>
5:13 pm - Monday April 19, 9075

መንግሥት ሰላም በማስፈን አገር ማረጋጋት ግዴታ ነው! (ደሳለኝ ወንበቶ)

መንግሥት ሰላም በማስፈን አገር ማረጋጋት ግዴታ ነው!

ደሳለኝ ወንበቶ
የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ ከሚወስኑ መሠረታዊ ነገሮች መካከል አንዱና ዋነኛው ሰላም ነው፡፡ የአገር ህልውናም ሆነ የሕዝብ ደኅንነት የሚወሰነው በሰላም ነው፡፡ ሰላም ከሌለ መንግሥት አይኖርም፡፡ ይኖራል ተብሎ ቢታሰብ እንኳ የጉልበተኞች ስብስብ ነው የሚሆነው፡፡ ሰላም የህልውና ዋልታና ማገር ቢሆንም በቀላሉ የሚገኝ ግን አይደለም፡፡ ሰላም እንዲሰፍን በሕዝብ መካከል መተማመን ሊኖር ይገባል፡፡ ልሂቃን በአገር ጉዳይ በግልጽ መነጋገር መቻል አለባቸው፡፡ ልዩነቶች በእኩልነት ተስተናግደው የተሻለ ሐሳብ ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችለው ሰላም ሲኖር ነው፡፡ ዋናው ጥያቄ ግን ሰላም እንዴት ይስፈን የሚለው ነው፡፡ ከግለሰብ ጀምሮ አገርን እስከሚመሩ ሰዎች ድረስ ለሰላም ትልቅ ዋጋ መስጠት አለባቸው፡፡
መንግሥት ጥያቄዎች ቀርበውለት በሕጋዊ መንገድ መመለስ ሲኖርበት ዳተኛ ከሆነ፣ ጥያቄ አቅራቢዎች ሌላ አማራጭ ሲፈልጉ ግጭት ይፈጠራል፡፡ በሕጋዊ መንገድ ጥያቄዎችን ማቅረብ ያለባቸው ኃይልን ተጨማሪ አማራጭ ሲያደርጉ፣ መንግሥት ሕግ ለማስከበር ሲል የኃይል ዕርምጃ ውስጥ ይገባል፡፡ ግለሰቦች በማኅበራዊ ትስስሮችም ሆነ በተለያዩ ዘዴዎች ሐሰተኛ ወሬዎችን ሲያሠራጩ፣ በስሜት የሚጋልቡ ሰዎችን በማነሳሳት ጥፋት እንዲፈጸም ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን በሠለጠነ መንገድ ለመነጋገር ሲቻል ልዩነት ቢኖር እንኳ የጋራ አማካይ መፍጠር አያዳግትም፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ ከእጅ እያመለጠ ያለው ፀጋ ይህ ነው፡፡ ለዚህም ነው መንግሥት አገር ሰላም እንዲሰፍን ጠንክሮ መሥራት ያለበት፡፡ ግዴታውም ነው፡፡
ከመንግሥት ጀምሮ እስከ እያንዳንዱ ግለሰብ ድረስ ከብሽሽቅ ፖለቲካ ውስጥ መውጣት ያስፈልጋል፡፡ በአገር ህልውና ላይ መቆመር የሚፈልጉ ግለሰቦችና ስብስቦች የብሽሽቅ ፖለቲካውን የሚያደሩት፣ ለገዛ ጥቅሞቻቸው ሲሉ እንጂ ለሕዝብ ጥቅም እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ለአገር አንዳችም አስተዋጽኦ አበርክተው የማያውቁ ወገኖች በሕዝብ ስም ሲነግዱ፣ ለሚፈጠረው ቀውስ ኃላፊነት አይወስዱም፡፡ ይልቁንም ከቀውሱ ለማትረፍ ይፈልጋሉ፡፡ እያደረጉ ያሉትም ይኼንን ነው፡፡ የመንግሥት ሥልጣን ይዘው ቀውስ ፈጣሪዎችን የሚፈሩ ወይም የሚታዘዙ አሉ፡፡ በሕግ የተሰጣቸውን ሥልጣንና ኃላፊነት በመተላለፍ ሕገወጥ ድርጊት የሚፈጽሙም አሉ፡፡ የመንግሥት ሥልጣንን ለግልና ለቢጤዎች ጥቅም ማግበስበሻ የሚያደርጉም እንዲሁ፡፡ በዚህ መሀል ተገፍተናል የሚሉ ወገኖች ቅሬታ ሲያቀርቡ ወይም መብቶቻቸውን ሲጠይቁ፣ የብሽሽቅ ፖለቲካውም ይጀመራል፡፡ ብሔር፣ እምነት፣ የፖለቲካ አቋምና ቋንቋ ሳይቀሩ ለግብዓትነት ይውላሉ፡፡ ፖለቲካው መሠልጠን ሲገባው የመንደር ጨዋታ ይመስል በየጎራው መሰዳደቡ፣ ዛቻውና ማስፈራራቱ የበላይነት ይይዛል፡፡ እንኳንስ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሠረት ለመጣል ለአገር ህልውና አደገኛ የሆኑ የቃላት ጦርነቶች ይጀመራሉ፡፡ የብሽሽቅ ፖለቲካው ማንነትንና እምነትን ማጥቂያ እየተደረገ፣ አገሪቱን ወደ እሳት ምድጃነት ለመለወጥ የሚደረጉ ጥረቶች አሉ፡፡ ይህ በፍፁም ከዚህ ዘመን ሰዎች የሚጠበቅ ተግባር አይደለም፡፡ ለአገርም አይበጅም፡፡ አሸናፊም ተሸናፊም አይኖርበትም፡፡ ከማንም በላይ ደግሞ መንግሥት ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡
የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ሰላማዊ ሐዲዱን ስቶ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሲነጉድ፣ በሴራ ትንተናዎች እየታጀበ ሁከት ቅስቀሳ ውስጥ ይሰማራል፡፡ ሁከቱ ያገኘውን እያዳረሰ ወደ ግጭት ሲቀየር፣ ሃይማኖትና ብሔር እያጣቀሰ ባገኘው አቅጣጫ ይፈሳል፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማካሄድ ከምንም ነገር በላይ በሰጥቶ መቀበል መርህ መሆን አለበት።
Filed in: Amharic