>

ከሐጫሉ ጋር ኦርቶዶክስን ለመቅበር የተደረጉ ሤራዎች! ️ (እውነት ሚድያ ማእከል)

ከሐጫሉ ጋር ኦርቶዶክስን ለመቅበር የተደረጉ ሤራዎች! 

እውነት ሚድያ ማእከል

✍️ የሐጫሉ ግድያ ለኦርቶዶክሳውያን ሁለት ጉዳት ሆኖ አልፏል፡- ሟች ኃይለ ገብርኤል የቤተ ክርስቲያኗ አባል ከመሆኑም በላይ በዚያ ሰበብ በተከሰቱ ጥቃቶች ኦርቶዶክስ የመከራው ገፈት ቀማሽ ሆናለችና!
✍️ ኦርቶዶክስን ከኦሮምያ ውስጥ በማጽዳት ‹‹እስልምናን የኦሮምያ መንግሥታዊ ሃይማኖት›› ማድረግ (“Islamic State of Oromiyaa” መመሥረት) ዋነኛ የጥቃቱ ዒላማ ነው!
✍️ የሚቃጠሉት የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ብቻ፣ የሚገደሉት ባለ ማዕተቦቹ ብቻ፣ ሀብትና ንብረት የሚወድምባቸውም ምእመናኑ ብቻ እየሆነ ‹‹በአጋጣሚ ነው›› ብሎ ለመደምደም ያዳግታል!
✍️ አጥቂዎቹ አስቀድመው የትኞቹ ቤቶችና ንብረቶች መቃጠል እንዳለባቸው፣ እነማን እንደሚገደሉ ጭምር ለይተውና በወረቀት ላይ ጽፈው መምጣታቸው ደግሞ ከፍተኛ ቅድመ ዝግጅት የተደረገበት፣ በተቀናጀ አመራር የተከናወነ፣ በሥልጠናና በጀትም የተደገፈ ጥቃት እንደነበር የሚያመላክት ነው፡፡
✍️ አደረጃጀቱ ‹‹ኦሮሙማ›› (ኦሮሞነት)፣ እንቅስቃሴው የቄሮ ይምሰል እንጂ ተዋናዮቹ አክራሪ ሙስሊሞች ናቸው፤ ‹‹ማተብና መስቀል ያሠረ ኦሮሞ አናውቅም!›› ብለው ኦሮሞ ኦርቶዶክሳውያንን ጭምር ገድለዋልና!!!
✍️ በሁለት ቀናት ብቻ በ10 የኦሮምያ ክልል ዞኖች ውስጥ በድምሩ #67 ኦርቶዶክሳውያን ተገድለዋል፤ ከዚህ ውስጥ #5ቱ የአንድ ቤተሰብ አባል ናቸው፣ #12 አንገታቸው ታርዶ፣ #1 በእንጨት ላይ ተሰቅሎ፣ #1 ቤት ውስጥ በማስገባት አብሮ በማቃጠል መገደሉ የጭካኔአቸውን ከፍታ ያሳያል፡፡
✍️ በምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት ብቻ በጥቅሉ #934 ተቋማት፣ #493 መኖርያ ቤቶች እና #72 ተሽከርካሪዎች ከጥቅም ውጭ መሆናቸው ከሀገረ ስብከቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
✍️ ጀዋር ተከበበ ተብሎ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትን ከብቦ ማጋየት፣ በሐጫሉ ሞት በማመካኘት ኦርቶዶክሳውያንን በአሰቃቂ ሁኔታ መጨፍጨፍ፣ የአንድን ሰው ቀብር ሥነ ሥርዓት ከለላ በማድረግም በኦሮምያ ምድር ኦርቶዶክስን ለመቅበር የሚደረገው የአክራሪነት ተልእኮ በመንግሥት ቁርጠኛ አመራር የማይገታ ከሆነ ኦርቶዶክሳውያኑ ባይገድሉም ዝም ብለው የሚሞቱበት ጊዜ ማብቃቱን ሁሉም ሊረዱት ይገባል!!!
 የሐጫሉን ሞት እንደ ምክንያት በማድረግ፣ በሥርዓተ ቀብሩ ሂደትም በማሳበብ በኦርቶዶክስና ኦርቶዶክሳውያን ላይ ሲሠራ የቆየውን ሤራ አስመልክቶ መጠነኛ ቅኝት እንዲሁም ስለደረሱት ጥቃቶች ተጨባጭ መረጃዎችን ልናቀርብላችሁ ወደድን፤ ተከተሉን! 
 
መንግሥት ለሐጫሉ መገደል ‹‹በጫካ ያሉ ኃይሎችን›› ተጠያቂ ያደርጋል፤ እነርሱ ደግሞ በተራቸው ‹‹መንግሥት ራሱ ይህንን እንደፈጸመ›› ይናገራሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ‹‹በሚዲያ ላይ በመናገሩ ምክንያት ይኸ ሕዝብ ነው የገደለው›› ብለው በወንድማማች ሕዝቦች መካከል ጠብ ለመጫር፣ እርስ በርስም ለማናከስ ሲጥሩ ተስተውሏል፡፡ አሁን የእኛ ጽሑፍ ዓላማ ስለ ሐጫሉ አሟሟት ለመናገር፣ አልያም ‹‹ገዳዩ ይኸ አካል ነው›› የሚል መረጃ ለመስጠት አይደለም፤ የማጣራቱን ድርሻ ለምድራዊው መንግሥት፣ ፍርዱን ደግሞ ለሰማያዊው መንግሥት (እግዚአብሔር) ሰጥተን መተው ይሻላል፡፡ ዋናው ትኩረታችን የሐጫሉን ግድያ ሰበብ በማድረግ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ እየተካሄደ የነበረውን የማጥፋት ተልእኮ ለመግለጥ ነው፤ ‹‹ሁለቱ ዝኆኖች ቢጣሉ ተጎጂው ሣሩ ነውና›› ኦርቶዶክስ የዚህ ዓይነት ዕጣ ፋንታ የደረሰባት ይመስላል፡፡
