>

ከ200 ዓመት በላይ ያስቆጠረውና በኒዮርክ ከተማ ሀርለም ውስጥ የሚገኘው የአቢሲኒያን መጥምቃዊ ቤተክርስቲያን... (ሳሚ ዮሴፍ)

ከ200 ዓመት በላይ ያስቆጠረውና በኒዮርክ ከተማ ሀርለም ውስጥ የሚገኘው የአቢሲኒያን መጥምቃዊ ቤተክርስቲያን…

ሳሚ ዮሴፍ
Abissinia Babtist Church
ስለአመሠራረቱ የቀድሞው የቤተክርስቲያኑ የረዥም ዓመታት መሪና የዩ.ኤ.ስ. መንግሥት የኮንግረስ አባል የነበረው አዳም ክሌይተን ፓወል-(ልጅየው JR) በአጭሩ እንዲህ ጽፏል…
“በቶማስ ጄፈርሰን (3ኛው ፕሬዚዳንት) የመጨረሻ የሥልጣን ዘመን ላይ ዛሬ ኢትዮጵያ ከምትባለው ሀገር ከአቢሲኒያ የመጡና በኒዮርክ የነበሩ ነጋዴዎች በዕለተ ሰንበት ማለዳ ወደ ቤተክርስቲያን መሄድ ፈለጉ። ቅርብ ከነበረውና በጎልድ ስትሪት ላይ ከሚገኘው የከተማው ብቸኛ የባፕቲስት ቤተክርስቲያን ሄዱ። በአጋጣሚ አቢሲኒያ በዓለም ላይ ጥንታዊ የክርስቲያን ሀገር ነች። አንግሎ ሳክሶኖች ለፀጉራቸው ማበጠሪያ መጠቀም ከመጀመራቸው ብዙ ዓመታት በፊት ማንበብና መፃፍ ከመጀመራቸውም እጅግ ቀደም ብሎ አቢሲኒያኖች የክርስትና ተቋም ተቀብለውና ባሕል አዳብረው ነበር።
“እነኝህ ሰዎች በሰንበት ለአምልኮ ከመጥምቋዊው (ከባፕቲስቱ) ቤተክርስቲያን ሲደርሱ ወዲያውኑ ወደባርያ መቀመጫ ቆጥ ተወሰዱ። ባለፀጋ፣ አዋቂዎች፣ የዓለም ተጓዦች፣ ኩሩዎችና በአዳራሹ ከነበሩት ከማናቸውም ሰዎች ያልተናነሰ የኃይማኖት ፍልስፍና የነበራቸው እነኝህ ሰብዓዊ ፍጡሮች በአድራጎቱ አዝነው በተቃውሞ ጥለው ወጡ።
“ከዚያም የራሳቸውን ገንዘብ አሰባስበው በሰኔ 1808 እ.ኤ.አ በወርዝ ስትሪት ላይ ቤት በመግዛት የአቢሲኒያን ባፕቲስት ቤተክርስቲያን መሠረቱ። ይህም በኒውዮርክ በረዥም ዕድሜው 2ኛው የባፕቲስት ቤተክርስቲያን በአጠቃላዩ በሰሜኑ አሜሪካ ክፍል ደግሞ ከዘረኝነት ነፃ የሆነ የመጀመሪያው ባፕቲስት ቤተክርስቲያን ለመሆን በቃ…”
Adam Clayton Powell (Jr.) Adam by Adam pp.46-47
የሚገርመው ነገር የአቢሲኒያን ባፕቲስት ቤተክርስቲያን መስራቾች በ1809 ለኒውዮርክ ማዘጋጃ ቤት ባስገቡት የፈቃድ ምዝገባና የምሥረታ ማፀደቂያ ሰነድ ላይ “አቢሲኒያን” የሚለው መጠሪያ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንኳ ሲተላለፍ እንዳይለወጥ የትኛውም መጪ ትውልድ ስሙን የመለወጥ ሥልጣን እንደሌለው መሥራቾቹ በጉባዔ መወሰናቸውና ይህም ድንጋጌ ከምዝገባና የፈቃድ ማጽደቂያው ሠነድ ጋር አብሮ ተመዝግቦ መገኘቱ ነው።
“አበሾቹ” (Abyssinians) የተባሉት ባህረኛ ነጋዴዎች የታሪካዊው ቤተክርስቲያን መሥራቾች በ1809 ያውም አብርሃም ሊንከን በተወለዱበት ዓመት የነፃነት ተምሳሌት ሆኖ የቆየውን የጥቁሮች ቤተክርስቲያን በኒውዮርክ ሲመሠርቱ ለማዘጋጃ ቤቱ ፍርድ ቤት (Municipal Court of New York) የተሰጣቸው የማፀደቂያ ውሳኔና የምሥረታ መዝገብ አሁን ድረስ በማዘጋጃ ቤቱ ቤተ መዛግብት (Archive) ውስጥ ይገኛል።
#ክብርለአባቶቻችን
Filed in: Amharic