>
5:13 pm - Sunday April 20, 8702

ወ ን ዝ  ያ ሻ ገ ረ ኝ ን  ኢ ት ዮ ጵ ያ ዊ ነ ት ፍ ለ ጋ.. ! !  ! (አሰፋ ሀይሉ)

ወ ን ዝ  ያ ሻ ገ ረ ኝ ን  ኢ ት ዮ ጵ ያ ዊ ነ ት   ፍ ለ ጋ.. ! !  !

አሰፋ ሀይሉ
 
“በእርግጥ ኢትዮጵያዊ ሆኜ የተፈጠርኩት 
ይሁንልኝ ብዬ አይደለም፡፡ ሳልጠይቅ የተ
ሰጠኝ ነው፡፡ ተላብሼ የቆምኩትን ኢትዮጵ
ያዊነት ግን በድንገት ከመሬት ወድቆ አላገ
ኘሁትም፡፡ በብዙ ውዝግብ፣ በብዙ ፍለጋ፣ 
በብዙ ዙረቶቼ መሀል የተገኘ ወንዝ ተሻጋሪ 
ማንነት ነው!
                   (- ከጽሑፉ የተወሰደ)
የሐረር ልጅ ነኝ፡፡ የአዲሳባም ልጅ ነኝ፡፡ ‹‹የዓለም ዜጋ ነኝ›› የሚል ጥቅስ የጥናት ቤቴ ግድግዳ ላይ ለጥፌ ያደግኩ ኢትዮጵያዊም ነኝ፡፡ የሰው ልጅ የሆነ ነገር ሁሉ ያስደስተኛል፡፡ ያደግኩባት ሐረር በእኔ ዘመን የሁሉም ዓይነት ሰው መኖሪያ ነበረች፡፡ እንኳን ሰውና ሰው – ሰውና ጅብ አብሮ በሰላም ተስማምቶ የሚኖርባት – የሰው ልጆችን ሁሉ እጇን ዘርግታ የምታለምድ – ውብ ምስራቃዊት የሥልጣኔ ደሴት ነበረች፡፡ ሐረር ማንጎና ጂልቦዋን እያጎረሰች አሳድጋኛለች፡፡
በእኔ ዘመን በሐረር – ክርስትያንና እስላም – ኩባና አርጎባ – አደሬና ትግሬ – አማራና ኦሮሞ – ከምባታና ጉራጌ – ጋምቤላና ሱማሌ – ሩሲያውያንና ማልታውያን – ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች – ጠንቋዮችና ጳጳሶች – ሼኮችና ቃልቻዎች – ቱጃሮችና ድሃዎች – ሁሉም ዓይነት ሰው – አንተ እንዲህ ነህ፣ እኔ እንዲህ ነኝ ሳይባባል – በልቶ፣ ጠጥቶ፣ ሠርቶ፣ ከፈለገም አውደልድሎ – ሁሉም በየፊናው ተደስቶ ያድራል፡፡
አሁን ያ ሁሉ ቀርቷል ሲሉኝ ጉድ እላለሁ፡፡ ይሄ ጎሰኝነት በሀገራችን ያላሳየን ጦስ ምን አለ? ለማመን ይቸግረኛል፡፡  ለእኔ እነዚህ ሁሉ የእድገቴ ሥፍራዎች ከማንም በፊት ሰብዓዊነትንና አብሮነትን ቀድመው ያስተማሩኝ – የኢትዮጵያዊነት መማሪያም፣ የኢትዮጵያዊነት ማሳያም ድንቅ የባህል ሜትሮፖሊታኒዝም መማሪያ መጽሐፎቼ ናቸው፡፡
ዕድሜዬ ገፋ እያለ ሲመጣ ግን በማላውቀው ምክንያት ራሴን ይበልጥ በአፍሪካዊነት መነፅር ወደ መመልከት አዘነበልኩ፡፡ ወደ አፍሪካዊ ነገሮቼ ይበልጥ እየተሳብኩ መጣሁ፡፡ የብዙ አፍሪካውያንን ታሪክና ስንክሳር፣ ልብወለዶችና ሌሎች የፈጠራ ሥራዎች በቻልኩት ሁሉ እያሰስኩ አፍሪካዊነቴን ይበልጥ ወደ መፈለግና ወደማወቅ አፍሪካዊ አድቬንቸር የተሰማራሁትም በዚህ ወቅት ነበር፡፡
