>
5:13 pm - Monday April 20, 2093

ወዮ ለዚህ ለጨለማው ዘመን ካህናት!!! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

ወዮ ለዚህ ለጨለማው ዘመን ካህናት!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

በዚህ የጨለማው ዘመን “የመንጋው እረኞች ነን!” ብለው ስለበጎቹ እራሳቸውን ቤዛ ማድረግ ሲጠበቅባቸው መንጋውን እያስፈጁ እንዳልሰሙና እንዳላዩ ለሚሆኑ ከዚህም አልፈው ይሄንን ፀረ ቤተክርስቲያን አገዛዝ እያገለገሉ ላሉ ምንደኛ ጳጳሳት፣ መነኮሳትና ቀሳውስት ወዮ!!!
“መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ይሰጣል፡፡ እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኩላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኩላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል፡፡ ሞያተኛ ስለ ሆነ ለበጎቹም ስለማይገደው ሞያተኛው ይሸሻል!” ዮሐ. 10፤12-13
ከቶ የት ገብተው የእግዚአብሔርን ቅጣት ያመልጡ ይሆን???
እሽ ከአገዛዙ ቅጣትስ በጎች (ነፍሰጡር እናቶችና ሕፃናት ሳይቀሩ) በአሰቃቂ ሁኔታ በአገዛዙ አካላትና በአረማውያን ጭፍሮቻቸው የተቀናጀ ጥቃት እየታረዱ ሲጣሉና ለቀብር እንኳ እንዳይበቁ ተደርገው አውሬ ሲበላቸው፣ የእግዚአብሔር ቤት እንደ ጥዋፍ ሲነድ፣ የእግዚአብሔር ክብር መገለጫ ንዋዬ ቅድሳት ክብራቸው ሲደፈርና ሲዋረድ…… እንዳላዩና እንዳልሰሙ ሆነው ዝም በማለታቸውና ከዚያም አልፈው ለአገዛዙ ጥብቅና በመቆም በካድሬነት በማገልገላቸው ሥጋን እንጅ ነፍስን መቅጣት የማይችለውን የአገዛዙን ቅጣትስ አመለጡት እሽ!!!
ነፍስንና ሥጋን አንድላይ ገሃነም በማውረድ የሚቀጣውን የእግዚአብሔርን ቅጣት ግን እንዴት ያመልጡት ይሆን???
“ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ!” ማቴ. 10፤28
የዛሬ ዘመን ካህናት እኮ አያፍሩም ይሄኔ እኮ በመቀለማመድ ሰውን እንደሚያታልሉ እግዚአብሔርንም ማታለል የሚችሉ ይመስላቸው ይሆናል እኮ!!! ሊቁስ “ኢትመኑ ሰብአ እንበለ ሰለሥቱ ሥላሴ፤ በሳምናዊ ዘመን አምጣነ አልቦ መነኩሴ!” ሲል የተቀኘው ለዚህም አይደል???
“እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፥ እንደ ሥራው ፍሬ እሰጥ ዘንድ ልብን እመረምራለሁ ኩላሊትንም እፈትናለሁ!” ኤር. 17፤10
“አቤቱ፥ ምሕረትም ያንተ ነው፤ አንተ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ፍዳውን ትሰጣለህና!” መዝ. 62፤12
“የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል!” ማቴ. 16፤27
“እርሱ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ያስረክበዋል!” ሮሜ 2:6
“ለሰው ፊትም ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ ብትጠሩ በእንግድነታችሁ ዘመን በፍርሐት ኑሩ!” 1ኛ ጴጥ. 1፤17
እውነቴን ነው የምላቹህ ብዙዎቹ እግዚአብሔርን እንደ ሰው ማታለል እንደሚችሉ ሳያስቡ አይቀሩም፡፡ ወይም ደግሞ ቆብና ቀሚስ አጥልቀው፣ መስቀል ጨብጠው ይታያሉ እንጅ በእግዚአብሔር መኖር አያምኑም!!!
እንዲህ ብለው ስለሚያስቡ ወይም ስለማያምኑ ካልሆነ በስተቀር ሥጋን ብቻ ለአጭር ጊዜ መቅጣት የሚችለውን ነፍስን መቅጣት ግን የማይችለውን የምድር ገዥ ፈርተው ለእሱ በመሽቆጥቆጥ እየተገዙና እሱን በታማኝነት እያገለገሉ ነፍስንና ሥጋን አንድ ላይ ለዘለዓለም በገሃነም መቅጣት የሚችለውን ሾሞ ያሰማራቸውን እግዚአብሔርን ግን ሊንቁ፣ ሊዳፈሩ፣ ሊያስቀይሙና ሊከዱ አይችሉም!!!
በእግዚአብሔር የሚያምን ሰው በመንገዱ ለደቂቃ እንኳ እግዚአብሔርን አይረሳም፣ እምነቱ በእግዚአብሔር ነው፣ ሥጋ ለባሽን አይፈራም፣ አኪያሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደርጋል፣ ፍርድና ቅጣቱን ዘወትር ያስባል፣ ታማኝነቱን ለእሱ ብቻ ያደርጋል ይሄንንም በሥራ ይገልጣል!!!
Filed in: Amharic