>
5:14 pm - Monday April 20, 6815

የሰሞኑን ‹‹ የፖለቲካ››  እስራትና ‹‹ የኅሊና እስረኞች ›› በሚመለከት የመጨረሻ ቃሌ...!!! (ግርማ በቀለ -የህብር ኢትዮጵያ ሊቀ መንበር)

የሰሞኑን ‹‹ የፖለቲካ››  እስራትና ‹‹ የኅሊና እስረኞች ›› በሚመለከት የመጨረሻ ቃሌ…!!!

ግርማ በቀለ -የህብር ኢትዮጵያ ሊቀ መንበር

 

ልደቱን (1986)፣ እስክንድርን (1990) ፣ይልቃልን (2005) ጀምሮ አውቃቸዋለሁ፡፡ እስክንድርን በጋዜጠኛነቱ (ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፖለቲካ እንቅስቃሴው)፣ሁለቱን በፖለቲካ ተሳትፎኣቸው ፤ በፖለቲካ መድረኩ ከኋላ የማውቀው ይልቃል ጋር ረጅምና የቀረበ ፣ከተዋወቅን ጊዜ ጀምሮ በአንድ ያቆመን ወዳጅነት አለን፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሦስቱም ጋር አብሮ ለመስራት ‹ጥረት›› አድርጌኣለሁ፡፡ ከኢዴፓና ኢሃን  በጥምረት ‹‹ አብሮነትን ›› መስርተናል፡፡ በአጭሩ በየመስመሩ ግንኙነታችን የማወቅ ዕድሉን አግኝቻለሁ፡፡የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ አመራሮችን ሥንታዬሁን  በአካል(2007)፣ ቀለብ ሥዩምን በአግ7 አባልነቷ ታስራ በነበረቺበት ጊዜ በሚዲያ  (2006) ጀምሮ አውቃቸዋለሁ፡፡
ከይልቃል በቀር ከሌሎች ጋር በፖለቲካ ስልት፣ በተለያዩ  ጉዳዮች በምንመርጠው አካሄድ ወይም በምንወስደው አቋም ልንለያይ እንችላለን፡፡ ከይልቃልም ጋር ቢሆን የተለያየንበት ጊዜ አለ፤ በተለይ ጠሚ ዐቢይ ወደ ሥልጣን በመጡበትና ‹‹የለውጥ ጅምር›› አለ/የለም በሚለው ላይ ተለያይተን፣ግን አንድ ሳምንት ካልተገናኘን እየተነፋፈቅን አሳልፈናል፡፡
ከሦስቱም ጋር ግን በአንድ ጉዳይ አንድ ነን ብዬ አምናለሁ፡፡ ‹‹ በኢትዮጵያ ዘላቂና አስተማማኝ ለውጥ መምጣት ያለበት በሠላማዊና ሠላማዊ ትግል ብቻ ነው›› በሚለው፡፡በዚህ ላይ ያላቸው እምነት የማይነቃነቅ፣የትግል መርሃቸው ነው፣በምንም መንገድ አንድ ጊዜ የሠላማዊ ትግል ሰባኪ፣ ሌላ ጊዜ ጦር ሰባቂ ሆነው አለመታየት ብቻ ሳይሆን ፣ከሰላማዊ መንገድ ውጪ ያለውን ትግል አለባብሰው ያለፉበትን ጊዜ አላውቅም ፡፡አሁን የተጠረጠሩበትን ‹ወንጀል› መቀበል የማልችለው ከዚህ በመነሳት ነው፤ለፖለቲካ ፍጆታ ካልሆነ ይህንን መንግስትም ጠሚ ዐቢይም ይረዱታል ብዬ አምናለሁ፡፡
