>

እዛጋ በዜጎች ሕይወት እና ንብረት ላይ ይቆመራል እዚህ ጋር ስለ አገር ልማትና እድገት ብቻ ስሙ... አዉሩ...እንባላለን?!? (ህብር ራድዮ)

እዛጋ በዜጎች ሕይወት እና ንብረት ላይ ይቆመራል እዚህ ጋር ስለ አገር ልማትና እድገት ብቻ ስሙ… አዉሩ…እንባላለን?!?

ህብር ራድዮ

የአንድነት ፓርክ ፕሮጀክት ስኬት ይበል ያሰኛል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀደም ሲል በእቅድ ደረጃ ተይዞ ለዓመታት የቆየን ፕሮጀክት አዳዲስ እቅዶችን አካተው አንድ ፎቅ ተጀምሮ ለማለቅ ዓመታት ተገትሮ በሚቀርበት አገር ይህን በአጭር ግዜ ማሳካት በእርግጥም ጥሩ ጅማሮ ነው።
የፕሮጀክቱን አፈጸም አንስቶ ብቻ ሙገሳ ማዥጎድጎዱ አበው እንዳሉት አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ ያሰኛል። የአንድነት ፓርክ የመጀመሪያ ምዕራፍ መጠናቀቅን አስመልክቶ ባለፈው ዓመት ሲገለጽ እነ ዶ/ር መረራ ሳይቀር ምንሊክ ቤተ መንግስት ውስጥ መታሰቢያቸው ቆመ በሚል ተቆጣጥረን አፍርሰን የእኛን ሐውልት እናቆማለን ብለው ነበር። ዛሬም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅርብ ሰው የሆኑት ሌንጮ ለታ የቀድሞ የኦነግ ሊቀመንበር ያንን ለመቃወም ጃዋርን ይዘው በዚያው የአንድነት ፓርክ ምርቃት እለት የጥላቻ ሐውልት ሊጎባኙ አኖሌ ጋር ሔደዋል።ያ ሰማይ የነካ ጥላቻ ግን በውጤቱ የዜጎችን የግፍ ግድያ አስከትሎዋል። ሻሸማኔን፣ዝዋይ(ባቱ)ን ጨምሮ  የታየው ጥቃት እና ውድመት እንደ ቀልድ ሕወሓት ወደ ተመኘው ዩጎዝላቪያ  ልንሄድ እንደምንችል በግልጽ ያየንበት ወቅት ነው። የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል። መጀመሪያ ተነጣፊዎች ካዱ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩም የዘር ማጥፋት አትበሉ እያሉ ነው። ያሳፍራል።
ከአለፈው ዓመት የአንድነት ፓርክ የቤተ መንግስቱ ያማረ እድሳት በሁዋላ ምን ሆነ? ያ ብዙ ተስፋ የተጣለበት የኢትዮጵያ ልማት ምን ደረሰ? ከጃዋር ተከብቤያለሁ እስከ አስርቲስቱ ግድያ ሽፋን ያደረገ ብሄር እና ሀይማኖት ላይ ያነጣጠረ ግድያ ተፈጸመ። ዜጎች በአክራሪዎች በገዛ አገራቸው ተጋድመው ታረዱ። ከአርባ ዓመት በላይ የለፉበት ንብረት በደቂቃዎች ዶግ ኣመድ ሆነ። ይህ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጦር ሀይሎች አዛዥ ፣የኦሮሚያ ክልልን ጭምር የሚያዛው ገዢው ፓርቲ ሊቀመንበር ናቸው።
