>

ከግብጾች ምን እንማር ወይ በምን እንቆጭ? - በአንድ ነገር ብቻ! (አሰፋ ሃይሉ)

ከግብጾች ምን እንማር ወይ በምን እንቆጭ? – በአንድ ነገር ብቻ!

አሰፋ ሃይሉ

ግብጾች ከጥንት ዘመን ጀምረው በስነጽሑፎቻቸውና በተለያዩ የዕደጥበብ ሥራዎቻቸው ራሳቸውን ለተቀረው ዓለም በሚገባ አስተዋውቀዋል፡፡ በጥንታዊ የግሪክ ፀሐፊያን ሥራዎች ውስጥ ስለግብጾች ተጽፎላቸው እናገኛለን፡፡ በአይሁዳውያን ጥንታዊ ታሪኮች ውስጥ ስለግብጾች ተጽፏል፡፡ የጥንታዊ ሮማውያን ጸሐፍትና ትያትረኞች ስለ ግብጾች ብዙ ክታብ አስፍረውላቸዋል፡፡ ከቅድመ ክርስቶስ ዘመን እስከ ኦቶማን ነገሥታት ዘመን ድረስ ሠለጠነ በሚባለው የምስራቁም የምዕራቡም ዓለም ግብጽ የሚለው ቃልና ሀገር – ያውም እየተዳነቀ – በሚገባ ተዋውቋል፡፡ ይሄ ‹‹ሰልፍ-ፕሮሞሽን›› (ወይም ራስን-ማስተዋወቅ ወይም ገጽታን-ማሻሻጥ) ከግብጾች ማንነት ጋር የተቆራኘ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ሌላ ቀርቶ በ19ኛው ክፍለዘመን ላይ ጦራቸውን አስከትተው ወደ ግብጽ ምድር ከዘመተው ናፖሊዮን ጋር ግብጽን የማየት ጉጉት ይዟቸው አብረው የዘመቱ ሳይንቲስቶችና የታሪክና ቅርስ ተመራማሪዎች ራሳቸው ነበሩ – ብዙ የታሪክና የጥበብ ቅርስ ያላትን የገዛ ሀገራቸውን ፈረንሣይን ማስተዋወቁን አቁመው – በአሁን ዘመን ላይ የሚታወቁትን ብዙዎቹን የግብጻውያን ጥንታዊ ቅርሶች፣ ጽሑፎች፣ ጥበባዊ የግንባታ ንድፎችና ታሪኮች በስፋት ለዓለም ያስተዋወቁላት፡፡
ኦቶማኖችም መጡ – እንግሊዞችም ተከተሉ – ሁሉም ራሳቸውን የግብጽ አይረሴ-ፕሮሞተሮች አድርገው አልፈዋል፡፡ እስከሁንም ድረስ በእንግሊዝና በፈረንሳይ – በጣሊያን፣ በሌሎችም በርካታ የአውሮፓና የአሜሪካ ታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ስለ ጥንታዊ ግብጻውያን እንደ አንድ ራሱን እንደቻለ የትምህርት ዓይነት የሚሰጥበት ምክንያቱ እነዚያ ራሳቸውን የግብጽ ቋሚ አስተዋዋቂ አድርገው ያለፉ የእንግሊዝና የፈረንሳይ ምሁራን ስለ ጥንታዊት ግብጽ ለዓለም ያስተዋወቋቸው ብዙ መሳጭ ግኝቶችና ንግርቶች ውጤት ነው ማለት ይቻላል፡፡
ዛሬ ላይ ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በኢጅይፕቶሎጂ (በስነ-ግብጽ) ላይ ፒኤች ዲያቸውን የሠሩ በርካታ ምሁራንን ማግኘት የሚገርም ጉዳይ አይደለም፡፡ የተለመደ የጥናት ዘርፍ ነው ኢጅይፕቶሎጂ፡፡ ልክ እንደ ባዮሎጂ፣ እንደ ኤትኖሎጂ፣ እንደ ጂኦሎጂ፣ አንትሮፖሎጂ፣ አርኪዮሎጂ፣ ሂስትሪዎሎጂ፣ ሁሉ – ኢጅይፕቶሎጂም ራሱን የቻለ አንድ የሳይንስ ጥናት ዘርፍ ሆኖ በዓለም ዙሪያ ይጠናላቸዋል፡፡
