>

የበሬ ካራጁ ውሉ (ኤልያስ ደግነት)

የበሬ ካራጁ ውሉ

የህወሓት እና የዎላይታ ነገር

ኤልያስ ደግነት /ኤልሻድ የሺ/


በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ እንደ ህወሓት ፓርቲም ሆነ እንደ መስራቾቹ ሰዎች እድለኛ አካል አለ ቢበላ ለመጥራት ያስቸግራል …ነገሩን እኛ እድል አልነው እንጂ የእድለኝነቱ ሌላ ገፅ ሲታይ ከሰይጣን ልቆ የገዘፈው የረቀቀ የተንኮል እና የሸር ችሎታው ዕድሜውን እንዳቆየለት እንገነዘባለን፡፡ ምናልባት እድለኛ ሊያስብላቸው የሚችለው ነገር ቢኖር ዛሬ ላይ ሀገሪቱን ነጭ እጥንቷን ሆና እስክተቀር፣ዘርፈው፣በልተው አባልተው፣ኢሰብዓዊ ድርጊት ፈፅመው ሳለ ዛሬም ያለምንም ፍርድ ውሃ በጠማው ሕዝብ መኃል ሆነው ውስኪ ሲጎነጩ መኖራቸው ለእስከዛሬው ዕድለኛ ሊያስብላቸው ይችል ይሆናል፡፡የወደፊቱን ግና ማን ያውቃል ሆነና የሚሆነውን አብረን እናያለን፡፡

ህወሓት ስልጣን በያዘ ማግስት ተንደርድሮ ማንንም ሳያሳትፍ ወይ የይስሙላ ተሳታፊዎች በተገኙበት አሻሻልኩት ባለው ሕገ መንግስት ውስጥ ዛሬም ድርስ የተሞላላትን ሰዓት እና ደቂቃ ጠብቃ የምትፈነዳ የጊዜ ፈንጂ/ታይም ቦንብ/ለማልበላባቸው ቀናት ጭሮ መድፊያዬ ይሆናሉ ብሎ ያስቀመጣቸው አንዳንድ አንቀጾች እንሆ እንዳለው የማይበላባቸው ቀናት መጡና የሀገሬውን ሰላም ጭረው ይደፉት ያፈነዱት ከያዙ ሰነባብተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም እነርሱ በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት እራሳቸው ፅፈው ባረቀቁት ሕገ-መንግስት መሰረት ከክልሎች ይቀርቡላቸው ለነበሩት የክልልነት ጥያቄ ይሰጡት የነበረው መልስ እጅጉን አስገራሚ ነበረ፡፡እልፍ ሲልም ይህንን የክልልነት ጥያቄ ሀሳብ አንስተዋል የተባሉ ሰዎች የት እንዴት እና ለምን እንደጠፉ በማይታወቅ መልኩ ድራሻቸው ሲጠፋ  ታይቷል፡፡ ገሚሶቹ ደግሞ ሌሎች የክልልነት ጥያቄ ለመጠየቅ አዝማሚው ላላቸው ወረዳዎች ማስፈራሪያ ተደርገው ሲቀጡ መሰንበታቸው የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት አሁን የዶ/ር ዓብይ መንግስት ስልጣን ላይ ሲመጣ የታየውን ያህል  የክልልነት ጥያቄ ጎልቶ ተነስቶ አያውቅም፡፡

ከላይ በመግቢያች ላይ እንደጠቀስነው የህወሓት ሰዎች ለማልበላበት ቀን ብለው ያኖራትን ጭሮ የመድፊያ አንቀጽ ይጠቀሙ የጀመሩት  ትላንት በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ዛሬ ላይ ደርሶ እንዲህ የቁም እስረኛ ያደርገናል ብለው ሊያስበቡ አይደለም ሊያልሙት ያልቻሉት እና አስበቶ ያረዳቸው ዶ/ር ዓብይ ወደ ስልጣን ከመጣ በኃላ ነበር፡፡