 አልታዘዝንም ብሎ መከላከያና የክልሉ ጽጥታ ያ ሁለ ግፍ ተፈጽሞ ስለ አገር ልማት የሚያወሩልን ጠቅላይ ሚኒስትር በስፍራው ሔደው ከጥቃቱ የተረፉትን  አልጎበኙም። ለመሆኑ እንደ አውሬ ታድናው በገዛ አገራቸው መንግስትን ደህንነቴን ይጠብቀኛል ብለው በግፍ ታርደው ተዋርደው አስከሬናቸው ተጎትቶ የሞቱ ዜጎች ጉዳይ፣ከጥቃት አምልጠው በየቤተ ክርስቲያኑና የተለያዩ ስፍራዎች የተጠለሉ ዛሬ መድረሻ አጣን ዳግም የግድያ ዛቻ ደረሰን እያሉ ስለ የትኛው አገር ልማት ነው የሚወራው? ልማት የሚጠላ የለም። እንዲህ እቅዱ ተግባራዊ ሆኖ ስናይ ደስ ይለናል ግን ደግሞ አገሪቱ የገባችበት የፖለቲካ ቅርቃር እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህግና ሥርዓት ለማስከበር ከመጀመሪያው የፈጠሩት የራስን የፖለቲካ እስካልናካ የኔን ሰዎች አይነኩ ድርጊት ቀላል የማይባል ዋጋ አስካፍሎዋል።ዛሬም ከዛ አጣብቂኝ ውስጥ አልወጣንም።
መፍትሄው ምንድነው!? 
የኦሮሞ ጥቅም የሚከበረው ኢትዮጵያ ፋርሳ በመቃብሩዋ ላይ ትንንሽ አገሮች ሲፈጠሩ ነው የሚለው ኃይል ጭምር በመንግስት መዋቅር ውስጥ በከፍተኛ ደርጃ ከላይ እስከ ታች እንዳለ ግልጽ ነው።  የሀጫሉን ግድያ አስታኮ በተቀነባበረ መንገድ የተወሰድው ጥቃት ማረጋገጫ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪና የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ም/ፕ ጠይባ ሀሰን ጭምር እንዳላችበት በገደምዳሜ መገለጹ ለዚህ ማስረጃ ነው።
 የፊት የፊቱን ብቻ እያየን ከበሮ መደለቅ አንፈልግም። እውነት የኢትዮጵያን ታላቅነት ለማምጣት ራዕይ ካለ የኢትዮጵያን አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ግልጽ ሁሉንም ወገኖች ያሳተፈ፣ዜጎች በየደረጃው በጊዜያዊነት የሚወከሉበት፣ፖለቲከኞች ብቻ የሚመክሩባት ሳይሆን የህብረተሰቡ የተለያዩ ተቁዋማት የሚወከሉበት ከሀይማኖት ተቋማት እስከ ሙያና የተለያዩ ማህበራት፣ከገበሬ እስከ ነጋዴ የሚወከልበት ሁሉን አቀፍ አገራዊ ገባዔ ይካሄድ ብሄራዊ መግባባት ይፈጠር።
ክልሎች መጀመሪያ የኔና ያንተ ሳይሉ ሁሉም የክልሉ ነዋሪ የሚወከልበት ፣የሁሉም ድምጽ የሚሰማበት መድረክ ተዘጋጅቶ እያንዳንዱ መክሮ ወኪሉን ለብሄራዊ መግባባት ኮሚቴ ይላክ። የኢትዮጵያ ችግር በአንድ በኩል እየተገነባ በሌላ በኩል ሌላው ያንን ብቻ ሳይሆን አገር አፍርሶ አገር ለመስራት እየተመኘ እና ለዚህም በዜጎች ሕይወት እና ንብረት ላይ እየተቆመረ በዚህ ሁሉ ውጥረት ውስጥ ሆኖ ስለ አገር ልማት ብቻ እየተወራ ነገሩን ማለባበስ ትርጉም የለውም። ብዙ ርቀትም አይወስደንም።
 ስለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ስኬት ለማስቀጠል ሲገፉት የቆዩትን ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ምክክር በማድረግ የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር  የአሻጥር እና የቁማር ፖለቲካ ቀርቶ እውነተኛ የዴሞክራሲ ሽግግር እንዲደረግ ይህን ስኬት በዚያ እንዲደግሙት ደፍረው እንዲገቡበት ለማስታወስ እንወዳለን።

https://www.facebook.com/461427310545569/posts/3514987238522879/

Filed in: Amharic