>
5:13 pm - Friday April 19, 2205

ኑ የኒህን ሦስት  የኢትዮጵያ እንቁዎች ልደት እና ክብር....!!! (ብርሀኑ ተክለያሬድ)


ኑ የኒህን ሦስት  የኢትዮጵያ እንቁዎች ልደት እና ክብር….!!!

ብርሀኑ ተክለያሬድ
 

*…በልደት አልተለያዩም! በአላማም እንዲሁ! የቆምነው በነሱ በደማቸው ፍሳሽ በአጥንታቸው ክስካሽ ነውና…  !!!

 
በአለም ላይ እግርህ እስኪነቃ ብትዞር የጦር ሰውነትን ከታጋሽነት ጋር ቁጡነትን ከሩህሩህነት ጋር ጀግንነትን ከሀይማኖተኝነት ጋር ይቅር ባይነትን ከድል አድራጊነት ጋር የዋህነትን ከጥበበኝነት ጋር አስተባብሮ ይዞ ሀገሩን የገነባ ሰው ብትፈልግ በቀዳሚነት የምታገኘው ሰው “ንጉሰ ነገስት ምኒልክ” ይባላል።
“ምኒልክ” የሚለው ስሙ ጣልያንን በድንጋጤ አሩጧል።ባንዳን ድንጋይ አሸክሞ አንደርድሮ እግሩ ስር አስደፍቷል። በእርሱ መወለድ ውስጥ የዛሬዋ ኢትዮጵያ አብራ ተወልዳለች።ይህ ከአንጎለላ የተገኘ “ሰው” ሃገሬን ከጨለማ ዘመን ወደብርሃን ያወጣ ዳግማዊ ሙሴ፣የድንቁርናን ባህር አቁሞ ወደ እውቀት ያሻገረ ዳግማዊ ኢያሱ፣”እነሱ በሀይል ከእኛ ይበልጣሉ፤ነገር ግን እኛ በአንድነት፣በፍቅርና በአምላክ ሀይል እናሸንፋቸዋለን” ብሎ ሃያላንን ያንበረከከ ዳግማዊ ካሌብ ነው።ታላቁ ምኒልክ!!!
  የዘመናዊት ኢትዮጵያ መስራች፣የኢትዮጵያ የመከራ ጊዜ ታዳጊ፣ሃያላንን በራሱ ቋንቋ ውሀ ውሀ ያሰኘ፣የጥቁር ህዝብ ሁሉ ተምሳሌት፣ምኒልክ ምኒልክ ምኒልክ
በእርሱ ሙሉ ሰውነት ላይ የንግስቱ የጣይቱ ፍቅርና ወኔ ሲጨመርበት በዚህ ፍቅር ውስጥም “ወደ ሸዋ የምትመለሱ ገበየሁ እንዴት እንደሞተ ንገሩ” ብሎ እየተቁነጠነጠ ወደ እርዱ ገብቶ የጠላትን ሬሳ እንደ ተራራ ከምሮ የወደቀው የልበ ሙሉው ገበየሁ ጀግንነት ሲጨመርበት “ሉአላዊነት” የተባለ ቃልን “ታላቅ” የተባለች ሀገርን ይፈጥራል።
ሉአላዊነት ማለት ምኒልካዊነት ነው።ከሀገር በፊት ለመውደቅ መሞከር፣በሀገር ጭንቀት ውስጥ መቃተት፣ የራስን ደም ከፍሎ ህመሟን ማከም፣ስልጣኔን ፍለጋ በጥበብ መጓዝ፣ከዚያ የማትናወጥ ሀገር ማቆም!!! ሉአላዊነት ይህ ነው።
የነዚህ የ3 እንቁዎች ዛሬ ልደታቸው ነው።በልደት አልተለያዩም። በአላማም እንዲሁ የቆምነው በነሱ ልፋት ነው።
ንጉሳችን ምኒልክ እንኳን ተወለድክልን
ብርሀናችን ጣይቱ እንኳን ተወለድሽልን
አጥራችን ገበየሁ እንኳን ተወለድክልን
Filed in: Amharic