>

“ባሕታውያን” እና "አጥማቂያን" በኢትዮጵያ ቤ/ክ - በወፍ በረር ቅኝት...!!! (መ/ር ቀሲስ  ንዋይ ካሳሁን)                

ባሕታውያን” እና “አጥማቂያን” በኢትዮጵያ ቤ/ክ – በወፍ በረር ቅኝት…!!!

  መ/ር ቀሲስ  ንዋይ ካሳሁን 
ክፍል አንድ

ባሕታዊ ማለት ራሱን ለቅድስና ለተጋድሎ አዘጋጅቶ ከላመ፤ ከጣመ ተቆጥቦ መኖርን የሚጠይቅ በገዛ ፈቃድ የሚደረግ የክርስትና ኑሮ ዘይቤ ነው። ሥርዓተ ብሕትውና የተጀመረው የአዳም ሰባተኛ በሆነው በሔኖክ ነው። በብሉይ ኪዳን እነ ኤልያስ፡ በጌታ መምጫ መንገድ ጠራጊ የነበረው ዮሐንስ ለበረሃ ሕይወት ወይንም ምነና ተጠቃሽ ናቸው። የሰዎቹ መነሳት  ብቻ ሳይሆን ምነናን በተግባር አሳይተው ያለፉም ናቸው።
ባሕታዊ ወይም ብሕትውና ቀላል ሕይወት አይደለም። ራስን ለእግዚአብሔር መንግስት ጃንደራባ አድርጎ ማቅረብ ስለሆነ። ቅዱስ ጳውሎስ “ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ”   ያለውን ኑሮ የኖሩቱ ናቸው። ይሕ መንፈሳዊ ሕይወት ከምናስበው በላይ ቅድስናን የተላበሰ ትልቅ ገድል፤ ትሩፋት ያለበት ነው።
 በክርስትና ሕይወት ምነና ከሶርያ ተነስቶ ወደ ግብጽ በረሃ እያደገ የመጣ የእንጦንስና የመቃርስ ኑሮ ነው። ምንኩስናን ከብሕትውና አስተባብረው የኖሩ። ወደ ኢትዮጵያም ገብቶ ገዳማዊነት፤ ምንኩስና እየሰፋ ሔደ። ብሕትውና ብዙውን የገዳም ኑሮ ነው። መንኖ ጥሪት። (ሐብት ንብረት መናቅ)
በዚህ የበረሃ ኑሮ ሁለት አይነት አኗኗር ተጀመረ። አንዱ ምንኩስና ማናኔ ሲሆን ሌላው ብህትውና ነው። ኑሮው እና አላማው ተመሳሳይ ሲሆንም ብሕትውና ለብቻ መሆንን ይዘወተራል። ለምሳሌ ዋሻ ውስጥ መሰወር ግንድ ወይም ዛፍ ላይ ወጥቶ ሳይወርዱ መኖርን ይመርጡ ነበር። በወቅቱ ምግብ ባለመመገብ ውሓ ባለመጠጣት ያሳልፉ እና ይሞቱም ስለነበር በምነናው ሕይወት፡ ራስን በምግብ እና ውሐ ማጣት መሞት ትክክል አይደለም በሚል የኑሮ ዘይቤው ብዙም አልተደገፈም። በተለይ (ኤሴያውያን የሚባሉ ቡድኖች የሚመሩት የነበረ ሕይወት)። ሊቁ አርጌንስም ከሊቅነት ባሻገር ምናኔ ትልቁ መታወቂያው ነበር። በዚህም ራሱን ጀንደረባ አድርጎ ስለ ነበር ከተነቀፈበት ተግባር አንዱ ይሕ ነበር።
ብሕትውያን በቤተክርስቲያን የቆየ ሕይወት ሲሆን። ከምናኔ ባሻገር እግዚአብሔር ሲልካቸው  ከበረሃ እንደ ኤልያስ ብቅ እያሉ ለንጉሡም ፤ለካህናቱም መልክት አስተላልፈው ወደ በዓታቸው ይመለሳሉ። ታድያ ይህንን ተገን አድርገው ባሕታውያን ወደ ከተማ መግባት የተጀመረው ቀደም ብሎ እንደ ሆነ ቆየት ያሉ መጻሕፍትን ስንመለከት ጠቋሚ ናቸው።