በመጨረሻም ‹‹ኖሮ ኖሮ ከመሬት፣ ዞሮ ዞሮ ከቤት›› እንደሚሉት አበው – እኔም ዞሬ ዞሬ በመጨረሻ ወዳበቀለችኝ ወደ አንዲቱ ኢትዮጵያ ሀገሬ ነገሮች በሁለመናዬ ተሳብኩኝ፡፡ በማንነት ፍለጋዎቼ ውስጥ ለእኔ ኢትዮጵያ ዋነኛ ዒላማዬ አልነበረችም፡፡ በመጨረሻ ግን ብዙ ነገሮችን ከዳሰስኩና ካስተዋልኩ በኋላ ነው በምርጫዬ ወደ ኢትዮጵያዊው ራሴ በወጣሁበት በር በቀስታ የተመለስኩት፡፡
ኢትዮጵያዊነትህ ሌሎች ውጪያዊ ተክለቁመናህን አይተው አንተን የሚለዩበት ማንነትህ ብቻ እንዳልሆነ ተረዳሁ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከልጅነት እስከ ዕውቀት ኖረህ የምትላበሰው ማንነት ብቻ እንዳልሆነ ተረዳሁ፡፡ ለእኔ ኢትዮጵያዊነቴ ሙሉ የሆነልኝ – እስከ ቻልኩትና አጋጣሚ እስከ ፈቀደልኝ ኢትዮጵያን ሁሉ ዞሬ ስመለከታት ነው፡፡ ሰዎቿ በዓይኔ ላይ ተቀርፀው ይቀራሉ፡፡ የተራሮቿ ማኅተም በውስጤ ታትሞ ቀርቷል፡፡
በህይወቴ ባለፍኩባቸው ያገሬ ሥፍራዎች ሁሉ የሚገጥመኝ… መብሉ፣ መጠጡ፣ አለባበሱ፣ የቋንቋ ጉራማይሌው፣ ህብሩ፣ የሰዎች መልክ፣ ህጻናቱ፣ ጎጆዎቻቸው፣ ታዛዎቻቸው፣ ሻሂያቸው፣ ቡናቸው፣ ጀበናቸው፣ ቂጣቸው፣ በርበሬያቸው፣ ሹሩባና ፍሪዛቸው፣ ነጠላ የተሸፈነ ጡት፣ ተፈጥሮ እንዳመጣቸው ሌጣውን የሚታይ ተረከዝ፣ ኮራ ያለ ዳሌ፣ ሸንቀጥ ያለ ባት፣ ዘረጥ ያለ ወገብ፣ ገፋ ያለ ቦርጭ፣ ቀጠን ያለ አንገት፣…
…ቆንጨር ያለ ጠጉር፣ በቅቤ የራሰ አፍሮ፣ አዲስ የተላጨ የህጻናት ቁንጮ፣ የሴቶቹ ጋሜ፣ የወጣቶቹ ጎፈሬ፣ የልጃገረዶች መሽኮርመም፣ የሰዉ ዓይን አፋርነት፣ ለዛቸው፣ ታሪካቸው፣ ቅርሳቸው፣ ዛፉ፣ ሳሩ፣ ቅጠሉ፣ ሜዳው፣ አበባው፣ ያፈጠጠው አለት፣ በፀሐይ ያረረው መሬት፣ በልምላሜ የሰከረው መስክ፣ ሁሉም ዓይነት ነገር፣ ሁለነገራቸው፣ ሁለነገራችን …. – በአንድ በማላውቀው ከሁሉም፣ ከሁላችንም ከፍ ብሎ በተሰቀለና እንደ ቀስተ ዳመና በሁላችንም ላይ እየሰፈፈ ሁላችንን በአንድ በሆነ በማናውቀው ተዓምራዊ መንገድ አንድ አድርጎ ያስተሳሰረ ትልቅ ኢትዮጵያዊ መንፈስን በሁለመናዬ ይዘራብኝ ነበር፡፡
ባጠቃላይ በኢትዮጵያ ምድር እግሬ በየረገጠባቸው አካባቢዎች የማገኛቸው የተለያዩ ኢትዮጵያውያን ያፈሯቸውና ተላብሰውት የማገኛቸው ነገሮች ሁሉ ለእኔ በልዩ ልዩ ህብረቀለማት እንደተሰሩ ልዩ ኢትዮጵያዊ የሞዛይክ ጥበባት ያሉ ነበሩ፡፡