እነርሱ በዘመናቸው ሲነሳባቸው ያንገሸግሻቸው የነበረውን የሲዳማ የክልልነት ጥያቄን የዓብይ መንግስት   እንዴት አይመልስም….ሊመልስላቸው ይገባል ሲሉ የጉዳዩን እሳት ከላይ ሆኖ ከማራገብ መለስ በስር በኩል ደግሞ የለውጡን አካሄድ ለማሳጣት ቅቡልነቱ እንዲጠፋ ነዳጅ በማርከፍከፍም ….ያቀጣጥሉት  ነበር፡፡ከሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የነገር ወናፍ በመንፋት የህወሓት ሰዎችን በማገዝ እና ኤጄቶ የተባለውን ንቅናቄ በህቡም ሆነ በገሃድ ሲደፍ የቆየው አቶ ጃዋር መሓመድ በበኩሉ ክልሉን ለእራት ሲያዘጋጀው መቆየቱ ይታወቃል፡፡ታድያ በእነዚህ ሁለት ሀገር አፍራሽ አካሎች ሳቢያ በ11/11/11 ዓ.ም ሰርቶ ገብቶ በልቶ ከማደር መለስ ፖለቲካ ይሉት ታሪክ የማይገባቸው ንፁሃን ዜጎች አለቁ…የተረፉትም ለቁም አሳር ተዳረጉ፡፡

የህወሓት ሰዎችም ሆኑ ዛሬ በእስር የሚገኘው አቶ ጃዋር ሞሓመድ የተረጋጋች ኢትዮጵያ እንዳትፈጠር ሌት ሳይተኙ ቀን ሳያርፉ የነገር ድንጋይ ሲፈነቅሉ ውለው …የተንኮል ኮረሪማ ሲሰቅሉ ያድራሉ፡፡ህወሓቶች ሲዳማ ላይ የቀበሯት የጊዜ ፈንጂ ብፍ ብላ እንደመፈንዳት ቢዳዳትም …የተወሰኑ ሰዎችን ሕይወት እና ንብረት ከማውድም በዘዘለ በሀገር አቀፍ ደረጃ  ባሰቡት መጠን ይሄ ነው የሚባል የከፋ ነገር ሳያመጣ ጥያቄውም ወቅቱን ጠብቆ ሊመለስ ችሏል፡፡በዚህም የህወሓት ሰዎች በንዴት  ጢማቸውን ሳይነቅሉ አልቀሩም፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በተመሳሳይ መልኩ ዎላይታ ላይ ያኖሯትን ፈንጂ ሊያፈነዱ ሌት ከቀን  ሽር ጉዳቸውን ይዘው መክረማቸው እና በድብቅ ሰው እየላኩ ስብሰባ እንደሚያደርጉ እንዲሁም አንዳንድ ተልዕኮ እንደሚቀበሉ እየተነገረባቸው ይገኛል። ይህም እውነት ስለመሆኑ የሚያረጋግጡ መረጃዎች  ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት እንደተገኘባቸው  ተሰምቷል።

 የዎላይታን የክልልነት ጥያቄ ተገን በማድረግ ለአስብቶ አራጁ ህወሓት ሲሰሩ የነበሩት ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኮምቤን ጨምሮ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች በመከላከያ ሠራዊት መያዛቸው ተሰምቷል።

በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አለማየሁ ባውዲ እንዳሉት የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች የተለያዩ ህገወጥ አደረጃጀቶችን ፈጥረው ግጭት የመቀስቀስ ፍላጎታቸውን እንዲያስፈጽሙ እንደነበር ይናገራሉ። የህወሓት ሰዎች በሚጫኗቸው አጉል ተስፋ ሰክረው የገዛ አካበቢያቸውን ሰላም እንና ደህንነት ለማደፍረስ እና እንደ ኤጀቶ ንቅናቄ በማስፈጠር መብታችንን እናስከብራለን በሚል ያልተገባ ነገር ለመፈጸም እንዳቀዱም ይነገርባቸዋል፡፡

እዚህ ጋር የሚያሳዝነው ነገር የህወሓት ሰዎች የሚያሳዩአቸውን ሳር ብቻ ተመልከትው ገደሉን ችላ ማለታቸው የሰዎችን የንቃተ ሕሊና ጉዳይ የሚያስገመትም ከመሆኑም ባሻገር በቅርቡ ዶ/ሩ  እኛ ኢትዮጵያዊያን የቅረቡን እንጂ የሩቁን ማስታወስ አንችልም ላሉት ነገር ልከኛ ምሳሌ ናቸው፡፡ዛሬ ለእስር የተዳረጉ የዎላይታ ዞን አስተዳዳሪዎችም ሆኑ እዚህ ግባ በማይባል የቀን አበል እና ሽርፍራፊ ሳንቲሞች ተታሎ ለትለቁም ለትንሹም ርዐሰ ጉዳይ በአፉ በኩል የውስጥ አግሩ እስኪታይ ባልተገባ መልኩ አፉን የሚከፍተው አቶ አሰፋ ወዳጆም ቢሆን  ከትላንት አራጃቸው ጋር ስለመተኛታቸው እንዴት ሊጠፋቸው እና ሊዘነጋቸው እንደቻለ ለማንም ግልጽ አይደለም፡፡

