>
5:14 pm - Friday April 20, 3325

አማርኛና አዲስ አበባን ከመስፋፋት መግታትም ሆነ ማዳከም አይቻልም!!! (ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ)

አማርኛና አዲስ አበባን ከመስፋፋት መግታትም ሆነ ማዳከም አይቻልም!!!

ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ

አማርኛ ከንጉስ ላሊበላ ጀምሮ የቤተመንግስት ቋንቋ መሆን እንደጀመረ የታሪክ መዛግብት ይገልጻሉ፣ ምንም እንኳ ንጉስ ላሊበላ አገው የነበረ ቢሆንምና የአካባቢው ህዝብም በብዛት አገውኛ ተናጋሪ እንደነበረ የሚታወቅ ቢሆንም አማርኛን የመንግስቱ የስራ ቋንቋ አድርጎ ተጠቀመበት፣ ይህም የሆነው የአማራው መሪ ወይም ህዝብ አስገድዶት አልነበረም፡፡ ይልቁንም መንግስቱን ለማዘመንና ለማስፋፋት ስለሚረዳው እንጂ፡፡
ከዛ በኋላ ምናልባትም በየጁ ስረዎ መንግስት (በዘመነ መሳፍንት) በነበሩት ጊዜያት የማዕከላዊ መንግስት በእጅጉ ተዳክሞ የነበረ ቢሆንም ጎንደርን የመንግስቱ ማዕከል አድርጎ ከአማርኛ ጎን ለጎን በመሳፍንቱና መኳንንቱ አካባቢ የኦሮምኛ ቋንቋ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ ሞከሮ እንደነበረ ይነገራል::
ይህም ሆኖ የኦሮምኛ ቋንቋ ከዛ በላይ ተስፋፍቶ አማርኛን ሊገዳደረውና ሊተካው አልቻለም፡፡  ሌላው ቀርቶ የትግራዩ ካሳ ምርጫ በአጼ ቴዎድሮስ የተሰጣቸው ዝቅተኛ ሹመት አበሳጭቷቸው ከሸፈቱ በኋለ ዋክሹም ጎበዜ የእህቱ ባል ስለነበሩ የደጃዝማችነት ማዕረግ በመስጠት የተንቤን አካባቢን እንዲገዙ ፈቀዱላቸው፡፡
ከዛም ዋክሹም ጎበዜና ደጃዝማች ካሳ ምርጫ የጋራ ጠላታቸው የነበሩትን አጼ ቴዎድሮስን እንግሊዞችን እንዲያልፉ ከመፍቀድ ጀምሮ መንገድ በመምራት ስለተባበሯቸው የአጼ ቴዎድሮስን ጦር አስመትተው ለስልጣን ሲሉ የሀገራቸው መንግስት እንዲሸነፍ በማድረግ የምርኮው ተቋዳሽ ለመሆን በቁ፡፡
ከዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ዘላለማዊ እረፍት በኋላ ዋክሹም ጎበዜ አጼ ተክለ ጊወርጊስ በሚል ስመንግስና ለሶስት አመታት ያህል ኢትዮጵያን ሲመሩ ቢቆዩም ደጃዝማች ካሳ ምርጫ ከእንግሊዝ ጦር ያገኘውን በርካታ የመሳሪያና የቁሳቁስ ድጋፍ በመጠቀም አጼ ተክለጊወርጊስን በጦርነት አሸንፈው አጼ ዮሀንስ 4ኛ የሚል የንግስና ስም በመያዝ ወደስልጣን መጡና አገሪቱን ለ17 አመታት ያህል ማስተዳደር ቻሉ፡፡
ሆኖም አጼ ዮሀንስ 4ኛ ትግሬ የነበሩ ቢሆንም የመንግስታቸው ቋንቋ ግን አማርኛ ነበር፡፡ ከትግራይ የሚመጡ ባለጉዳዮች ሳይቀሩ አቤቱታ ሲያቀርቡ ንጉሰነገስቱ ራሳቸው በአስተርጓሚ ይጠቀሙ እንደነበረ በታሪክ ተጽፎ አንብበናል፡፡ ለምን ቢባል በዙሪያቸው የነበሩት መሳፍንትና መኳንንት ትግርኛ ስለማይሰሙ ፍርድ ለመስጠት ይቻል ዘንድ አብዛኛው ሰው የሚሰማውን አማርኛ መጠቀም ግድ ነበርና፡፡
ይኸ ሁሉ ሲሆን አማርኛ የመንግስትም ይሁን የስራ ቋንቋ እንዲሆን ያስገደደ ንጉሰ ነገስትም ሆነ ንጉስ ወይም የተደራጀ ህዝብ አልነበረም፡፡ ከግዕዝ ቀጥሎ የአማርኛ ቋንቋ በስፋት አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ ረገድ ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ መንግስታት ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ አድርገው ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም የሆነው አማርኛ በቀላሉ የሚለመድና በጽሁፍም ለመጠቀም የሚያስችል ብቃት ስለነበረው ነው፡፡
እናም የአማርኛ ቋንቋን እንዲለምድ የተደረገ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የዘመኑ የብሔር ፖለቲከኞች ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በመጮህ አማርኛን የገዥ መደቡ ቋንቋ ስለሆነ እንዳይስፋፋና እንዲዳከም ለማድረግ የሚያስችል ፖሊሲ ቀርጸንና ፖለቲካዊ ውሳኔ አሳልፈን መስራት አለብን እንደሚሉት እንዲሁ በቀላሉ የሚዳከም ቋንቋ አይደለም፣ ለምን ቢባል አማርኛ ከሞላ ጎደል አብዛኛውን የኢትዮጵያ ህዝብ ያግባባላ፡፡