ኢትዮጵያ የማታሳይህ ዓይነት ሰው፣ የማታሳይህ ዓይነት ኑሮ፣ የማታሳይህ ዓይነት መልክዓምድርና የማታሳይህ ዓይነት ባህልና ልማድ የለም፡፡ ካንተ የሚጠበቀው አዕምሮህን፣ ልብህን፣ አንጀትህን፣ ዓይንህን፣ ጆሮና ቀልብህን ሁሉ ከፍተህ መመግመግ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት በሰራ አካሌ የገባው በዚህ ዓይነቱ ማግበስበስ ነው፡፡ በኢትዮጵያዊነቴ ከመጣህብኝ አልጠረቃም፡፡ የምትመጸውተኝን ምንምን ነገር ሆዴን አስፍቼ እቀበልሃለሁ፡፡ ስለሌሎች አላውቅም፡፡ በበኩሌ የምመሰክረው እውነት ይሄንን ነው፡፡
ኢትዮጵያዊነት የማይሞላ ጎተራ ነው፡፡ አንድም ቀን የኢትዮጵያዊነት ጎተራዬ ሞልቶብኝ አያውቅም! በልቤ ለሁሉም የሚሆን ቦታ አለኝ፡፡ ሁሌ አዲስ አዲስን ነገር ልከትበት ተዘጋጅቼ ነው ስለ ኢትዮጵያ የተጻፈን ድርሳን የምገልጠው፡፡ የኢትዮጵያን ምድር የምራመደው፡፡ ሌላ ቀርቶ የኢትዮጵያን አየርና ውሃ የምቀዝፈው፡፡ ይሄ ሁሉ ሲያልቅብኝ በሃሳቤ ሁሉ እጨምርበታለሁ፡፡ ደግሞም በፍለጋዬ ከስሬ አላውቅም፡፡ ሁሌም አንድ አዲስ ነገር እንዳገኘሁበት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ለእኔ የማያልቅ ሙላት ነው፡፡ የማይሞላ – በቃኝ ብለህም የማትጠግበው – እየታከትክም መልሰህ የምትራበው ፀጋም ነው፡፡
የሚገርመው በተለይ በበረሃም በደንም በተሞሉ ሩቅ የሀገራችን ሥፍራዎች የሚኖሩት ወገኖቼ ጋር እግር ጥሎኝ ዱብ ስል – አንዳንዶቹን በጥቅሻም በመንፈስም የተግባባኋቸው የመሰሉኝን – ጠጋ ብሎ የመጠየቅ ልማድ አለኝ፡፡ ዕድሉን ሳገኝ በምችለው መንገድና ትርጁማን እጠይቃቸዋለሁ፡- ‹‹ኢትዮጵያዊ ነሽ? ኢትዮጵያ የቱ ጋ ነው ያለችው? አሁን የኢትዮጵያ መንግሥት ማነው? ይሄን ፍሬ እናንተ ምን ብላችሁ ነው የምትጠሩት?›› እያልኩ እጠይቃቸዋለሁ፡፡
አብሮኝ ያለ ሰው በጥያቄዬ ግራ ይጋባል፡፡ የቀውስነት መጀመሪያ ሊመስለው ይችላል፡፡ እኔ ደግሞ እነርሱ ሀገራቸውንና ራሳቸውን ዙሪያገባቸውን በሚያዩባት በዚያች ያልተበረዘችው የራሳቸው የሆነች መነፅራቸው በኩል ማየቱ ነው ከምንም በላይ የሚያስቦርቀኝ፡፡ እና አንዳንዴ ግሩሟን በትምህርትም በስብከትም ያልተገራች እውነተኛ አሳባቸውን ያካፍሉኛል፡፡
አንዳንዱን ከራሳቸው አንደበት የምሰማውን እውነት ስነግረው ሰው ሰምቶ ላያምነኝ ይችላል፡፡ ብዙዎቹ እኔና አንተ መንግሥት፣ ዘረኝነት፣ ዲሞክራሲ፣ ነፃ ገበያ፣ ክልልና ክፍለሀገር፣ ልዩ ጥቅም፣ ልዩ ኃይል፣ ምናምን.. ምናምን.. እያልን ስለምንባላባቸው ሺህ ዓይነት ዝባዝንኬ ነገሮች ሽራፊዋ እንኳ ሃሳብ የላቸውም፡፡ ማን መንግሥት ይምጣ፣ የቱ መንግሥት ይሂድ፣ የትኛው ይከተል፣ ኢትዮጵያ የምትባለዋ ሀገር በየት በኩል ይሁን መግቢያዋ፣ በየት በኩል ይሁን ማምለጫዋ፣ የባንዲራችን ቀለም ይለወጥ፣ ወይስ የጥንቱ ራሱ ይሁን፣ አምባሻ ይደፋበት፣ ኮከብ ይውደቅበት፣ አንበሳ ያጋሳበት፣ የፒኮክ ጭራ ይበተንበት… ይሄ ሁሉ ለእነዚህ ወገኖቻችን ጉዳያቸው እንዳይደለ አይቼያለሁ፡፡