አሁን ለዎላይታ የክልልነት ጥያቄ በሚል ሽፋን ከህወሓት ጋር የቆሙ ሰዎች እንደምን ህወሓት ትላንተ የሰራባቸውን የማይነገር ግፍና በድል ረሱ…እንደምንስ ይህንን የገዛ ወገኖቹን  እርቅ ብሎ ጠርቶ …ማታ አብሎቶ ለሊት ያስረሸነ አካል አመኑት የሚለው ጥያቄ ትልቁ እና ዋነኛው ነው፡፡

ሌላው ቢቀር በራሱ ህዝብ ላይ የደረሱትን እነዚህን በደሎች እንደምን ይረሳል፡፡ በደርግ መውደቅ ማግሰት በደስታ እና በእልልታ የተቀበለውን ያን ምስኪን የወላይታ ሕዝብ በአረካ ከተማ በሚቀመው ትልቁ ገበያ መሃል ለተራ የፖለቲካ ፍጆታ ቦንብ በመወርወር ቁጥራቸው 200 የሚደርሱ አረጋዊያንን፣ወጣቶችን፣ህፃናትን መጨረሱን እንደምን እረሱት?……

ማንነቱን ተነጥቆ አዲስ ማንነት የተጫነበት የወላይታ ህዝብ ማንነቴ ይመለስልኝ፣ ቋንቋዬን ልናገር፤ ራሴን በራሴ የማስተዳድርበት የዞናዊ መዋቅር ይሰጠኝ… በማለት ያነሳውን ህገመንግስታዊ ጥያቄ ህወሃት/ኢህአዴግ ጆሮ-ዳባ በማለቱ ጥያቄውን በአደባባይ ለማሰማት ሠላማዊ ሠልፍ መውጣቱን “የመንግስት ግልበጣ ሙከራ” በሚል ውንጀላ በሺዎች የሚቆጠርና እስከ አፍንጫው የታጠቀ መከላካያ ሠራዊት ከወረቀትና ከባዶ እጅ ውጭ ምንም ባልያዘው ህዝብ ላይ በማሠማራት በዕለቱ በወሰደው እርምጃ በጥይት ከተገደሉ 5 ተማሪዎች በተጨማሪ ከዕለቱ ጀምሮ ለሳምንታት ጊዜ በተከታታይ በፈፀመው የድብደባ፣ የእስራትና የማሰቃየት እርምጃ በደረሰባቸው ጉዳት ውሎ አድሮ ህይወታቸውን ያጡ፣ አካለ ጎዶሎ የሆኑ እንዲሁም የጭካኔ እርምጃውን በመፍራት የተሰደዱ፣ የተፈናቀሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የብሔሩ ተወላጆች (ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ሌሎች የመንግስት ሠራተኞች፣ ነጋዴዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች …ወዘተ) የህወሃት ህገወጥ እርምጃ ሰለባ መሆናቸውስ እንደምን ይረሳል?….

 በርግጥ በደልን መርሳት እና መተው እጅጉን ተገቢ ቢሆንም የህወሓት ሰዎች ዳር ዳርታ እና ጠጋ ጠጋ ግና ዕቃ ለማንሳት እንደሆ የዎላይ ልሂቃንም ሆኑ ወጣቶች ሊገባቸው ይገባል፡፡የህወሓት ሰዎች ከጅማሮ ታሪካቸው እስከ ቅርብ ጊዜ ትውስታችን ድረስ ማስተዋል የቻልነው …ነገርን ሁሉ የበላይ ሆኖ መምራት እና ሌላን አካል መረማመጃ ማድረግ እንጂ fair play ይሉት ጨዋታ ጨርሶውን አያውቁም፡፡

እናም ዎላይታዎች ጥያቄያቸው  የቱንም ያህል ትክክል ቢሆንም መልሶቻቸውን እንዴት ባለ መልኩ ማግኘት እንዳለባቸው ቆም ብለው ማሰብ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ከነው ለውጥ በጭራሽ አይመጣምና!

Filed in: Amharic