>

ጎበዝ አኀዝ ብቻ ሆነን ቀርተናል...!!! (አሰፋ ሀይሉ)

ጎበዝ አኀዝ ብቻ ሆነን ቀርተናል…!!!

አሰፋ ሀይሉ

ዩኒቨርሲቲዎቻችን ውስጥ ያየሁት የተለመደ ተሞክሮ ነበረ። ለተማሪ ሁሉ ቁጥር ማደልና በቁጥሩ ለይቶ መቅረት። የተማሪ አይዲ ካርድ አለ። ካምፓስ ገብተህ እስክትወጣ ዩኒቨርሲቲው የሚያውቅህ በዚያ ቁጥርህ ነው። የሚል ካርድ (የመመገቢያ ካርድም) አለ። የካምፓሱ ካፊቴሪያ ተጀምሮ እስኪያልቅ የሚያውቅህ በሚል ካርድ ቁጥርህ ነው። በአዲሳባ ዩኒቨርሲቲ እያለን ቴብል ቴኒስ እንቆምር የነበረ አንድ ጋሻው የሚባል የተማሪ ካፌ ተቆጣጣሪ ነበር። እና ከብዙ ዓመት በኋላ ስንገናኝ “ስምህ ጠፍቶብኛል ግን 2199 ነበርክ አይደል?” አለኝ። በሳቅ ፈነዳሁ። እሱ የሚያስታውሰኝ በሚል ካርድ ቁጥሬ ነበሮ ለካ! ማንዴላ ስለ ረዥሙ የእስርቤት ህይወቱ ሲፅፍ ከሁሉም ነገር የሚመረኝ በየእስርቤቱ የሰውን ልጅ ወደጰተራ ቁጥርነት የሚያወርዱበት ደረጃ ነው በማለት ይነግረናል። ማንዴላ ወደ ሩብን ደሴት እስርቤት ከረገጠባት ጊዜ ጀምሮ የሚጠራባት ቁጥር 466/64 ነበረች።

በ1964 ዓ.ም. ላይ ወደ ከርቸሌው ከወረዱ እስረኞች 466ኛው ነበረ ማለት ነው። እና አንድ ቀን በስሙ ሳይጠራ 27 ዓመት ታስሮ ወጣ። እና – ይላል ማንዴላ – ይሄ ሆን ተብሎ የሚፈፀም ሰው የሰውነት ክብሩ ተገፍፎ ሰውን ወደ ቁጥር ደረጃ የማውረድ ተግባር ነው ይለናል። ኮሞዲፋዪንግ ሂዩማን ቢንግስ። ሆነ ብሎ የሰውን ልጅ ወደ ሸቀጥነት ወደ ቁስነት የማውረዱ ሂደት አንዱ አካል ነው ይለናል። አንዳንዴ ታዲያ የሰው ልጅ ህይወት ወደ ተራ ቁጥርነት ተለውጦ ሳይ አዝናለሁ። ልብ ብለን ካየነው ብዙው ሰው ስም የለውም። ቁጥር ነው።

በኦሮሚያ ክልል 340 ሰዎች ተገደሉ። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 13 ሰዎች ተገደሉ። የሀጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ 286 ሰዎች ተገደሉ። የጃዋርን ተከበብኩኝ መልዕክት ተከትሎ 76 ሰዎች ተገደሉ። በቃ ቁጥር ነው የሚዘንበው። ሞት የሚለካው በቁጥር ነው። የሰው ህይወት ቁጥር ብቻ ሆኖ ቀረ። ያሳዝነኛል ይሄ ነገራችን።

የሰው ልጅ እናት አለው። አባት አለው። እህት ወንድም ጎረቤት አለው። ዘመድ ወዳጅ አለው። ታሪክ አለው። ሕልምና ያለፈበት መንገድ የተወው አሻራ ሚስት ቴዳር ጎጆ ልጅ አያት ሀገር ብዙ ነገር አለው አንድ ነጠላውን የሰው ልጅ። ይህ ሁሉ ነገር ቀርቶ ሁለነገራችን ቁጥርጰብቻ ሆኖ ቀረ። የኢትዮጵያ ሕዝብ 130 ሚሊየን መድረሱን እንጂ መቶ ሠላሳ ሚሊየን ሕይወቶች መኖራቸውን የሚያስታውስ ጠፋ። አኀዝ ብቻ ሆነን ቀርተናል። ለሕይወት፣ ለሕይወቶች ዋጋ መስጠት ሳንጀምር ሩቅ የምንደርስ አይመስለኝም። ፈጣሪ ከቁጥርነት ከፍ ያርገን። ለሕይወት ዋጋ እንስጥ። ለፍቅር ጊዜ እንስጥ። ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ።
Filed in: Amharic