>

ምን አዲስ ነገር ተገኘ? (አሰፋ ታረቀኝ)

ምን አዲስ ነገር ተገኘ?

 

አሰፋ ታረቀኝ


ሰሞኑን የኦሮሚያ ም/ፕሬዚዳንት የአማራንና የኦሮሞን ግንኙነት በተመለከተ የማይገባ ንግግር አደረጉ በማለት የተነሳው አቧራ  አየሩን ጋርዶታል፡፡ “አማራ” ብሎ የሰየመውን የሕብረተሰብ ክፍል ቢቻል ድራሹን ለማጥፋ ያ ካልሆነ የደነዘዘና ተስፋ የቆረጠ ትውልድ ለማዘጋጀት ፕሮግራም ነድፎ ሐያ ሰባት አመት ሙሉ ተጠምዶ ሲሠራ ከነበረ ህዋህት ጋር እጂና ጓንት ሆኖ ሲሠራ የነበረው ሁሉ፤ የአቶ ሺመልስን ንግግር የተለያየ ቀለም እየቀባ ማበጃጀቱን ተያይዞታል፤ የደረስንበት ዘመን ሚዛኑን የሳተ ትውልድና እንደአሸን የፈላው ማኅበራዊ ሜዲያ የተገጣጠሙበት ወቅት ነው፤ ስለ ትናንት በጥልቀት ያነበቡ፤ ዛሬን በትክክል የሚኖሩና ነገን በተስፋ የሚጠባበቁ፤ ተስፋ ቆራጮች በሚያስነሱት የአቧራ ግርዶሺ ውስጥ፤ የነገዋ የተዋበች ኢትዮጵያ ትታያቸዋልች፤ ሥለሆነም ሟርተኛውን ሁሉ አያዳምጡም፤ በሚፈጠሩ ችግሮችም አይደናገጡም፡፡በአቶ ሺመልስ የሰሞኑ ንግግር መነሻነት የሚጎርፈውን ውርጅብኝና ውዝግብ ስከታተል የተረዳሁት፤ የአንዳንዶቻችን ትናንትን የመርሳት አቅማችን የቱን ያህል ፈጣን እንደሆነ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ የመረዳት ችሎታችን የቱን ያሕል ግልብ እንደሆነና የጎሳው ፖለቲካ ውስጣችንን በእጅጉ እንደሸረሸረው ነው፡፡

