>

ሰይጣን የሚለቅቀው በስሙ ሲጠራ ነው...!!! (አባይነህ ካሴ)

ሰይጣን የሚለቅቀው በስሙ ሲጠራ ነው…!!!

አባይነህ ካሴ

፱ሺ፭፻ (9500) ማሰር ጥቃቱን በስሙ ከመጥራት እኩል አይደለም። 
እንደዚህ ብሎ ለማሞኘት የተደረገው ሙከራ ያልተሳካ ጥሪ ነው። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የደረሰውን አሰቃቂ ጥቃት በቃል ለመግለጥ የማይቻል ማለታቸው ደኅና ነበር። ስሙን ለመጥራት ግን ሲተናነቃቸው ታይቷል።
እኛ መንግሥትን ስንቃወም ባለማሰሩ ብቻ አይደለም።
፩. እስራቱ አህያውን ፈርቶ ዳውላውን እንዲኾን አንሻም። ለምሳሌ ኦሮሚያ እና ሐረሪ ላይ ቀጥተኛ ተጠያቂነት ከፕሬዝዳንቶቹ ይጀምራል። በተደጋጋሚ ከአጥቂዎቹ ጎን ተሰልፈው ተገኝተዋልና።
በዚህም ላይ የቄሮ አግቢና አውጪ እኛ ነን ሲሉ ኃላፊነት የወሰዱ አካላት መኖራቸውን ከአንደበታቸው እግዚአብሔር እንዳላሰማን እንሆንላቸው ዘንድ ጠሚሩ ለምን ፈለጉ? ጥቅምት ፳፻፲፪ ዓ.ም. ላይ ሰውየው ተከበብሁ ሲል የወጣው ቄሮ ማዘዣ ጣቢያው እኔ ዘንድ ነበረ ብሎ ያመነ መንግሥት በምን ምክንያት ይታለፋል?
፪. አንድ ሰው ተከበብሁ ስላለ ያ ሁሉ ሰቅጣጭ የሞት ዐዋጅ ከታወጀ ኃይለ ገብርኤል (ሀጫሉ ሁንዴሳ) ሲገደል ምን እንደሚነሣ ቀድሞ ያልገመተ መንግሥት እና ደኅንነት የማንን ጎፈሬ ሲያበጥር ነበር። በዚህ የእኔን እለፉኝ ጨዋታ አንሞኛኝ።
፫. የደረሰው ጥቃት ኦርቶዶክስ ጠል ብቻ ሳይኾን የተወሠኑ ክልሎችን ከኦርቶዶክስ ነፃ የማድረግ ዓላማ እንዳለው ፍጹም ገሀድ ከኾነ ሰነበተ።  አልሰማሁም ብለው አሁንም ሊያሞኙን ይፈልጉ ይኾን? ጥቃቱን በስሙ እስካልጠሩት ድረስ ከመጠየቅ ያመልጡ አይመስለኝም። በቁስላችን ላይ መርዝ እየነሰነሱ የጥቃታችንን ጥዝጣዜ እንዳያባብሱ ማሰብ ሲሳንዎ መካሪ እንኳ ማጣትዎ የበለጠ ያሳምማል።
በቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት እና ሥርዓት ሰይጣን የሚለቅቀው በስሙ ተጠርቶ ነው። ስሙ ካልተጠራ ንቅንቅ አይልም። በዘወትር ጸሎታችን እክህደከ ሰይጣን የምንለው ለዚህ ነው። ካሽሞነሞኑት ፈንጠር ብሎ ይቆይና ተመልሶ ከራሱ በላይ የከፉትን ሌሎች አጋንንት ይዞ ይመጣል። በአግባቡ ያልጸዳ ከፊቱ የኋላው ይከፋል። እየኾነ ያለውን ግፍ መንግሥት ሽፍንፍን አድርጎ ለስሙ በታሰሩ ሰዎች ብዛት የድጋፍ ሰልፍ እንድወጣለት ከጠበቀ አልተገናኞቶም።
የሃይማኖት ጥቃት መፈጸሙን መጀመሪያ ይመን። ኦርቶዶክስን የመንቀል (Religious Genocide) ጥቃት መፈጸሙ የማይካድ ወይም ሊያሳብሉት የማይችሉት ደረጃ ላይ እንደደረሰ ካላወቁ ይወቁ። በሽታውን ደብቆ ክትባቱ ወይ መድኃኒቱ ተገኝቷል ቢባል ማን ይሰማል?ላልታመነ በሽታ (በተለይ በሐኪሙ) የሚፈውስ መድኃኒት እንካችሁ አለን?
፬. በባሌ አካባቢ የኃይለ ገብርኤልን ሞት ሰምቶ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ የነበረው ሕዝብ ቤተ ክርስቲያን መቀበሩን ሲሰማ እኛ እኮ ኦሮሞ መስሎን ነበር እስከማለት የደረሰው ምንን ያመለክታል?
ስለዚህ ፡-
ሀ. ጥቃቱን በስሙ ጠርተው እስካላወገዙ፣
ለ. መንግሥትዎ ይቅርታ እስካልጠየቀ፣
ሐ. ቀንዳም አጥፊዎቹ በሕግ እስካልተጠየቁ፣
መ. ጥቃት የደረሰባት ቤተ ክርስቲያን እና የግፍ ግፍ የደረሰባቸው ልጆቿ ተገቢው ካሣ እስካልተሰጣቸው፣
ሠ. አስተማማኝ ዋስትና ተሰጥቷቸው የተፈናቀሉት ሁሉ ተመልሰው እስካልተቋቋሙ ድረስ በበኩሌ መቼም መች አንስማማም።
Filed in: Amharic