በዚህ በኩል ምናልባት ግሪኮች ይበልጧቸው እንደሆን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ዓለም ሁሉ ነው ግሪኮችን ያጠናቸውና ያስተዋወቃቸው፡፡ የጥንተ ሮማ ታሪክም እንዲሁ፡፡ ይሁን፡፡ ሮማውያንና ግሪኮች በዓለም ላይ ታሪካቸውና የጥበብ ቱሩፋታቸው በስፋት ፕሮሞት በመደረግ ደረጃ ይበልጧቸው ይሆናል እንበል፡፡ ነገር ግን እንዲያም ሆኖ ከግብጾች በላይ የአንድ ሀገር ኢሜጅ ፕሮሞሽን ከፍታ እንዲህ ወደ ዓለማቀፍ ዘመናዊ ሳይንስነት ደረጃ አሳድጎ ለማሳየት የተሳካለት ሀገር ያለ አይመስለኝም፡፡ አሁንኮ የግብጾች ጥንታዊ ስልጣኔ ታሪክ የሰው ልጅ ሁሉ ሥልጣኔ ታሪክ ተደርጎ የተቆጠረበት ዘመን ላይ ነን፡፡
በዚህ ጉዳይ ግብጾቹም አስተዋዮች ናቸው፡፡ የጥንት አባቶቻቸው ታላላቅ ፒራሚዶችንና የጥበብ ቱሩፋታቸውን አኑረውላቸው ያለፉት – የግብጽ ጥንታዊ ታሪክ ተረስቶ እንዳይቀር – በተከታታይ ትውልዶች ማንነታቸው እየተዘከረላቸው እንዲኖር ከነበራቸው ጥልቅ ፍላጎት የተነሳ መሆኑን – እስከ አሁኑ ዘመን ያሉት የኋለኛ ዘመን ግብጻውያን በሚገባ አውቀውታል፡፡ እናም የአባቶቻቸውን ፈለግ ተከትለው ይጓዛሉ፡፡ የጥንቶቹም ሆኑ የአሁኖቹ ግብጾች ራሳቸውን ከማስተዋወቅ መቼም ቦዝነው አያውቁም፡፡ የወደፊቶቹም ከዚህ የተቀደሰ ተግባራቸው ይቦዝናሉ ተብሎ አይታሰብም፡፡
ግብጾቹ ሁለነገራቸውን ለዓለም ያሻሽጣሉ፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት 5,000 ዓመተ ዓለም እስከ 3,200 ዓመተ ዓለም ድረስ ካለው ቅድመ ታሪካቸው ጀምሮ – በአሁኗ ዘመናይቷ ግብጽ እስከሚፈሰው የናይል (የአባይ) ወንዝ ታሪክና አፈታሪኮች ላይ ግብጻውያኑ ለዓለም የማይጽፉትና የማያስተዋውቁት አንዳችም ነገር የለም፡፡ ዛሬ ግብጽ የአውሮፓና የአሜሪካ ጋዜጦችና ማህበራዊ ሚዲያዎች ተነባቢዎቻቸውንና አዳማጮቻቸውን የሚመስጡባት የተከታይ መማረኪያ ቅመማቸው ነች፡፡ ቢያንስ በሳምንት አንዴ ‹‹በጥንታዊ ግብጽ የንጉሣውያን መቃብር ውስጥ የተገኘው ይሄን ያህል ኪሎ የሚመዝን በወርቅ የተለበጠ ጥንታዊ ቅርስ በቁፋሮ ተገኘ››፣ የሚሉና የመሳሰሉ የግብጽ ትንግርት ዜናዎችን በየዓለሙ ማዕዘን ከሚገኙ የዜና አውታሮች ገጽ ማግኘት የተለመደ ሆኗል፡፡