17 አመት በበረሐ፤ 27 አመት የመንግሥትን መዋቅር በመጠቀም ህዋህት ፖሊሲ ቀርጾ በአማራ ህዝብ ላይ ዘምቷል፡፡

እንደህዋህት የፕሮፖጋንዳ ዘመቻና እንደ ኦነግ ዕቅድ ቢሆን ኖሮ “ኦሮሚያ” በሚባለውና በደቡብ ክልል ‘አማራ’ የሚባል የሰው ዘር ስለመትረፉ ማንም እርግጠኛ አይሆንም ነበር፡፡ ሟቹ አቶ መለስ ዜናዊና ካድሬወቻቸው የተለሙት ሕዝብን የማጫረስ እቅድ በኦሮሞና በደቡብ ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ሲያጣ፤ ተሿሚወቻቸውን አሰልፈው የምዕራብ ሐረርጌን፤ የገለምሶንና የአርባ ጉጉን እልቂት እንዳስፈጸሙት ታሪክ መዝግቦታል፤ በመንግሥት የፕሮፖጋንዳ መዋቅር “አንተን አይመስልም፤ መሬትሕንም በጉልበት የወሰደብህ እሱ ነው፤ በለው” እየተባለ ሲቀሰቀስ ታዝቦ ያሳለፈ ታላቅ ሕዝብ ነው፡ ታሪኩ የጥቁሮች ስለሆነ ክበር ተስጥቶት አለተነገርም እንጅ፤ የመንግሥትን የፕሮፖጋንዳ ተቋም በተቆጣጠር ሐይል “ተነስ ተጋደል” ቢባልም፣ ተረጋግቶ ያሳለፈ ሕዝብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ነው፤ ሰርቦችና ሩዋንዳወች ያለፉበትን አስከፊ ሰቀቀን ከረሳን የኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅነት አይገባንም፤ ‘ጥፋት ዘመን’ በተሰኘው የሙሉቀን ተስፋው ጥናት መሰረት ከ1983-2007 ባሉት ጊዚያት ውስጥ በተለያየ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 547 የአማራ ብሔር ተወላጆች ተገድለዋል፡፡ ይኸ ቁጥር በጁሐር ሙሐመድ ግሪሳ የተፈጁትን አይጨምርም፤ አዎ የሞቱት ያሳዝናሉ፤ በግፍ ስለተገደሉት፣ ሰወች ዝም ቢሉም እግዚአብሔር ዝም አይልም፡፡ ለእያንዳንዱ ዋጋውን በጊዜው ይከፍለዋል፡፡ መዘንጋት የሌለበት ግን ይኸ ሁሉ ፍጅት ከመልካሙና ሩኅሩሁ የኦሮሞና የደቡብ ህዝብ ከራሱ የመነጨ ሳይሆን በሕዋህት የፖሊሲ አስገዳጅነት የተፈጸመ መሆኑን ነው፡፡ የሰሞኑ የአቶ ሺመልስ አብዲሳ ንግግር መታየት ያለበት ከዚሁ አቅጣጫ ነው፤ አድማጫቻው ማነው? ለሚለው ጥያቄ የምንሰጠው መልስ አባባላቸው የሚያስከትለውን “አደጋ” ይወስነዋል፡፡ እኔ እስከተረዳሁት ድረስ አድማጫቸው (Audience) ያው በማጭበርበርና በማምታታት የሰለጠነው ‘ምሁር’ ተብየው እንጅ ኢትዮጵያዊው ኦሮሞ አልነበረም፡፡ ተለምዷዊ እና ተፈጥሯዊ በሆነው አነጋገር ሰው ነፍስና ሥጋው እስካለ ድረስ ሞተ አይባልም፡፡ ነፍስና ሥጋቸው ሳትለያይ ሰብዕናቸው ከውስጣቸው ተሟጦ አልቆ ግን ቆመው የሚሔዱ ሙታን አሉ፤ እንደ አውስትራሊያና እንደ አሜሪካ ባሉ የእንሥሣት መብት በሚከበርበት ሐገር ሀገርና ዘመን እየኖሩ ለዘመናት አብሮ የኖርን ሕዝብ ፍለጠው ቁረጠው እያሉ መልዕክት ወደ ሀገር ቤት በማስተላለፍ ትውልድን ማስጨርስ ከሙት መንፈስ እንጅ ከህያዋን መንፈስ አይመጣም፡፡ አቶ ሺመልስ አብዲሳ የኦሆዲድ ካድሬ የነበሩ ናቸው፤ እሆዲድ ደግሞ ልክ እንደ ብአደንና እንደ ደቡብ ሕዝቦች ድርጅት በህዋህት ምህዋር ላይ የሚሺከረክር ድርጅት ነበር፡፡

