>

የእነ አዳነች አበቤ የለየለት አፓርታይዳዊ አስተሳሰብ እና ክሹፍ መረጃቸው...!!! (ጌታቸው ሽፈራው)

የእነ አዳነች አበቤ የለየለት አፓርታይዳዊ አስተሳሰብ እና ክሹፍ መረጃቸው…!!!

ጌታቸው ሽፈራው

( “ኦሮሚያ ውስጥ ያሉ  ቅርንጫፎች (የፌደራል ተቋማት) ኃላፊዎች ኦሮሞ መሆን አለባቸው”)
የገቢዎችና ጉምሩክ ሚኒስትሯ ወ/ሮ አዳነች አበቤ ቢቢሲ ላይ ቀርበው ስለተቋማቸው ለማስተባበል ጥረዋል። ይሁንና  ሌላ ተጨማሪ ስህተት ፈፅመዋል። ሕዝብ አያውቅም ብለው አሳሳች መረጃዎችን ተናግረዋል። ከእነዚህ መካከል አንደኛው “አብዛኛው የጉሙሩክ ቅርንጫፎች ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነው ያሉት ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሞጆ፣ አዳማ፣ ጅማና ሞያሌ የፌደራል ጉሙሩክ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች በመኖራቸው  በነዚህ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች የክልሉን ቋንቋና ባህል የሚያውቅ አመራር መመደቡን አረጋግጠዋል።” ሲል ቢቢሲ ዘግቧል። ይህ ሀተታ ሀሰትም እውነትም አለበት። እውነታው አሥራት ላይ እንደተነገረው አብዛኛዎቹ የጉምሩክ ኃላፊዎች በኦሮሞዎች የተያዙ መሆኑ ነው። ወይዘሮ አዳነች ይህን ለማስተባበል ሲባል አብዛኛዎቹ ቅርንጫፎች ኦሮሚያ ውስጥ ስለሚገኙ ነው ብለዋል። አብዛኛዎቹ ቅርንጫፎች ኦሮሚያ ውስጥ ስለሆኑ ነው ያሉት የአመራሩን ስብጥር ማስተባበል ስለማይችሉ ነው። ይህ አደባባይ የወጣ ሀቅ ሆነባቸው።  ስህተቱ ግን ብዙ ነው። ሁለቱን ብቻ ልጥቀስ።
1) ገቢዎችና ጉምሩክ የፌደራል ተቋም ነው። የፌደራል ተቋም ደግሞ የሚሰራው በኦሮምኛ ሳይሆን በአማርኛ ነው። የሚቀጥረው ቅርንጫፉ የተከፈተበት አካባቢ የተወለደን ሳይሆን የትኛውንም ኢትዮጵያዊ ነው። ቅርንጫፎቹ የተከፈቱት ለኦሮሚያ ሲባል ሳይሆን  ለኢትዮጵያ ያስፈልጋሉ ተብለው ነው። አሰራሩም ኦሮሚያ ላይ ኦሮሞ ብቻ መመደብ አለበት አይለም። ይህ ወይዘሮ አዳነች አበቤ ከሕወሓት የተረከቡትን ተቋም ወደ ኦዴፓ ማዞራቸውን ማስተባበል ስለማይችሉ ያቀረቡት ውሃ የማይቋጥርና የማይረባ መልስ ነው። ከመልሳቸው ስህተትነት ባሻገር ግን በየቦታው ኦሮሞ መድበው  ሲተቹ ኦሮሚያ ውስጥ ያሉ የፌደራል ተቋማት ውስጥ ከኦሮሞ ውጭ ሌላ ሊመደብ አይችልም ማለት የለየለት አፓርታይዳዊ አመለካከት ነው። ሌላ ሊባል አይችልም!
2ኛ)  ኃላፊዎቹ የአካባቢውን ቋንቋ ባገናዘበ መልኩ ቢቀጠሩ ኖሮ በርካታ ኦሮሞዎች በሌሎች ቅርንጫፎች በኃላፊነት ባልተቀመጡ ነበር። ከመቼ ወዲህ ነው ጅቡቲ ኦሮምኛ መናገር የጀመረችው? የጅቡቲ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ኦሮሞ አይደሉም እንዴ? ረዳታቸውስ ምንድን ናቸው? የጋላፊ ስራ አስኪያጅ ገላን ሰበቃ በዳኒ አፋር ሆነው ነው የተመደቡት? ኦሮሞ አይሉም እንዴ? ምክትላቸው ከበደ ቤኛ በደዳዳስ አፋር ሆነው ስማቸውን ወደ ኦሮሞ ስም ቀይረው ነው ኃላፊ የሆኑት ሊሉን ነው?  የሀዋሳ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ  ፍቃዱ ወልደሰንበት ጉዳ ኦሮሞ አይደሉም እንዴ?  ወይዘሮ አዳነች አበቤ ባሉት የስህተት አመክንዮ መሰረት ሲዳማ ወይስ ወላይታ ጠፍቶ ነው? ኦሮሚያ ውስጥ ከኦሮሞ ውጭ ኃላፊ መሆን አይችልም። ሌላ ቦታ ግን ኦሮሞ ኃላፊ መሆን ይችላል ከተባለ ደግሞ አስተሳሰቡ ከአፓርታይድነትም በላይ ነው። የቅኝ ግዛት አይነት መሆኑ ነው።