ጥንቱንም ጀምረው ኦርቶዶክስን ለማዳከም፣ ከተቻላቸውም ለማጥፋት አቅደው ሲሠሩ የነበሩ አካላት እንደነበሩ ይታወቃል፡- አንዳንዶች በዘር (ቋንቋ) መከፋፈል ላይ የተመሠረተ ፖለቲካቸውን ከግብ ለማድረስ ሲሉ የኦርቶዶክስን ‹‹አከርካሪዋን መስበር›› ስልታቸውን በዋና ማኒፌስቶአቸው ላይ ጭምር ጽፈው በእጅጉ ሲተጉ የነበሩ ናቸው፤ ዛሬም ከዚህ የጥፋት ዒላማቸው ፍንክች አላሉም፡፡ ሌሎች ደግሞ ክርስትናና እስልምና በኢትዮጵያ ውስጥ የነበሯቸውን መልካም የጋራ እሴቶችን በመናድ፣ ሕዝቡንም በሃይማኖት በማጋጨት፣ በተለይም ኦርቶዶክስን ከኦሮምያ ውስጥ በማጽዳት ‹‹እስልምናን የኦሮምያ መንግሥታዊ ሃይማኖት›› ለማድረግ (“Islamic State of Oromiyaa” ለመመሥረት) ማለም ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡
እናም ‹‹ከኦርቶዶክስ የጸዳች ኦሮምያን መመሥረት›› የሚለውን ይህንኑ ቅዠታቸውን እውን ለማድረግ ደግሞ በተገኘው አጋጣሚና ክፍተት ሁሉ ኦርቶዶክሳውያንን መግደል፤ አብያተ ክርስቲያናትን ማቃጠል፤ የክርስቲያኖችን ሀብትና ንብረት ሁሉ መዝረፍና ማቃጠል የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ሆኗል፡፡ ባሳለፍነው ወርኃ ጥቅምት፣ 2012 ዓ.ም በምዕራብ አርሲ፣ በባሌ፣ በሐረርጌና በጅማ አካባቢዎች የታየውም ይኸው ሐቅ ነበር፡፡ የሰሞኑ እንቅስቃሴም የዚሁ ተልእኮ ቀጣይ ምዕራፍ እንጂ አዲስ ክስተት አይደለም፡፡ የቀድሞው ደም ሳይደርቅ ሌላ ደም ፈሰሰ፤ በአንድ ሰው ሞት ምክንያትም የበርካቶች ነፍስ በአሰቃቂ ሁኔታ ተቀጠፈ! ሐጫሉ አሁን ላይ አርፏል፤ በርሱ ሞት ምክንያት ሰቀቀን የሚደርስባቸው ኦርቶዶክሳውያን ግን ዛሬም ድረስ እረፍት ሊያገኙ አልቻሉም!
ጀዋር ተከበበም፣ ሐጫሉ ተገደለም በልዩ ትኩረት ጥቃት የሚደርስባቸው፣ እየታደኑ የሚገደሉት ኦርቶዶክሳውያን ናቸው፡፡ ይህም ስለሆነ በአዲስ አበባ ላይ ለተከበበውና ለተገደለው አንድ ነፍስ በማሳበብ በአብዛኞቹ የኦሮምያ ክልል (ሙስሊም በዝ) ቦታዎች በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንና ተከታዮቿ ላይ የማያቋርጥ ሰቀቃ እየደረሰ ነው፡፡ በጥቅምቱ (2012 ዓ.ም) ግርግር ብቻ #86 ኦርቶዶክሳውያን በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፤ #31 አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፤ ኁልቆ መሣፍርት የሌላቸው የምእመናኑም ሀብትና ንብረት ወድሟል፡፡ ሰሞኑንም ተመሳሳይ ሁኔታዎች በመከሰታቸው በልዩ ክትትልና ጥንቃቄ የተሰበሰበውን መረጃ በመጠኑ እንደሚከተለው እንጠቁማችሁ፡፡
የጥቃቱ ቅርጽና ትኩረት
===============
የእነዚህ አክራሪ ሙስሊሞች ሙሉ የጥፋት ትኩረት በኦርቶዶክስና ኦርቶዶክሳውያን ላይ እንደነበር አመላካች ሁኔታዎችና ተጨባጭ ኩነቶች አሉ፤ የተጎጂዎቹ ማንነት ሲፈተሽ የአንገት ላይ ምልክታቸው (ማዕተባቸው) አንድ ያደርጋቸዋልና፡፡ የሚቃጠሉት የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን ብቻ፣ የሚገደሉት ባለ ማዕተቦቹ ብቻ፣ ሀብትና ንብረት የሚወድምባቸውም ምእመናኑ ብቻ መሆናቸው ‹‹በአጋጣሚ የተከሰተ ነው›› በሚል መደምደም አይቻልም! ይህንን ሁሉ ድግግሞሽና ብዛትስ እንዴት ‹‹በአጋጣሚ የሆነ›› ብለን ልንቀበል እንችላለን?!
✍️ ምንም እንኳን ‹‹በኦሮሙማ›› (ኦሮሞነት) ስም የዘር ብቻ መስሎ ይወራ እንጂ ሙሉ በሙሉ ኦርቶዶክሳውያን ላይ ያነጣጠረ እንደነበር የሚያመለክተው ኦሮሞ የሆኑ ኦርቶዶክሳውያን ጭምር በመገደላቸው ነው፡፡ ‹‹እኔ ኦሮሞ ነኝ እኮ!›› እያሉ ነፍሳቸውን ለማትረፍ የሞከሩት እንኳን ከመገደል አልዳኑም፡- አጥቂዎቹ ‹‹ማተብ፣ መስቀል ያሠረ ኦሮሞ አናውቅም!›› ብለው እቅጩን ነግረው እስከወዲያኛው አሰናብተዋቸዋል፡፡
✍️ ከብሔረሰቡ አብራክ የወጡ፣ በሕዘቡም ቋንቋ እየተናገሩ በባህሉ መሠረት የሚያገልግሉትን አቡነ  ሄኖክን ጭምር በሻሽመኔ መኖርያ ቤታቸው (ምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት) ለመግደል ሙከራ ማድረጋቸውም ይኸንኑ የሚያረጋግጥልን ነው፡፡
✍️ በአንጻሩ ደግሞ በዘር ኦሮሞ ያልሆኑ፣ ነገር ግን የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ ሌሎች ነዋሪዎች ከአክራሪዎቹ መዳናቸው ደግሞ ሌላኛው አመላካች ነጥብ ነው፡- እውን ‹‹የኦሮሞ ቄሮ እንቅስቃሴ›› ወይስ ‹‹የአክራሪ ሙስሊሞች ቡድን›› ያሰኛል!