 አጼ ኃ/ሥላሴ በአንድ ወቅት “አንድ ባሕታዊ ለንጉሡ መልእክት አለኝ ተልኬ ነው አስገቡኝ ይላል። ሄደው ለንጉሡ አንድ ባሕታዊ መልእክት አለኝ ልግባ ይላል ብለው ጠባቂዎቹ ይናገራሉ በዚህም ንጉሡ “እውነተኛ ባሕታውያንን እንኳን መጥተው ሔደንም አናገኛቸውም” ብለው መለሱ ይባላል። ብለው መምሕራችን እንደነገሩን አስታውሳለሁ። ለመነሻ ይህንን ካልኩ ወደ ዋናው ኅሳቤ ልመለስ።
የዚህ ጽሕሁፍ ዓላማ ስለ ምናኔ ወይም ብሕትውና ጥልቅ ትምህርት መስጠት ሳይሆን   አሁን በተለይም ከ 1984  ዓ.ም ወዲህ በኢት ዮጵያ ቤተክርስቲያን ባሕታውያን የሚታወቁበት መንገድ ከመሰረታዊው የብሕትውና ሕይወት በማይገናኝ መልኩ ፈር የለቀቀ ሆኗል።
 በዚህም ዛሬ ላይ  “ባሕታውያን፤ አጥማቂ” ነን በማለት ሕዝቡን ላልተፈለገ ውዝግብ  ቤተክርስቲያኒቱን ለሁከት ሲዳርጉ ይታያል። እስቲ በእኛው ዘመን የተነሱትን ጥቂቶችን ለአብነት እንመልከት፦
ባሕታዊ” ገብረ መስቀል
የመንግስትን ለውጥ ተከትሎ ብቅ ያሉ ሲሆን በወቅቱ ይበርዳል ያልተባለ ንቅናቄ በማድረግ ለአመታት ሕዝብ ያሰለፉ፤ብዙ አመጾችን ያስተባበሩ ነበር። ሑሌም ቢሆን “ባሕታውያን” ነን የሚሉት ሰዎች ምንም ያልተከሰተን ነገር በማንሳት ሰውን ቀልብ መያዥ፤ መጣልህ ትጠፋለህ፤ ተበላህ የሚል ውዥንብር በመንዛት ይታወቃሉ።  ጠጉር አርዝመው የኢትዮጲያን ባንዲራ አስረው በመንግስትም ይሁን በተለይ በቤተክህነቱ ላይ ዘመቻ ከፍተው በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሰው ስራውን ትቶ ቀን ከሌሊት ጫማ አውልቆ ተከትሎ ነበር።
 በወቅቱ የባሕታዊ ገ/መስቀልን ፎቶና መልእክት ያልያዘ መጽሔት አይሸጥም የተባለ ይመስል ሁሉም በእርሳቸው ቃል ምልልስና መልእክት የተሞላ እንደ ነበር የቆየ መጽሔት ካየን ማስረጃ ይሆናል።  በቤተክርስቲያን ሕገ ወጥ የሆነውን አካሄድ ብትቃወምም ማንም ባለ መስማት እንደውም የወንጌል ጠላት እንደ ሆነች በመቁጠር በቤተክርስቲያን ላይ ድንጋይ የሚወረውሩ ተከታዮች አፍርተው ነበር።
መላእክት መብራት ሲያበሩላቸው ያድራሉ፤ ምግብም ከሰማየ ሰማያት በመና መልክ ይመጣላቸዋል፤ እንደተክልዬ ሰባት ክንፍ ሊያወጡ አራቱን አብቅለው ሦስቱ እያጎነቆሉ ነው … ተብሎላቸውም ነበር። ድንቄም ክንፍ። ከዘፍጥረት እስከ ራዕይ ተገለጠልኝ አለ። ማወናበዱን ተያያዘው።
