>

‹‹የታናናሾችን ምክር ከመስማት ጆሮውን የሚመልስ ይጠፋል!››  — ቅዱስ መጽሐፍ (አሰፋ ሀይሉ)

‹‹የታናናሾችን ምክር ከመስማት ጆሮውን የሚመልስ ይጠፋል!››  — ቅዱስ መጽሐፍ

አሰፋ ሀይሉ

ዛሬ ጥቂት ያልተቀባባች መልዕክቴን ለመናገር ፊት ለፊት መጣሁ፡፡ ህሊናና እውነት ስላስገደደኝ ነው፡፡ የኢትዮጵያዊነት ዕዳም፣ የሀገር ውለታም እንድናገር ገፋፍቶኛል፡፡ በችግርና ፈተና ወቅት ወጥቶ ፊት ለፊት ለመናገርና ለመነጋገር አለመድፈራችን ብዙ ነገሮችን አሳጥቶናል፡፡ ፊት ለፊት መናገርና መነጋገር በዓለም ሁሉ የተበረታታው – በቃላት ለመመሰጥና ለአልኩ-ባይነት ብቻ ሳይሆን – ሁላችንም የማንፈልገውን ፊት ለፊት መተኳኮስን ስለሚያስቀርልን ነው፡፡ ንግግር የሰላም አባት ስለሆነ ነው፡፡ ቃል ህይወት ስለሆነ ነው፡፡ ለዚህስ ሲል ንግግር ለዘለዓለም ይኑር፡፡
ይህን ካልኩ ዛሬ ፊት ለፊት ልናገር የፈለግኩት በሰሞኑን እያየለና ወዳልተፈለገ አደገኛ ብሽሽቅና የኃይል ትዕይንቶች እየተሸጋገረ ስለመጣው የትግራይ ክልልን በሚያስተዳድረው ኃይልና የማዕከላዊ መንግሥቱን በሚያስተዳድረው ኃይል መካከል እየታየ ስላለው አስጊ ፍጥጫ ነው፡፡
በነገራችን ላይ አንድ የታዘብኩት ነገር – ወያኔ (ህወኀት) ‹‹በክልሌ ምርጫ አካሂዳለሁ!›› ስትል፣ ማዕከላዊው መንግሥትና የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምርጫው ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ከማገዝ ይልቅ ‹‹ምርጫ ታካሂጂና እንተያያታለን!›› የሚል አፀፋ መስጠቱ፣ እና አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብም ‹‹ምርጫ ይካሄድ!›› ከሚለው የወያኔ አስገራሚ አቋም ይልቅ ‹‹ምርጫ አይካሄድም!›› የሚለውን አዳፍኔ አቋም የመደገፉን አስገራሚ እውነታ ስናይ የምንገነዘበው ቁልጭ ያለ እውነታ አለ፡፡ ያም በግልጽ እየታየ ያለ እውነታ ወያኔ ከምሥረታዋ ጀምሮ ባሳለፈችው አራት አሰርት ዓመታት በፈጸመቻቸው ክፋቶቿና የመንግሥነትንም ወግ ማዕረግ አግኝታ አስፍና በቆየችው አፋኝና ጨቋኝ የታጣፊ ክላሽ አገዛዟ የተነሳ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በደምሳሳው (ምናልባትም ‹‹በጭፍን›› ሊባል በሚችል ደረጃ) – በወያኔ ላይ ከፍ ያለ ጥላቻ የማሳደሩን እውነታ ነው፡፡
ይህ በግልጽ የምናገረው ዛሬ በብዙዎች ላይ በግልጽ የሚነበበው ፀረ-ወያኔ አመለካከት በወያኔ ላይ የኃይል እርምጃ እንዲወሰድ እስከመገፋፋትና በማንኛውም ፀረ-ወያኔ በሆነ እርምጃ ደስ እስከመሰኘትም የደረሰ መሆኑ ሲታይ – የኢትዮጵያ ህዝብ በወያኔ ላይ ያሳደረው ተራ ጥላቻ ብቻ ሳይሆን – ቂም ያረገዘ ጥላቻ ጭምር መሆኑን መረዳት አያዳግትም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ለመጥላትም ሆነ ለመውደድ ችኮላ የማያሳይ ህዝብ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ቂም ካረገዘ ደግሞ ቂሙን ሳይወጣና ሳያጠፋ ረክቶ እንደማይኖር በብዙ የታሪክ አጥኚ ምሁራን በጥናት የተረጋገጠ የኢትዮጵያውያን የታወቀ ህዝባዊ ባህርይ ነው፡፡ ይህን አምነን ከተቀበልን – ወያኔ ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር የገባችበትን መቆራቆዝና እልህ ቀጥላበት ፍትጊያው ጠብመንጃ ወደ መማዘዝ ቢያመራ – ወያኔ – ብዙዎችንም የትግራይ ወጣቶችን ይዛ – ራሷን ለዓመታት የተጠራቀመ የኢትዮጵያ ህዝብ ብሶት መወጫ ለማድረግ ወስና ወደ ጥፋቱ አቅጣጫ እየገሰገሰች እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡
ይህን የኢትዮጵያን ህዝብ የቂመኝነት ባህርይ ለመረዳት በ1990/91 ከኤርትራ ጋር ጦርነት በተለኮሰ ወቅት ህዝባችን ለጦርነቱ ጥሪ የሰጠውን አስገራሚ አጸፋ ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ ጦር ሜዳ ሄዶ ለመዋጋት ግልብጥ ብሎ የወጣው ኢትዮጵያዊ ወጣት ከመብዛቱ የተነሳ ዕድሜን በመሳሰሉ የተለያዩ ምክንያቶች እየተሰጣቸው ከምልመላ እንዲመለሱ የተደረጉ ብዙ ሺህ ዜጎች መገኘታቸው በወቅቱ ሁኔታውን እየተከታተሉ ይዘግቡ ለነበሩት ምዕራባውያን ተንታኞች ሳይቀር እጅግ አስገራሚ እውነታ ነበር፡፡ የወያኔን ከፋፋይ ሥርዓትና የለየለት አምባገነን አገዛዝ አምርሮ ይጠላል ተብሎ የሚታሰብና – ስለሆነም ከማንኛውም ወያኔን ለመውጋት ከመጣ ኃይል ጋር ዓይኑን ሳያሽ ይተባበራል ተብሎ የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ህዝብ – እንዴት ከወያኔ ጎን ተሰልፎ ኤርትራን ለመውጋት ሆ ብሎ ወጣ?
መልሱ ቀላል ነው፡፡ በስሙም መጠራት አለበት፡፡ ህዝባዊ ቂም ነው፡፡ የሀገር ፍቅርም የታከለበት ቀኑን የጠበቀ ቂም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በሻዕቢያ ላይ የተጠራቀመ ቂሙን ከተወጣ በኋላ ግን በጥቂት ዓመታት ውስጥ የተላበሰውን ይቅር ባይነት ለማወቅ ኢሳያስ አፈወርቂ በቅርቡ አዲስ አበባ በመጣበት ወቅት ሕዝቡ በሙሉ ግልብጥ ብሎ በደስታና ሆታ የተቀበለበትን አኳኋን ማየት ነው፡፡ ያም የነቂስ አቀባበል – ባንድ በኩል ለኢሳያስ የተበረከተ ይቅርታና እርቅ ቢሆንም – በዋነኝነት ግን የኢትዮጵያ ህዝብ በወያኔ ላይ ያደረበት ጥላቻ የቱን ያህል ከፍታ ላይ እንደደረሰ ማሳያ አብነት መሆኑን የማይገነዘብ ካለ ጅል ብቻ ይሆናል፡፡
