ እየተመለከተ የተቀመጠ ህዝብ – አሁንም ገና ብዙ ግፍ እጁን አፉ ላይ ጭኖ ‹‹ጉድ›› እያለ ያሳልፋል፡፡ ግፍን የሚጠላ ማኅበረሰብ እስካልተፈጠረ ድረስ ግፍና ግፈኞች ይቀጥላሉ፡፡ ግፍን እስክንጠላ ድረስ ያው መሸከም ነው፡፡ ፈጥሮብን – ቢጭኑት አህያ፣ ቢጋልቡት ፈረስ፣ ቢረግጡት መሬት… ሆነናል አንዴ! ምን ይደረጋል!? መቻል ነው!
ለዶ/ር ሰማኸኝ መላ ትኩረቱን ሰጥቶ በየጊዜው ሳይታክት ለሚያካፍላቸው ምጥን ያሉ እጅግ ጠቃሚ ሃሳቦች እንደ አንድ የማደንቀው አክባሪው ምስጋና ይድረሰው ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ፈጣሪ አብዝቶ ይባርከው፡፡ እንደ እሱ ያሉ ለሀገርና ለህዝባቸው ሃላፊነትና መቆርቆር ያደረባቸው ኢትዮጵያውያንን ያብዛልን!
«You might imprison peaceful freedom fighters like Eskinder Nega and others. But it doesn’t mean that you can imprison freedom! It means that, you’ll come up with freedom fighters that don’t answer peacefully.»
«ዛሬ እንደ እነ እስክንድር ነጋ የመሠሉ ሠላማዊ የነጻነት ታጋዮችን ልታስር ትችላለህ፡፡ ይህ ማለት ነፃነትን አስረህ እስከ መጨረሻው ትዘልቃለህ ማለት አይምሰልህ፡፡ ለሠላማዊ ንግግር መስሚያ ጆሮ የሌላቸውን ቁርጠኛ የነፃነት ታጋዮች ታፈራለህ ማለት ነው፡፡»
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ልጆች ሁሉ አብዝቶ ይባርክ!
መልካም ጊዜ፡፡
Filed in: Amharic