ሦስቱም በሥራ ላይ ያለው እንዲሻሻል የሚታገሉት ህገመንግስት ጠበቃ ናቸው፣የማያወላውሉ፣ በተደጋጋሚ ቢታሰሩም ዕድሉ እያላቸው ከአገራቸው ሰማይ ሥር የማይሸሹ ሠላም ሰባኪ ናቸው፡፡  ዛሬ ለሚጠቀስባቸው የህግ የበላይነት መከበር አስፈላጊነትና ወቅታዊነት ሲወተውቱ፣ ያለመከበሩ የሚያስከትለውን አደጋ ሲያመላክቱ የነበሩ ናቸው፡፡
ወንጀላቸው በህገ መንግስት የተሰጠንን መብት በግዴታቸው መሰረት ያለማወላወል የሚጠቀሙ፣ጠሚ ዐቢይ ከበዐለ ሲመታቸው ጀምሮ የገቡትን  ቃል በተግባር እንዲተረጉሙ፣ቃልና ተግባራቸውን እንዲያድደዱ ግንባራቸውን ሳያጥፉ የሚጠይቁና የሚከራከሩ መሆናቸው ነው፡፡በህገ መንግስት የዜጎች(በዘር እንጂ በዜግነት ባያውቃቸውም) የተሰጡ መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ በግልጽና በአደባባይ የሚጠይቁ፣ሲጣሱ ባልተሸፋፈነ ግልጽ ቋንቋ የሚያወግዙ መሆናቸው ነው፡፡ዛሬ እነርሱ የተጠረጠሩበት ‹ወንጀል› ፣በውጤቱ የዘር ማጥፋት (ጄኖሳይድ) የሆነው እነርሱ ባይታሰሩ እንዲህ ተድበስብሶና ተለባብሶ ባልቆዬ ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡
ስለሆነም ለእኔ የባልደራስ አመራሮች፣ ልደቱና ይልቃል እስራት የህግ የበላይነት ማስከበር ጉዳይ ሳይሆን ፖለቲካዊ ነው፣ እነርሱም የኅሊና እስረኞች ናቸው፡፡
ወደ  ርዕሰ ጉዳዬ ልመለስ፡፡
እኔ፣ ከማንም ጋር በሃሳብ ልለያይ እችላለሁ፣መለያየት ተፈጥሮኣዊ ነውና  አልገረምም፣አልፈራውምም ፡፡ የምፈራው ከፈጣሪዬ እንዳልጋጭ ፣ከራሴ እምነትና እሴት/ኅሊና  እንዳልጣላ ብቻና ብቻ ነው፡፡ ከማንም እና ከየቱም ወገንና አቅጣጫ በእምነቴ ጉዳይ የሚመጣ ተቃውሞም ሆነ ትችት ብዙም አያስጨንቀኝም፣ግን አላገናዝበውም ማለት አይደለም፡፡
በማንም ላይ የቱንም ያህል ተቃውሞ ቢኖረኝ ጥላቻ የለኝም፣ቢያስተምሩኝ፣ ቢያሰለጥኑኝ ጥላቻ አልችልም፡፡በተለይ ጠሚ ዐቢይ ላይ ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሁሉ የበለጠና የተሻለ አመለካከት/ አተያይና ድጋፍ አለኝ፡፡ በኢትዮጵያዊ አመለካከታቸው/ኢትዮጵያዊነታቸውና በመልካም አንደበታቸው (ባይተገብሩትም)  ይለያሉ፡፡