ለዚህ ነው አሁን ወያኔ (ህወኀት) ይሄንን በተለያዩ መልኮች ራሱን እየገለጸ ያለ የኢትዮጵያ ህዝብ ያረገዘባትን ተራራ የሚያክል (የገዘፈ) ቂም በጽሞና ከማስታመምና በጊዜ ሂደት የሚቀዛቀዝበትን ሠላማዊ መላ ከመፈለግ ይልቅ ወደ እልህና ፍጥጫ፣ ወደ ኃይልና ፅንፍ ወደ ወጣ የተንኳሽ-ተናካሽነት ተግባር ራሷን ማሰማራቷ ታሪካዊ ስህተት የሚሆነው፡፡ ወያኔ ራሷን በኃይልና ፍጥጫ ተግባራት ወደ መግለጽ ባዘነበለችና ራሷን ወደ ‹‹ዎር ሞንገሪንግ›› ተግባራት ባሰማራች ቁጥር – እና ‹‹ሌጂትሜሲዋን›› (ወይም የህልውናና የቅቡልነት ምክንያቷን) በኃይሌና-በጉልበቴ-ብቻ እያለች በመጣች ቁጥር – የኢትዮጵያ ህዝብ ሊመዝባት ያለው ለረዥም ጊዜ የተሳለ የበቀል ሰይፍ እየከፋ፣ የተቋጠረባት የዓመታት ቂምም ከማሰሪያው እየተዘረገፈ በግልጥ የሚወጣበት ወቅትም እየባተ እንደሚሄድ አሳምራ ማወቅ አለባት፡፡
ምንም እንኳ ለእውነት እና ለመብት እና ለዲሞክራሲ የሚከፈለው ‹‹መስዋዕትነት›› የምንለው ታላቅ ዋጋ ታላቅ ክብር የሚሰጠውና የሚያሰጥ የታላቅ ሰዎችና የታላቅ ህዝቦች አኩሪ ተግባር ቢሆንም – ምንም እንኳ ‹‹በጉልበት አልንበረክክም›› ብሎ ራስን ለመስዋዕትነት በማቅረብ ለሚመጣው አጥፍቶ መጥፋት መዘጋጀት የጀግና ወግ ቢሆንም – ከሀገሪቱ ጫፍ እስከ ጫፍ እንደ ሱናሚ ማዕበል – ባለ በሌለ ኃይሉ አጥለቅልቆ ድራሿን ለማጥፋት የአንድ ጀብደኛ መሪን ፊሽካ ብቻ አሰፍስፎ የሚጠባበቀው በሚሊዮን ከሚቆጠረው የተከፋና የተገፋ የኢትዮጵያ ህዝብ ብሶትና ቂም ጋር – በዚህ አጉል ሰዓት ጦርነት ገጥሜ አሸንፋለሁ – ወይም በተጋፋጭነቴ አተርፋለሁ ብሎ ማሰብ – ከእውነታው እጅጉን የራቀ ‹‹ቅዠት›› ብቻ ሳይሆን ‹‹እብደት›› ጭምር ነው፡፡ እብደት ብቻም ሳይሆን ‹ጄኖሳይዳል ኮንሰኩዌንስ› ያለው ‹ሱሳይዳል› (ራስን በገዛ እጅ ማጥፋት) አቋም መሆኑን ወያኔ አሳምራ መረዳት ያለባት ጊዜ ነው፡፡
አሁን በኢትዮጵያችን የመንግሥትን ሥልጣን ተረክቦ የሚገኘውን ማዕከላዊ ኃይል አቅፈው ደግፈው ወደ ሥልጣን ያመጡት የኦሮሞ ብሔርተኞች ተሰነጣጥቀው ፊታቸውን እያዞሩበትና አድማ እያስተባበሩበት ነው፡፡ በአማራና በደቡብ ክልልም ክልሎቹን በሚመሩትና ከኦሮሞው ብሄርተኛ ኃይል ጋር ተባብረው ወያኔ በቀጥታና በሪሞት ስትቆጣጠረው የነበረውን ሥልጣን ተካፍለው በሚገኙት የየክልሉ ሕዝብ አስተዳዳሪዎችም ላይ የቱንም ያህል በይፋ የተገለጠም ይሁን የታፈነ – ከፍ ያለ ሕዝባዊ ተቃውሞ፣ መቀናቀንና እምነት ማጣት እየደረሰባቸው ነው፡፡
በዚህ የህዝባዊ ድጋፍ ድርቅ በመታውና ሥልጣኑ በአስጊ አጣብቂኝና ስጋቶች መሐል በተወጠረው – የማዕከላዊው ሥልጣን በብዙ አጣብቂኝ ኃይሎች ተጽዕኖ ሥር በወደቀበት በዚህ አሳሳቢ ወቅት ላይ – የማዕከላዊው መንግሥት አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ሥር የሰደደ ቂም በቋጠረባት በወያኔ ላይ ጦርነት ቢያውጅ – አንድም ማዕከላዊ መንግሥቱ ከመታው የሕዝባዊ ድጋፍ ድርቅ በአንዴ አገግሞ ለመነሳት እንደሚያስችለው ያውቃል፣ በሌላም በኩል ገና ባልበረደ ቂም ወቅት ይህ ቢፈጠር በወያኔ ላይ የሚደርስባት መቅሰፍት እጅጉን የከፋና የሚያሰቅቅ እንደሚሆንም ያውቃል፡፡