መጨረሻው ግን የሚፈልጉትን ካገኙ በኋላ”ባሕታዊው”  ያጠመቃትን ፈረንጅ – ወለተ መስቀል “ጆንሃንሰን” ሰጠችው በተባለው ላንድክሩዘር እየተምነሸነሸ ሚስቱን አግብቶ ዓለሙን ይቀጭ ጀመር  መቅጨቱ አያስቀናም  በእግዚአብሔር ስም ማጭበርበሩ እንጂ። ቀድሞ የወለደችለትን ሴት የቤት ሰራተኛ አድርጎ ሌላዋን
በቅርብ ያገኟትን ሴትም  አገቡ።
 ቀጨኔ መድኅኔ ዓለም አካባቢ ግለሰብ ሰጥቷቸዋል የተባለ ቤት ይዘው ኑሮ መሰረቱ። ሕዝብም ተበተነ። የሚገርመው አመታትን ዝም ብለው ጉዳዩ ከተረሳ በኋላ ስምም ቀይረው “መምህር” ገ/መስቀል ተበለው ብቅ ብለው በየመድረኩ ውር ውር ሲሉ ይታየል። ቅዱስ ጳውሎስ ሳስተምር መምህራን ለተማሪዎች የምንሰጠውን የትምህርት ጽኁፍ(handout) በማሰባብሰ የራሳቸው አድርገው እንዳሳተሙት በተማሪዎቻችን አማካኝነት ሰምተናል።
ይህ ብቻ ሳይሆን አዚያው ቤታቸው ውስጥ ከቤተክርስቲያን ያልተናነሰ አዳራሽ አሰርተው ጉባኤ፤ የማሕበር ጸሎት  አለ። ልብሰ ተክህኖ ተለብሶ እጣን ይታጠናል። ይህንንም ማንም ምንም ሳይል እንደ ቀልድ ዝም ተብሏል። የቀጠለ ስህተት።
ባሕታዊ አምሃ ኢየሱስ
ባሕታዊ አምሃ ኢየሱስም የዚያው ወቅት ባሕታዊ ሲሆኑ።  በተለይም በዲላ በነበረው የቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁከት ትልቁን ሚና ይዘው ነበር።   በዚህም ወቅት እነ በጋሻው ባሕታዊውን በትከቻ ላይ ተሸክመው “አምሃ አንበሳ” የሚለውን ጭፈራ እየጨፈሩ በአጃቸው ባንዲራ አስረው ቤተክርስቲያኑን ይዞሩም ነበር። ይህ ነበር የነበጉም መነሻ። በኋላም በጎንደር አካባቢ መንግስት የሚፈጽመው ትክክል አይደለም በሚለው ትምሕርት ታስረው ትልቅ መከራን እንደተቀበሉ ይታወቃል። አራት አመት በጨለማ ቤት። አሁን የጎላ እንቅስቃሴም አይታዩም። መንግስት በህዝቡ ላይ የሚፈጽመውን ግፍ በድፍረት ተው የሚል ባህታዊ ሲገኝ በርታ መባል ይገባዋል። መገስጽ ነውና።
“ባህታዊ” ሶፎንያስ 
እንዲሁ ጡጉራቸውን አሳድገው ከተነሱት መካከል ናቸው። የጎላ እንቅስቃሴ ያደረጉ አይመስለኝም። ከሌሎቹ ለየት የሚሉት ወንጌልን በአግባብ ለመስበክ የሚሞክሩ ናቸው። በኋላም ከኛው ከወጣቱቹ ጋር ተሰልፈው ቤተክህነቱ በሚሰጣቸው መድረክና ቦታ ማገልገል ላይ ናቸው። ባሕታዊ የሚለውን ሕይወትም እና ስም ግን የሚያስኬድ አይመስለኝም። እርሳቸውም ስለ ጀመሩት እንጂ ብዙም ምየሚወዱት አይመስልም። የላመ የጣፈጠ ከሕዝብ ጋር እየተኖራ በደሞዝ ተቀጥሮ ብሕትውና የለም። ከተማ ሆኖ የብሕትውና  ኖሮ አይቻልም የሚል ምልከታ ግን የለኝም።  ሁሉም ባሕታዊ ነኝ ባዮች ያንጀረገጉት  ጠጉር እርቲፊሻል ጠጉር (ዊግ) እንጂ እውነት አለመሆኑን እወቁ።
