>

እስልምናን እና ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት›› ምን አገናኛቸው? (እውነት ሚድያ አገልግሎት)

እስልምናን እና ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት›› ምን አገናኛቸው?

እውነት ሚድያ አገልግሎት

✍️ እስልምና (የግራኝ አህመድ ወረራ) እና የኦሮሞ ሕዝብ (በተለምዶ ‹‹የኦሮሞ እንቅስቃሴ›› የሚባለው) ታሪካዊ የክስተት ግጥምጥሞሽ ነበራቸው፤ ዛሬም ድረስ ‹‹የጋራ ጠላታችን›› የሚሏቸውም አካላት ከዚያን ወቅት ጀምሮ በነበረው ማሕቀፍ መሠረት ነው፡፡
✍️ ‹‹በግዳጅ ወደ አቢሲኒያ ኤምፓየር እንድንጠቃለል አድርገውናል›› ለሚሏቸው ቀደምት የኢትዮጵያ ነገሥታት ያላቸውን መራር ጥላቻ ጨምሮ የሁለቱም ወገን ጽንፈኞች የሚያቀነቅኗቸው አስተሳሰቦች ከዚያ ታሪካዊ ተራክቦ የተቀዱ ናቸው፡፡
✍️ ኢትዮጵያን በታትነን አዲሱን ‹‹የኩሽ ሕዝቦች ኤምፓየር እንመሠርታለን›› በሚል የሀገሪቱ የአንድነት ማሠርያ ማዕተቦች (ምልክቶች) የመናድ ተግባራት ላይ ተጠምደዋል፡፡
✍️ ‹‹የነገሥታቱ የጭቆና መሣርያዎች›› ተብለው የተፈረጁት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና በዓርማነት ሲጠቀሙት የነበረው አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራ እንዲወገዱ ይፈለጋል፡፡
✍️ በተለይ አጼ ሚኒልክ ‹‹ደመኛ ጠላታቸው›› ነው፡- ኦሮሞና ሙስሊም የሆኑትን የአርሲ ሕዝቦች እንደጨፈጨፋቸው ከሚነገረው የአኖሌ ትርክት የተነሣ፤ እንዲሁም ዓድዋ ከሰሜናዊነትና ከኦርቶዶክሳዊነት ጋር (ታቦተ ጊዮርጊስን ጨምሮ) የሚያያዝባቸው ዐውዶቹ ስለሚበዙ፡፡
✍️ ልጅ ኢያሱ ከንግሥና መንበሩ በግፍ የተባረረው ‹‹ኦሮሞም፣ ሙስሊም ወዳጅም በመሆኑ ብቻ›› እንደሆነ ይስማማሉ፤ እናም ‹‹የነፍጠኛው ሥርዓት ምንጭ›› ብለው የፈረጁትን የአማራ ሕዝብ ይጸየፋሉ፡፡
✍️ ‹‹አላህም፣ ዋቃም አንድ ናቸውና›› በሚል ኦሮሞና እስልምና የአስተምህሮ መመሳሰል እንዳላቸው ይሰብካሉ፤ ስብከቱ ለጊዜያዊ ትብብር የሚሆን እንጂ ልባዊ እምነት ባለመሆኑ የእምቧይ ላይ ካብ ቢሆንም ቅሉ፡፡
✍️ ጽንፈኛ የኦሮሞ ፖለቲከኞቹ ‹‹የኦርቶ-ነፍጠኛው ሥርዓት›› እያሉ አምርረው ከመጥላታቸውም ባሻገር እስልምናን ‹‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው›› በሚመስል አካሄድ ‹‹ከባህላችን ጋር የማይጎረብጥ ሃይማኖት›› እስከማለትም ደርሰዋል፤ እነርሱ እንደሚሉት ኦርቶዶክስ ‹‹ሰሜናዊት››  አይደለችም እንጂ ብትሆን እንኳን ከኢትዮጵያዊው ባህል ይልቅ የአረቡን ባህል መምረጣቸውን ግን ልብ ይሏል፡፡
✍️ በሕዝብ ብዛት (Demography) ስሌት መሠረት አብዛኛው የኦሮሞ ሕዝብ ሙስሊም ስለሆነ ‹‹ኦሮሞ ሲነካ እስልምና ይነካል፤ እስልምና ሲነካም ኦሮሞ ይነካል›› የሚል ድምዳሜ አላቸው፡፡
✍️ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ፊት ለፊት ገጥሞና በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ተከራክሮ ማሸነፍ እንደማይቻል ከታሪክ ስለተረዱ መዋቅሯን የመክፈል አዲስ ስልት ይዘው ብቅ ብለዋል፡፡
✍️ ኦሮሞውን ‹‹ጋላ››፣ ሙስሊሙን ‹‹አህዛብ፣ አረመኔ›› ብለው የሚፈርጁ አንዳንድ አዋልድ መጻሕፍት ላይ የጋራ ቅሬታ አላቸው (አብዛኞቹ መጻሕፍት ግን ቤተ ክርስቲያኒቱ በኦፊሴል እውቅና የሰጠቻቸው ሳይሆኑ በግለሰቦች እየተባዙ የሚሠራጩ መሆናቸውን ልብ ይሏል)፡፡
✍️ እናም ለዘመናዊው የጋራ ግባቸው ዛሬም ‹‹ፖለቲካዊ ጋብቻን›› መርጠዋል፡- በተለይ ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት›› አቀንቃኞች ለዓላማችን መሳካት ስንል ከሰይጣን ጋርም ቢሆን እንተባበራለን ብለው ቆርጠዋል፤ በኦሮምያ ውስጥ ከተቃጠሉት አብያተ ክርስቲያናትና ከታረዱት ኦርቶዶክሳውያን ይልቅ ለሞጣ መስጊዶች ከገንዘብ አስተዋጽዖ ጀምሮ የፍትህ ጥብቅና መቆምን መርጠዋል፤ የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ንቀው በአክራሪ ሙስሊሞቹ ‹‹ቄሲ ኬኛ›› ውዳሴ ጮቤ ረግጠዋል!
ግን ለምን??? እንዴት??? ጋብቻውስ እስከየት ድረስ ይዘልቃል??? ሙሉ ጽሑፉን አንብቡት!
ክርስትናና እስልምና ለረጅም ዘመናት ተከባብረው በአብሮነት ኖረዋል፤ እየኖሩም ነው፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአንዳንድ አክራሪ ሙስሊሞች እየተስተዋሉ ያሉት የሰላም ማደፍረስ ተልእኮዎች ነባሩን እሴት እየሸረሸሩት፣ የክርስቲያኑንም ትዕግሥት እየተፈታተኑት ይገኛሉ፡፡ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች አብያተ ክርስቲያናትን በማቃጠል፣ ካህናትን በማረድ፣ ምእመናንን በማሳደድና ነባር ይዞታዎቿን በመቀማት ሲሳተፉ የሀገር ሰላምና አንድነት የሚያሳስባት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ግን ሁሉንም በትዕግሥት አሳልፋለች፡፡
በሰሞነኛው ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት›› እንቅስቃሴ ውስጥ ደግሞ ሙስሊሞች  ይፋዊ ድጋፍ በመስጠት፣ ጉዳዩን የሚያራግቡ ሚዲያዎችን በማመቻቸት፤ እስከ ሰሜን አሜሪካ ድረስ በተዘረጋ ሰንሰለት ‹‹ዋና ባለጉዳይ›› ሆኖ መታየት (አየር መንገድ ድረስ እየተገኙ መቀበልና መሸኘት፣ በልዩ የምግብ ግብዣዎች ደስታቸውን መግለጽ፣ በተለያዩ መድረኮች አብረው ሲመክሩ መታየት፣ የሞራልና ገንዘብ ድጋፎችን ማድረግ፣ ወዘተ.)፤ በኢ-ኦርቶዶክሳዊ አካሄዳቸው ምክንያት በካህናቶቿ ላይ ቀኖናዊ እርምጃ ሲወሰድ እንኳን ‹‹የመብት ተሟጋች›› እና ‹‹ዓለም አቀፋዊ የፋይናንስ ድጋፍ አሰባሳቢ›› በመሆን የመሪነቱን ሚና የተጫወቱት እነዚሁ አክራሪዎች መሆናቸው ‹‹ለምን?›› ያሰኛል፡፡
‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት አደራጆች ነን›› የሚሉትም ስለዚሁ አሰላለፋቸው ሲጠየቁ ‹‹ለዓላማችን መሳካት ከሰይጣንም ጋር ቢሆን እንተባበራለን!›› በሚል ይፋዊ ቁርኝታቸውን ገልጸዋል፡፡  ለመሆኑ ግን እስልምናንና ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነትን›› እንዲህ ያዛመዳቸው ምንድን ነው? ሙስሊሞችስ ይህንን እንቅስቃሴ ወገባቸውን አጥብቀው የሚከራከሩለት ለምንድን ነው? ለእነዚህ መሠረታዊ ጥያቄዎች መጠነኛ ምልከታ ማቅረብ የዚህ ጽሑፋችን ዋና ዓላማ ነው፤ ተከተሉን!