ትናንትም ፣ዛሬም ሆነ ዕድሜ እስከሰጠኝ ነገ የምቃወመው፣ አብዝቼ የሚጸየፈውና የምጠላው ፈጣሪ በአምሳሉ የፈጠረው የሰው ልጅ ላይ በሸፍጥ፣ በሴራ፣…የተመሰረተ የፖለቲካ ቁማር ለመጫወትና አፍኖ መብቶቻቸውን ለመርገጥ፣ሠላምና ደህንነታቸውን ለማወክ በማንም፣መቼም የሚደረገውን ጭቆና፣የመብት ረገጣና ረጋጭ ሥርዓትን እንጂ ግለሰብን አይደለም፣ በሥርዓቱ ውስጥ የመሪው ወሳኝ ሚናና በመልካም መደገፉ፣ በጥፋትና ድክመት መወቀስና መተቸቱ  እንደተጠበቀ ሆኖ ፡፡ ይህ ‹‹የህይወት ጥሪዬ›› ነው፡፡
በጣም ፣እጅግ በጣም የማዝነው ትናንት ስንት ተስፋ ያደረግንበት ብቻም ሳይሆን ድጋፋችን የለገስነው ‹‹የሽግግር መንግስት›› ደጋፊዎች ፣መንግስትን ፣ጠሚ ዐቢይን መደገፍ (ሲያልፍም የማምለክ ) መብታቸውን አከብራለሁ፡፡ ግን (የህግ ባለሙያዎችን ጨምሮ) ለመደገፍ ሲሉ የማይወዳደረውን በማወዳደር (እስክንድር/ማንም  ከኢትዮጵያ አይበልጥም፣የህግ የበላይነት መከበር አለበት ሆኖም  ዛሬ  ህወኃት ስለተባረረ የፍትህ ሥርዓቱን ጠርጥሮ ወይም የዜጎችን አላግባብ መታሰር ተቃውሞ ‹‹ይፈቱ››ማለት ወንጀል ነው፣) በአድርባይነት፣ከታሳሪዎች የረጅም ሠላማዊ ትግል እውነት በተቃራኒ ቆመው፣ትናንት ከቆሙበት የእውነት መስመር ተንሸራተው ለጭፍን ድጋፍ ወደ ጭፍን ጥላቻ ተሸጋግረው ‹‹ግደለው፣ፍለጠው፣ ይታሰር፣ ይቆረጥ››…እያሉ ጠሚ ዐቢይን ከሰውነት/ሰብዐዊነት  በላይ ‹‹ፍጹም›› ለማድረግ የሚያደርጉትን  ሳይሆን ሌላው ላይ ‹‹የፍርድ ብይን›› ሲያስተላልፉ፣‹የእስር ዋራንት ሲቆርጡባቸው› መስማት ነው፡፡በተለይ ህመሜን የሚያከፋው እነዚህ ዓይነት ‹‹ደጋፊዎች›› ባህር ማዶ ሆነው ለጠሚ ዐቢይ የበቀል በትር የሚያቀብሉትን ስመለከት ነው፡፡ እንኳን እነርሱን ‹ጦር ሰብቀው› ጫካ የነበሩትን፣‹በሽብር› ተወንጅለው ወህኒ የተጣሉትን ጠርቶ/ፈትቶ የሚያስተናግድ፣እንዲህ የሚደግፉት መንግስት፣‹የሚያመልኩት› መሪ እያላቸው ስለምን መጥተው እንደማያገለግሉን መልስ የማይሰጡንን ነው፡፡
እኔ በብሄራዊ መግባባትና ዕርቀ ሰላም ጉዳይ ታህሳስ 9-13 /1986 (የግዮን አገር አቀፍ የሠላምና ዕርቅ ጉባኤ 5 አስተባባሪዎች አንዱ ሆኜ) ጀምሮ በዚህ ዓላማ በተደረጉ ጥረቶች ሁሉ እየታገልኩ ነው፡፡በአገራችን ከነባር ያልተመለሱ ጥያቄዎች በተጨማሪ ህገመንግስትና  መዋቅር ወለድ የፖለቲካ ችግሮችና ደንቃራዎች ትንታኔና መፍትሄዎቻቸው ባለን ልዩነት፣ (የታሪክ/ትርክት ልዩነቶች፣የአሳታፊ ዲሞክራሲ/አግላይ ጠቅላይ ኃይሎች፣…መካከል)የተፈጠሩ የፖለቲካ አደረጃጀትና ያስከተሉት ውጥረቶች፣ …ለማርገብ እንዲሁም  በተለያዩ ጊዜያት የሚያጋጥሙን የፖለቲካ ለውጥ /ሽግግር