 አርቲስት “ባሕታዊ” ጀማነሽ ሰሎሞን
ሁሉም ሰው የሚያከብራት የሚወዳት ሙያዋን በእውቀት የምትኖር ምርጥ ኢትዮጵያዊ አርቲስት ነበረች። ምክንያቱ ባልታውቀ መልኩ አዲስ የመጣ የሃይማኖት አስተሳሰብ ነቢዩ አልያስ ጳግሜ 1 ቀን 2003 ዓ.ም ተገልጧል፤ በሚል ከውትድርና የተመለሰ አንድ የከተማ ጩሉሌ ጆቢራ አባ ዮሴፍ ነኝ ባይን ተከትላ ባላት እውቅና ስዎችን አስከተለች። ሰዎችም ተከተሏት። ጀማነሽ ፡ሃይማኖታችን ተዋህዶ እንጂ ኦርቶዶክስ አትባልም፤ኤልያስ በዚህ ዘመን ተገልጧል።
 ጆቢራው “ባህታዊ” ተዋህዶን ሲተነትን ተዋህዶን የተናገረው ኤልያስ ነው፡ ካለ በኋላ፤ ተዋህዶ ማለት ሥላሴ ሶስት ሲሆን አንድ ብሎ ማመን ነው ይላል። እንደው የሚባለውን እንኳ በቅጡ ሰምቶ ቢሆን መልካም። ሃይማኖት ሰምተው የሚያወሩት ሳይሆን ተረድቶ የሚያስረዱት ነው። ትዝ ያለንን የምንቀባጥርበት ፍልስፍና አይደለም፤ ግምትም አይደለም።
 እሁድ ሰንበት አይደለም ውሸት ነው በሚል ማሕበረ ሥላሴ ዘደቂቀ ኤልያስ የሚል ማህበር አቋቋመው ዘመቻ ከፍተው ዛሬ በየገዳማቱ እየዞሩ ስንቱን እንዳሚያሳስቱ ገና ያልተገነበዘብን ብዙ ከመሆናቸውም በላይ ተምረዋል ከሚባሉት አስከ ተረንተራው ሕዝብ ድረስ እየተከተላቸው ያለ ይሕው መፍቀሬ ባህታውያን ሕዝብ ነው።
“ማርያም  ነኝ” ባይዋ ሴት
ይህች ሴት መነሻዋ   ከየት እንደ ሆነ አላውቅም መመርመር ያስፈልጋል። ቁም ነገሩ “አለምን ለማዳን መጥቻለው” ባይ ናት። በደብረ ሊባሎስ ገዳም በመገኘት ትልቅ ሁከት እንደ ነበር ትዝታችን ነበር።  የተነሳነው ከአንጦጦ ነው ስባት አመት ሆኖናል። “ድንግል ማርያም ተገለጠችልን ፣ ገብርኤል ገለጠልን እናንተንም 3 ቀን ሱባኤ ብትገቡ ትገለጥላችኋለች፤ እሳተ መለኮት ተሸክማላች፤ ተሰዳላች፡ እንደ መላእክት ትበራለች”:-
የሚሉ አኩያን፤ ሃሳውያን ተነስተው በአደባባይ ሲዘላንብዱ ያየነው በዚሁ ዘመናችን ነው።  ይህም ሆኖ ተከታይ ነበራት።
 ከደብረ ሊባኖስ ግርግር ተፈጥሮ የአካባቢው ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሏት ነበር።አሁን የደረሰችበትን ባልውቅም። እርሷም እንዲሁ ተከታይ ነበራት።
“መምህር” ግርማ ወንድሙ