✍️ ‹‹ኦርቶዶክሳውያን ያልሆኑ ሌሎችም ተገድለዋል›› የሚል ቢኖር ምናልባት ጥቂት ቢኖሩ እንኳን አንድም በስህተት የተገደሉ፣ አልያም ደግሞ ከጸጥታ አካላት በተተኮሰ ተባራሪ ጥይት ተገድለው ሊሆን ቢችል እንጂ ልክ እንደ ኦርቶዶክሳውያኑ በልዩ ትኩረት፣ በዒላማ እየታደኑ የተገደሉ አለመሆናቸው ሊሠመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
በአርቲስት ሐጫሉ ሞት በማሳበብ የተፈጸሙ ጥቃቶች ተጨባጭ መረጃዎች
==================================
ለምሳሌ፡- በሁለቱ ቀናት (ሰኔ 22 ምሽት እስከ ሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም) ብቻ፡-  
✍️ በጥቅሉ በ10 የተለያዩ የኦሮምያ ክልል ዞኖችና በ45 ወረዳዎች (ከተሞችን ጨምሮ) ውስጥ በድምሩ 67 ኦርቶዶክሳውያን ተገድለዋል (ከእነዚህ መካከል የ55 ሟቾች ዝርዝር መረጃ ደርሶናል)፡፡ ከእነዚህም ውስጥ #12 አንገታቸው ታርዶ፣ #1 በእንጨት ላይ ተሰቅሎ፣ #1 ቤት ውስጥ በማስገባት አብሮ በማቃጠል፣ #5 የአዳሚ ቱሉ ነዋሪዎች ደግሞ የአንድ ቤተሰብ አባልና ሁሉም ኦሮሞ የነበሩ መሆናቸው የጥቃቱን ጭካኔ ከፍታ ያሳያል፡፡
✍️ አካላቸው የተጎዱ፣ ቤት ንብረቶቻቸው በቃጠሎ ከመውደሙ የተነሣ በየአብያተ ክርስቲያነቱ ተጠልለው የሚገኙት በድምሩ #7,000 ሲሆኑ ከዚህም #99 በመቶ የሚሆኑቱ ኦርቶዶክሳውያን ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል የምዕራብ አርሲ (ሻሽመኔ አከባቢ) ብቻ #3,362 መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
✍️ ከእነዚህ ዞኖች ውስጥ 244 ቤታቸው የተቃጠለባቸው አባወራዎች ዝርዝር ደርሶናል፡፡
✍️ ምንም እንኳን የወደሙትን ንብረቶች ሁሉንም ዘርዝሮ ለመጨረስ ቢያቅትም፡- በምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት ብቻ በጥቅሉ #934 ተቋማት (የግልና የመንግሥት)፣ #493 መኖርያ ቤቶች (#9 የካህናት ነው) እና #72 ተሽከርካሪዎች ከጥቅም ውጭ መሆናቸው ከሀገረ ስብከቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ እስካሁን ድረስ በዞኖቹ ውስጥ የወደሙ የ #286 ተቋማት ዝርዝር መረጃ ደርሶናል፡፡
✍️ አጥቂዎቹ አስቀድመው የትኞቹ ቤቶችና ንብረቶች መቃጠል እንዳለባቸው፣ እነማን እንደሚገደሉ ጭምር ለይተውና በወረቀት ላይ ጽፈው መምጣታቸው ደግሞ ምንም እንኳን የሐጫሉ ሞትን ያመካኙ እንጂ ምን ያህል ቅድመ ዝግጅት የተደረገበት ጥቃት እንደነበር የሚያመላክት ነው፡፡ በዚያውም ላይ አጥቂ ቡድኑን ይመሩ የነበሩ ግለሰቦች በመኖራቸው ምክንያት በአንድ ግድግዳ ብቻ ይለያዩ የነበሩ ቤቶች እንኳን ተለይተው መቃጠላቸው መታወቅ ይኖርበታል፡፡
✍️ ይህንን ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ ደግሞ ከጀርባ ሆኖ ያቀናጅ የነበረ ኃይል ለመኖሩ፣ አጥቂዎቹም በቂ ሥልጠና መውሰዳቸውን፣ የሚያጠቁበት ማቀጣጠያ ነገሮች ቀድሞውንም ተገዝተው የተዘጋጁ እንደነበር (ከሐጫሉ መሞት በኋላ አንድ ሰዓት እንኳን በማይሞላ ጊዜ ውስጥ የተደራጀ ጥቃት ተጀምሯልና)፣ እነዚህን ሁሉ ለማስፈጸምም አስፈላጊው በጀት እንደተበጀተላቸው በቂ ማሳያ ነው፡፡
✍️ ከእነዚህ ሁሉ ጋር ደግሞ አክራሪዎቹ ጥቃቶቹን ይፈጽሙ የነበሩት ‹‹አላሁ አክበር!›› የሚል መፈክር እያሰሙ እንደነበር በቦታው የነበሩ የዓይን እማኞች ያረጋግጣሉ፡፡
✍️ መንግሥት በቅርብና በተሟላ ጥንቃቄ አለበት ተብሎ በሚታወቀው በአዲስ አበባ ውስጥ እንኳን ሌሊቱን ሙሉ በተለያዩ አቅጣጫዎች ያሉትን አብያተ ክርስቲያናት በአንዴ ለማቃጠል የተቀናጀ የጥፋት እንቅስቃሴ ሲደረግ ነበር፤ ምእመናኑ ነቅተው በመጠበቅ አተረፏቸው እንጂ፡፡ እጅግ የሚገርመው ግን የመንግሥት አካላት በአሰቃቂ ሁኔታ ለተገደሉ ኦርቶዶክሳውያን ሳይደርሱላቸው ቀድሞ እርምጃ መውሰድና በእስር ማጎር የጀመረው ራሳቸውን ከአጥቂው ቡድን በተከላከሉ፣ አብያተ ክርስቲያናቱንም ከመቃጠል በታደጉት የአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ መሆኑ  ነው፡፡
በልዩ ጥናት፣ ከነተጠቂዎቹ ስም ዝርዝርና የጥፋቱ መጠን ተጣርቶ ከተላኩልን መካከል ደግሞ የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፡-
1. በጅማ ዞን፡- 
———–
✍️ በጅማ ከተማ #22፣ በሰቃ ጨቆርሳ ወረዳ ደግሞ #3፤ በድምሩ #25 ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ በከተማው ውስጥ በ #11 ሰዎች ላይ ደግሞ የድብደባ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል፡፡