የከሸፉት  ዕድሎች ዛሬም እንዳይደገም፣የአገራችን የፖለቲካ ችግርና ያለንበት ምስቅልቅል ከገዢው ፓርቲ  የመሸከም አቅምና መፍትሄ መስጠት ብቃት በላይ ነውና  ‹‹ሁሉን አቀፍ ዘላቂ  የፖለቲካ መፍትሄ ለማምጣት ብሄራዊ መግባባት እና ዕርቀ ሰላም ›› ለማውረድ ውይይት፣ ምክክርና ድርድር እንዲደረግ ፣ ከውይይቱ አስፈላጊ ከሆነ የሽግግር መንግስት ማቋቋም በጽናት የምታገልለት ነው፡፡ ይህንን የሥልጣን ጥማት (በአቋራጭ)ይባል ሌላ ከጭፍን ድጋፍ የሚመነጭ የማሸማቀቂያ ፕሮፖጋንዳ ከሚል ሌላ ትርጉም የምሰጠው አይደለምና አይገደኝም፡፡
ሁላችሁም እንድታውቁልኝ የምፈልገው ጉዳይ ማን፣ምን አለ ‹‹ ስለ ሰዎች ልጆች ነጻነት፣ እኩልነት፣ መብትና ክብር ፣ለአገሬ ሉዓላዊነት፣አንድነት፣ ልማት፣ ሠላምና መረጋጋት…በእውነት ላይ ቆሜ በጽናት መታገል  የህይወት ጥሪዬ ነው›› ብዬ ስለማምን /ስለተቀበልኩ እስከ መጨረሻው በየቱም አደረጃጀት (ፖለቲካ፣ የሰብዐዊ መብት ተሟጋችነት፣…) መጮሄን ፣መታገሌን አላቆምም፣ በአገርና ህዝብ ተስፋ አይቆረጥምና አልቆርጥም ፡፡
በእኔ እምነት  የባልደራስ አመራሮች፣ ልደቱና  ይልቃል ፣(ከላይ በገለጽኩት መንገድ ስለማውቃቸው) የታሰሩት በፖለቲከኝነታቸው እንጂ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ (ነፍስ ይማር) ሞት  ተከትሎ በተፈጸመው የሰው ህይወት ቅጥፈት፣ የንብረት ውድመት፣ የዜጎች መፈናቀልና ስቃይ ጋር የተያያዘ አይደለም፣ …ብዬ አምናለሁ፡፡ እነዚህ ላይ የሃሰት ክስ የሚያቀርቡ፣ ከማንም አይበልጡም፣ መንግስት የህግ የበላይነት ማስከበር አለበት ብለው የእነርሱን ጥያቄ ነጥቀው የሚጮሁ  የመንግስት ደጋፊዎች፣የጠሚዐቢይ አምላኪዎች ፣ በጭፍን ድጋፍና አድርባይነት ካልሆነ ይህ እንደማይጠፋቸው ወይም ስለሚሉት አጥጋቢ መከራከሪያ እንደሌላቸው ያጡታል ብዬ ለመቀበል እቸገራለሁ፡፡ እንግዲህ ከእነዚህ ‹ አውቀው የተኙ › ጋር መከራከርም ሆነ መመላለስ ከንቱ/ ባዶ ንትርክ ነው ፡፡
በዚህ ጉዳይ  ሁለተኛ አልመለስበትም፣ጥያቄ አልመልስምም፡፡ ግን ከተጠየቅሁ፣ ስለ እነዚህ የኅሊና እስረኞች ለሰላም ስላላቸው እምነትና ሰላማዊ ታጋይነት  ተጨማሪ ማብራሪያ  ለማቅረብ ዝግጁ ነኝ፡፡
                       ========
ግልባጭ  :-
ጋዜጠኛ ሀብታሙ አያሌው( ኢትዮ 360)
=====
 ለአቶ ከባዱ በላቸው (ዋሽንግተን ዲሲ)
Filed in: Amharic