>
5:14 pm - Thursday April 20, 2090

"ንዴት" ያቀናጃቸው አምስት ተፃራሪ ኃይሎች...!!! (ኤርሚያስ ለገሰ)

“ንዴት” ያቀናጃቸው አምስት ተፃራሪ ኃይሎች…!!!

ኤርሚያስ ለገሰ

 ከብአዴን( የአማራ ብልጽግና) ፓርቲ መግለጫ ምን ልጠብቅ?
የሰሞኑ የኦሮሚያ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ የተናገረው ምስጢራዊ መረጃ በመውጣቱ ፀጉሩን እየነጨ ያለው ማነው?… በእኔ እምነት በቅደም-ተከተል እንደሚከተለው አስባለሁ፣
፩: – አክራሪ የኦሮሞ ሃይል ሆኖ የኦሮሚያን ብልፅግና ፀረ-ኦሮሞ አድርጐ እንዲሳል ያደረገው ቡድን ነው። ከዚህ አንፃር ኦነግ፣ ኦፌኮና በፕሮፌሰር እስቅኤል ጋቢሳ የሚመራው ፀረ ኢትዮጵያ ቡድን በቅድሚያ የሚጠቀስ ነው። ይሄ ጽንፈኛ ቡድን የተናደደበት መሰረታዊ ምክንያት በስልጣን ላይ ያሉትን “ኦሮሞ አይደሉም” ፣ “ፀረ-ኦሮሞ ናቸው” ፣ “አሃዳዊ ናቸው” የሚለውን ትርክቱን ጥላሸት ይቀባበታል።
፪: – በሁለተኛ ደረጃ የተናደደው ቡድን ዶክተር አብይ አህመድ (ሽመልስ አብዲሳ) የሚመራው የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ነው። ይሄ ቡድን የሚያብገነግነው መሰረታዊ ምክንያት ድምፃችንን አጥፍተን ብዙዎችን አሳምነን፤ አላምን ያሉንን ግራ አጋብተንና ስኳር አልሰን እየሰራነው ያለነው ሚስጥር ተጋለጠብን በሚል ነው።
፫:- ሶስተኛው ቡድን “ተደጋፊ ተደማሪ” የፓለቲካ ድርጅቶች፣ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች፣ ኦሮሞ ያልሆኑ ባለሃብቶች እና ምሁራን ናቸው። እነዚህ ሃይሎች በአንድ በኩል ማህበራዊ መሰረት የሌላቸው፣ ወይም ማህበራዊ መሰረታቸውን የካዱና በኦሮሚያ ብልጽግና ግንድ ላይ እንደ ሐረግ በመጠምጠም አፈር፣ ውሃና አየር የሚያገኙ ናቸው።
፬:-  አራተኛው ቡድን የኦሮሞ ብልጽግናን የበላይነት ተቀብለው በአድርባይነት ስልጣናቸውን አስጠብቀው ተመቻችተው ሲኖሩ የነበሩ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ናቸው። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑት አቶ ንጉሱ ጥላሁን፣ ደመቀ መኮንንና ተመስገን ጥሩነህን የመሳሰሉ ባለስልጣናት ናቸው።
፭:  አምስተኛው ቡድን ፀረ- ኢትዮጵያ የሆነው ኦሮሞ አክራሪ እንደ ትሮይ ፈረስ በመጠቀም ኢትዮጲያን ለማፈራረስ ቀን ከሌት የሚሰራው የትግራይ ነፃ አውጪ(ህውሓት) ነው።
 
 
ይህን ተከትሎ ከብአዴን( የአማራ ብልጽግና) ፓርቲ መግለጫ ምን ልጠብቅ?
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ በነገው ዕለት ያጠናቅቀዋል ተብሎ በሚጠበቀው ” ጥልቅ ግምገማ” መሰረት በማድረግ የቀጣይ ” ጥልቅ-ተሃድሶያዊ” ጉዞአቸውን የሚያመላክት መግለጫ ያወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
 እንደ አንድ ሞጋችና በጭላንጭል ተስፋ ውስጥ ቢደገፉ ብሎ እንደሚያስብ ሰው በመግለጫቸው ውስጥ የሚከተሉት ቁም-ነገሮች እንዲካተቱ ምክረ-ሃሳቤን አቀርባለሁ፣
፩:- በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ዳተኝነት እና በውስጡ ባሉ አመራሮች ተሳትፎ በአማራ ተወላጆች ላይ የተፈፀመውን ጄኖሳይድ ማውገዝ።
፪:- በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የተፈፀመው ዘርና ሐይማኖት ተኮር ጄኖሳይድ በአስቸኳይ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ መጠየቅ።
፫:- በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በተፈፀመው ጄኖሳይድ ሰለባ ለሆኑ ማቋቋሚያ የሚሆን በፌዴራል መንግስት ” መልሶ ማቋቋሚያ ኮሚሽን” እንዲቋቋም መጠየቅ። ለጄኖሳይድ ሰለባዎቹ በአዲስ አበባ “አይደገምም!” የሚል ስያሜ ያለው ሙዚየም እንዲቋቋም ማድረግ።
፬:- በመላው ኢትዮጵያ( ፌዴራልና ክልል) አማርኛ ቋንቋ የአገሪቷ ብሔራዊ ቋንቋ እንዲሆን መጠየቅ። በሁሉም ክልላዊ መንግስቶች (በተለይም ብልጽግና በሚመራቸው) አማርኛ ቋንቋ ተጨማሪ የስራ ቋንቋ እንዲሆን መጠየቅ።
፭:- የአዲስ አበባ ባለቤት የመላዊ ኢትዮጲያዊ ሆኖ የአዲስ አበባ ክልል መተዳደር ያለባት በአዲስአበቤ ብቻ መሆኑን ማረጋገጫ መስጠት። የኦሮሚያ ብልጽግና ከአዲስ አበባ ላይ እጁን እንዲያነሳ መጠየቅ።
፮:- የፀረ-ኢትዮጲያ ፊት-አውራሪ በመሆን በአጉራዘለልነት ኢትዮጵያን ለማተራመስ ከኦነግና ግብጽ ጋር የተቀናጀው ህውሓት በፌደራል መንግስቱ በሽብርተኝነት እንዲፈረጅ ማድረግ። ይህ የፌዴራል መንግስትን ባልጠበቀው ሰአት የተነጠቀ ዘረኛ አናሳ ቡድን የትግራይ ህዝብ ጠላት መሆኑን መግለጥ። ህውሓትን ከጫንቃው ላይ አንስቶ የመጣል ዋነኛ ሃላፊነት የትግራይ ህዝብ ቢሆንም የአማራ ብልጽግና አስፈላጊውን ድጋፍ ለትግራይ ህዝብ እንደሚሰጥ ማረጋገጥ።
፯:- የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ሰሞኑን የክልላዊ መንግስቱ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ የሰጡትን የፀረ-ኢትዮጲያ መግለጫ በመመርመር የኢትዮጵያን ህዝብ በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ ማድረግ። የአማራ ብልጽግና እንደ ሽመልስ አብዲሳ አይነት አመለካከት ካላቸው ሀይሎች ጋር በጋራ መስራት እንደሚቸግረው ማሳወቅ።
በለማ ተስፋ አልቆርጥም¡
በሽመልስ ተስፋ አልቆርጥም¡
Filed in: Amharic