2. በኢሉ አባ ቦራ ዞን፡- 
—————–
✍️ በመቱ #3 ቤቶች (የመኖርያ፣ ግሮሰሪና ሆቴል) ተቃጥለዋል፡፡
3. በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን፡- 
——————
በሐረር፣ በሐሮማያ፣ በባቴ፣ በጉርሱም፣ በኮምቦልቻና አሌ በድምሩ #124 ቤቶች፣ #23 የንግድ ተቋማት ተቃጥለዋል፤ አንድ ሰውም ተገድሏል፡፡
✍️ ሀረማያ ወረዳ (ባቴ ቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ዙርያ)፡- #48 አባወራዎች (#119ሰዎች) ተፈናቅለዋል፤ በግምት #7.9ሚሊዮን የሚሆን ንብረት ወድሟል፡፡
✍️ በኮምቦልቻ፡-  (መንግሥት በራሱ ባጠናዉ መሠረት እንኳን) #20 አባወራዎች (ጠቅላላ#80 ሰዎች) ተፈናቅለው በአሁኑ ጊዜ በወታደር ካምፕ ዉስጥ ይገኛሉ፡፡ የአንድ ግለሰብ ብቻ በግምት አንድ ሚሊዮን የሚያወጣ ንብረት ጠፍቷል፤ የሌሎቹ ግን ገና አልተገመተም፡፡
✍️ በጃርሶ (በአሌ ቀበሌ) #49 አባወራዎች #180 ሰዎች፤ በአወዳይ #4 አባወራዎች (ጠቅላላ#20 ሰዎች)፤ በሚዳጋ ደግሞ 12አባወራዎች (ጠቅላላ#51 ሰዎች) ተፈናቅለዋል፤ አሁን የሚገኙት ባስጠለሏቸው ቤት ነዉ፡፡ ንብረታቸዉ በግምት #3.5 ሚሊዮን ብር ይገመታል፡፡
✍️ በሚዳጋ፡- ንብረታቸዉ በግምት #2.5 ሚሊዮን ብር ይገመታል፡፡
4. በምዕራብ ሐረርጌ ዞን፡-
——————
በጭሮ (አሰበ ተፈሪ) ከተማ፣ በአሰቦትና በሚኤሶ በድምሩ #19 ቤቶች፣ #52 ተቋማትና #1 ተሽከርካሪ ተቃጥለዋል፤ #6 ሰዎች ደግሞ ተገድለዋል፡፡
✍️ በጭሮ (አሰበ ተፈሪ) ከተማ  ክርስቲያኑ ባለሀብት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድሏል፤ በግፍ ከተገደሉቱ በተጨማሪ #6 ሰዎች ክፉኛ ተደብድበዋል፤ #40የንግድ ቤቶችና አንድ ትልቅ ሆቴል ተቃጥለዋል (የባለሃብቱን ሙሉ ንብረትና ሆቴል ከነ ሙሉ ዕቃዉ ከመውደሙም በላይ እርሱንም  ገድለዉታል)፡፡
✍️ በጭሮ/አሰበተፊሪ ዙርያ፡- #80 አባወራዎች (#225ሰዎች) ተፈናቅለዉ በአሶቦት ገዳም ይገኛሉ፤ የተወሰኑት ደግሞ በሰዉ ቤት ተጠልለው ይገኛሉ፡፡
✍️ በሚኤሶ፡- #15 ሰዎች ቤታቸው ሙሉ በሙሉ ተቃጥሎባቸዋል፤ በሰዎች ቤት ተጠልለው ይገኛሉ፡፡
✍️ በጭሮ (አሰበ ተፈሪ) ከተማ፡- #6የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል፣ #20 አባወራዎች (100ሰዎች) ተፈናቅለዋል፤ #6አባዎራዎች ከቤተ ክርስቲያን ናቸዉ ፡፡
5. በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፡- 
———————
✍️ በወሊሶ #15 ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ #600 የተፈናቀሉ የነበሩ ሲሆን ከ #87 አባወራዎች በሰተቀር ሌሎቹ በመንግሥት ወደ ቤታቸዉ ተመልሰዋል፡፡ #87 አባወራዎች ግን በቤታቸዉ ላይ ከባድ ጉዳት በመድሱ ምክንያት  በቤተ ክርስቲያን  ተጠልለዉ ይገኛሉ፡፡
6. በምሥራቅ ሸዋ ዞን፡- 
—————-
✍️ በአዳማ፣ በዝዋይ (ባቱ)፣ በመቂ፣  በአርሲ ነገሌ፣ በሻሽመኔና በቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) በድምሩ #26 ቤቶች፣ #191 ተቋማትና #1 ተሽከርካሪ ተቃጥለዋል፤  #18 ሰዎች ተገድለዋል፡፡
7. በአርሲ ዞን፡- 
————–
በአሰላ፣ በቀርሳ፣ በቦቆጂ፣ በዴራ፣ በአርቦዬ፣ በአሳሳ፣ በጉልቻና በዱግዳ በድምሩ #18 ቤቶችና #3 ተቋማት ተቃጥለዋል፤ #14 ሰዎች ተገድለዋል፡፡
✍️ በዝዋይ ጉግዳ፡- #2ሰዎች በግፍ ተገድለዋል፤ #6 የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ቤታቸዉ የተቃጠለና ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸዉ #15 አባወራዎች (#140 ተፈናቃዮች) በቤተ ክርስቲያን ናቸዉ፡፡
✍️ በዴራ፡- #3 ሰዎች በግፍ ተደግለዋል፤ #10ሰዎች ቤታቸዉ ተቃጥሎባቸው ቤተክርስቲያን ውስጥ ተጠልለዋል፡፡
✍️ በቀርሳ፡- #7ሰዎች በግፍ ተገድለዋል፤ #2ቱ ከፍተኛ አካል ጉዳት ደርሶባቸዋል (አሁንም  ሆስፒታል ውስጥ ይገኛሉ፤ ሁሉም የሰበካ ጉባኤ አባላት ናቸዉ)፡፡
8. በምዕራብ አርሲ ዞን፡- 
————————–
✍️ በቆሬ ከተማ በከተማዉ #26፣ በገጠር #9 (በጠቅላላ#35 አባወራዎች፣ #855 ሰዎች) ሙሉ ንብረትና  ሀብታቸዉ ወድሟል፤ ሁሉም አሁን ቤተክርስቲያን ውስጥ ተጠልለዉ ይገኛሉ፡፡
✍️ በአወደላ፡- #21 አባወራዎች ሙሉ ንብረታቸዉ በመውደሙ ሁሉም ተፈናቅለዋል፡፡