እና ግብጽ ራሷን፣ ታሪኳን፣ ቅርሶቿን፣ አቅሟን፣ ገጽታዋን፣ ሁለነገሯን ለዓለም ማሻሻጥን፣ ማስተዋወቅን፣ መቸብቸብን ችላበታለች ብቻ አይገልጸውም፡፡ ተክናበታለች፡፡ በሰልፍ-ፕሮሞሽን ከመካኗ የተነሳ በአሁን ዘመን የሚገኘውን አብዛኛውን የዓለም ኗሪ ብትጠይቀው ‹‹ሪቨር ናይል›› ከጥንት ዘመን ጀምሮ ከግብጻውያን አማልክት፣ ከግብጻውያን ህይወትና ታሪክ ጋር አብሮ ተቆራኝቶ የኖረ የግብጽ የሺህ ዓመታት የሕይወት ምንጭ እንጂ ሌላ ምን እና የማን ሊሆን ይችላል? ብሎ እንዲያምን፣ እንዲገረም፣ ኢጅይፕቶሎጂስት እንዲሆን አድርጋዋለች፡፡
የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ ጥቂት የታወቁ የምዕራቡ ዓለም የ18ኛውና የ19ኛው ክፍለዘመን ተጓዦች ወደ አፍሪካ ዘልቀው የፃፉትን የጉዞ ማስታወሻ የማንበብ ዕድሉ ገጥሞኛል፡፡ የሚገርመው ሁሉም ማለት ይቻላል – ናይል ወንዝን – አባይን – ልክ የግብጽ ሥልጣኔ ምንጭ – የግብጽ ግርማሞገሳም ሀብት – የግብጽ ታሪካዊ የግል ንብረት አድርገው ነው በየመጽሐፎቻቸው የጻፉላት፡፡ ቅኔን የተቀኙላት፣ ግጥምን የደረደሩላት፡፡ ስለ ግብጽ አንስተው ሺህ ዓመታትን ስላስቆጠሩ ታሪካዊ ቅርሶቿና ስለናይሏ (የእሷ የግሏ አባይ!) ሳይጽፉ ከግብጽ ምድር አይወጡም፡፡ ይገርመኛል፡፡ ይህ ነገራቸው ያስደምመኛል፡፡ ግብጾቹ ለዘመናት ሳይፎርሹ ራሳቸውን ለዓለም ሲያስተዋውቁ የኖሩበት መንገድ – እንደ አንድ የዚህ ዘመን ኢትዮጵያዊ ሆኜ ሳስበው – የምሬን ያስቀናኛል፡፡ ያስቆጨኛል፡፡ ያንገበግበኛል፡፡
የኛን ሀገር ከረሃብ ጋር አቆራኝቶ የሣለው ዓለም፣ እና በዘወትር ልመናና የእርዳታ ጥሪ ይሄንኑ ምስል ዘወትር የሚያገዝፉ ድኩማን የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች – ለዓመታት በተገቢው መንገድ ቢተዋወቅ ኖሮ ለሀገራችን ስንት ቱሩፋት ይዞ ሊመጣ ይችል የነበረውን የሀገራችንን የ5ሺህ ዓመታት ታሪክ፣ የሀገራችንን ስንት የጥበብ ቱሩፋት፣ ስንት አኩሪ ታሪክ፣ እስከዛሬም ተጠብቀው የቆዩ ቋንቋዎቻችን፣ ስነጽሁፎቻችን፣ ቅርሶቻችን፣ ባህሎቻችን፣ ስንት ስንት የተፈጥሮና የታሪክ አንጡረ ሀብቶቻችንን – በወጉ አጥንተውና ለትውልድ አስጠንተው፣ ለዓለም አስተዋውቀው ሀገራችንን ለታላቅ ዝናና ተግባር ማብቃት ሲችሉ – ኢትዮጵያ የ100 ዓመት ታሪክ ነው ያላት ወደሚል ስንኩል የታሪክ ውርዴ ውስጥ ይዘውን ገቡ! ያሳዝነኛል ይሄን ሳስብ ስለሀገሬ፡፡