በኢትዮጵያ በቅርቡ ይህ እንዳይሆን ለማስቀረት ሁለት ነገሮች ያስፈልጋሉ፡፡ አንድም የሕዝባዊ ድጋፍ ድርቁን ለማስወገድ ሲል ጦርነትን እንደ ዓይነተኛ ስልት ሊጠቀምበት ለሚሻው ማዕከላዊ መንግሥት ተባባሪ የማይሆን ሕዝብ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ራስን ለሌሎች የሥልጣን ማጠናከሪያ ፍላጎት መሣሪያ ላለማድረግ የሚመርጥ ህዝባዊ ውሳኔ፣ ወይም ራስን ማቀብ ወይም በሌሎች ቅስቀሳና ጥሪ ላለመነዳት በኢትዮጵያ ህዝብ በኩል ሊታይ የሚችል ቁጥብነት – በተግባር ሲፈተሽ እና በተለይም የፕሮፓጋንዳ ኃይል ሲቀጣጠልበት – የቱን ያህል ሊሳካ እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ አስቸጋሪ ነው፡፡ ነገሮች አንዴ አይቀጣጠሉ እንጂ – አንዴ ነገሮች ከሰከነ ሠላማዊ ሁኔታ ውጭ ወደ ኃይል እንቅስቃሴ ከተሸጋገሩ በኋላ – ምክንያታዊነት ስሜታዊነትን የመግራት ኃይሉ (እና ዕድሉ) እጅግ የመነመነ የመሆኑን ሀቅ አለመዘንጋት አስተዋይነት ነው፡፡ እና ወደ ጦርነት ላለማምራት ሊደረግ በሚችል ህዝባዊ እምቢተኝነት ላይ መተማመን አይቻልም ማለት ነው፡፡
ስለዚህ አሁን በወያኔ ላይ የተደቀነባትን የጥፋት ሱናሚ ለመቀልበስ የቀረው ሌላው ብቸኛው መፍትሄ ያለው በራሷ በወያኔ እጅ ላይ የወደቀ ነው ማለት ነው፡፡ ወያኔ ጠብን ከሚቆሰቁሱ ትንኮሳዎችና የጉልበቴን እዩልኝ-ስሙልኝ ተግባራት መቆጠብ አለባት፡፡ ወያኔ ከፊት ለፊት መቆራቆዝና የቃላት እንካ ሠላንቲያ በፍጥነት መውጣት አለባት፡፡ ወያኔ ለድርድር (ለመቀበልም ለመስጠትም) ራሷን ክፍት ማድረግ አለባት፡፡ ወያኔ ሸሮቿን ገሸሽ አድርጋ፣ ፍቅሯን ባደባባይ ደግማ ደጋግማ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መግለጥ ይኖርባታል፡፡ ወያኔ ከማዕከላዊው መንግሥትም ሆነ ከጎረቤት ክልሎችና ሀገራት ጋር በግልጽም በስውርም ዲፕሎማሲያዊ የንግግር ጥረቶቿን አጠናክራ መቀጠል አለባት፡፡
ወያኔ አሁን የተሰማራችበት የእልህ አካሄድ ቀጥሎ ኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ ለዓመታት ያረገዘውን የቂም ዶፍ የሚያወርድባት ከሆነ (ወይም ሲያወርድባት) – ያን ጊዜ አሁን የምታሳየው ማስፈራሪያና ሽለላ ቀርቶ – ‹‹ጄኖሳይድ (የዘር ማጥፋት) ታውጆብኛል፣ የዘር ጭፍጨፋ እየተፈጸመብኝ ነው፣ ድረሱልኝ!›› ብላ ለዓለማቀፉ ማኅበረሰብ በማይቀለበስ ሰዓት ለመጮህ ከመገደዷ በፊት – አሁኑኑ ባማረባትና ከነቁመናዋ ባለችበት ሰዓት – ዓለማቀፉን ማኅበረሰብ አስታራቂና ሚዛናዊ የሰላም መፍትሄ እንዲፈልጉላት መጮህና መጣር ያለባት ጊዜ አሁን ነው፡፡
