>
5:13 pm - Monday April 19, 9593

እምዬ ደስተኛ ነበሩ...!!! (አበበ ሀረገወይን)

እምዬ ደስተኛ ነበሩ…!!!

አበበ ሀረገወይን

እምዬ ምኒልክ ጥዋት የሚነሱት ገና ሳይነጋ ከሌሊቱ 10 ሰአት ነበር። መጀመሪያ ጸሎት ቤታቸው ገብተው አንድ ሰአት ያህል በጸሎት ከቆዩ በኋላ ቀለል ያለ ልብስ ለብሰው ሀኪማቸው ቪታልየን እንደመከራቸው ባሽከሮቻቸው ተከትለው ፈጠን ብለው በመራመድ ወደ አንድ ሰአት የሚፈጅ ጊዜ ያሳልፋሉ። የሚከተሏቸው ብርድ ፈርተው በቡልኮ ሲሸፋፈኑ እሳቸው ካለ ምንም ድርብ ሲሄዱ ያዩ በሽታ እንዳይዛቸው እያሉ ይፈሩ ነበር።  በኋላም ስትሮክ የያዛቸው በጥዋት ስለ ነበር ብርድ መቷቸው ነው ይባል ነበር።
እምዬ አልፎ አልፎ በበቅሎዋቸው ሆነው በከተማ ይዘዋወሩና ከህዝብ ይገናኙ ነበር። በገበያውም ፣ ባደባባዩም ይዞራሉ። ሱቆች ከበቅሎ ወርደው ይገባሉ። የህዝብን ስሜት ለማወቅ ከማንም ጋር ያወሩ ነበር። ጨዋታ የሚያውቅ ሰው ካለ እየሳቁ ተጨዋውተው አመስግነው ያልፋሉ።
ምንም የእምዬ ቀን ብዙ ስራ ያለበት ቢሆንም ፣ መዝናናትም የጨመረ ነበር። ጨዋታ አዋቂዎችና አዝናኞች በቤተ መንግስት መተው እሳቸውንና መኳንንቶቻቸውን አስቀው ይሄዱ ነበር። አለቃ ገብረ ሀና ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናቸው። እምዬ በአጼ ቴዎድሮስ ቤት እንደአለቃ ዘነብ አይነት አዋቂና በሳል ጎንደሬዎች ጋር ስላደጉ የሰሜኑንም የመሀል አገሩንም አማርኛና ፈሊጦች በደምብ ስለሚያውቁ የቋንቋ ጨዋታዎችን ይወዱ ነበር።  እምዬ የመዝናናት ለኑሮና ለስራ ስኬታማነት ጠቃሚነቱን ስላወቁ ያገርን ብቻ ሳይሆን የባህር ማዶውንም ለሕዝባቸው እንዲመጣ ይጥሩ ነበር። ለዚህ ነው ሲኒማ ቤትና የፎኖግራፍ ሙዚቃ እንዲስፋፋና እንደ ነጋድራስእሸቴን አይነት ወጣቶች የአርት ጥበብ እንዲቀስሙ ወደ አውሮፖ የላኳቸው።
እምዬ አዳዲስ ነገር በተለይ ላገር ይጠቅማል የሚል ቴክኖሎጂ አፍቃሪ ነበሩ። ይህን የተማሩት ከአጼ ቴዎድሮስ ነበር።  በጥረታቸው የፈረንጆችን አሻጥር በመቋቋም የአጼ ቴዎድሮስን ህልም ባቡሩንም ፣ መኪናውንም ፣ ሰአቱን ፣ ካሜራውን ፣ ብስክሌቱን ወዘተ ያስመጡት። የመጣውን ሁሉ ደሞ ራሳቸው መርምረው ማወቅ ይፈልጋሉ።  ለምሳሌ የጅ ሰአት ሲያስመጡ ፣ ቢበላሽስ ማን ይጠግነዋል በማለት ከስዊስ ባለሙያ አስመጥተው ጥገናውን እራሳቸው ተምረው የተበላሸበት ሰው ሰአቱን ለእደሳ እሳቸውጋ ያመጣ ነበር። ቢስክሌት ሲያስመጡም ንጉስ ነኝ ሳይሉ እየወደቁ እየተነሱ ተለማምደዋል።  ወደኩ ብለው አያፍሩም።  ቢስክሌት የተማሩ አካባቢ የአሜሪካን ልኡካን መተው ቢስክሌታቸውን ነድተው በማሳየት እዝናንተዋቸዋል።
እምዬን አንዱ ልዩ የሚያደርጋቸው ርህሩህነታቸው ነበር። ለምሳሌ በሩሲያው ሆስፒታል በዚያን ዘመን ኦፕራሲዮን ሲደረግ ማደንዘዣ ስላልነበረ እምዬ እዚያ ተገኝተው በሽተኛው በስቃይ ሲያለቅስ እጁን ይዘው አይዞህ እያሉ የሱንም የራሳቸውንም እምባ ያብሱ ነበር።
እምዬ የተሟላ ስብእና የነበራቸው ያገራችን አባት ናቸው። 
የእምዬን ነፍስ አምላካችንይማር።
Filed in: Amharic