ይሄ ሁሉ ለእነሱ ጉዳያቸው አይደለም፡፡ ጉዳያቸው አንተ አጠገባቸው የተደቀንከው ሰው ነህ፡፡ እና ዓይነውሃህን ነው የሚመለከቱህ፡፡ ኢትዮጵያዊነት እንደ ጥሩ ወግ በዓይን የሚገባ መሆኑን ያስተዋልኩት ‹‹ወግ ባይን ይገባል›› ከሚሉት የወሎ ሰዎች ቀጥሎ – ከእነዚህ ንፁህ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ነው፡፡
ማጋነን አይምሰልህ፡፡ እነዚህ በኢትዮጵያ በየሥፍራው እየዞርክ ባጦቻችንንና ቆጦቻችንን ስትወጣ የምታገኛቸው ንፁህ (በነገር ያልተበረዙ፣ በፖለቲካ ያልጦዙ፣ በትምህርትና በሚዲያ ያልተጀነጀኑ – ንፁህ) ወገኖች ብዙ ስለ ሀገር ሲፈላሰፉ አታገኛቸውም፡፡ ብቸኛ ፍልስፍናቸው የራሳቸውን ያለቻቸውን ኑሮ ታግለው በሚያውቁት ወግ መምራት ነው፡፡
ስለሌላው ኢትዮጵያዊ ማንነትና ህይወት መረጃውም ዕውቀቱም የላቸውም፡፡ በሰፊው የኢትዮጵያ ሠማይ ሥር ተጠልለው የሚመላለሱባት ምጥን ህይወት – የራሳቸውን የዕለት ተግባር ከመከወን በቀር – ስለሌላው ለመቃረም አንድ ሚሊዮንኛ እንኳን ዕድሉን አልሰጠቻቸውም፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ከመጣህባቸው፣ እና ቸር ከመሰልካቸው፣ ከአንተ ዓይነቱ አላፊ አግዳሚ ጋር ቸር ቸሩን ሁሉ ተካፍለው ይቆያሉ፡፡ በትዕግሥት ተቀብለው፣ በሠላም ይሸኙሃል፡፡ በዚህ ዓይነት ለዘመናት ኖረዋል በኢትዮጵያ ምድር ላይ፡፡
ይህን ከራሴ ትንሽዬ ዓለም ወጥቼ አስሼ ዳስሼ የማገኘውን ማስመሰል ያልታከለበት የኢትዮጵያዊነት መንፈስ እወደዋለሁ፡፡ ለእኔ እነዚህ ሁሉ ኢትዮጵያዊነታቸውን የማያወሩት – ግን በፅሞና የሚኖሩት – ኢትዮጵያውያኖች ጭምር ናቸው – የኢትዮጵያዊነት ዓለሜን፣ የኢትዮጵያዊነት ፍቺዬን ምሉዕ አድርገው የሚከስቱልኝ፡፡
ለእነዚህ ወገኖቼ – ኢትዮጵያዊነት ማለት – እንደ ምስራቃዊ የዜን መንፈሳውያን – ዝም ብለህ ጥርስህን ነክሰህ የምትኖራት ህይወት እንጂ – የምትነታረክባት ሃሳብ አይደለችም፡፡ ድርሰትና ታሪኮችን እያዘነብክ የምትመሰጥባትም የምትናቆርባትም የቴያትር መድረክ አይደለችም ሀገር ለእነዚህ ሰዎች፡፡ ኢትዮጵያዊነት በቃ ዝም ብለህ መኖር ነው፡፡ ህልውና ነው፡፡ ወልደህ፣ ከብረህ፣ ኖረህ፣ አኑረህ፣ በሠላም፣ በፅሞና በምድርህ ላይ መገኘት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ትሆነዋለህ እንጂ አታወራውም፡፡ ከገበያ አትገበየውም፡፡ ገበያም አታወጣውም፡፡ጨዋ ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ይማርካል፡፡ ልቤን ይማርከኛል ባሰብኩት ቁጥር፡፡