አረንጓዴ፤ ብጫና ቀይ ባንዲራ የቅኝ ገዥ ባንዲራ ነው፤ የዛሬዋ ኢትዮጵያ የሚኒልክ ወረራ ውጤት ነች የሚለውን የፈጠራ ታሪክ ትውልዱ እየተጋተ እንዲያድግ ሲፈርድበት፤ ኦሆዲድ በአስፈጻሚነት፤ ህዋህት በመመሪያ ሰጭነት አለቃና ሎሌ ሆነው ሠርተዋል፡፡ የተምታታው የታሪክ ትንታኔና የህዋህት አፈና አላራምድ በማለቱ በአራቱም ማዕዘን የተቀጣጠለው የሕዝብ አመጽ የነዶ/ር አብይን አመራር አዋልዶ ህዋህትን ላትመልስ ሸኝቷታል፡፡ ለ27 አመታት እተኮተኮተ የፋፋው አውዳሚው የጎሳ ፖለቲካ ግን እንደካንሰር ተበትኖ የዶ/ር አብይን መንሥት ከወደፊት ጉዞው ማስቆም ባይችልም፤ ግስጋሴውን በማዘግየት በኩል የሚያሳድረው ትጽዕኖ ቀላል አልሆነም፡፡ ሲቻለው ፊት ለፊት ይዋጋል፤ ካልተቻለው ለጠላት ፕሮፖጋንዳ አመቺ የሆነ ቀዳዳ በመክፈት ውዥንብር እንዲፈጠር ያደርጋል፤ የጎሳው ካንሰር በይፋ የመንግሥት ፖሊሲ ሆኖ ለ27 አመት የሠራ ሲሆን፤ ለውጡ ደግሞ የሁለት አመት ህጻን ነው፡፡ በማደግ ላይ ያለውን ሕጻን ከሚንከባከቡት ጋር መሰለፍ ወይም እየጨለመበት ባለው የጎሳ ጉረኖ ውስጥ መቆየት የአቶ ሺመልስ አብዲሳ ምርጫ ነው፤ የሚደንቀው ደግሞ፤ በብልጽግና ውስጥ የኦሮሞ ትውልድ ያለው ፖለቲከኛ አምኖበትም ይሁን ተሳሥቶ አማራን ጎንጥ የሚያደርግ ነገር ከተናገረ፡ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይን ተጠያቂ ለማድረግ የሚደረገው ሩጫ ነው፡፡ መጻፍና መናገር የቻለ ሁሉ በጠቅላይ ሚንስትሩ ላይ መዝመቱን የዕውቀቱ መመዘኛ ያደረገው ይመስላል፡፡በዕድሜየ የዶ/ር አብይ መንግሥት አራተኛው መንግሥት ነው፡፡ በውጭና በውስጥ ያለው ውጥረት የደርግንና የዶ/ር አብይን መንግሥት ተመሳሳይ ቢያደርጋቸውም፤ ደርግ በሁለት በኩል እድለኛ ነበር፡፡ በተለያዩ መንደሮች የተከለለ ሳይሆን በአንድት ሐገር የሚያምን አንድ ባንዲራ ያለው ህዝብ ነበረው፡፡ የፈጠራ ‘ታሪክ’ የተጋተ ሳይሆን በሃገር ፍቅር የነደደ ትውልድ ነበረው፡፡ዶ/ር አብይ ግን ለዚህ አልታደሉም፤ የጣሊያን ፋሺስት ሰላይ በነበሩ አባቶቻቸው ተኮትኩተው ያደጉ ህዋህቶችና ‘የሚኒልክ ወረራ’ በሚል ፈፋ በማይሻገር ፖለቲካ የሚናውዘው  ወለጌው ኦነግ በሁሉም የሐገሪቱ ቀጠና ጦርነት ከፍተውባቸዋል፡፡

ኑ ሃገራችንን ከወደቀችችበት እናንሣት ብለው ያሰባሰቧቸውም፤ በጠላትነት ተሰልፈውባቸዋል፡፡ እሱ ብቻም አይደለም፤ ሳይመዝኑ የሚናገሩ የአቶ ሽመልስ አይነቶቹም የሚያስነሱትን አቧራ የማጥራቱ ሥራ የዶ/ር አብይ ሃላፊነት እንደሆነ የሚጮሁት በርክተዋል፡፡ ምናልባት የብልጽግና ፓርቲ ከመመሥረቱ ጋር ተያይዞ እንድጦዝ ካልተፈለገ በስተቀር፤ አማራን ‘ሰበርነው አደቀቅነው’ የአቶ መለስና የአቶ ሥብሃት ነጋ የየለቱ ድንፋታ አልነበረም ወይ? አቶ ሽመልስም ሆኑ ከሳቸው በፊት ይደነፉ የነበሩት ያልገባቸው፤ እንደሕዝብ የሚሰብርም የሚሠበርም አልነበረም አይኖርምም፡፡
ከስታሊን በኋላ ሶቬዬት ኅብረትን የመሩት የኒኪታ ክሩቸቭ አባብል ለክቡር አቶ ሽመልስ አብዲሳ አባባል የሚመጥን ይመስለኛል “Politicians are the same everywhere. They promise to build a bridge even when there is no river”. በየትም ቦታ ያሉ ፖለቲከኞች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ወንዝ ሳይኖር ድልድይ እንሠራለን ብለው ተስፋ ይገባሉ፡፡ ነበር ያሉት፡፡