በለውጥ ፈላጊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጩኸት ተገፍቶ የማዕከላዊውን መንግሥት ሥልጣን የተቆናጠጠው ወያኔን ብቻ አስወጥቶ ስሙን ቀይሮ የቀጠለው የቀድሞው ኢህአዴግ – የአሁኑ ብልጥግናም – ጦርነትንና የኃይል ተግባርን የህዝባዊ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ምንጭ አድርጎ ለመጠቀም እያሳየ ያለውን አዝማሚያ በፍጥነት ማስተካከል ያለበት ወቅት ላይ መሆኑን ማስተዋል ያሻል፡፡ በመንግሥት መሪዎችና አካላት የሚሰነዘሩ አስተያየቶች፣ ፕሮፓጋንዳዎችና የቃላት ዘመቻዎች በህዝብ ውስጥ የጦርነትን ነጋሪት እያቀጣጠሉ እንደሚመጡ ማስተዋል ብልህነት ነው፡፡ ወያኔ ታልፋለች፡፡ ኢህአዴግም ያልፋል፡፡ ግጭትና ጦርነት ተቀስቅሶ የሚሞተው ወጣት ህይወት ግን አይመለስም፡፡ የሚፈሰው ደም አይመለስም፡፡ የሚቀረው የደም መቃባት የታሪክ ጠባሳ አይመለስም፡፡
በተለይ ወያኔ ከሻዕቢያና ከሌሎች የኢትዮጵያን ሕዝብ ከሚወጉ ታሪካዊ የውጭ ጠላቶቿ ጋር ተሰልፋ የኢትዮጵያን ህዝብ ስታደማ መኖሯ – ከሻዕቢያ ጋር ወግና ኤርትራን በማስገንጠሏ – የኢትዮጵያን ህዝብ ወደብ-አልባ ህዝብ በማድረጓ – ሁሉም የእኔ የሚላትን ሀገርና ብሔራዊ ጀግናን በማሳጣቷ – ለውጭ ጠላቶች ፍላጎት ተንበርካኪና ተላላኪ በመሆን በሀገርና በህዝብ ላይ የፈጸመችው የባንዳነት ተግባርና ሀገርንና ህዝብን እንደ ዶሮ ብልት ገነጣጥሎና ከፋፍሎ የማናቆር ሥራዋ – አሁን ድረስ ሰማይን የሚያህል ቂም እንዲረገዝባት እንደበቃች – ገና ያ ሰማይን አክሎ በኢትዮጵያ ህዝብ የተረገዘባት ቂም ገና እንዳልተወራረደ አጥብቆ መገንዘብ ከወቅቱ የሀገሪቱ መሪዎች የሚጠበቅ የአስተዋይነት ተግባር ነው፡፡
ትናንት የወያኔን ከውጪ ኃይሎች ጋር ተባብሮ የገዛ ወገንን የመውጋትና የማስወጋት ባንዳዊ ድርጊት ያወገዘውና ቂም የያዘው ህዝብ – ዛሬ ደግሞ የለውጡ ማግስት የኢህአዴግ (የብልጥግና) መሪዎችም – ከኤርትራም ሆነ ከሌላ የውጪ ሀገር ጋር ተባብረው – የገዛ ወገናቸው የሆነውን የትግራይ ኃይል (ወያኔን) ለመምታትና ለማስመታት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ – የወያኔን የባንዳነት ታሪክ ዛሬ ላይ የሚደግም – እና ዳግም በኢትዮጵያ ታሪክ የማይረሳ ጥቁር ጠባሳውን አሳርፎ የሚያልፍ – ከታሪክ ተወቃሽነትም የማያተርፍ ኢትዮጵያዊነት ያልተላበሰ ወራዳ ተግባር መሆኑን አበክረው ሊያስቡት ይገባቸዋል፡፡
በተረፈ ግን – ወያኔን አጠፋለሁ ብሎ ከኢህአዴግ ጉያ የሚነሳ ማንኛውም ኃይል – ከሁለት ዓመት በፊት – ከወያኔ ጋር አብሮና ተባብሮ የኢትዮጵያን ህዝብ በአምባገነን መዳፍ ሲገዛ የነበረና ከወያኔ ጋር በአንድ ገበታ ቀርቦ ሲጎርስና ሲጎራረስ የነበረ አካል መሆኑን መቼውንም መዘንጋት አያስፈልግም፡፡ አንዱ ሌላውን ለማጥፋት፣ አጥፊው ከጠፊው የተሻለ የንፅኅና ሚዛን እንዲኖረው ይጠበቃል፡፡ ይህን አበክሮ ማወቅ ከብዙ አላስፈላጊ ጥፋቶች ያድነናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ሁሉ እስርቤት አጉሮ የሀሰት ክሶችን እየፈበረከ ከፍርድ ቤት ከርቸሌ ሲያመላልስ የምናየው መንግሥታዊ አካልና መዋቅር – ያው ራሱ በወያኔ የሥልጣን አውራነት ዘመንም የነበረው አካል መሆኑን አስተውሎ ማየት በጭፍን ለአንድ ወገን ፍላጎት ማስፈጸሚያነት ከመነዳት ሁላችንንም ያድናል፡፡ በሥልጣን ሥር ተሻርከው የኢትዮጵያን ህዝብ ለዓመታት በጋራ ሲገዙ በነበሩ ኢህአዴጋውያን መካከል በተፈጠረ የሥልጣን ይገባኛል ጸብና መቆራቆዝ የተነሳ የምስኪኑ ኢትዮጵያዊ ወገኔ ደም እንዳይፈስ ከልቤ እመኛለሁ፡፡
በዚህ ዘመን ላይ ሆነን – በብዙ አፍሪካውያን ህዝቦች ላይ የምናየውን ዓይነት – ሥልጣን ላይ ያነጣጠረ ደም መፋሰስንና ጥሬ የጠመንጃ መንገድን በሀገራችን ላይ ለመድገም መሽቀዳደም – ቁርጡ የታወቀን የተሸናፊነትና የውድቀት ጎዳና ለሕዝባችን መምረጥ ነው፡፡ ለይስሙላም ከልብም እንደሚባለው – ለኛ ከምንም በላይ የሚያስፈልገን ሠላም ነው፡፡ ሠላምን እጅግ ተጠምተናልና ሠላም በእጅጉ ያስፈልገናል፡፡ በጥላቻዎችና ግጭቶች ‹‹ቶክሲክ›› እንዲሆን በተደረገ፣ እና በጥላቻ በደፈረሰ አካባቢና ሀገር ላይ ግን ይህን የምንመኘውን ሠላም ማምጣት አይቻልም፡፡ የጥላቻና የጦርነት ንግርት እየጎሰምንም የዜጎችን አዕምሯዊ ሠላም ማምጣትም፣ መገንባትም አንችልም፡፡
ዛሬ ላይ አመንንም አላመንንም በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በስደት በዓለሙ ሁሉ ተበትነን ያለን ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገርና እንደ ህዝብ ሠላማችንን ካጣን ቆይተናል፡፡ በያለንበት የሚያስጮኸንና የሚያባላን የሠላም እጦት ነው፡፡ እና ከምንም በላይ ሠላም ያስፈልገናል፡፡ ነገር ግን ይህ አጥብቀን የምንሻው ሠላም የጥይት ድምጽ አለመሰማት፣ ወይም የባሩድ ሽታ ያለመትነን ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ይህ ሠላም የጦርነት አለመኖር ብቻ፣ አሊያም የጦርነት ሥጋት አለመኖርም ብቻም አይደለም፡፡
ሠላማችንን ተጎናፀፍን የምንለው በሀገርና በትውልድ አዕምሮ ውስጥ ለብሩህ የወደፊት ተስፋ ከሌሎች ጋር በቅንነት ተባብሮና ተከባብሮ ለማሰብና ለመሥራት የሚያስችለንን አዎንታዊ አመለካከት ተላብሰን ለመገኘት ስንችል ብቻ ነው፡፡ የምንናፍቀው ሠላም ሌላ ሳይሆን ሁላችንም ኢትዮጵያውያን መንፈሳችን በጥላቻ ሳይደፈርስ በቅንነት መንፈስ እየተያየን መመላለስ የምንችልበት ሀገራዊ የአስተሳሰብ አውድ መፈጠር ነው፡፡ ሠላማችን ሠላማዊ ሀሳቦችን ለመፍጠር የሚያስችል አካባቢያዊ ሁኔታዎች መስፈን ነው፡፡ ሠላም አለን የምንለው ህይወትንና ኑሮን ለማቃናት ዜጎች ሠላማዊ መላዎችን የሚያውጠነጥኑ ሆነው መገኘት የሚችሉበት የአስተሳሰብ ሠላማዊነት በሀገራችን ሲሰፍን ብቻ ነው፡፡
