>

የዓባይ ግድብ (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም)

የዓባይ ግድብ

(ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም)
የዓባይ ግድብ ኢትዮጵያን ገፍቶ ወደፊትና ወደላይ እንደሚያስፈነጥራት ሳይታለም የተፈታ ነው፤ እንደልብ በርካሽ የሚገኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ባለቤት መሆን ብዙ የልማት በሮችን ይከፍታል፤ እንጀራ ጋጋሪ ሴቶችም በኮሬንቲ ምጣድ እንጀራም ወጥም እንደሚሠሩ በቲቪ ሲናገሩ ሰምቻለሁ፤ በተለያዩ ኢንዱስትሪዎችም በኩል የሚደረገው እመርታ ብዙ ተነግሮለታል፤ ምንም አያጠራጥርም፡፡
ነገር ግን አንድ እንደሚመስለኝ ያልታሰበበትና እኛ የሌለን ጠባይ አለ፤ ይህ ጠባይ ለኢንዱስትሪ ልማት ቁልፍ ነው፤ ይህንን ጠባይ ይዘን በኢንዱስትሪ ለመልማት መሞከር የማያዛልቅ ነው፤ አንዱና ዋናው ከኢንዱስትሪ ጋር የማይሄደው ጠባያችን ሰዓትን ማክበር ነው፤ እንኳን በኢትዮጵያና በአሜሪካ ለሠላሳና አርባ ዓመታት ቆይተው በሰባት ሰዓት ለተጠሩበት ሰርግ በዘጠኝ የሚመጡ ብዙ ናቸው፤ በስምንት ሰዓት ለተጠራው ስብሰባ ጥቂቶች በአሥራ ሁለት ሲደርሱ አይቻለሁ፡፡
ለጊዜ መለኪያ አለው፤ ለመሬት መለኪያ አለው፤ ለእንጨትም ሆነ ለብረት መለኪያ አለው፤ ለጤፍም ሆነ ለገብስ መለኪያ አለው፤ ለዘይት ሆነ ለውሀ መለኪያ አለው፤ ሥጋ መለኪያ አለው፤ በረጅሙ ታሪካችን መለኪያዎችን አልፈጠርንም፡፡
የሚጎድሉን ሌሎችም ጠባዮች አሉ፡፡
መለካት ባለመቻል የተነሣ በርም ሆነ መስኮት፣ ቁም-ሣጥንም ሆነ ጠረጴዛ መጋጠሚያው ላይ ሁሌም ችግር አለ፡፡አንድ ሌላ ለኢንዱስትሪ ልማት አስፈላጊ ሆነ ጠባይ ትብብር ነው፡፡እንግዲህ የዓባይን ግድብ ሙሉ ጥቅሙን እንድናገኝ ከፈለግን ጠባያችንን ማሳመር ያሻል! ለዚህ የትምህርት ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን፣
ትምህርት ቤቶች ብቻ ሳይሆኑ የመንግሥት ሠራኞች ሁሉ ተማሪዎች መሆን ያስፈልጋቸዋል፤ አገዛዙ ከአሁኑ ቢያስብበትና አስተማሪዎችን ቢያሠለጥን መልካም ይመስለኛል፡፡
Filed in: Amharic