 
1. ታሪካዊው የኦሮሞ እና የእስልምና ግጥምጥሞሽ
——————————————————–
ወደ ታሪክ የኋልዮሽ ስንመለከት የአህመድ ግራኝ ወረራም (ሙስሊሞቹ እንደ ጀግንነት ታሪክ የሚቀበሉት)፣ በተለምዶ ‹‹የኦሮሞ እንቅስቃሴ›› (The Oromo Movement) ተብሎ የሚታወቀው የኦሮሞ ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል መስፋፋትም የተከሰቱት በ16ኛው መ/ክ/ዘመን ነው፡፡ ምንም እንኳን በዚህ መልኩ ‹‹የኦሮሞና የእስልምና መስፋፋት ቀጥተኛ ግንኙነት ነበራቸው›› ብሎ በእርግጠኝነት ለመደምደም ጥልቅ የታሪክ ምርምር ቢያስፈልገውም (እርስ በርስም የተዋጉባቸው ጊዜያት ነበሩና) የሁለቱ ክስተቶች ታሪካዊ ግጥምጥሞሽ አንዳች ግንኙነት ይኖራቸው ይሆን? ብሎ ከመጠርጠር መጀመሩ አይከፋም፡፡ ደግሞም የያኔው ታሪካዊ ተራክቦ ባይኖር እንኳን የዛሬዎቹ ጠርዘኛ አቀንቃኞች በዚያ ዘመን አንጻር የዛሬውን ትብብር  ለመፍጠር መምረጣቸው መነሻች ግምታችንን ያረጋግጥልናል፡፡
ዐብዱልጀሊል ዐሊ (ተምኔታዊ ደሴት፤ 2012 ገጽ.249 ላይ) እንደሚገልጸው በ16ኛው መ/ክ/ዘመን የክርስቲያኑ መንግሥትና ግራኝ አህመድ ሲጋጠሙ (ወደ ሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል በመስፋፋት ላይ የነበረው) የኦሮሞው ቡድን የጦርነቱን ውጤት ሲጠብቅ ነበር፤ በመጨረሻም ግራኝ ሲያሸንፍ ከእስልምና ጋር ሆነው ግዛታቸውን ለማስፋፋት ከተዳከመው ጦር (ክርስቲያን ነገሥታት) ጋር መግጠም እንደሚሻላቸው ተገነዘቡ ይለናል፡፡ ይህ ማለት በታሪክ አጋጣሚም ቢሆን አብዛኛው ኦሮሞ ወደ እስልምና ለመቀላቀል ያስቻለው፣ በአንጻሩ ደግሞ ከክርስትናው ጎራ ጋር ለመዋጋት የወሰነበት ጊዜ ነበር፡፡ በዚህቺው መነሻነት ታዲያ ከዚህን በፊት በዚሁ አስተሳሰብ የተመሩ፣ አሁንም እንዲሁ የሚያስቡ፣ ወደፊትም ተመሳሳይ ሕልም የሚያልሙ ሰዎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡
 
2. ስለ ቀደምት የኢትዮጵያ ነገሥታት ያላቸው አቋም
————————————————————
አስቀድሞ ከተጠቆመው የታሪክ ተራክቦ (Historical Encounter) የተነሣም ሙስሊሞችና ‹‹የኦሮምኛ ቤተ ክህነት›› አቀንቃኞች ስለቀደምት የሀገሪቱ ነገሥታት ተመሳሳይ አቋም አላቸው፡- ወደማንፈልገው የአቢሲኒያ ኤምፓየር በግዳጅ ተጠቃለናል ብለው ያስባሉ፤ በዓድዋ ጦርነትና በዓሉ አከባበር ጉዳይ ቅራኔዎች አሏቸው፤ የአኖሌው ጭፍጨፋ ትርክት አዛምዷቸዋል፤ ‹‹የግፈኛ አጼዎቹ ምንጭ›› ለሚሉት የአማራ ማኅበረሰብ መራር ጥላቻን አዳብረዋል፤ በባንዲራ ፖለቲካ ሰክረዋል፤ ኦሮሞም፣ መፍቀሬ-እስልምናም የነበረውን አጼ ኢያሱን ‹‹ያልተዘመረለት ጀግና ንጉሥ›› ብለዋል፤  በአጠቃላይ ‹‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው›› ፖለቲካዊ ጋብቻ ፈጥረዋል፡፡
 
2.1. ‹‹በግዳጅ ተጠቃለናል››
———————————-
በእስልምናውም ሆነ በጠርዘኛ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ዘንድ የሚቀነቀነው ዋናው ጥላቻ በየዘመናቱ የተነሱት ነገሥታት ተባብረው የቀድሞዋን አቢሲኒያ (ሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል) የማስፋፋት፣ ደቡባዊውን ሕዝብ በግዳጅ የመጨፍለቅና የመዋጥ ፖሊሲአቸው ነው፡፡ ሰሜኑ (በዋናነት አማራና ትግራይ) ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎችን እንዲውጡ [በእነርሱ አገላለጽ ‹‹ቅኝ እንዲገዙ››]፣ በሃይማኖት ስም ባህልና ቋንቋቸውንም በሌሎች ሕዝቦች ላይ እንዲጭኑ መንገድ ጠርገዋል ይላሉ፡፡ ‹‹…የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ በቤተ ክርስቲያኗ የኢትዮጵያ ግዛት (የክርስቲያን ደሴት) የፖሊሲና የተስፋፊነት ማዕከል ላይ ያደረገ በመሆኑ ግዛቱን ወደ ጠረፍ ሲያስፋፉ ያስገበራቸው ባመዛኙ ሙስሊሞችና ለእስልምና የተጋለጡ ሕዝቦችን ነው›› ያሉ አሉ (Eloi Fiequet, “The Ethiopian Muslims: Historical Processes and Ongoing Controversies”, 2015:107).
‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት›› ቡድንም ሃይማኖታዊ መዋቅር መስሎ ይጀመር እንጂ በዚህ አስተሳሰብ መሪዎች የሚደገፍና ለሤራቸውም መሣርያ በመደረጉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይህንኑ አስተሳሰብ ሲያቀነቅን እያስተዋልን ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ሙስሊሞቹ ‹‹በእነ አጼ ዮሐንስ አማካይነት በግዳጅ ክርስትና ተነስተናል›› ብለው እንደሚያምኑት ሁሉ (ዐብዱልጀሊል፤ 2012፡167) እነዚህም ‹‹ኦሮሞ በአደባባይ ላይ በሚረጭ ውኃ ብቻ በግዳጅ ክርስትናን እንዲቀበል ተደርጓል›› የሚለውን የፖለቲከኞቹን የፈጠራ ትርክት ሲያስተጋቡ እያስተዋልናቸው ነው፡፡
በአጠቃላይ ‹‹ቀሳውስት የጥላቻና የጦርነት ስብከቶች አድርገው፣ ጦረኛ የሃይማኖት ነገሥታትን ፈጥረው አወድሰውና አጀግነው ከኦርቶዶክስ ውጭ ባሉ የኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ ጦርነት ያዘምታሉ፤ ቀሳውስትም ታቦት ተሸክመው ጦር ሜዳ ይወርዳሉ›› (ዐብዱልጀሊል፤ 2012፡130-131) የሚለውን ተረክ ሁለቱም አካላት ሃይማኖታዊ ልዩነቶቻቸውን ቸል ብለው በጋራ የሚያምኑት ነው፡፡
2.2. ስለ ዓድዋ ጦርነት
—————————
ምንም እንኳን ሁሉንም የቀድሞ ነገሥታት ቢጠሏቸውም በተለይ ለአጼ ምኒልክ ያላቸው ጥላቻ ግን ከልክ ያለፈ የሚባል ነው፤ ከሞቱ ከስንት መቶ ዓመታት በኋላ እንኳን አስከሬናቸው እረፍት ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ከሁሉም በላይ መላው የአፍሪካ ሕዝብ የሚኮራበትን፣ ጥቁሮችን እንደ ገል ቀጥቅጠውና እንደ ሰም አቅልጠው ዝንተ ዓለም ለመግዛት ሕልም የነበራቸው ነጮቹ አንገታቸውን የደፉበትን ድንቅ የዓድዋ ድል ላይ እንኳን አጼ ምኒልክን የሚያጣጥሉ አመለካከቶች ማንጸባረቃቸው ያገርማል፡፡
ቀድሞ ነገር ሁለቱም (የኦሮሞ ፖለቲከኞችና አክራሪ ሙስሊሞች) የእኛ ታሪክ በዚህ ድል ውስጥ ጎላ ብሎ አልተተረከም ብለው ያስባሉ፡፡ እናም ሙስሊሙ በዓድዋ ተራሮች ከተዋደቁት ወታደሮች የሚበዙቱ ሙስሊሞች ሆነው ሳለ እንኳንስ ዝናቸው ሊነገር ቀርቶ አስከሬናቸውን የሚቀብር እንኳን ጠፍቷል የሚል አዲስ ተረክ ይዘው ብቅ ሲሉ ኦሮሞው ደግሞ ‹‹ዕድሜ ለኦሮሞ ፈረሰኞችና ፈረሶች እንጂ ጣሊያንን አናሸንፍም ነበር›› እስከማለት ደርሰዋል፡፡ የዓድዋ ጦርነት ከክርስትናና ከክርሲያኖች ጋር መገናኘቱ፣ የታቦተ ጊዮርጊስ ታሪክ ሳይነጣጠል አብሮ መነገሩ፣ መታሰቢያ በዓሉ ዛሬም ድረስ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት መሆኑ፣ ወዘተ. ያበሳጫቸዋል (ዐብዱልጀሊል፤ 2012፡154)፡፡
2.3. የአኖሌ ትርክት
———————–
ሁሉንም ዜጎች ከማያስማሙ ያለፉት የኢትዮጵያ ታሪኮች፣ ይልቁንም  ‹‹ተከስተዋል›› ተብለው በጥቂት ቡድኖች ከሚታመኑ ነገር ግን እስካሁን ተጨባጭ ማስረጃ ካልተገኘላቸው ትርክቶች ውስጥ የአኖሌ ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ ጠርዘኛ የኦሮሞ ፖለቲካን ተከትለው ከሚነጉዱት ጥቂት ምሁራን በስተቀር ብዙዎቹ የታሪክ ምሁራን በአኖሌ ተፈጽሟል ተብሎ ስለሚወራው የእጅና ጡት ቆረጣ ትርክት አይስማሙም፤ ማስረጃ ይምጣልን ብለውም ይሞግታሉ፡፡
እስካሁን ድረስ ‹‹ተደርጓል›› የሚለውን ድምዳሜ እንደ እምነት ወስደው ብቻ ከሚያቀነቅኑት ባሻገር አንዳች ታሪካዊ ማስረጃ አገኘሁ ካሉት ውስጥ በቅርቡ አባስ ሐጂ ገነሞ በአንድ ሚዲያ ላይ ሲናገሩ፡- ‹‹ለመጀመርያ ጊዜ የጻፍኩት እኔ ስሆን መረጃውን ያገኘሁትም ከአከባቢው ሽማግሌዎች ነው›› ብለው ነበር፡፡ አንድ ሰው ብድግ ብሎ በጻፈው ትርክት ሀገር ስትታወክ ኖራለች፡፡ በርካቶች ግን የሕወሓትን ከፋፍለህ ግዛ ስትራቴጂና መሰል ልቦለዶችን እንደወረደ ተቀብለው ከማስተጋባት ያለፈ  የታሪክ ማስረጃ ሊያቀርቡ አልቻሉም፡፡ በዚሁ የ2012 ዓ.ም እንኳን ጀዋር መሐመድ ‹‹ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የምኒልክን ቤተ መንግሥት የሚያሳድስ ከሆነ የአኖሌ ሀውልትም ቤተ መንግሥቱ ውስጥ መቆም አለበት›› ብሎ መከራከሩ አይረሳም፡፡
ያም ሆነ ይህ ግን የአኖሌ ትርክት በአርሲ (ሙስሊም በዝ በሆነ አከባቢ) የተካሄደ ጭፍጨፋ ነው፣ ጭፍጨፋውን ያካሄደውም ምኒልክ ነው ተብሎ ከመታመኑ ጋር ተያይዞ ሙስሊሞቹንና የኦሮሞ ፖለቲከኞችን ያስተሳሰረ ሆኗል፡፡ አክራሪ ሙስሊሞችና ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት›› ቡድንም ለአማራ ገዢዎች ካላቸው ጥላቻ ጋር ተዳምሮ የጋራ ቃልኪዳን ቀለበት እንዲያስሩ ያበቃቸው ይኸው ትርክት መሆኑ አያጠራጥርም፡፡
2.4. የአማራ ጥላቻ
በእነርሱ እምነት አስቀድመን የጠቆምናቸው ነገሥታት አብዛኞቹ ‹‹አማራዎች›› ስለነበሩ ለዚህ ማኅበረሰብ ያላቸውን ጥላቻ ባገኟቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ያንጸባርቃሉ፡፡
የኦሮሞ ብሔረሰብ በቀደሙት ታሪኮቹ ክርስትናዉን ትቶ ወደ እስልምናው እንዲያጋድል ያደረገውም እርሱ ‹‹አማራ›› ለሚላቸው ነገሥታትና ወታደሮቻቸው የነበረው ጥላቻ እንደነበር በተለያዩ ድርሳናት ተመዝግቦ እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ፡- ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ከአለቃ ታዬ መጽሐፍ እንዲህ ጠቅሰዋል፡- ‹‹ኦሮሞ ያማራን ወታደር ስለጠላ ክርስቲያን ከመሆን እስላም መሆንን ይመርጣል፡፡ … ለዚህ እንጂ የእስላም ቢሆን የክርስቲያን ሃይማኖትን ክፋትና በጎነት ለይቶ ስላወቀ አይደለም፡፡›› (የአባ ባሕርይ ድርሰቶች፤ 1997፡178)፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በኃሮ ቢያንሳም ክስተቱ (ኦሮሞ ከክርስትና ይልቅ ወደ እስልምና ያዘነበለበት) ከነጻና ምክንያታዊ ምርጫነቱ ይልቅ ፖለቲካዊ ይዘቱ የጎላ እንደነበር፡- ‹‹ኦሮሞዎች ከአብሲኒያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እምነት ይልቅ የእስልምናን እምነት በስፋት ሊቀበሉት የበቁት የአብሲኒያውያን የክርስትና እምነት ከጭቆናቸውና ከጨቋኝ መንግሥታቸው ጋር መሳ ለመሳ አድርገው በመውሰዳቸውና ኦሮሞዎች እንደ አብሲኒያ ሕዝብ ሁሉ የተሟላ ስብእና ባለቤት መሆናቸውን ለማስመስከርም ሲሉ ነው›› በማለት ገልጸውታል (ኦሮሚያ፤ የኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ፣ 1985፡35)፡፡ ይኸው ጸሐፊ፡- በረከት የተባሉ ጥናት አቅራቢን (1980) ጠቅሶ፡- ‹‹…በአርሲ ክልል የሚኖሩት ኦሮሞዎች የእስልምናን እምነት በብዛት ሊቀበሉ የቻሉት ፀረ-አማራ ስሜታቸውን ለመግለጫና ከገዢ ኃይላት የተያያዙትን ማናቸውንም እሴቶች እንደማይቀበሉ ለማሳየት ሲሉ ነው›› ያለውን ተጋርቷል፡፡ በመጨረሻም አለቃ አጽሜ ጽፈውታል ያለውን፡- ‹‹…ኦሮሞ እስላም ሊሆን የበቃው በአማራው ቄስ ላይ ባለው ከፍተኛ ጥላቻ የተነሣ ነው›› የሚለውን በመጥቀስ ሀሳቡን አጠናክሯል፡፡