ከእነዚህ የሀገሬ ልዩ ልዩ ሰዎች ካየሁትና ካስተዋልኩት ነገር ተነስቼ ነው – ኢትዮጵያዊነት ከሆነ የሀገሪቱ ገዢ አካል፣ ወይም ከሆነ ታዋቂ መሪ፣ ወይም ከሆነ ክስተትና መልክዓ ምድር፣ አሊያም ከማንም መንግሥት፣ ከየትኛውም አይዲዮሎጂ፣ ወይም ከማንም ትርክት፣ ወይም ከየትኛውም ታሪክም ሆነ ከየትኛውም ባህል በላይ ያለ – ከሁላችንም በላይ የዋለ – ሁላችንንም በምድሪቱ አርግቶ የሚያኖረን – የሆነ አንዳች በምድራችን ላይ እንደ መንፈስ የተዘረጋ – እኛን በየትኛውም ዓለም የተበተንን ጭምር ነዋሪዎቿን ሁሉ – በአንዳች ዕትብታዊ ተዓምር እርስበርስ አቆራኝቶ የሰፋን – ሁሉንም ዓይነት ሕዝብ፣ ሁሉንም ዓይነት መሬትና ልማድ ያበቀለውን ማንነትና ፀባይ – ሁሉንም እንደየዓመሉ አግባብቶ – ሁላችንንም በአንድ የወገንነት መንፈስ የሚያገናኝ – አንድ ድንቅ የማይለወጥ፣ የማያረጅ፣ ለዘመናት የኖረና ገና ወደፊትም የሚኖር – ከቃላት በላይ የሆነ የአብሮነት መንፈስ መሆኑን ለመረዳት ችዬአለሁ፡፡
ኢትዮጵያዊነት ትርጉሙ ጥልቅ ነው፡፡ ሰበዙ ብዙ ነው፡፡ የማይሞላ ሙላት ነው፡፡ የማያልቅበት ሥጦታ ነው፡፡
እንዲህ እንዲህ እያልኩ – ከመላው ዓለም መርጬ – በምመላለስባት ባበቀለችኝ ምድር ኢትዮጵያና – በኢትዮጵያዊነት ታሪኬ ላይ በሰፊው በመመሰጥ ዕድሜዬን የሙጥኝ አልኩ፡፡ ቀስ በቀስ ኢትዮጵያዊ ናሽናሊስት ሆንኩ፡፡
እንዲህም ስልህ የማልሸሽግህ የማንነት ፔንዱለሜን ሳትረሳ ነው፡፡ ህይወት ዥዋዥዌ ነች እንዳለው ፈላስፋ – ኢትዮጵያዊነትም በዥዋዥዌ ሳታንከራትትህ በዋዛ የምትለቅህ ፔንዱለም አልመሰለችኝም፡፡ የቱንም ያህል ጽኑ ኢትዮጵያዊ ብትሆን፣ የቱንም ያህል ከሠማይ አልወርድም ያልክ ፅኑ በራሪ ብትሆን፣ ጊዜና ሥፍራ ጠብቀህ እንደ ፔንዱለም ከአንዱ ወዳንዱ የማትወዛወዝበት የኢትዮጵያዊነት ጸጋ ለማንም አልተሰጠም፡፡
ለምሣሌ በተለያዩ አቅጣጫዎች ያነጣጠሩ የግፍ ቀስቶች ሲወረወርበት ተመልክቼ – ከኢትዮጵያዊነት ማማዬ ላይ ወርጄ አማራ ሆኜ አውቃለሁ፡፡ በተመሳሳይ ምክንያት ከትግሬው ብሼ ትግሬ ሆኜም፣ ከኦሮሞውም በላይ ኦሮሞነትን ተላብሼ የተገኘሁባቸው የህይወት ዘንጎቼም ጥቂት አይደሉም፡፡