✍️ በኮፈሌ፡- #69 ቤቶች ተቃጠለዋል፤ አሁን ፖሊስ ጠቢያ  ተጠልለዉ ይገኛሉ፡፡
✍️ በጉቺ መድሃኒአለም፡-#15 ቤቶች ተቃጠለዋል፤ #15ቱም አባወራዎች (ሁሉም የሰበካ ጉባኤ አባላት ናቸው) ከነ ቤተሰቦቻቸዉ ደቡብ ክልል ጉግማ ከተማ ሄደዉ ከዘመድ ቤት ይገኛሉ፡፡
✍️ በሽሬ ኪዳነ ምህረት፡- #36 አባወራዎች (ጠቅላላ#345 ሰዎች) ተፈናቅለዋል፤ ሙሉ ንብረታቸዉ ጠፍቷል፤ ምንም መፍትሄ ስላላገኙ አስከአሁን ድረስ ቤተክርስቲያን መቃብር ቤት  ናቸዉ፡፡
 
9. በባሌ ዞን፡- 
———–
በአቤቱ፣ በአጋርፋ፣ በአዳባ፣ በሐቆና በኮኮሳ በድምሩ #5 ቤቶችና #4 ተቋማት ተቃጥለዋል፤ #14 ሰዎች ተገድለዋል (በአቤቱ#5፣ በአዳባ #6)፤ #1 ቤተ ክርስቲያን ከነ ንዋየ ቅዱሳቱ ሙሉ በሙሉ ወድሟል፡፡
✍️ #1,300 ተፈናቃዮች በአጋርፋ ግብርና ኮሌጅ በመማሪያ ክፍሎች ዉስጥ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡
✍️ በኦዳ ነገሌ  የ #4ሰዎች ቤታቸዉ ሙሉ በሙሉ ተቃጥሎ ወድሟል፡፡
✍️ በአዳባ  ብቻ #323 ሰዎች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጠግተዉ ይገኛሉ፤ #110 የሚሆኑቱ ደግሞ ሀቆ ከተማ ወስጥ ናቸው፡፡
✍️ በኮኮሳ ወረዳ ውስጥ #20 አባወራዎች (#52ሰዎች) ተፈናቅለዋል፤ የ#3 ሰዎች (የቤተ ክርስቲያን የሰበካ ጉባኤ አመራር የሆኑ ) ቤታቸዉ  ከነሙሉ ንብረታቸዉ ወድሟል፡፡
✍️ በኮኮሳ ወረዳ ውስጥ የሚገኘው የሆግሶ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ከነ ንዋያተ ቅድሳቱ ሙሉ በሙሉ በቃጠሉ መውደሙም ታውቋል፡፡
10. በቡኖ በደሌ ዞን፡-
———————–
✍️ በጮራ ወረዳ #7 ቤቶች፣ #13 ተቋማትና #1 ተሽከርካሪ ተቃጥለዋል፡፡
የመንግሥት (የሕዝብ) ተቋማትም ጭምር የጥቃቱ ሰለባ ነበሩ
====================================
ጥቃቱ ዒላማ ያደረገው የግል ንብረቶችን ብቻ ሣይሆን የመንግሥት (የሕዝብ ተቋማትን) ጭምር መሆኑ ደግሞ ይበልጥ ግርምታን ይፈጥራል፡፡ ለምሳሌ፡- አጥቂዎቹን ጨምሮ የአከባቢው ማኅበረሰብ ልጆች ሁሉ ይማሩማቸው የነበሩ ትምህርት ቤቶች፤ ማኅበረሰቡ ሲታመም የሚታከምባቸው፣ የወሊድ ክትትል የሚያደርግባቸው የጤና ተቋማት፤ የወረዳዉ መሥሪያ ቤቶች ሁሉ ብዙዎቹ የጥቃቱ ሰለባዎች ነበሩ፡፡
ከዚህ አንጻር የሚከተሉትን ነጥቦች መረዳት እንችላለን፡-
1ኛ) ምንም እንኳን የጥቃቱ ዋና ዒላማ በኦርቶዶክሳውያን ላይ የነበረ ቢሆንም የአከባቢው ሕዝብ ሁሉ ባሉት መሠረተ ልማቶች ሁነኛ ተጠቃሚ እንዳይሆን (በሕዝብ ላይ ጭምር) የተሸረበ ሤራ መሆኑን፤
2ኛ) ከዚህም አንጻር ጥቃት አድራሾቹም ሆኑ ከጀርባ ሆነው ያሰማሯቸው አካላት እንታገልለታለን ለሚሉት ሕዝብ ጭምር የማይራሩ ጨካኞች መሆናቸውን፤
3ኛ) የመንግሥት የአስተዳደር አካላትንና ተቋማትን ጭምር በማንአለብኝነት በማጥቃት ‹‹በሀገሪቱ ውስጥ መንግሥት የለም›› በማስባል የመንግሥትን ሥልጣን ለመቆናጠጥ ያኮበኮቡ አካላት መኖራቸውን፤
4ኛ) መሰል መሠረተ ልማቶችንና ማኅበራዊ ተቋማትን በተደጋጋሚ በማጥቃት የአከባቢውን (ብሎም የክልሉን) ገጽታ ማበላሸትና በማንኛውም የልማት ዘርፍ ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉ ባለሀብቶች ዳግም በዚያ አከባቢና በመላው ኢትዮጵያ እንዳይሠማሩ ለማድረግ ሠርተዋል፤ (ይህም ምን ያህል ኢትዮጵያ የምትባልን ሀገር ለማዳከምና ለመበታተን አቅደው ከሚሠሩት የውጭ አካላት ጭምር ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚችል ሊያመላክት ይችላል)፡፡
የአከባቢው ማኅበረሰብ መልካም ትብብሮች
‹‹ጥቃቱን ያደረሱት ሙስሊሞች ናቸው›› ብሎ መናገር ትክክል የማይሆነው በጥቃቱ ወቅት የአከባቢው ሙስሊሞች ጭምር ሲከላከሉ፣ አጥቂዎቹን ሲማጸኑና ክርስቲያን ወገኖቻቸውን ቤታቸው ውስጥ በመሸሸግ ጭምር ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሲጥሩ እንደነበር ስናስተውል ነው፡፡ በእውነትም ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከዚህን በፊትም እንዲህ ዓይነት የአጥፊነት ጠባይ አልነበራቸውም፤ አሁንም የላቸውም፡፡ በሙስሊሞች ስም፣ በእስልምና ውስጥ ተደብቀው አረባዊ የጭካኔ ክዋኔዎችን እየፈጸሙ ያሉት ከሃይማኖቱም ሆነ ከሃይማኖተኞቹ ጋር አንዳችም ሞራላዊ ግንኙነት የሌላቸው አክራሪዎች መሆናቸውን ተረድተናል፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊም በዚሁ አግባብ እንዲረዳ ለመጠቆም እንወዳለን፡፡
