>

ሊነሱ ከሚገባቸው ብዙ ጥያቄዎች ጥቂቱ፤ ተጠያቂው ማን ነው? (ያሬድ ሀይለማርያም)

ሊነሱ ከሚገባቸው ብዙ ጥያቄዎች ጥቂቱ፤ ተጠያቂው ማን ነው?

ያሬድ ሀይለማርያም

በኦሮሚያ ክልል በዜጎች ላይ ለተፈጸመው ዘር እና ኃይማኖት ተኮር ጭፍጨፉ እነማን ናቸው በሕግ ሊጠየቁ የሚገባው? ምናልባት እነዚህ ጥያቄዎች መልስ ሲያገኙ ተጠያቂዎቹ እነማን እንደሆኑ በቅጡ መረዳት ይቻላል።
+ ክልሉ ተደጋጋሚ እና ዘር ተኮር ጥቃቶችን ሲያስተናግድ ቆይቷል። በመሆኑም የሰሞኑ የሃጫሉን ሞት ተከትሎ የተከሰተው አስነዋሪን እና አስከፊ ተግባር አዲስ ዱብ እዳ አይደልም። ታዲያ እንዲህ ያሉ ጥቃቶች ተደጋግመው ከተከሰቱ እና ሊከሰቱ የሚችሉበት በርካታ እና በግልጽ የሚታዩ ምልክቶች ከነበሩ መንግስት ምን ቅድመ ዝግጅት አደረገ?
+ ቀደም ሲል በቡራዩ፣ በሰበታ፣ ሻሸመኔ፣ ሐረር እና ድሬዳዋ እንዲሁም ከጥቅምቱ የሰማኒያ ስድስት ሰዎች ግድያ ተነስቶ መንግስት፤ በተለይም ችግሩ ተደጋግሞ የሚከሰትበት የኦሮሚያ ክልል ምን አይነት የግጭት ማስወገጃ እና መቆጣጠሪያ ስልቶች ነደፈ?
+ ከላይ የተነሱት ሁለት ነገሮች በመንግስት ተከናውነው ከሆነ ታዲያ ለምን በሥራ ላይ ማዋል አልተቻለም? ጭራሽ ጉዳዩ ትኩረት ያላገኘ እና ያልታሰበበትም ከሆነ ለዚህ ዳተኝነት ማነው ኃላፊነቱን የሚወስደው? ማነው ተጠያቂው?
+ በየሦስት ወሩ እሪባን እየቆረጡ እና እየደገሱ ሚሊሻ እና ልዩ ኃይል የሚያስመርቁት የክልሉ ባለሥልጣናት ይህን ኃይል ጥቃትን እንዲያስቆም እና ዜጎችን እንዲከላከል ትዕዛዝ መስጠት ለምን አቃታቸው? ሰራዊቱስ ለመቼ እና ለምን ተልዕኮ ነው በግብር ከፋዩ ገንዘብ ሠልጥኖ እና የወር ደሞዝ እየበላ ካምፕ ውስጥ ቁጭ ብሎ የሚቀለበው?
+ የክልሉ መንግስት በክልሉ ውስጥ ለሚኖሩ ዜጎች በተደጋጋሚ ጥበቃ ማድረግ ባለመቻሉ የብዙ ዜጎች ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ አልፏል፣ ከፍተኛ ግምት ያላው ሃብት ወድሟል። ለእዚህ ማነው ኃላፊነት መውሰድ ያለበት?
+ ከዚህ አሰቃቂ ጭፍጨፋ የተረፉ እና ቤት ንብረታቸው ተቃጥሎና ተዘርፎ በየቤተክርስቲያኑ የተጠለሉ ሰዎች ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ምስክርነት እስካሁን በመንግስት ባለሥልጣናት እንዳልተጎበኙ እና ምንም አይነት ድጋፍ እንዳልተደረገላቸው፤ በተቃራኒው ከተጠለሉበትም ቤተክርስቲያን ለቀው እንዲወጡ አሁንም ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል። ከዛም አልፈው መንግስት አለ ወይ እያሉ ሲጠይቁ ይሰማል። ዛሬስ መንግስት ምን እየሰራ ነው? ለቅሶ ደራሽ የነበሩት ባለስልጣናቱስ ምን ሰወራቸው? ለተጎጂዎች ተገቢውን እርዳታ እና የመቋቋሚያ ድጋፍ ለምን እስካሁን ማድረግ አልጀመሩም?