ግብጾች ኢጅይፕቶሎጂን በታላላቅ የዓለማችን ዩኒቨርሲቲዎች ያስጠናሉ፡፡ ሌላ ቀርቶ ኢራኖች – በመዲናችን አዲሳባ መሐል ‹‹ኢራኖሎጂ›› የሚል ኮርስ ነድፈው ለፈቃደኞች በነጻ ያስተምራሉ፡፡ በአንድ ወቅት በኢራን ካልቸራል ሴንተር (በኢራን ኤምባሲ የባህል ማዕከል አማካይነት) ‹‹ኢራኖሎጂን›› የመማር ዕድሉ ገጥሞኛል፡፡ ኮርሱን በመጽሐፍ መልክ ያዘጋጁላቸው የአዲስ አበባው ረ/ፕሮፌሰር አረካ ይሰኛሉ፡፡ ከጥንታዊ ፋርስ እስከ ዘመናዊ ኢራን ድረስ ያለውን ውብ ታሪክና ጥበባቸውን ያስተምሩሃል ኢራኖች – በኢራኖሎጂ፡፡ ከፈለግክም በነጻ ስኮላርሺፕ ይሰጡሃል፡፡ በታሪክ፣ በቋንቋ፣ በስዕል፣ በሙዚቃ፣ በፊልም፣ በዕደጥበባት፣ በፈለግኸው ሰውኛ ሳይንስ የኢራን የሆነውንና በኢራኖች የበለጸገውን ትውፊት ሁሉ ተሂራን ድረስ ወስደው ለ3 ዓመት ያስተምሩሃል፡፡ ፍላጎቱ ካለህ፡፡ ጽናቱ ካለህ፡፡ ቅርበቱ ከተሰማህ፡፡
የዛሬዋ ዓለም – ራስህን ሳታስተዋውቅ፣ ራስህን ሳታሻሽጥ – ሀገርህ ያላትን ፖቴንሻል ሁሉ አሟጠህ ለዓለም ሳታሳይ – የምትታወስባት ዓለም አይደለችም፡፡ ሰዎች የአንተ የሆነውን እንዲረዱልህና እንዲደግፉህ – የግድ የአንተ የሆነውን አክብረህ – በአክብሮት ለሌሎች ማጋራት አለብህ፡፡ የዘመናዊው ዓለም ሀገራዊ ፕሮሞሽን ቀመር ይሄው ነው፡፡
በእኛም ሀገር ከግብጾች ያልተናነሰውና – እስካሁንም በህይወት ባሉት በእነ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ጎንደር፣ ጀጎል፣ ሶፍኦማር፣ በፊደሎቻችን፣ በትውፊቶቻችን፣ በባህሎቻችን፣ በልዩ ልዩ ቋንቋና ታሪኮቻችን የታጀበው – አኩሪና መሳጩ የኢትዮጵያ ታሪክ አዕምሮ ያላቸው መሪዎች ቢኖሩን ኖሮ የሀገራችን ገጽታ ዛሬ በዓለም – የግብጾችን ያህል እንኳ ባይሆን – የትና የት በደረሰ ነበር፡፡
መቼም ፈጣሪ ሳይደግስ አይጣላም ሆኖ ግን – የኢትዮጵያ ድንቅና አኩሪ ታሪክ በወያኔ-ኢህአዴግ መንግሥት የአዕምሮ-ዱልዱሞች እንዳይሆን ተደርጎ ተደፍጥጦ ወደ መቶ ዓመት ታሪክነት ቁልቁል ከተፈጠፈጠ በኋላም እንኳ – ደግሞ ማን እንደመከራቸው ወይ ምን ቅዱስ ነገር እንደተጠጋቸው ባይታወቅም – በስተመጨረሻ ላይ ታሪኳንና ክብሯን የተረማመዱባትንና በውርደቷ ላይ ውርደትን የጨመሩላን ሀገር – ገጽታዋን እንገነባለን ብለው ተነስተው ነበረ፡፡ ለምን ጉዳይ እንደሚውል ባይታወቅም በየዓመቱ ጠቀም ያለ መንግሥታዊ በጀትም ለገጽታ ግንባታ እየተባለ መመደብ ጀምሮም ነበር፡፡ እስካሁንም ያለ ይመስለኛል፡፡