አንድ ነጠላዬን ሆኜ ሳለሁ – በሃሳቤና በመንፈሴ ከአፋሩም ጋር አፋር፣ ከሶማሌውም ጋር ሶማሌ፣ ከሙርሌውም ጋር ሙርሌ፣ ከሐመሩም ጋር ሀመር፣ ከጌዲኦውም ጋር ጌዲኦ፣ ከጋሞው ጋር ጋሞ፣ ከድሃውም ጋር ድሃ፣ ከሃብታሙም ጋር ሃብታም፣ ከተራበውም ከጠገበውም፣ ከጥቂቱም ከሁሉምም ጋር፣ ሁሉንም ዓይነት ሆኜ ያሳለፍኳቸው የአብሮነት ቅጽበቶቼ ተቆጥረው አይዘለቁም፡፡ በተለይ ዕድሉ ያለው ሰው ከቆመበት ወጣ፣ ከተገኘበት ትንሽ እልፍ ብሎ – ብዙ ማየት፣ ብዙ መዳሰስ፣ ብዙ መጋራትና ብዙም መሆን እንደሚችል ከልቤ አምናለሁ፡፡
እና አሁን እኔ ማን ነኝ? ኢትዮጵያዊነታቸውን በጽሞና ከሚኖሩት መካከል እንዳልሆንኩ አሳምሬ አውቃለሁ፡፡ ኢትዮጵያዊነትን በዝምታ እንደሚኖሩት እንጂ እየዞሩ እንደማይለፍፉት እንደ እነዚያ በብዙው የሀገራችን ክፍል እንደማውቃቸው ጨዋና ባለንፁህ ልብ ኢትዮጵያውያን ነኝ ብዬ አልመጻደቅም፡፡ ብሆን ምንኛ ደስ ባለኝ፡፡ ግን ራሴን አልዋሸውም፡፡ የማልክደው አንድ ከባድ ልክፍት አለብኝ፡፡ ወፈፍ የሚያደርግ፣ ወዠብ የሚያደርግ፣ ከመሬት አንስቶ ስለ ሀገርና ስለ ወገን የሚያስቃዥ የሚያስለፈልፍ – እስካሁን ሁነኛ መድኃኒት ያልተገኘለት – ክፉ የኢትዮጵያዊነት ልክፍት አለብኝ፡፡
እና ጭው ባለ በረሃም ላይ አውጥተህ ብትጥለኝ ስለ ኢትዮጵያዊነት መለፍለፌን አላቆምልህም፡፡ እንደ ዮሐንስ መጥምቁ ኢትዮጵያዊነትን ሰሚ በሌለበት በረሃ ላይ ጮክ ብዬ ከመስበክ ወደ ኋላ አልልም፡፡ ሰው የማያይልኝን ባንዲራዬን ከፍ አድርጌ በምድረበዳ ላይ ለመስቀል ዓይኖቼን አላሽም፡፡
‹‹ኢትዮጵያዊን ከሀገሩ ታወጣዋለህ እንጂ፣ ኢትዮጵያዊነትን ከልቡ ውስጥ አታወጣውም››፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን፣ ነብር ዥንጉርጉርነቱን›› አይተውም፡፡ እኔም አፌን ሞልቼ እልሀለሁ፡-
‹‹ከሀገሬ የወጣሁ – ነገር ግን ሀገሬ
ከውስጤ ያልወጣች – እንደ ነብር
የተዥጎረጎርኩ – ገንዘብ ሊገዛው
የማይችል የኢትዮጵያዊነት መንፈስ
የተጣባኝ – ባለብዙ ታሪክ፣ ባለብዙ
ላባ፣ ባለብዙ ማንነት፣ ባለብዙ ዝና –
ዝንጥ ያልኩ ኢትዮጵያዊ ነኝ!››
እልሀለሁ፡፡‹‹የእኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለት ቅር ካሰኘህ ግን፣ ‹ገደል ግባ!› እልሃለሁ››፡፡ በፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማኛ ስታይል፡፡
ዘመንህ፣ ዘመንሽ፣ ዘመንዎ፣ ዘመናችን – የተባረከ ይሁን፡፡ ጎተራችን ይሙላ፡፡ ኢትዮጵያችን ጥጋብ ትሁን፡፡ ጥጋበኞቿን ይያዝላት፡፡
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡
Filed in: Amharic