ሌላኛው የወይዘሮ አዳነች አበቤ የስህተትና ማወናበጃ መረጃ “በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኙ በነዚህ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች አብዛኞቹ ምክትል ኃላፊዎች የሌላ ብሔር ተወላጆች ናቸው።” የሚል ነው። ወይዘሮ አዳነች ለቢቢሲ ይህን መረጃ ሲሰጡ እየፈፀሙ ያለውን አፓርታይዳዊ አሰራር በአመክንዮ ማሸነፍ ስላልቻሉ የሀሰት ማስረጃ ማቅረብ አዋጭ ሆኖ ሳያገኙት አልቀረም። ነገር ግን አያዋጣም። መረጃው የሚለው ከወይዘሮ አዳነች የተውሸለሸለ መልስ ተቃራኒውን ነው፣ እውነቱ ሌላ ነው። ወይዘሮ አዳነች ኃላፊዎቹ የአካባቢውን ቋንቋ የሚችሉ መሆን ስላለባቸው እንደተመደቡ ቢገልፁም ይህ ሀሰት መሆኑን አፋር፣ ጅቡቲ፣ ሀዋሳ የተመደቡት ዋና ስራ አስኪያጆች ኦሮሞ መሆናቸውን ስናይ ለቢቢሲ የሰጡትን መረጃ ክሹፍ ያደርገዋል። ወይዘሮ አዳነች አበቤ ታዲያ በዚህ ሀሰት አልተመለሱም። ኦሮሚያ ውስጥ ባሉት ቅርንጫፎች ምክትሎቹ  የሌላ ብሔር ናቸው ብለዋል። ይህኛውም ሌላኛው ክሹፍ መረጃ ነው። ሀሰት ነው። ለምሳሌ ያህል  ናዝሬት ላይ አስቴር አዱኛ ምክትል ናቸው። ሞጆ ላይ  ግርማ በንቲ ምክትል ናቸው። ኦሮሞ ናቸው። በሌሎቹም ተመሳሳይ ነው።
ወይዘሮ አዳነች አበቤ ዝም ቢሉ ይሻላቸው ነበር። የመጀመርያው ነገር ኦሮሚያ ውስጥ ያሉ የፌደራል መስርያ ቤቶችን ከኦሮሞ ውጭ አይመራቸውም ማለት የለየለት አፓርታይዳዊ አስተሳሰብ ነው። እነ አዳነችን የመሰሉ ብሔርተኞች አዲስ አበባም የኦሮሚያ ነች እያሉ ነው። በዚህ ሰበብ ኦሮሚያ ክልል የሚገኙት ብቻ ሳይሆን አዲስ አበባ ውስጥ ያሉትን የፌደራል ተቋማትንም ሌላ ብሔር ድርሽ አይልባቸውም ሊሉን ነው። ቤተ መንግስቱም እነሱ በስግብግብነት “ፊንፊኔ ኬኛ” ከሚሏት አዲስ አበባ ውጭ ቅርንጫፍም ምንም የለውምና ከኦሮሞ ውጭ ማንም ወደ ቤተ መንግስት መግባት አይቻለውም ማለት ነው። እንደ አዳነች አበቤ የዛሬ አፓርታይዳዊ አስተሳሰብ ከሆነማ ከአሁን በኋላ ኦሮሞ ብቻ ነው “ስዩመ እግዚያብሔር”
ሌላው ግን በምክትል ያሉት የሌላ ብሔር ተወላጆች ናቸው የሚለውና የአካባቢውን ቋንቋ በመቻል ነው የሚለውም የሀሰት መሆኑን ተመልከተናል። ከዚህ ባሻገር ግን ብዙ ሰራተኛ ቅሬታ አላቀረበም የሚል መረጃውም በሀሰት ተሰጥቷል። ይህ የለየለት ውሸት ነው። ከ600 የማያንሱ ሰራተኞች ቅሬታ አቅርበዋል። ቅሬታው የተወሰኑ ሰዎች ነው የሚባለውም የአፓርታይዳዊ አሰራርን መሸፈን ካለመቻል የመጣ የጭንቀትና የድርቅብዬ መረጃ እንጅ በርካቶች ለተቋሙ ቅሬታ አቅርበው። የተወሰኑት ብቻ “ቅሬታው ተቀባይነት አግኝቷል” ሲባሉ በርካቶች አላገኘም ተብለዋል። አዳነች የሚሉት ሌላ እውነት ሌላ ነው።
በእርግጥ ወይዘሮ አዳነች አበቤ ከእነ ስህተቱ አመለካከታቸው አንድ ሀቅ አምነዋል። አብዛኛዎቹ የተቋሙ ቅርንጫፎች ኦሮሚያ ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል። በዚህም አላበቁም። ኃላፊ የሚሆኑትም የአካባቢውን ቋንቋና ባህል የሚያውቁ ናቸው ብለዋል። በግልፅ ኦሮሞዎች ማለት ነው።  በዚህ መረጃቸው አብዛኛዎቹ ኃላፊዎች እነማን እንደሆኑ  ሀቅን ለማስተባበል ሲለፉ ነግረውናል።
Filed in: Amharic