>

የቴሌፎን ታሪክ በኢትዮጵያ ( አበበ ሀረገወይን)

የቴሌፎን ታሪክ በኢትዮጵያ 

አበበ ሀረገወይን

* እምዬ በካህናቱ ተናደው ሰበሰቧቸው ። እንዲህም አሏቸው ፣ እኔ አገሬን ለማሰልጠን በስንት መከራ ያመጣሁትን ስልክና ማንኛውንም ያልገባችሁን ነገር ሁሉ ሰይጣን አመጣ እያላችሁ ታውኩኛላችሁ ። የናንተ ነገር አገሬን እንዳላሰለጥን የሚያደርግ ስለ ሆነ ይህን የማይቃወሙት ካቶሊኮችጋ እገባለሁ ፣ አሁኑኑ ንገሩኝ አሏቸው…
—-
ቴሌፎን በአሌክሳንደር ግራሀም ቤል በ1876 በተገኘ በ14 አመቱ በ1890 ኢትዮጵያ ውስጥ ጠቀሜታ ላይ ዋለ ። አሁን ስልክ ስለ ተለመደ ድንቅ አይመስለንም እንጂ ስልክ ኢትዮጵያ ሲገባ አብዛኛው አፍሪካና ታዳጊው አለም ስልክ መፈጠሩንም አያውቅም ነበር ። አሜሪካን አገርም ቢሆን በትልልቅ ከተሞች እንጂ ሌላውጋ ወሬውም ያልተዳረሰበት ጊዜ ነበር ።
ታሪኩ እንዲህ ነበር ። ያገራችን የቴክኖሎጂ አባት የነበሩት እምዬ ምኒልክ እንደተለመደው ስለ ስልክ ሲሰሙ ወዲያው ፈልጋችሁ አምጡልኝ ብለው ማፈላለግ ጀምረው ነበር ። ፍላጎታቸው የተሳካላቸው ግን ራስ መኮንን ለአውሮፖ ጉብኝት ሄደው በ1890 ስልክ ይዘው ሲመጡ ነበር ። እምዬም ምንም ጊዜ ሳይፈጁ ከግቢና ግምጃ ቤት መጀመሪያ ፣ በኋላም መስመር እየተዘረጋ በየመስሪያ ቤቱና ፣ ከዚያም ቀጥሎ እስከ ጠቅላይ ግዛት ባጭር ጊዜ እንዲስፋፋ አደረጉ ።
ስልክ መጀመሪያ አገር ሲገባ እምዬ ሹማምንትና ካህናትን ግቢ ሰብስበው ስለ ስልክ ጠቀሜታ እያንዳንዳቸው እንዲሞክሩ አድርገው ነበር ።
ነገር ግን ካህናቱ ይህ የሽቦ ንግግር የሰይጣን ስራ ነው ብለው ተቃወሙ ። እንዲያውም ከካህናት አንዱ የአፈ ንጉስ ነሲቡ መስቀሎ የነፍስ አባት ሌሎች ከግቢ ሲወጡ መጋረጃ ስር ተደብቀው በኋላ ቤት ባዶ ሲሆን ስልኩን ነቅለው ወስደው ውጭ እንጨት ከምረው አቃጠሉት ።
እምዬ በካህናቱ ተናደው ሰበሰቧቸው ። እንዲህም አሏቸው ፣ እኔ አገሬን ለማሰልጠን በስንት መከራ ያመጣሁትን ስልክና ማንኛውንም ያልገባችሁን ነገር ሁሉ ሰይጣን አመጣ እያላችሁ ታውኩኛላችሁ ። የናንተ ነገር አገሬን እንዳላሰለጥን የሚያደርግ ስለ ሆነ ይህን የማይቃወሙት ካቶሊኮችጋ እገባለሁ ፣ አሁኑኑ ንገሩኝ አሏቸው ። እነሱም ተመካከሩና እምቢ ቢሏቸው ጉድ ይፈላል ብለው ከዚያ በኋላ እንቅፋት እንደማይሆኗው ቃል ገቡላቸው።
ስልክ አገራችን በገባ 130 ቢያልፍም እስካሁን ድረስ የመቋረጥ ፣ አስተማማኝ ያለመሆን ችግር አለብን ። በማንኛውም ረገድ በእምዬ ቅጽበትና ትጋት ሁሉ ነገር ቢሰራ አገራችን ይሄኔ የትና የት በደረሰች ነበር ።
Filed in: Amharic