2.5. የባንዲራ ፖለቲካ
————————
የቀደምት የሀገሪቱ ነገሥታት መገለጫ ነው ብለው የሚያምኑትን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማን አምርሮ መጥላትም የእነዚሁ አካላት መገለጫ ነው፡፡ ሙስሊሞቹ የሚጠሉት ነገሥታቱ  በባንዲራው ተጠቅመው ክርስትናን አስፋፍተውበታል ብለው ሲሆን  ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት›› ቡድን ደግሞ ‹‹ኦሮሞ የተጨፈጨፈበት ዓርማ ነው›› የሚለውን ትርክት ተቀብሎ ነው፡፡
ሁለቱም መነሻ የሚያደርጉት ለስሙ የጥንቱን ታሪክ ይሁን እንጂ ሰንደቅ ዓላማውን አሁን ላይ ማየት የማይፈልጉበት ዋናው ምክንያታቸው ግን የአማራው ፖለቲከኛ ጽንፍ መገለጫ ሆኖ ዛሬም ድረስ ሥራ ላይ መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የአርበኞች ግንቦት ሰባት እና ኢትዮጵያ ዜጎች ማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ይህንን ሰንደቅ ዓላማ በመለዮነት ከሚጠቀሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ናቸው፡፡ በዚህ መልክ የጥንቱን ባንዲራ ከዛሬዎቹ ፓርቲዎች ጋር አጃምለው ይጠሉታል፡፡
2.6. ልጅ ኢያሱ፡-‹‹ኦሮሞም፣ ሙስሊምም የሆነ ብቸኛ ንጉሥ›› 
ሁለቱም ስለ አጼ ኢያሱ አዲስ ተረክ በማቀናበርና ተመሳሳይ አቋም በመያዝ ተዛምደዋል፡፡ ለምሳሌ፡- አክራሪ ሙስሊሞቹ ‹‹ተራማጅና አቃፊ ሆነው ሳለ ኦሮሞና ሙስሊም ስለሆኑ ብቻ በአቢሲኒያ ነገሥታት ከሥልጣናቸው እንዲወገዱ ተደርገዋል›› ብለው ያምናሉ (ዐብዱልጀሊል ዐሊ፤ 2012፡142)፡፡ ‹‹ኦሮምያ፤ የተደበቀው የግፍ ታሪክ›› የሚል መጽሐፍ የጻፉት ወልደ ዮሐንስ ወርቅነህና ገመቹ መልካም በተመሳሳይ መልኩ ስለ አጼ ኢያሱ በግፍ መሰደድና ከሥልጣን መውረድ በቁጭት ጽፈዋል፤ እነርሱ ‹‹አቢሲኒያውያን›› የሚሏቸውን የአማራና ትግራይ ማኅበረሰቦችንም ተጠያቂ አድርገዋል፡፡
በዚህ መሠረት ‹‹ልጅ ኢያሱ ከኢትዮጵያ ቤተ መንግሥት ተገፍተዋል›› በሚለው ሁለቱም ይስማሙና ምክንያታቸው ግን ለየቅል ነው፡- አክራሪ ሙስሊሞቹ ‹‹በአባታቸው ሃይማኖታቸው ምክንያት፣ የሙስሊሞችን መብት ስላስከበሩ›› ሲሉ፣ የኦሮሞ ጠርዘኛ ፖለቲከኞች ደግሞ ‹‹ብሔራቸውን ንቀው›› ይላሉ፡፡ ሁለቱንም የንጉሡን ሰብእና የጠሉት አካላት ደግሞ በኦርቶዶክስ ውስጥ የተጠለሉ ‹‹አማሮች›› ናቸው ብለው ያምናሉ፡፡ እናም ሁለቱም በዚህ ጉዳይ በግልጽ እየተባበሩ፣ ተመሳሳይ አቋምም እያንጸባረቁ ናቸውና እነርሱ ‹‹የልጅ ኢያሱ ጠላት›› የሚሏትን ‹‹የአቢሲኒያ ኦርቶዶክስ›› ለማፈራረስ ቢተባበሩ የሚገርም አይደለም፡፡
3. ኦሮሞነት እና  እስልምና እንደ ‹‹የአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽታዎች›› 
የአክራሪ እስልምና እና ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት›› ቡድኖች በጋራ ለመታገል ከሚስማሙባቸው ነጥቦቻቸው አንዱ ኦሮሞነትን ከእስልምና ጋር አንድ የማድረግ አዝማሚያቸው ነው፡፡ ምንም እንኳን ከተለያዩ ነጥቦች አንጻር ኦሮሞነትንና እስልምናን እንደ ‹‹አንድ›› ለማዋሐድ የሚሹ፣ እጅግም ወጃጅነት እንዳላቸው የሚያራግቡ የዘመናችን ፖለቲከኞች ቢኖሩም ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ግን እነዚህ ሁለቱ እንዲያውም ‹‹ደመኞች ነበሩ›› ይሉናል (የአባ ባሕርይ ድርሰቶች፡- ኦሮሞችን ከሚመለከቱ ሌሎች ሰነዶች ጋራ፤ 1997:178)፡፡  ታዲያ እነዚህን ሁለቱን ‹‹አንድ›› ለማስመሰል የሚጥሩቱ መሠረታቸው ምንድን ነው?
3.1. በአስተምህሮ ለመመሳሰል መሞከር፡- ‹‹አላህም፣ ዋቃም አንድ ናቸው!››
የአክራሪ እስልምናውና ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት›› የጋራችን የሚሉት የኦሮሞ ሕዝብ በሃይማኖት ያልተለያየ መስሎት በእነርሱ ወጥመድ ውስጥ እንዲገባ ‹‹ያው አንድ ነው›› የሚል ፈሊጥ አለቻቸው፡፡ ጥንቱን ‹‹ዋቃ ቶኪቻ፣ አንዱ እግዚአብሔር›› ብሎ  የሚያምነውን የኦሮሞ ሕዝብ ‹‹አላህ አንድ ነው፤ አይወልድም፣ አይወለድም›› ከሚለው የእስልምና አስተምህሮ ጋር በማዛመድ ‹‹ኦሮሞ ሁሉ ሙስሊም ነው›› ወደሚል አዲስ አሰላለፍ ሊወስዱት ሲጥሩ ይታያል፡፡
በእርግጥም ኦሮሞ ከጥንቱ በእግዚአብሔር ያምን የነበረ ብሔረሰብ ነው፡- ‹‹የሚያምኑትም በቋንቋቸው ‹ቶኪቻ ረቢ፣ዋቃ ኬኛ› (አንዱ እግዚአብሔር፣ አምላካችን) በሚሉት ነው›› እንዲል (ባላምበራስ ጀቤሣ እጀታ፤ የኦሮሞ ብሔር ባህልና አጭር ታሪክ፤ ገጽ.93)፡፡ ይህ እምነታቸው ደግሞ የእስልምናው ሃይማኖት ‹‹ራቢ ቶኪቻ›› በማለት ከእነርሱ ጋር ስለተመሳሰለላቸው ወደ እስልምናው እንዳዘነበሉ የጻፉም አሉ (ባላምበራስ ጀቤሣ፤ ገጽ.102)፡፡
ሙስሊሞቹም ይህቺን ሁኔታ እንደ ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ‹‹ኦሮሞ ሁሉ ጥንቱን የእስልምና እምነት ተከታይ ነበር›› የሚለውን ፕሮፖጋንዳ ለመጠቀም እንከመሞከር ደርሰዋል፡፡  በተለይ በምሥራቅና በደቡብ ምሥራቅ የሀገራችን ክፍል ዋናው የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ተግዳሮትም ይኸው ነው፡፡
 
3.2. ‹‹የማይጎረብጥ›› የባህል ውሑድነት 
———————————————
አጼ ምኒልክ ከ1882 እስከ 1886 ባደረጓቸው ዘመቻዎች ደቡባዊውን የሀገሪቱን ክፍል ሲቆጣጠሩ፡-  ‹‹አማርኛ ቋንቋን፣ የሰሜኑን ባህልና ክርስትናን ባስገበሩበት የኦሮሞና የሙስሊም ኃይል ላይ አስፋፍተዋል›› በሚል የጻፉ አሉ (Cherri Reni Wemlinger, Identity in Ethiopia. The Oromo from 16th to the 19th Century)፡፡
በአንጻሩ ደግሞ እስልምና ይከተል የነበረው የባህልና የቋንቋ አካሄድ ለኦሮሞ ሕዝብ ‹‹የማይጎረብጥ›› መሆኑ አብዛኛው የማኅበረሰቡ አባላት በኃይል ከተጫነበት ባህል ይልቅ ወድዶ ወደተቀበለው ሳያጋድል እንዳልቀረ ተገምቷል፡፡ ከምንም በላይ ‹‹ከእስልምና ጋር እስካልተጋጨ ድረስ የሀበሻን ባህል ጠብቁት፣ ተጠቀሙበት›› ከሚለው የነቢዩ ትእዛዝ (ሐዲስ) የተነሣ መሆኑም ይነገራል፡፡ እንዲያውም አፋን ኦሮሞ ከማለት ይልቅ ‹‹አፋን ኢስላማ›› የሚሉ እንደነበር የጠቆሙ አሉ (ዐብዱልጀሊል፤ 2012፡261)፡፡ ለእስልምናው ጥብቅና በመቆም የሚታወቁት እንደ ፕሮፌሰር መሐመድ ዓይነቶቹ፡- ‹‹ምንም እንኳን አብዛኞቹ የእስልምና አመራሮች የሴም ቋንቋ ተናጋሪዎች የነበሩ ቢሆንም ከኩሽ ነገድ ጋር ተጋብተውና ተዋልደው፣ የኩሽ ነገዱን ባህልና እሴት ጠብቀውና እውቅና ሰጥተው ቀጥለዋል›› ሲሉ ይገልጻሉ (Mohammed  Hassen, The Oromo of Ethiopia, 1500-1850: with special emphasis on the Gibe Region, the University of London, 1983).