ለዚህ ድምዳሜአችን ደግሞ ማሳያ የሚሆኑ የአርዓያነት ተግባራት በተጨባጭ አሉ፡-
✍️ የምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ (ከራሳቸውም አንደበት እንደተደመጠው) ላይ ጥቃት ለማድረስ፣ ሀገረ ስብከቱንም ለማቃጠል ወደዚያው አቅንተው የነበሩት አክራሪዎቹ በሩን በኃይል ይመቱ በነበረ ጊዜ የአከባቢው (ጎረቤት) ሙስሊሞች ጭምር ተማጽነው እንዳተረፏቸው ተናግረዋል፤
✍️ በሌሎችም ቦታዎች በነበሩ ጥቃቶች ጎረቤት ሙስሊሞቹ በየቤቶቻቸው ደብቀው ለማትረፋቸው በቂ ማሳያዎች አሉ፡፡
በመንግሥት በኩል፡- አዎንታዊና አሉታዊ ምላሾች ከቀጣይ የቤት ሥራዎች ጋር 
መንግሥት የምንለው ከፌደራሉ መዋቅር እስከ ታችኛው የቀበሌ አስተዳደር ድረስ ያለውን ሁሉ ስለሆነ ሁሉንም በአንድ ላይ ጨፍልቆ በአዎንታዊነት አልያም በአሉታዊነት መፈረጅ አግባብነት የለውም፡፡ እናም ከጥቃቱ ጋር በተገናኘ በየደረጃው ያሉት የመንግሥት አካላት ያደረጓቸውን (ያላደረጓቸውንም) እንቅስቃሴዎች በጥቂቱ ለመጠቆም፡-
1) አዎንታዊ እንቅስቃሴዎች፡-
——————
✍️ በተለይ በፌዴራል መንግሥት በኩል (ጠቅላይ ምኒስትሩን ጨምሮ) ድርጊቱን ፈጥኖ ከማውገዝ ጀምሮ ሕግን ለማስከበር ለሕዝብ ቃል የተገቡ ዲስኩሮች፤
✍️ በአንዳንድ ቦታዎች ሕገ ወጦቹ ጥቃት አድራሾች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ መሆናቸው፤ (ለምሳሌ፡- በአቤቱ 40 ሰዎች፤ ከኮኮሳ ዙሪያና ከወጊሶ አካባቢ 30-40 የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች፤ በአርሲ ዴራም የተወሰኑቱ እንደተያዙ መነገሩ)፡፡
✍️ ጥቃቱ ይፈጸም በነበረበት ወቅት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ባልተወጡ ጥቂት የአስተዳደር አካላት ላይ ምርመራ እንደተጀመረ መጠቆሙ፤
✍️ ዘግይቶም ቢሆን የጸጥታ አካላትን ወደ ቦታዎቹ ለማንቀሳቀስ መሞከሩ፤
✍️ በአንዳንድ አከባቢዎች ከአከባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመሆን (ቢያንስ የዕለት ምግብ) ድጋፍ ማድረግ መጀመሩ፤ (አቤቱ፤ በኮኮሳ ጥቂት ቦታዎች፤ ዝዋይ ዱግዳ፤ ወዘተ)፡፡
✍️ ከባቴ አካባቢ ለተፈናቀሉት የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ለእያንዳንዳቸዉ ፍራሽ፣ ብርድልብስና አንሶላ ሰጥቷል፤ ቆርቆሮ ለመስጠትም ቃል ገብቷል (በእጅጉ የሚያስመሰግነው ተግባር ነው)፡፡
✍️ አንዳንዶችን ወደነበሩበት ቀዬአቸው (ቤታቸው ያልተቃጠለባቸውን) ለመመለስ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው (ደቡብ ምዕ/ሸዋ ወሊሶ አንዱ ነው)፡፡
✍️ በአንዳንድ ቦታዎች የብዙዎቹ ከብቶች ተዘርፈው የነበሩ ቢሆንም  መንግሥት ለማስመለስ ሙከራዎችን እያደረገ ነው (ለምሳሌ፡- ዝዋይ ዱግዳ)፡፡
✍️ በአርሲ ዴራ ደግሞ ማዘጋጃው 100,000 ብር ይዞ እርቅ ጠይቆ ነበር፤ ህዝቡ ግን የጥፋቱ ምክንያት መሆናችሁን ኃላፊነት ካልወሰዳችሁ አንታረቅም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
2) አሉታዊ ገጽታዎች፡- 
————–
✍️ ጥቃቱ ከመከሰቱ በፊት መንግሥት አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ አለማድረጉ ያስወቅሰዋል፤ ምክንያቱም መሰል አጋጣሚዎችን በመጠቀም ይህ ዓይነት ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል ከዚህን በፊት ከነበሩት ተሞክሮዎች ትምህርት ተወስዶ ነበርና፡፡
✍️ ችግሩ በተከሰተ ጊዜም በስልክ ጭምር ተደውሎ ተነግሮአቸው ሰምተው እንዳልሰሙ ከመሆናቸውም በላይ ስልካቸውን በማጥፋት ዝምታን መርጠዋል፤ ((በተለይ ሻሽመኔ ላይ))
✍️ ጥቃቱ እየተፈጸመ እንኳን ቆመው የሚመለከቱ የመንግሥት ጸጥታ አስከባሪዎች ነበሩ፤ ‹‹መመሪያ አልደረሰንም!›› በሚል፡፡
✍️ አንዳንዶች መረጃ ይደብቃሉ፤ ችግር የሌለ አስመስለውም ለበላይ አካል ያስተላልፉ ነበር (የኦዳ ነገሌ ቀበሌ አስተዳዳሪ ለዚህ በቂ ማሳያ ነው)፡፡
✍️ ከዚህን በኋላ ላለውም ‹‹መንግሥት ስለነፍሳችሁ ምንም ዋስትና አይወስድም›› ተብለው በግልጽ የተነገራቸው አሉ፤ ምንም ዓይነት እርዳታም አልሰጧቸውም (ጭሮ/አሰበ ተፈሪ አከባቢ)፡፡
✍️  ጥቃት አድራሾቹ ተለይተው በቁጥጥር ሥር በዋሉባቸው ቦታዎች እንኳን በፖሊስ ጣቢያዎች ከማቆየት ያለፈ በሕግ እንዲጠየቁ የማድረግ እንቅስቃሴ አይስተዋልም፤ (ለምሳሌ፡- አዳባ)፡፡
✍️ አሁንም ድጋፍ ያላገኙ ተፈናቃዮች አሉ (በተለይ አዳ ነገሌ፣ ኮኮሳ አንዳንድ አከባቢዎች)፡፡
3) መንግሥት በቀጣይስ ምን ማድረግ ይጠበቅበታል?