ግድቡን ‹‹ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ…›› ብሎ መሰየምን ጨምሮ ብዙ የሀገሪቱን ስም ከፍ የሚያደርጉ ነገሮችም የተጀመሩት ከነዚያው ከባነኑባቸው ሰሞናቸው ጀምሮ ነበረ፡፡ እና ኢህአዴግ የኢትዮጵያን ኢሜጅ ለመገንባት ብዙ ሚሊየን ዶላሮችን ከስክሶ ከስክሶ ሲያበቃ – በመጨረሻ አሜሪካ ሄደህ ድንገት ለሻይ በተቀመጥክባት ዛኒጋባ ሱቅ የቴሌቪዥን ማስታወቂያ ቀና ብለህ ስትመለከት – የኢትዮጵያ መንግሥት በዩኤን በኩል ለዓለም ያስነገረውን አጥንታቸው በገጠጡ ምስኪን ኢትዮጵያውያን ህጻናት የታጀበ የእርዳታ ጥሪ ማስታወቂያ ትመለከታለህ፡፡ የኢሜጅ ግንባታውን ሚሊየን ዶላሮች – የልመናው አመል በቅጽበት ዶጋ አመድ እያደረገው – ይኸው ፈጣሪ ይመስገነው እዚህ ደርሰናል፡፡
ብቻ ግን ያስቆጫል፡፡ የግብጾቹና የእኛ ልዩነት፡፡ ግብጾቹ አሁን ድረስ ኢጅይፐቶሎጂን እንደ ሳይንስ በዓለም ዩኒቨርሲቲዎች ይሰጣሉ፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በዓለም ሁሉ ማዕዘኖች ‹‹ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ›› እያልን ሀገራችን ከተፈጠፈጠችበትም ዝቅታ በላይ ገና ቁልቁል እንድትፈጠፈጥ ባለ በሌለ ኃይላችን አበክረን እንጮኃለን፡፡ ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ፡፡ አፕ አፕ ኢጅይፕቶሎጂ፡፡ የጉድ ዘመን፡፡ ስታሊን በመጣና በፈጀልን ያስብላል እኮ ደምህን ሲያፈላብህ የሆንነውና የምንሆነው ነገር፡፡ ታከተኝ አሁንስ፡፡ በቃኝ አቦ፡፡
ፈጣሪ ልቦናውን ይግለጽልን፡፡ ኢትዮጵያችንን አብዝቶ ይባርክ፡፡ ጥበብንና ማስተዋልን በውስጣችን ያፍስስልን፡፡ የተስፋ ቀንዳችንን ይሙላ፡፡ ከወደቅንበት ማጥ ወደ ታላቁ ሰገነታችን ከፍ ከፍ ያድርገን የኢትዮጵያ አምላክ፡፡
የነገን ማን ያውቃል? አንድዬ ብሎልን እኛም ነገ ‹‹ኢትዮሎጂ›› ወይም ‹‹ኢትዮጲኮሎጂ›› ‹‹ኢትዮጵያኒዝም›› የሚባል ሳይንስና ርዕዮተ ዓለምን ለዓለም ታላላቅ የትምህርት ተቋማት የሚያዳርስልንን ትውልድ ፈጣሪ አምላክ ባርኮ ሊሰጠንም ይችል ይሆናል፡፡ አምላክ እንዲባርከን ግን በቅድሚያ ትክክለኛውን መንገድ እንያዝ፡፡ የቅድስና ጨርቁን እንያዝ፡፡ ወደ እዝነታችን እንመለስ፡፡ ከልቦናችን እንሁን፡፡ ከቀልባችን እንሁን፡፡ ከራሳችን ጋር የገባነውን ጸብ እናብርድ፡፡ ከራሳችን እንታረቅ፡፡ በረካ ሁኑልኝ፡፡ መልካም ጊዜ፡፡
Filed in: Amharic