እናም ሙስሊሞቹም ሆኑ ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት›› ቡድን ከሃይማኖታዊ መሠረታቸው ይልቅ የጋራችን ለሚሉት የኦሮሞ ባህል ጥብቅና መቆምን ቀዳሚ አጀንዳቸው አድርገውታል፡፡
3.3. የኦርቶ-ነፍጠኛው ሥርዓት መታገያ አይዶሎጂ
———————————————————-
እስልምና እንደ ሃይማኖት ብቻ ሣይሆን ሁለቱም በጋራ የጠሉትን የነፍጠኛውን ሥርዓት የሚገረስሱበት አስተሳሰብ (ideology) አድርገው መጠቀማቸውም ሌላኛው ነጥብ ነው፡፡ ምክንያቱም ኦሮሞ ወደ ሰሜን ለመስፋፋት ሲያስብ መካች ኃይል ሆኖ ከፊቱ የተጋረጠውን የክርስቲያን ነገሥታት (ኦርቶ-አማራ) ጦር ‹‹የጠላቴ ጠላት›› በሚል በጋራ ለመፋለም፣ የጠሉትን ሥርዓት መገርሰሳቸውም ብቻ ሣይሆን እርስ በርሳቸውም የሚዋሐዱበት ዋነኛ የጭቁኖች የኑባሬአዊ ርዕዮተ ዓለምና መሰባሰቢያ ዋልታ (as major unifying factor) አድርገው እስልምናን ተቀብለውታል (ዐብዱልጀሊል፤ 2012፡254፤ Abbas, 2002)፡፡
ቀድሞም ከተፈጠሩት ታሪካዊ ግጭቶች የተነሣ ሕዝቡ ‹‹እስላምና አማራ›› በሚል ትርክት ‹‹አማራ›› የሚለውን ‹‹ክርስቲያን›› በሚለው እየተካ ሲጠቀም ኑሯል፡፡ ዛሬም ድረስ ይህ አገላለጽና ‹‹እስላም ነህ ወይስ አማራ?›› የሚለው መጠይቃዊ ብሂሎች ያልቀሩባቸው ገጠራማ ቦታዎች አሉ፡፡ ይህ አካሄድ ታዲያ ዛሬ ላለው ፖለቲካዊ አሰላለፍና አስተሳሰብ አልተወደደም፤ ሊወደድም አይችልም፡፡ ዛሬ ላይ ‹‹ስህተት ነው›› ማለት ግን ‹‹ከዚህን በፊትም መሆን አልነበረበትም›› የሚል የኋሊት ታሪክ ወቀሳ ውስጥ አይከትም፤ ሁሉም በጊዜውና በቦታው ትክክል ነበርና፡፡
3.4. ‹‹እስልምና ሲነካ ኦሮሞ ይነካል፤ ኦሮሞ ሲነካ እስልምና ይነካል›› የሞኝ ፖለቲካ
—————————————————————————-
በሕዝብ ብዛት (Demography) ስሌት መሠረት አብዛኛው የኦሮሞ ሕዝብ ሙስሊም እንደሆነ፣ ክልሉም ‹‹ሙስሊም በዝ›› መሆኑ ይታመናል፡፡ ለምሳሌ፡- Abbas (2002) ‹‹ዛሬ በርካታው የኦሮምያ ቀጠና የሚያርፈው ቀድሞ በአረቡ ዓለም የዘይላዕ አገር ተብለው በነዑመሪ በተገለጹት ሰባቱ ኢስላማዊ ስርወ-መንግሥታት ቀጠና ላይ ነው›› ሲል ይገልጻል፡፡  በዚሁ ታሪካዊ መልክዓ ምድራዊና ዲሞግራፊያዊ አግባብ መሠረትም ሁለቱ (ኦሮሞና እስልምና) ለቀጣይ ትብብር ተግባራት ከመተባበር የተሻለ አማራጭ ላይኖራቸው ይችላል፡፡
ለኦርቶዶክስና ኦርቶዶክሳውያን የተቆረቆሩ መስለው፡- ‹‹ኦሮሞ የራሱ ቤተ ክርስቲያን ሊኖረው ይገባል›› ብለው በአደባባይ ሲናገሩ የነበሩት፣ ዛሬም ይህንኑ ሤራቸውን እውን ለማድረግ ደፋ ቀና የሚሉትም እነዚሁ አክራሪ ሙስሊሞች ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በውስጥ ጉዳዮቿ እየገቡ ‹‹አዲስ አደረጃጀት እንፍጠርልሽ›› የሚል የአዛኝ ቅቤ አንጓች አካሄድ ጀምረዋል፡፡ መችም ቢሆን ይህንን የሚያደርጉት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ተቆርቁረው እንዳልሆነ ግልጽ ነው፤ ምናልባትም ማእከላዊነቱን የጠበቀና ለአንድነቷም ወሳኝ የሆነውን አደረጃጀት በማዳከም ከሚፈጠረው መከፋፈል ለማትረፍ የታሰበ ስልት ካልሆነ በቀር፡፡
በአክራሪ ሙስሊምነቱ የሚታወቀው ጃዋር፡- ‹‹እስልምና ሲነካ ኦሮሞ ይነካል፤ ኦሮሞ ሲነካ እስልምና ይነካል›› ያለበት ንግግሩ አንድምታው ‹‹ኦሮሞ ሁሉ ሙስሊም ነው፤ ኦሮሞ ሆኖ በሌሎች ቤተ እምነቶች ውስጥ መሆን አይቻልም›› የሚል  ፕሮፖጋንዳ አካል እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ብሔርን ከሃይማኖት እያላተሙ የመተንተን ‹‹ጊዜያዊ ጋብቻም›› ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም ካልሆነ በቀር ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡
ምንም እንኳን ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት›› ኮሚቴ መሪ ነኝ ባዩ ‹‹ቀሲስ›› በላይ ‹‹ጃዋር ሃይማኖተኛ ሣይሆን ፖለቲከኛ ብቻ ነው›› ቢሉም ከራሱ አንደበት የሰማናቸው፣ በተጨባጭ ተግባራቱም የታዘብናቸው ሁኔታዎች ግን ይህንን ሀሳብ የሚደግፉ አይደሉም፤ ጃዋር ‹‹ሃይማኖተኛ›› ሊባል ባይችልም አክራሪ ሙስሊምነቱ ግን ገሃድ ሆኗል፡፡ ለምሳሌ፡- በሰሜን አሜሪካ ዲሲ ተዘጋጅቶ በነበረው የሙስሊም ዲዮስጶራዎች መድረክ (January 26, 2013) ላይ ጃዋር ተገኝቶ ‹‹የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ትግል ከዚህ በኋላ ምን መምሰል አለበት?›› በሚል ርዕስ ምክርና አቅጣጫ ሲሰጥ ነበር፡፡ በዚህ ዲስኩሩም ሦስት የትግል ደረጃዎችን ገልጾ ነበር፡- አሳምኖ መመለስ (conversion)፣ ማስገደድ (coercion) እና በኃይል ማስወገድ (disintegration)፡፡ አክራሪው የእስልምና ቡድንና ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት›› በአሁኑ ጊዜ የትኛው የትግል ደረጃ ላይ እንደደረሱ በትክክል ለማስቀመጥ ባይቻልም እንኳን ስልቶቹን ቃያይረው በጋራ ኦርቶዶክስን በመታገል ላይ ለመሆናቸው ግን ጥርጥር የለውም፡፡
 
4. ከታሪክ ተሞክሮ የተገኘ አዲስ ስልት! 