——————————————————
እንዲህ ዓይነት ነገሮችን ስንገልጽ ምናልባትም ‹‹የሃይማኖት ጦርነት አወጃችሁ፤ አጋነናችሁ›› የሚሉ ይኖሩ ይሆናል፡፡ እኛ ግን እንኳንስ ማጋነን የደረሱትን ጥቃቶች ሁሉ ካለማካተታችንም በላይ የአሰቃቂነታቸውንም ደረጃ በጽሑፍ ደረጃ ለማስፈር አልፈለግንም፤ ይሰቀጥጣሉና፡፡ እንዲያውም ለሀገር ሰላምና ለሕዝቦች አንድነት ሲባል በርካታ መረጃዎችን ወደ ሚዲያ ከማድረስ ለመቆጠብ ቢሞከርም በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንና ኦርቶዶክሳውያን ላይ የሚካሄደው ጦርነት ግን ሊያባራ አልቻለም፡፡ መንግሥትም በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በኩል እየቀረቡ ያሉ ስሞታዎችንና የአድኑን ጥያቄዎች ቸል ከማለቱ የተነሣ ደጋግሞ ለመጮኸ ግድ እያለን ነው፡፡ መሰል ጥቃቶች እየተበራከቱ፣ በአንጻሩ ደግሞ በመንግሥት በኩል ለአቤት ባይ ኦርቶዶክሳውያን ጆሮ እየተነፈጋቸው የሚቀጥል ከሆነ ደግሞ በሂደት ኩርፍያና አለመተማመን ከመፍጠሩም በላይ ‹‹ተኝቶ ከመሞት›› በሚል ራስን ለመከላከል የሚያስገድዱ ሁኔታዎችን ሊጋብዝ  ይችላል፤ ተፈጥሯዊ ነውና፡፡
ይኸ አካሄድ ደግሞ ለዜጎች አንድነትና ለሀገሪቱም መረጋጋት ስለማይጠቅም መንግሥት የሚከተሉትን ዋና ዋና ተግባራት ቢያከናውን ብለን እንጠቁማለን፡-
1) ብዙውን ጊዜ እየተጠቁ ላሉት አካላት (ኦርቶዶክሳውያን) እና ተቋማት (አብያተ ክርስቲያናትና የምእመናኑ ንብረቶች) ልዩ ጥበቃ ማድረግ፣ እሮሮአቸውን ጆሮ ሰጥቶ ማድመጥ፣ እንደ አንድ ዜጋም መብትና ደኅንነታቸውን በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ፤
2) የተፈናቀሉትን መልሶ ከማቋቋም ጀምሮ ለጠፋው የሰው ሕይወትና ለወደሙት ንብረቶችም አስፈላጊውን ካሳ መክፈል፤
3) ለሀገር ሰላም የምትጸልይ፣ ለሕዝቦች አንድነት የምትተጋን ቤተ ክርስቲያን ይበልጡን የለውጡ ፊታውራሪ አድርጎ ከጎኑ ማሰለፍ ሲችል በቸልተኝነት ከመመልከት፣ ከ50 ሚሊዮን በላይ የሀገሪቱን ዜጎች ያቀፈች እምነትንም ቸል ከማለት መቆጠብ (ለራሱም ቢሆን አላስፈላጊ ዋጋ ያስከፍለዋልና)፤
4) በሕዝቦች መካከል ጠብን የሚዘሩ፣ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን የሚያጥላሉና አስተዳደሯንም ለመክፈል የሚሯሯጡ ሚዲያዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ቢያደርግ፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ግን በቅርቡ OMN በመሳሰሉ ሚዲያዎች ላይ መውሰድ የጀመራቸው እርምጃዎች የሚበረታቱ ናቸው፤ ቀድሞውንም በተጨበጡ ማስረጃዎች ጭምር አቤቱታ ሲቀርብበት መንግሥት ከገደብ ያለፈ ትእግሥትና ቸልተኝነት ማሳየቱ አግባብነት አልነበረውምና፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በማኅበራዊ ሚዲያዎች (በተለይ Facebook ዓይነቶቹ ላይ) ተመሳሳይ የጥላቻና ከፋፋይ ፖለቲካዎችን የሚዘሩ ግለሰቦችና ድርጅቶችንም እየተከታተለ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል፤ የሚዲያ አጠቃቀም ሕጉም በአግባቡ ለመተግበሩ ተጨባጭ ማረጋገጫዎች መታየት ይኖርባቸዋልና፡፡
5) በልዩ ቅንጅትና ዝግጅት የሚደረጉ መሰል ጥቃቶችን [የራሱን መዋቅርና ባለ ሥልጣናትን ሱታፌ ጨምሮ] አስቀድሞ በማነፍነፍ የቅድመ መከላከል ሥራዎችን በተደራጀ መልኩ ማከናወን አለበት፤ ይልቁንም ለመሰል ጥቃቶች በተደጋጋሚ የሚጋለጡ ሙስሊም በዝ አከባቢዎች ልዩ ጥበቃ ማድረግ ይኖርበታል፡፡
6) በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በዚህ ጥቃት ውስጥ የተሳተፉትን አካላት ሁሉ አድኖ በመያዝ ለሕግ ማቅረብ፣ አስተማሪ ቅጣቶችንም በመስጠት የሕግንም የበላይነት ማስከበር ይኖርበታል እንጂ በተለመደው ቅላጼ ‹‹እያጣራን ነው›› በሚል ማታለያ አድበስብሶ ማለፍ የለበትም!