ከዛም አልፎ ይህችን ሀገር መምራትም ሆነ በሚኒስትርነት ማገልገል የሚፈለግ ማንኛውም ፖለቲከኛ ቢያንስ አማርኛ መቻል ይኖርበታል፣ ስለሆነም ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ አለዚያ ድንጋይ ነው ብለው ይወረውሩሀል የሚለው አባባል ስራ ላይ መዋሉ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ሌላው ቢቀር በዚህች አገር ውህድ ማንነት ያለውን ኢትዮጵያዊ ጨምሮ አማርኛ ተናጋሪው ህዝብ ብዙ ስለሆነ ድምጹ ይፈለጋል፡፡
ባለፉት 29 አመታት ከአማራ ክልልና ከፌዴራሉ መንግስት በተጨማሪ ቀደም ሲል የአፋር ክልል አማርኛን ይጠቀም ነበር፣ አሁንም ቢሆን ሙሉ ለሙሉ የተወው አይመስለኝም፣ እስካአሁን ድረስ ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ብ/ብ/ህ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝና ጋምቤላ ክልሎች አማርኛን የስራ ቋንቋቸው አድርገው እየተገለገሉበት ነው፡፡ አዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞችም የስራ ቋንቋቸው አማርኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ከዛም አልፎ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኙትን ጨምሮ አብዛኛዎቹ የአገሪቱ ትላልቅ ከተሞች የመግባቢያ ቋንቋቸው አማርኛ ነው፣ ከተሜነት እየተስፋፋ ሲሄድም ይኸው ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛች አገር በመሆኗም ህዝቦቿ በውጭ ቋንቋ የመወረር እድላቸው ዝቅተኛ ነበር፣ በእርግጥ የኦሮሞን ጨምሮ አንዳንድ የብሔር ፖለቲከኞች አማርኛን ያዳከሙ መስሏቸው የላቲን ፊደልን ለመጠቀም ተገደዋል፡፡ በዚህም ከስረው ሊሆን ይችላል እንጂ እንዳላተረፉበት ግልጽ ነው፡፡
ከመገናኛ ብዙሀን አጠቃቀም ጋር ያለውን ሁኔታ ስንመለከትም በትንሹ ባለፉት መቶ አመታት አማርኛ የህትመትና የኤሌክተሮኒክስ ሚዲያውን በሚገባ ተቆጣጥሮት ቆይቷል፣ ሌላው ቀርቶ አማርኛን የሚጠሉት የዘመናችን ብሔር ተኮር የመገናኛ ብዙሀን እንኳ አማርኛን ለመጠቀም ተገደዋል፡፡
በዚህ ረገድ የትግራይ ቴሌቪዥን፣ ድምጽ ወያኔ ቴሌቪዥን፣ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ፣ የኦሮሚያ ብሮድካስት ኔትወርክ ወዘተ በአማርኛ ዜና ከማቅረብ አልፈው በፕሮግራም ስርጭት ይጠቀሙበታል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያውም እንዲሁ፡፡ የሚያሳዝነው ነገር ብዙዎቹ የብሔር ፖለቲከኞች አማርኛን ለማውገዝና ለማጥላላት አማርኛን ጥሩ አድርገው መጠቀማቸው ነው::
መቼም እንደመለስ ዜናዊ በአማርኛ አቀላጥፎ የሚናገርና የሚጽፍ ሰው አልነበረም፣ ሽመለስ አብዲሳም ቢሆን ከእኛ እኩል አማርኛን ይራቀቅበት ጀምሯል፣ በዚህም እነዚህ ፖለቲከኞች በእጅጉ ተጠቀሙ እንጂ አልተጎዱም፡፡ መለስ አማርኛ ባይችል ኖሮ በትግራይ ክልል ብቻ ተወስኖ ይቀር እንደነበር ልብ ማለት ተገቢ ይመስለኛል፡፡
ይህ ማለት ትርጉሙ ብዙ ነው፣ ይልቁንም የሚሻለው የአማርኛን መስፋፋት መግታትና ከዛም አልፎ ማዳከም ሳይሆን ጎን ለጎን ኦሮምኛን ጨምሮ ሌሎቹም የሀገራችን ቋንቋዎች እንዲስፋፉና የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ መግባቢያ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡
አለበለዚያ ልጆቹን በእንግሊዘኛ/ በፈረንሳይኛ/ በአረብኛ ለማስተማር ከአቅሙ በላይ የሆነ ገንዘብ ለማውጣት የሚገደድ ሰው አማርኛ ላይ ቅናት በማሳደር ለማዳም ጥረት ማድረግ ኢትዮጵያ የጋራችን እንድትሆን እንሰራለን ከሚሉ ፖለቲከኞች በፍጹም አይጠመቅም፡፡
Filed in: Amharic