———————————————
ባለፉት የታሪክ ገጽታዎቻችን ውስጥ በጉልበትና በይፋዊ ተቃርኖ ኦርቶዶክስን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ሲደረጉ የነበሩ እንቅስቃሴዎች ሁሉ አልተሳኩም፤ እንዲያውም የበለጠ ሲያጠናክሯትና ሲያስፋፏት ተስተዋሉ እንጂ፡፡ ለምሳሌ፡- በግራኝ አህመድ ወረራ ዘመን ኦርቶዶክሳውያኑን በግዳጅ የማስለም ድርጊቶች ተፈጽመው ነበር፤ ሕዝቡም ወደ እስልምና ሲገባ አምኖበት ሣይሆን ተገዶ ስለነበር ጊዜ እስኪያልፍ ሲጠባበቅ ቆይቶ ነበር፡፡ እናም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እነዚያ የመከራ ዘመናት ሲያልፉ ሃይማኖታቸውን እንዲክድ ተገደው የነበሩ ምእመኖቿን መልሳ ወደ ጉያዋ ለመሰብሰብ እንዲያስችላት ‹‹አንቀጸ አሚን›› የተባለ የማስተማርያ መጽሐፍ አዘጋጅታ፣ ‹‹መጽሐፈ ቄዴር›› የተባለ  የማጥመቅያ ሥርዓትም ሠርታ ተልእኮዋን መልሳ ለማጠናከር ችላለች (Trimingham, J.S, Islam In Ethiopia; 1952:90). ኦርቶዶክሳዊነትን ለማክሰም የተሠራ ሤራ ጭራሹን እንዲጠናከር ዕድል መፍጠሩን ይህ አንዱ የታሪክ ምስክርነት ነው፡፡ ስለዚህ በግላጭ ማስገደዱን ካልሞከሩባቸው ጉዳዮች ይህ አንዱ እውነታ ነው፡፡
በኋላ በጣልያን ወረራ ጊዜም ካቶሊኮች የእስልምናውን ክንፍ በመደገፍ ሁለቱ ‹‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው›› በሚመስል መርሕ  ተባብረው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም ሲሠሩ ነበር፡፡ ለምሳሌ፡- በካቶሊኮቹ ሤራ ‹‹ሁለቱ እሾሆች›› የተባሉ ቅባትና ጸጋ በኢትዮጵያ ምድር በተተከሉ ጊዜ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን እነርሱን ለምንቀል ትግል ላይ ስትጠመድ እስልምናው ደግሞ ድምጹን አጥፍቶ ውስጥ ውስጡን  ሲስፋፋ እንደነበር ተዘግቧል (Trimingham, 1952:101)፡፡ በዚህ ታሪካዊ ተሞክሮ መሠረት ደግሞ የጋራ ጠላትን እንዴት በትብብር መዋጋት እንደሚቻል ልምድ ተቀስሞበታል፤ ይበልጥ አዘምኖና አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግም የታመነበት ይመስላል፡፡
ስለዚህም እስልምናም ሆነ ሌሎች ቤተ እምነቶች ኦርቶዶክስን እስካዳከመላቸው ድረስ ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት›› ጨምሮ ሌሎች ተቀናቃኝ አካላትን ሁሉ ከመደገፍ ወደ ኋላ እንደማይሉ ከታሪክ የምንማረው ነው፡፡ በተለይ የራሷ የሚመስለውን መዋቅር መደገፍ ደግሞ በግልጽ ጠላትነትም ስለማያስፈርጅ ‹‹ለኦርቶዶክስ ብለን ነው›› ቢሉም ሁኔታውን በጥልቀት የማያውቁ በርካቶችን እውነት አስመስሎ ለማሳሳት ይቀላቸዋል፤ እየሆነ ያለውም ይኸው ነው፡፡
5. ሁለቱም በአንዳንድ የአዋልድ መጻሕፍት ላይ ያላቸው ቅራኔ
——————————————————————–
የታሪክም ሆነ የሃይማኖት መጻሕፍት ከተጻፉበት ዘመን አንጻርና ከጸሐፊዎች ማንነት የተነሣ ይዘታቸውም ሆነ የሚጠቀሟቸው ቃላት ከዛሬው ማሕቀፈ እሳቤ ቢለዩ ሊገርመን አይገባም፤ የተጻፉት በወቅቱ ለነበረው ማኅበረሰብና የአስተሳሰብ ደረጃ ስለሆነ፡፡ እናም  ዘመናትን ወደኋላ ተመልሰን ዛሬ ባለው መክብበ እሳቤ መዳኘት የታሪክ አተያይ ወንጀለኛ ያደርጋል፡፡ አብዛኞቹ የአክራሪ እስልምናና ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት›› ቡድን አባላት የተንሸዋረረ አመለካከትም የሚመነጩት ከዚሁ የግንዛቤ ክፍተት ነው፡፡
ለምሳሌ፡- ሁለቱም አካላት ቤተ ክርስቲያኒቱ ‹‹አህዛብና አረመኔ ብላናለች፤ የሁለታችንም ስም ጠፍቷል›› ብለው ያስተጋባሉ፡፡ ለዚህም አንድ ዘመን ‹‹…ጋላ፣ ሻንቅላና እስላም…›› የሚሉ ቃላት ተገኙበት የሚባለው ‹‹ራዕየ ማርያም›› በዋናነት ይጠቀሳል፤ ቃላቱ በግለሰቦች ትርጉም የተጨመሩ እንጂ በዋናው መጽሐፍ ላይ አለመኖራቸው፣ የቤተ ክርስቲያኒቱም አቋም እንዳልሆነ፣ ለዚህም ማስረጃው በ1960 ዓ.ም ታተመ የተባለው መጽሐፍን ጨምሮ መሰል ቅጂው ዛሬ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ አለመኖሩ በቂ ምስክር ነው (ወደፊት በተለየ ርዕሰ ጉዳይ እንመለስበታለን)፡፡
በተመሳሳይ መልኩ በተዓምረ ማርያም ላይ ስለ ሙስሊሞችና አህመድ ግራኝ የሚነበቡ ታሪኮች፤ በግራኝ ዘመን በግዳጅ የሰለሙትን ምእመናን ወደ ሃይማኖታቸው ለመመለስ የተደረሱትን አንቀጸ አሚንና መጽሐፈ ቄዴር የመሰሉ መጻሕፍት፤ ሰሎሞናዊውን ሥርወ መንግሥት (ለእነርሱ አቢሲኒያዊ አገዛዝ) እንዲተከል አስተዋጽዖ እንዳደረገ ለሚታመነው ክብረ ነገሥት፤ ወዘተ. የሚኖራቸው አመለካከት ከመሰል ስሌት የሚመነጩ ናቸው (ዐብዱልጀሊል፤ 2012፡155)፡፡
6. ዛሬም ለጋራ ግብ በፖለቲካዊ የትብብር ጎዳና ላይ 
———————————————————-
አክራሪ እስልምናውም ሆነ በ ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት›› ስም የሚቀነቀነው የፖለቲካ ክንፍ በዋናነት ‹‹የእኔ›› የሚሉት ብሔረሰብ ኦሮሞን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህንን የጋራ ትኩረታቸውን ደግሞ እንደ ስልት (means) ብቻ ሣይሆን እንደ ግብም (end) ጭምር ሊቀራመቱት ይፈልጉታል፡፡ በዚህ መልኩ ሊኖሯቸው የሚችሉ የትኞቹንም ልዩነቶቻቸውን አጥብበው አንድ በሚያደርጓቸው ነገሮች መተባበር፣ ወደ ጋራ ግባቸው የሚመራቸውን መንገድ ተባብሮ መጥረግ፣ በአጠቃላይ ሁለቱን የጋራ ተጠቃሚ በሚያደርጓቸው አካሄዶች ሁሉ የአንድነት ግንባር መፍጠር ዋና ትኩረታቸው ነው፡፡
6.1. ‹‹ለዓላማችን መሳካት ከሰይጣንም ጋር እንሠራለን!››  
————————————————————
አስቀድመን ከጠቆመንናቸው ነጥቦች አንጻር አክራሪ እስልምና እና ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት›› ግልጽ ትብብር እያረጉ መሆናቸው ተስተውሏል፡፡ በተለይ በአክቲቪስት ጃዋር መሐመድ የሚመራው የአክራሪነቱ ክንፍ ይህንን የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን የውስጥ ተቀናቃኝ ቡድን አጥብቆ እንደሚሻው አስካሁን ከተስተዋሉት መስተጋብሮች ለማስተዋል ተችሏል፡፡