የአቶ ሽመልስን አነጋገር ሳስታውስ በልጅነቴ የሰማሁት ተረት ትዝ ይለኛል፡፡ ሰውየው አነጋገሩ ለሰሚ ስለማይመች እናቱ ሁልጊዜ ይጨነቃሉ፡፡ ልጃቸውን ይድሩትና አማቶቹ ቤት መልስ ተጋብዘው ይሔዳሉ፤ ሥጋት ያደረባቸው እናት ልጃቸው ከመሄዱ በፊት ነጠል ያደርጉና “ አደራህን ልጀ አንተ ጨዋታ ስለማያምርልህ ተጨዋት ከተባልክ ዝም እንድትል” ይሉታል፤ አዲሱ አማቻቸው ጸጥ ሲልባቸው የተጨነቁት አማቱ እንድጫወት ሲጥይቁት፤ እንዳይጫወት እናቱ ያስጠነቀቁት መሆኑን  ይነግራቸዋል፤ አይ ያንተጨዋታ ለኔ ይጥመኛል በማለት ይገፋፉታል፡፡ጨዋታውን የጀመረው የሚስቱን እህቶችና ወንድሞች በመቁጠር ነበር፡፡ በመጨርሻ የራሱ ቅል ትልቅ እሆነው ልጅ ላይ ሲደርስ፤ “ይኸም የርሰወ ልጅ ነው”? ብሎ ይጠይቃል፤ ‘አዎ የኔ ልጅ ነው’ ይላሉ አማት፤ ‘ታዲያ ይህንን ሲወልዱ …….. አልተቀደደም’? ይላል አዲሱ አማች፤ በመልሱ የተገርሙት አማት ‘ ልጀ እናትህ ትክክል ናቸው ዝምታሕ ይሻላል’፤ አሉት ይባላል፡፡ አቶ ሽመልስ አብዲሳ አንደበታቸውን በክፈቱ ቁጥር የሚወክሉትን ሕዝብ የማይመጥን ቃላት መወርወር ከጀመሩ ቆይተዋል፤ ወይ ዝም ይበሉ፣ ወይ ቦታውን ለሌላ አስረክበው ገለል ይበሉ፡፡ በወሬ ችርቸራ የተጠመደውም ክፍል ለዕውነትና ለተባበረ አንድነት የሚሟገቱትን የአቶ ታዬ ደንደአን፣ የስዩም ተሾመንና የአስቴር በዳኔን ገንቢ ትንታኔወች እንደዋዛ ባያልፋቸው መልካም ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ፍርስራሽ ትርፍ እናገኛለን ብለው ጧቱኑ የጀመሩት በዶ/ር አብይ ላይ ቢዘምቱ ሥራቸው ስለሆነ አያስገርምም፡፡  የሚያስገርመው “ሞቴን ከኢትዮጵያ በፊት ያድርገው” የሚሉቱ የዶ/ር አብይን መንግሥት በማጥላላቱ በኩል ከህዋህትና ከኦነግ ጋር መሰለፋቸው ነው፡፡

በግ ረኛው ዳዊት እምነቱን በአምላኩ ላይ አድርጎ ጎሊያድን ድል እንደሚያደርገውና የእሥራኤልን ሕዝብ ውርደት እንደሚያስወግድ ሲነግራቸው ተቃውሞው የጀመረው ከወንድሞቹ ነው፣ በሕዝቡ አልፎ ተቃውሞው እስከ ንጉሡ እስከ ሳኦል ደረሰ፡፡ ጎሊያድ እንደሚሸነፍ የሚያውቁት እግዚያብሔርና ዳዊት ብቻ ነበሩ፡፡የሆነውም ያ ነው፡፡ ለዘመናት የፈሰሰው የኢትዮጵያውያን እንባ የሚታበስበት ዘመን ተጀምሯል፤ የዘመኑ መጀምር የገባው መሪ ቦታውን ይዞ ሌት ከቀን እየሠራ ይገኛል፡፡ የጠላት ሠራዊትም ባገኝው አጋጣሚ ሁሉ ውጊያውን ቀጥሏል፡፡ ኢትዮጵያም እግዚያብሔር ወደወሰነላት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደተመኙላት የብልጽና ማማ ላይ ያለጥርጥር ትደርሣልች፡፡ የአቶ ሽመልስ አብዲሳም፣ ሸወድናቸው፣ ሰበርናቸው፣ ፉከራ ጓደኞቻቸውን ከማስጨብጨብ ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡ ድንፋታውምኮ እንደፈጣሪወቹ ህዋህቶች አርጅቷል!

Filed in: Amharic