>

ከእንግዲህ የጥላቻ ንግግር አዋጁን በመጣስ በሚል ሌላ ሰው ሊከሰስ አይገባም - ምክንያቱም...!!! (የህግ ባለሙያ አቶ ውብሸት ሙላት)

ከእንግዲህ የጥላቻ ንግግር አዋጁን በመጣስ በሚል ሌላ ሰው ሊከሰስ አይገባም – ምክንያቱም…!!!

የህግ ባለሙያ አቶ ውብሸት ሙላት
1. ሽመልስ አብዲሳ በጥላቻ ንግግር ወንጀል ካልተከሰሰ፣ የጥላቻ ንግግር አዋጁን በመጣስ በሚል ሌላ ሰው ሊከሰስ አይገባም።
2. ሽመልስ አብዲሳ ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት፣ ግጭት ቀስቃሽ ንግግር በማድረግ ካልተከሰሰ፣ ሌሎች ሰዎችም ግጭት ቀስቃሽ ንግግር በማድረግና በማነሳሳት በሚሉ ወንጀሎች ክስ ማቅረብ አድሏዊ (Discriminatory) ነው።
3. ሽመልስ አብዲሳ ባለፈው ዓመት መስከረም ላይ እና (በቅርቡ ይፋ የወጣው)ጥር ላይ ካደረገው ንግግር አንጻር ሲታይ፣ ኦሮሚያ ውስጥ ለተፈፀሙት ጥቃቶች፣ ጭፍጨፋዎች፣ ግድያዎች፣ ንብረት ማውደም፤ በጥቅሉ አገር የማውደም ወንጀሎች በቀጥታ ትእዛዝ ባይሰጥ እንኳን በዝምታ፣ የመከላከል ሥራ ባለመሥራት፣ አጥፊዎች ላይ እርምጃ ባለመውሰድ እና በመሳሰሉት ድርጊቶች የእሱም ሚና የለበትም ማለት አይቻልም። ንግግሮቹ ምስክር ናቸው። ስለሆነም  ከፖለቲካዊ ውሳኔ ባለፈ፣ የወንጀል ምርመራ ማድረግ ተገቢ ነው።
4. ሽመልስ አብዲሳ፣ ከፌደራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነቱ ካልለቀቀም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠርቶ መጠየቅ አለበት። ከአባልነቱ ለቅቆ ከሆነ፣ ክስ ለመመሥረትም ምርመራ ለማድረግም ያለ መከሰስ መብት ስለሌለው ፖሊስ እና ዐቃቤ ሕግ ምርመራ በቀላሉ መጀመር ይችላሉ። ከአባልነቱ ካልለቀቀም ሥርዓቱን ተከትሎ ያለመከሰስ መብቱን ማንሳት ነው። አንድ የምክር ቤት አባል እንደ ሽመልስ አብዲሳ እንዲያወራ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሥነ ምግባር ደንብ (አሠራር) አይፈቅድም። ይከለክላል። ከምክር ቤት አባልነትም ለማባረር በቂ ምክንያት ነው።
************
(ሽመልስ አብዲሳን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ወይም የፌ/ፖ/ኮሚሽነር እንዳሻው ጣሰው ይከሱታል በሚል እሳቤ አይደለም ይህንን የጻፍኩት!! መሆን የነበረበትን/ያለበትን ነው ያነሳሁት)
Filed in: Amharic