ያን ሠላም ለመፍጠር የሚያስፈልግ ሪሶርስ የለም፡፡ የሚፈስ ሀብት የለም፡፡ የሚከፈልበት ህይወት፣ የሚከሰከስበት አጥንት የለም፡፡ የአዕምሮ ዝግጁነትና አስተዋይነት ብቻ፡፡ ቅንነት ብቻ፡፡ በኢትዮጵያዊ ወገንተኝነት፣ ወንድማማችነት፣ እህትማማችነት መንፈስ መነሳሳት ብቻ፡፡ ይዘግይም ይፍጠንም ይሄ በእጃችን ላይ በነጻ ያለ ምንም ዋጋ የማይከፈልበት ታላቅ የሠላም ጸጋችን ብዙ ዋጋና ህይወት የሚያስከፍለንን ታላቅ የጠብ ኃይላችንን እንደሚያበርደው ጥርጥር የለኝም፡፡
እኔ የማስበውን፣ እና በግልጽ አውጥቼ የጻፍኩትን ሀሳብ ብዙዎችም እንደሚጋሩኝ ከፍ ያለ እምነት አለኝ፡፡ ሁላችንም ‹‹ትክክለኛ›› ለመባልና ሀቅን ለመቀባባት የምናወጠውን ዕውቀትና ጉልበት – ፍላጎታችንን እና ሀቃችንን በግልጽ አውጥተን ለመነጋገር ብንጠቀምበት የመገናኛ መንገዳችንን ያሳጥርልናል የሚል የፀና እምነት አለኝ፡፡
የሚበጀን ልዩነታችንን ያከበረ፣ ለሁላችንም እኩል ዕድል የሚሰጠን፣ ወደተሻለ ህይወት ሊያደርሰን የሚችል፣ በዜግነታችን ለሁላችንም የደህንነትና የኑሮ ዋስትና የሚሆነን፣ በማንነታችን እውቅናና ክብሩን የማይነፍገን… የዓለምን ኢኮኖሚና ፖለቲካ ግምት ውስጥ ያስገባ፣ እና ለልጆቻችን የምትሆነንን ነጻነት የሰፈነባትን ዲሞክራሲያዊት ሀገር መገንባት የሚያስችለንን ወጥ ሀገራዊ ጎዳና … በሰፊ አንጀት፣ በሰፊ ልብ፣ በሰፊ አዕምሮ፣ እና ከጉልበተኝነትና ከቂም፣ ከጥላቻና ከእልህ፣ ከማን-አህሎኝነትና ከጠብ በጸዳ የረጋ መንፈስ ቁጭ ብለን ተነጋግረን ተወያይተን መቅረጽ ነው፡፡ ያን እንድናደርግ ፈጣሪ ይርዳን፡፡
ይህን የምጽፈው ለወያኔ ካለኝ ፍቅር የተነሳ ወይም ወያኔ እንዳትጠፋብኝ ባለችኝ ትንሽዬ አቅም ለመምከርም ፈልጌ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ዳግም ሊከሰት የሚችለው የደም መፋሰስ ታይቶኝ – እና የአንድም ኢትዮጵያዊ ደም እንዳይፈስ – ቢያንስ ከዚህ በኋላ… የአንዲትም ኢትዮጵያዊት እናት እንባ በልጇ ሞትና ስብራት የተነሣ እንዳይፈስብን ከልብ ከመመኘቴ የተነሳ እንደ አንድ ተራ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ፊት ለፊት ወጥቼ የጻፍኩት ምንም ያልተቀባባ ማንምም ለመወገን ተብሎ ያልተጻፈ ግልጽ መልዕክቴ ነው፡፡
ፈጣሪ ክፋትን ወደ አፎቱ ይመልስልን፡፡ ቂምን ከልባችን ማኅደር ይፋቅልን፡፡ በመካከላችን የተዘራብንን የጠብ መንፈስ ያብርድልን፡፡ የማይቻለውን የምንችልበትን አስተዋይነት ይስጠን፡፡ ጥልቅ ልቦናውን ይስጠን፡፡ ከጸባችንና ከጥላቻችን ባሻገር ለሺህዎች ዓመታት አባቶቻችን እናቶቻችን የጾሙለትን፣ የጮሁለትን፣ የዘመሩለትን፣ የቀደሱለትን ያን ለህይወታችን እጅግ ተፈላጊ የሆነውን መንፈሳዊነት በኢትዮጵያውያን ትውልዶች ሁሉ ልብ ውስጥ ያስርጽብን ፈጣሪ አምላክ፡፡ የሠላም አምላክ ሠላምን ይስጠን፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡ 
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡ 
አበቃሁ፡፡
Filed in: Amharic