+ የክልሉ መንግስት ከታች እስከ ላይ ያለው መዋቅር ለዜጎች ጥበቃ ማድረግ ሳይችል፤ በአንዳንዱ ቦታም ሆን ተብሎ በሚመስል መልኩ የጸጥታ ኃይሎች ጥቃቱን ከማስቆም ይልቅ የማባባስ ሥራ ይሰሩ በነበረበት ሁኔታ በጠዓት የሚቆጠሩ የወረዳ እና የከተማ ሹማምንቶችን በማሰር ብቻ የክልሉ መንግስት ሕግ በማስከበር እረገድ ላሳየው ክሽፈት ማቅኛ ይሆናል ወይ? ነገሩን በዚህ መልክ አደባብሶ ማለፍስ ይቻላል ወይ?
+ የክልሉ ም/ሊቀመንበር አቶ ሽመልስ፣ የክልሉ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ እና በየደረጃው ባሉ የክልሉ ከፍተኛ ሹማምንት ላይ ምርመራ ማድረግ እና ባሳዩት ቸልተኝነት ልክ በሕግ ሊጠየቁ አይገባም ወይ?
+ የፌደራል መንግስቱስ በአግባቡ የክልሉን ባለሥልጣናት ለደረሰው ውድመት እና ለዜጎች ጥበቃ ባለማድረግ በሕገ መንግስቱ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ባልተወጡት ሹማምንት ላይ እርምጃ ካልወሰደ ተጠያቂነቱ ወደ ፌደራል መንግስቱ መምጣት የለበትም ወይ?
+ ቤት አቃጣዮቹን፣ የሰውን ልጅ ቆራርጠው በጭቃኔ መንገድ የገደሉትን ጨፍጫፊዎች፣ ከጀርባ ሆነው ያነሳሱዋቸውን እና ያደራጁዋቸውን ሰዎች ለፍርድ ማቅረቡ የመንግስት አንዱ ግዴታ ስለሆነ ሰሞኑን እየተወሰደ ያለው እርምጃ ይበል ያስብላል። ነገር ግን ዜጎችን ከእንደነዚህ አይነት ጨካኞች የመታደግ፣ የመንግስትን እና የግለሰቦች ሃብትን ከዘራፊዎች እና ከወሮበሎች የመጠበቅ ኃላፊነቱን ያልተወጣውንስ መንግስት የጸጥታ ኃይል ኃላፊዎች፤ የደህንነት ቢሮ፣ የሚሊሻ፣ የልዩ ኃይሎ፣ የክልሉ ፖሊስ አዛዥ እና የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊዎችንስ መመርመር እና ተጠያቂ ማድረግ አይገባም ወይ?
ይህ አይነቱ የነውር ሥራ የተፈጸመው በጨዋ አገር፣ ጨዋ እና ስልጡን ፖለቲከኞች ባሉበት አገር ቢሆን ኖሮ እንኳን ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ዝምድና ያላቸው አይደሉም ጥቃቱን ለማስቆም ምንም እድል እና ኃላፊነት የሌላቸው ሹማምንት በራሳቸው ፈቃድ ከሥልጣን ይለቁ ነበር። ያንን እንኳ ባያደርጉ አደባባይ ወጥተው ለዚህ ጥቃት እና ውርደት ያጋለጣችሁን መንግስታዊ አካል የማገለግል ሰው በመሆኔ ሃፍረት ይሰማኛል፣ ይቅርታ አድርጉልኝ፣ ማሩኝ፣ እክሳችኋለው ብሎ የጸጸት እና የተስፋ ቃል ያሰሙን ነበር። እኛም አልሰለጠንም፤ ፖለቲካችንም ገና አልሰለጠነም።

አሁንም ጭፍጨፋው በተፈጸመባቸው እና በተጎዱ ወገኖች ስም ፍትሕ እንጠይቃለን!!!

Filed in: Amharic