ከሁሉም አስቀድሞ የጃዋርን ሙስሊምነት የሚጠራጠር ስለማይኖር ጃዋርና ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት›› ግን ያላቸው አብሮነት ምን ይመስላል? የሚለውን ብቻ ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት›› አደራጅ ኮሚቴ አባላት ነን የሚሉ ግለሰቦች ከጃዋር ጋር በተደጋጋሚ መታየታቸው ተገልጾ ‹‹እንዴት ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ  ጥላቻ ካለው ግለሰብ ጋር እንዲህ ዓይነቱን መልካም ግንኙነት ልትመሰርቱ ቻላችሁ?›› ተብለው በተጠየቁ ጊዜ የመለሱት ምላሽ፡- ‹‹ለዓላማችን መሳካት ሲባል [እንኳንስ ከጃዋር ጋር] ከሰይጣንም ጋር ቢሆን እንተባበራለን!›› የሚል ነበር፡፡ ይህ ሁኔታቸው አንዳች የጋራ ግብ እንዳነገቡ ከሚያመላክቱን ነጥቦች መካከል አንደኛው ነው፡፡
እውነትም ‹‹በተግባር አብረው እየሠሩ ይሆን እንዴ?›› የሚለውን ጥርጣሬአችንን ከፍ የሚያደርግ ሌላም ማስረጃ አስተውለናል፡፡ በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ-3 (በተለምዶ ካራ ቆሬ በሚባው ሠፈር) አክራሪ ሙስሊሞቹ ጥቅምት 06-07 ቀን 2012 ዓ.ም በዚያ አከባቢ በሚገኘው ቤተ ክርስቲያንና ክርስቲያኖች ላይ ያደረሱትን ጥቃት በተመለከተ ለቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት አቤቱታ ለማቅረብ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ግቢ የተገኙ ምዕመናን በአንድ ቪዲዮ ላይ ይታያሉ፡፡ በጥቅምቱ የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ታድመው ከአዳራሽ በመውጣት ላይ የነበሩ በርካታ ሊቃነ ጳጳሳትም በምዕመናኑ የአቤቱታ ድምጽ ተሸንፈው ቆም ብለው ማድመጥ፣ የምስል ወድምጽ ማስረጃዎችንም ማየት ጀመሩ፡፡ ወዲያው ግን ክሱ በአክራሪ ሙስሊሞች ላይ መሆኑን የተረዱት ሁለት ሊቃነ ጳጳሳት (አቡነ ሣዊሮስና አቡነ ዲዮስቆሮስ) አንዳች ነገር አጉረምርመው ከጳጳሳቱ ተለይተው ወደ ማረፊያቸው ሊሄዱ ጉዞ ሲጀምሩ አረጋዊው አባት ብጹዕ አቡነ ቀውስጦስ ወደነዚህ ጳጳሳት እየተመለከቱ፡- ‹‹እንዴት አያገባንም? ያገባናል እንጂ!›› ብለው ሲቆጡ ይታያል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳት ‹‹ታዲያ ምን አገባን?›› ብለው አቤት ባዮቹን ጥለው እንደሄዱ ነው፤ አቡነ ቀውስጦስንም ያስቆጣቸው ይኸው ነው፡፡ እናም፡- ‹‹እነዚህ ጳጳሳት ለምን ‹አያገባንም› ሊሉ ቻሉ? ጵጵስና የሚሰጠውስ ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ አይደለም ወይ? ለምንስ አቡነ ሳዊሮስና አቡነ ዲዮስቆሮስ ብቻ ሆኑ?›› የሚሉት ጥያቄዎች ወደ አእምሮአችን ይመጣሉ፡፡ አዎ፡- በአንክሮ እንመርምር ከተባለ ከአክራሪዎቹ ጋር አብረው ለመሥራታቸው ማሳያ ሊሆን ይችላል፤ አቡነ ሳዊሮስ ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት›› አባት አይደሉ? አቡነ ዲዮስቆሮስ ደግሞ ምናልባትም ‹‹የትግራይ ቤተ ክህነት›› የሚባለውን ሌላኛ ጽንፍ ለመቀላቀል ከአቡነ ሳዊሮስ ልምድ እየወሰዱ ይሆን? ብለንም ለመጠርጠር ያስገድደናል፤ ጊዜ ዳኛው ሁሉን በሂደት የሚገልጠው ቢሆንም፡፡
6.2. ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ ለመስጊድ የሚያደላው ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት››
——————————————————————————
አስቀድመው ‹‹ከሰይጣንም ጋር እንሠራለን›› ባሉት መሠረት፡- ከአክራሪው ጀዋርና ፖርቲው ኦፌኮ ጋር የተቀነባበሩ ሤራዎችን አካሂደዋል፤ በአርሲ፣ በባሌና በሐረርጌ አብያተ ክርስቲያናት በአክራሪ ሙስሊሞች ሲቃጠሉ ‹‹የተቃጠለ ቤተ ክርስቲያን የለም›› ብለው በተለመደው ኦ ኤም ኤን ሚዲያቸውና በዋናው ገጻቸው ላይ መግለጫ ሰጡ፤ በአንጻሩ ደግሞ የሞጣ ሁለት ብቻ መስጊዶች ሲቃጠሉ ‹‹የሐዘን መግለጫ›› ከመስጠትም አልፈው የአደራጅ ኮሚቴው ጸሐፊ አቶ ኃ/ሚካኤል ታደሰ 10,000 ብር የእርዳታ ገንዘብ መስጠቱን በማስረጃ አረጋገጥን፡፡ እነዚህን ሁሉ ድርጊቶቻቸውን ስንመለከት ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት›› ከክርስትናው ይልቅ ምን ያህል ወደ እስልምናውና ሙስሊሞች ማድላቱን እናረጋግጣለን፡፡
6.3. የሀገሪቱን የአንድነት ማሰርያ መቁረጥ  
———————————————
አክራሪዎቹ በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች በየሚዲያዎቹ ሲናገሯቸው የነበሩ የሤራ እቅዶቻቸው ኢትዮጵያን እንደ ሀገር፣ ኦርቶዶክስንም እንደ ሃይማኖት ዒላማ ያደረጉ የጥፋት መልእክቶች ነበሩ፤ የአንድነትን ማሠርያ መቆራረጥ! ለምሳሌ፡- ‹‹ኢትዮጵያ የምትባለዋን ሀገር መበታተን አለብን!››  ብለው ከመናገራቸውም በላይ  ከኦርቶዶክስ በተቃራኒ የተሰለፉ ቤተ እምነቶችን በመጠቀም ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚለውን ስም ያላካተተ ‹‹መጽሐፍ ቅዱስ›› እስከማሳተም ደርሰዋል:: ይህ ‹‹መጽሐፍ ቅዱስ›› የታተመው በተሃድሶው አባት ሉተር 500ኛ ዓመትን ለመዘከር ተብሎ መሆኑ ደግሞ የሤራውን አስኳል ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡
ይህንን ‹‹ኢትዮጵያን የመበታተን›› ዕቅዳቸውን ደግሞ በአግባቡ ከግብ ለማድረስ ታሪካዊውን የአንድነት መሠርያ መቁረጥ (የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ማፈራረስ) የግድ ይላቸዋልና ወደዚህ ትኩረታቸውን ያደረጉ ይመስላል፡፡ ለዚህ ደግሞ የራሷን ልጆች ከውስጥ መቀስቀስና በመብት ስም እንዲያስጨንቋት፣ በሂደትም የራሳቸውን ፖለቲካዊ መዋቅር ፈጥረው እንዲያፈነግጡ፣ እንዲከፍሏትም ሁኔታዎችን ማመቻቸት አንዱ ስልታቸው እንደሆነ እየታየ ነው፡፡ እናም ‹‹ኢትዮጵያን እንበታትናታለን›› ብሎ የዛተው የአክራሪ እስልምናው ቡድን አሁን ደግሞ ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት›› እንቅስቃሴን ፈጥሮ እየደገፈ ይገኛል፡፡
6.4. ለአዲሱ ‹‹የኩሽ ሕዝብ ኤምፓየር›› ምሥረታ መሸጋገርያ ድልድይ
——————————————————————————
አክራሪ ሙስሊሞቹም ሆነ ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት›› ሰሜናዊውን የኢትዮጵያ ክፍል ከነጮች ሤራ በተዋሱት ጽንሰ ሀሳብ ‹‹የምኒልክ አቢሲኒያ›› ብለው ነው የሚጠሩት፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንንም ከኦሮሞና ሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ነጥለው ‹‹የአማራ›› ለማለት ያበቃቸው ይኸው ነው፡፡ አሁን ይህንን የቃላት ንግርት በመልክዓ ምድራዊ አጥርም ጭምር ለማስመር ሌላ እንቅስቃሴ ጀምረዋል፤ ‹‹የኩሽ ሕዝብ ኤምፓየር ምሥረታ››፡፡
በዚህ አዲሱ ኤምፓየር የኩሽ ሕዝብ መልክዓ ምድራዊ ካርታን በምናብ ስለዋል፤ በሀገር ውስጥ ደቡቡንና ምሥራቃወቂውን የኢትዮጵያ ክፍል የሚያካትት፣ ሰሜኑን አግልሎ ከውጭ ግን ግብጽን ለማካተት የሚሞክር፡፡ ይህ እንቅስቃሴ በሂደት አሁን ያለችዋን ሀገር (ኢትዮጵያን) አክስሞ፣ ‹‹የነፍጠኛ ሃይማኖት›› የሚሏቸውንም ኦርቶዶክሳዊ እሴቶች አዳክሞ ሌላ ሰብእና የመፍጠር አካሄድ ነው፡፡ ‹‹የጋራ ታሪክ የለንም›› የሚለው የቅርብ ጊዜ ንግግራቸውም ለዚህ መንገድ ለመጥረግ ይመስላል፡፡ በሰሞንኛው የዓባይ ግድብ ውዝግብ እንኳን በግልጽም ባይሆን ለኢትዮጵያ ጠላቶች የሚወግን አቋም እንደማያንጸባርቁ ዋስትና የለም:: ይህንና መሰል ትርክቶችን እየሰማ የሚያድግ አዲሱ ትውልድም ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ባዳ መሆኑ፣ ‹‹ኦርቶዶክስ የሰሜን /አቢሲኒያ/ ሃይማኖት እንጂ የኦሮሞ አይደለችም›› ለሚለው የሀሰት ትርክታቸውም መጋለጡ ጥርጥር የለውም፡፡
 
6.5. የአቶ ጁነዲን ሳዶ ‹‹ቄሲ ኬኛ›› አነጋገር
——————————————————-
የቀድሞው የኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጁነዲን ሳዶ ለረጅም ዓመታት ከሠሩባቸው ሁሉም ሥልጣኖቻቸው ተባርረው የቀሩት በተለይ ለአክራሪው የእስልምና ክንፍ ዋና ሰንሰለት ሆነው የኢትዮጵያን ሰላም ለማደፍረስ በሠሯቸው ተግባራት እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከእነዚህም አንዱ ማሳያ ከአረብ ሀገራት ጋር ጠንካራ ትስስር ፈጥረው በሚያስገቡት ቱባ ዶላር ገጠሪቱን የኦሮምያ ክልል በመስጊድ የማጥለቅለቃቸው አካሄድ ነበር፡፡ ባለቤታቸው ወ/ሮ ሀቢባ መሐመድ ሐምሌ 9 ቀን 2004 ዓ.ም አዲስ አበባ ከሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲ በርካታ ገንዘብና የእስልምና መጻሕፍት ተረክበው ሲወጡ እጅ ከፍንጅ መያዛቸው፣ በዚህም ምክንያት በቁጥጥር ሥር ውለው ማረሚያ ቤት መቆየታቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ያ ሲነቃባቸው አሁን በቅርቡ ደግሞ ‹‹ሸገር›› የሚባል ባንክ ማቋቋም እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው ታውቋል፡፡
ይህ ከሆነ ዘንዳ ታዲያ ‹‹ለኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መጠናከር እየሠራሁ ነው›› ብሎ ከሚንቀሳቀሰው ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት›› ቡድን ጋር ምን ሊያወዳጃቸው ይችላል? ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው፡፡ ወዳጅነታቸው ከምሥጢራዊነቱም አልፎ በቅርቡ በአሰላ ከተማ ተዘጋጅቶ በነበረው መድረክ ላይም፡- ‹‹ቀሲስ በላይ፤ ቄሲ ኬኛ፣ በርቱ በምታደርጓቸው ትግሎች ሁሉ እኛ አብረናችሁ ነን!›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በአክራሪ ሙስሊምነታቸው ምክንያት  ከሀገሪቱ ሥልጣን ገለል የተደረጉት አቶ ጁነዲን ታዲያ እነ በላይን ‹‹የኛ ቄስ›› ለማለት ያስደፈራቸው ምን የውስጥ ግንኙነት ቢኖር ነው? የሚለው ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡ ለመሆኑ ኦርቶዶክሳዊ ‹‹ቄስ›› የአክራሪ ሙስሊም ሊሆን የሚችለውስ በምን ሂሳብ ነው? ትክክለኛ ምላሹን እስክናገኝ ግን ግልጽ እየሆነ የመጣ አንድነታቸው ‹‹ኦርቶዶክስን መዋጋት›› እንደሆነ በቂ ፍንጮችን እያገኘን ነው፡፡
በአጠቃላይ አክራሪ እስልምናና ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት›› እንቅስቃሴ ተራክቦ የሚፈጽሙባቸው እስካሁን ግልጽ የሆኑ እነዚህና መሰል ዐውዶች አሏቸው፤ የተሠወረውና ከዚህም የባሰው ወደፊት ሊገለጥ እንደሚችል ይታሰባል፡፡ የሚታወቀውንም ሁሉ ገልጸናል ለማለት አያስደፍርም፤ ‹‹ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል›› እንዲሉ ለጊዜው የምንተዋቸው አሉ፡፡ በዚህ ጽሑፋችን የተቃወምነው ‹‹መተባበራቸውን›› ሣይሆን በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሕልውና ላይ በጋራ መረባረባቸውን ነው፡፡ አንዳንች ስውር ስምምነት ከሌላቸው በቀር የእስልምናውን ክንፍና ‹‹ከክርስትናው ወገን ነኝ›› የሚለውን ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት›› ቡድን ምን ሊያወዳጃቸው እንደሚችል ያጠያይቃልና!
#
ውነትን_በመግለጥና_ሀሰትን_በማጋለጥ_የሀገርን_ሰላምና_የሕዝብን_አንድነት_ለመጠበቅ¬_እንትጋ!
Filed in: Amharic