7) በመጨረሻም ሁሉም የሀገሪቱ ዜጋና ተቋም ከመንግሥት ጎን ቆሞ የሀገርን ሰላምና የራሱንም ደኅንነት ይጠብቅ ዘንድ እስካሁን ያደረጋቸውን የመከላከል ተግባራት፣ በጥቃት ሂደቱ ውስጥ የተሳተፉ አካላትን እንዲሁም የተወሰዱ ቅጣቶችን ከቀጣይ የማኅበረሰቡ ሚና ጋር ጭምር ለሕዝቡ ግልጽ ማድረግ አለበት፤ ይህ ለሕዝቡ ያለውን ተዓማኒነትና ሕግን ለማስከበርም ያለውን ቁርጠኛ አቋም የሚያረጋግጥበት መልካም አጋጣሚ ነውና፡፡
ቀጣይ ሥጋቶች!
============
✍️ በአንዳንድ ቦታዎች ምንም እንኳን በሀገር ሽማግሌዎች አማካይነት ተፈናቃዮቹ ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ ጥረት ቢደረግም አጥፊዎች የሰፈር ሰዎች ጭምርም ስለሆኑ ሰዎቹ ወደ ቦታቸዉ ለመመለስ ፈቃደኛ አይደሉም፤ ተጨማሪ ጥቃት እንዳይፈጸምባቸው ስለሰጉም በየቦታው ተደብቀው ይገኛሉ! ((አዳባ፣ ምሥ/ሐረርጌ (ጃርሶ)… ይጠቀሳሉ))
✍️ በተጠለሉባቸው አብያተ ክርስቲያናት፣ የጎረቤት ቤቶችና በተሸሸጉባቸው ቦታዎች በቂ የምግብና መጠጥ አቅርቦት ባለመኖሩ በረሃብ ላይ ያሉ አሉ፡፡ ((በተለይ ምሥራቅ ሐረርጌና ምዕ/አርሲ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ))
✍️ በአንዳንድ አከባቢዎች ደግሞ በመንገድ መዘጋት ምክንያት ሌሎች ድጋፍ አድራጊዎች እንደልብ ተንቀሳቅሰው መራዳት አልቻሉም፤ ((እንደ አዳባ ባሉት ቦታዎች))
✍️ በአንዳንድ ቦታዎች ‹‹ከሞትንም እንሙት›› ብለዉ ወደ ቤታቸዉ ቢመለሱም እንኳን ዛቻና ማስፈራራቱ አሁንም ድረስ እንደቀጠለ ነዉ፡፡ ((ለምሳሌ፡- ጭሮ/አሰበ ተፈሪ አከባቢዎች))
✍️ በአርሲ (ጎልጃ) የተፈናቀሉ ሰዎች በአሰላ ዩኒቨርሲቲ መኪና ወደ ቤት ተመልሰው የነበር ቢሆንም  አሁንም ግን በፍራቻ  ዕቃቸዉን እየጫኑ መሆናቸው ታውቋል፤ በዝዋይ ዱግዳ ደግሞ ዳግም ጥቃት በመፍራት አጥቂዎቹን ለመጠቆም ፈርተዋል፡፡
✍️ በሁሉም አከባቢዎች በተለይ የመከላከያ ኃይል ከቦታዎቹ ከወጣ ጥቃቱ ተባብሶ ሊቀጥል እንደሚችል ተሰግቷል፡፡ ((በአርሲ አሳሳ 350 ሰዎች ፈርተው ከአከባቢው ወጥተው አሁን ቢመለሱም አሁንም ግን ከሥጋት አልወጡም))
✍️ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅራት ምዕመናኑን ከጥቃት
ለመከላከልም ሆነ ከጥቃቱ በኋላ መልሶ ለማቋቋም እንቅስቃሴ እያደረጉ አለመሆናቸው ሌላኛው ጉዳይ ነው ((የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ለዚህ ዐቢይ ተጠቃሽ ነው))፡፡
ማስታወሻ፡- በአጥቂዎቹ የተፈጸሙ አንዳንድ ጸያፍ ድርጊቶችንና በመንግሥት አካላት እየተደረጉ ያሉ ግልጽ ጫናዎችን በተመለከተ ተጨባጭ ማስረጃ ጭምር በእጃችን ቢኖርም ለሰዎቹ ደኅንነት ሲባል ትክክለኛ ቦታዎችን ከመጥቀስና ማስረጃዎቹንም ከማቅረብ መቆጠባችን እንዲታወቅልን እንፈልጋለን!
በአጠቃላይ፡- በተለያዩ አከባቢዎች የሚከሰቱትን ችግሮች ሰበብ በማድረግ ኦርቶዶክስን ከኦሮምያ ውስጥ ለማጥፋት የሚደረገው እንቅስቃሴ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል! እንደ እውነቱ ‹‹ኦርቶዶክስን ከኦሮምያ ማጽዳት›› በሚል መፈክር በአክራሪ ሙስሊሞች የሚደረገውን ሤራ መንግሥት ፈጽሞ አያውቅም ብሎ ለመገመት ይከብዳል፡፡ ካወቀ ደግሞ ‹‹ለምን ዝም ብሎ ማየትን መረጠ? ይህንን ዒላማ የሚደግፍ እስኪያስመስለው ድረስስ ለምን ጉዳዩን ቸል አለው? የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንና ኦርቶዶክሳውያንን ትእግሥትና የሀገር ማረጋጋት ሚናስ ለምን እንደ ፍርሃት ተቆጠረ?›› ሲሉ የሚጠይቁ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ጀዋር ተከበበ ተብሎ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትን ከብቦ ማጋየት፣ በሐጫሉ ሞት በማመካኘት ኦርቶዶክሳውያንን በአሰቃቂ ሁኔታ መጨፍጨፍ፣ የአንድን ሰው ቀብር ሥነ ሥርዓት ከለላ በማድረግም በኦሮምያ ምድር ኦርቶዶክስን ለመቅበር የሚደረገው የአክራሪነት ተልእኮ ‹‹ቁጭ ብለው የሰቀሉት ቆሞ ለማውረድ ይቸግራል›› የሚለውን እንዳያስተርት ሊታሰብበት ይገባል እንላለን!!!
የሞቱ ወገኖቻችንን ነፍስ ይማርልን፤ የሰማዕታትንም ዋጋ ያድልልን!!!
አውነትን በመግለጥና ሀሰትን በማጋለጥ የሀገርን ሰላምና የሕዝብን አንድነት ለመጠበቅ እንትጋ!
Filed in: Amharic