>

"ቁስልን ማመርቀዝ እና አመርቅዞ እንዳይድን ማድረግ የታሪክ አላማ አይደለም!!!"(የታሪክ መምህር እና ደራሲ ታዬ ቦጋለ)

“ቁስልን ማመርቀዝ እና አመርቅዞ እንዳይድን ማድረግ የታሪክ አላማ አይደለም!!!”

 የታሪክ መምህር እና ደራሲ ታዬ ቦጋለ
ቁስልን መጫር፣ ጭሮ መቧጨር፣ ቧጭሮ ማቁሰል፣ አቁስሎ ማመርቀዝ እና አመርቅዞ እንዳይድን ማድረግ የታሪክ አላማ አይደለም ሲሉ የታሪክ መምህር እና ደራሲ ታዬ ቦጋለ ገለጹ። ህወሓት/ ትህነግ ስልጣን ዘመኑን ለማርዘም አማራና ኦሮሞን እንደማህበረሰብ ማጋጨትን እንደ አንድ ስልት አድርጎ ይዞት እንደነበረም አስታወቁ።
የታሪክ መምህር እና ደራሲ ታዬ ቦጋለ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ቁስልን መጫር፣ ጭሮ መቧጨር፣ ቧጭሮ ማቁሰል፣ አቁስሎ ማመርቀዝ እና አመርቅዞ እንዳይድን ማድረግ የታሪክ አላማ አይደለም፤ የታሪክ ትርክቶች ከታሪክ ዓላማ ውጪ ከሆኑ የታሪክ ትርክቶች ሳይሆኑ የፖለቲካ ፈጠራ ናቸው ብለዋል።
የፖለቲካ ፈጠራ የታሪክ ትርክቶቹ መነሻቸው አገር ማፍረስ እና በማህበረሰብ መካከል ግጭት መፍጠር እንጂ ለአሁኑ ትውልድ ዳቦ አይሆኑም ያሉት አቶ ታዬ ቦጋለ፤ የታሪክ ትምህርት ዓላማው ያለፈውን ለማጥራት፣ ዛሬን በጥሩ መሰረት ላይ ለማነጽ እና ነገን በብሩህ ሁኔታ ለመገንባት መሆኑንም ተናግረዋል።
“ህወሓት/ ትህነግ ሲቋቋም በጥቂቶች የተመሰረተው ቡድን ነው። ይሄ ስርዓት ውስብስብ ባህሪያት ያሉት ነው። በፖለቲካ ቋንቋ መግለጽ ያስቸግራል። አንደኛው መለስ ዜናዊ በነበረበት ረጅም ጊዜ በአንድ በኩል ሞኖክራሲ ነበር። ሞኖክራሲ ማለት የአንድ ሰው አምባገነን አገዛዝ ነው። የኢኮኖሚ ባህሪያቱን ስንመለከት ደግሞ አሪስቶክራሲ (ኦሊጋርኪ) ነው። የጥቂቶች የበላይነት የሚንጸባረቅበት ስርዓት ነው። ይሄ ስርዓት በባህሪው መቆየት እንደማይችል፣ አምባገነን እንደሆነ፣ በፍርሃት የተከበበ ስሜት ይዞ ስለተነሳ እንዲቆም አማራና ኦሮሞን እንደማህበረሰብ ማጋጨትን አንድ ስልት አድርጎ ይዞ ነበር” ብለዋል ።
አማራውን ትምክህተኛ፣ ኦሮሞን ጠባብ፣ ደቡቡን የስብዕና መሸርሸር ያለበት፣ አርብቶ አደር አካባቢ፤ ሱማሌ፣ አፋር፣ ቤንሻንጉል፣ ጋምቤላ፣ ሐረሪን ደግሞ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ለመሸከም የሚያስችል ቁመና የሌላቸው አጋር ሆነው የሚቀጥሉ በማድረግ ስርዓቱ እንዲቀጥል ማድረጉን አመልክተዋል።
ምሁራንን የቀለም አብዮተኞች፣ የሻዕቢያ ተላላኪዎች፣ የግብጽ ተላላኪዎች፣ ወጣቱን የጎዳና ላይ ነውጠኞች በሚል እያንዳንዱ ታፔላ ተለጥፎበት እንደነበረም አስታውሰዋል። ዛሬም የምናየው የግጭት ምንጭ ይሄንን ነው። ሲዳማን ከወላይታ ጋር፣ ስልጢን ከጉራጌ ጋር ከመጀመሪያው ከመለያየት ጀምሮ ሰዎች አብረው ተያይዘው እንዳያድጉ በማድረግ እስከ ሰፈር ድረስ የከፋፍሎ ግዛት ስልት እንደነበረው ገልጸዋል።
ህወሓት በሰፊው ስልጣን ላይ እንድትቆይ በአለም ታሪክ ውስጥ ተፈጽመው የማይታወቁ ግን አስከፊ ወንጀሎች ተፈጽመዋል ሲሉም ተናግረዋል። ለምሳሌ ህወሓት የዘር ጭፍጨፋ አድርጓል። መንግስታዊ ሽብርተ ኝነትን ፈጽሟል። የተለያዩ ማህበረሰቦችን የማውረድ ነገር ተጠቅሟል። ከፋፍሎ መግዛትን አድርጓል። ያልተገቡ ጨረታዎች፣ የባንክ ብድሮች፣ የተደራጁ ዘረፋዎችን አካሂደዋል ሲሉም ከሰዋል።
በማረሚያ ቤት በሰው ልጅ ላይ ሊፈጸም ይችላል ብለን የማናስበው ጥፍር መንቀል፣ የወንድ ብልት ላይ ኮዳ ማንጠልጠል፣ በሴቶች ማህጸን ብረት መክተት፣ በወንዶች ብልት ጫፍ ብረት መክተት፣ ገልብጦ መግረፍና የመሳሰሉትን እጅግ አስከፊ ነገሮችን ማድረጉንም ገልጸዋል።
የኦሮሞ ፖለቲከኞችም ሁለቱን ህዝቦች በማጋጨት በግርግር ወደ ስልጣን መምጣት እንደሚፈልጉ አመልክ ተው፣ ግብጽ የአባይን አጠቃላይ ግድብና የአባይ ተጠቃሚነታችንን ማፍረስ የምትችለው ሁለቱን በማጋጨት እንደሆነም ጠቁመዋል።
ወደ አናርኪ ከማምራት በውይይት የአመለካከት ለውጥ ማምጣት የመጀመሪያ መፍትሄ ማድረግ ጠቃሚ መሆኑንም አመልክተዋል። የወንድማማችነት ‹‹እርታ ልርታ›› ስሜት በሚገባ መዳበር ይገባዋልም ብለዋል።
“ለችግሮቻችን መፍትሄ የሚሆነው አባቶቻችን የኖሩ በትን ፍቅር መመለስ ነው። በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ መወያየት ነው። የኦሮሞ ጥቅም የት ጋር ነው የተነካው? የአማራ ጥቅም የት ጋር ነው የተጎዳው? የሶማሌ ጥቅም የት ጋር ነው ያነሰው? የሌላው የት ነው እንጀራው በአንድ በኩል አይወፍር ብሎ ቁጭ ብሎ በሰከነ መንገድ መወያየት ነው” ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2012
ዘላለም ግዛው
Filed in: Amharic