ግለ ታሪካቸው ላይ ማተኮር አልሻም። ቤተ ክርስቲያን ለሚያስተምር፤ ተምሮ ለሚካን፤ ለሚቀድስ፤ ለሚያጠምቅ ለሚመነኩስ ሥርዓት ሰርታለች። ችሎታ፤ “ፀጋ ” አለኝ የሚል ሁሉ ዘሎ እንደ አይድል ሾው፡ ወይም አሜሪካን ታለንት ሾው ይመስል ወደ መድረክ ብቅ የሚልባት አይደለችም። ዛሬ ሰዉ የሚያየው የሚፈውሰውን ሰው ነው። ተአምር ብቻ የሚማርከው፤ ሕሊናቸውን የሚያሸንፈው እርሱ ነው። እንዴት በምን የሚለውን ለመመርመር የቤተ ክርስቲያንን ትምህርትም ግንዛቤም ስለሌለው ያንን መመርመርም አይፈልግም።
ባየው ነገር ያምናል ከዚያ የፈለገውን ዋጋ ይከፍላል። ሽንጡን ገትሮ ይከራከራል። አጥማቂ ወይም ሞት ይላል። ለነ በጋሻውም ይሀ ነበር የነበረው። ጊዜው እስኪደርስ ድረስ።
 ሰው በጠበል ሲፈወስ በመጽሐፍ ቅዱስም በቤተ ክርስቲያንም እንግዳ ነገር አይደለም። ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵያውያንን የፈውስ  ቀዳሚዋ ሆስፒታል ናት። እነዚህ የፈውስ ቦታዎች    በኢትዮጵያውያን ዘንድ የታወቁ ናቸው። ሲፈውሱ ኖረዋልም። ዛሬ በቅዱስ ዮሐንስ ጠበል (ሸንኮራ)፤ ጻድቃኔ ማርያም ፤ እንጦጦ ኪዳነ ምሕረት፤ ስናይ የፈውስ ቦታዎች ናቸው። በነዚህ ቦታዎች ሁሉ የሚያጠምቁ አባቶች አሉ። አንድም ሰው ግን አባ አከሌ ፈወሱኝ የሚል የለም። እመቤቴ ፈወሰችኝ ፤ ጻድቁ ፈወሰኝ እንጂ።
 ዛሬ አጥማቂዎች መጠየቅ ያለብን ብዙ ጥያቄዎች አሉን።
ስለ መናፍስት አሰራር ማወቅ፡ 
 
1.  ቅድስና ወይም ጻጋ የሌለው ተአምር አድራጊ
በቅዱሳት መጻሕፍት በገድል በድርሳናት ስለ ፈውስ ብዙ ተጠቅሷል። በክርስትና ውስጥ በተለየ የመንፈሳዊነት፤ የገዳማዊነት  በተአምር አድራጊነት፤ የተመሰከረለት ሕይወት ሳይኖረው በፈውስ የታውቀ ጻድቅ፤ ወይም ቅዱስ  አልነበረም። አንድም ቦታ የለም። አንድም ቦታ ፈዋሽ ስለመሆናቸው ማስታወቂያ አያስነግሩም፤ እኔ ፈወስኩ የሚሉ አባቶች የሉንም አልነበሩንም። ዛሬ ግን አለምን የሞላው ሰው ወደ ግለሰቦች አይኑን አዙሯል።
2. ተአምር  የወንጌልን ትምሕርት ለማጽናት እንጂ መሰረታዊ ጉዳይ አይደለም።
 ተአምር ማድረግ የአንድ ሰው እውነተኛነትን አያረጋግጥም። የፈርዖን ጠንቋዮች እንደ ሙሴ ሁሉ በትራቸውምን አባብ አድርገዋል። ተአምር እውነት ከሆነ ለምን አናምናቸውም? ዘጸ. 7:9 ። ሳኦል ወደ ጠንቋይዋ ሴት በመሔድ ሳሙኤልን አስነሺልኝ በማለት ይጠቃታል። እርሷም ሳሙኤልን ጠርታ አስነስታ ለሳኦል አሳየችው ይላል። ታድያ ጠንቋይ ልንከተል ነው?። 1ሳሙ. 28:8
ተአምራትን እንደ እውነተኛነት ማሳያ ማየት ሞኝነት ነው። ጌታ ስለ ነጣቂ ተኩላዎች ተግባር ሲያስተምር በግራ እንዲቆሙ የፈረደባቸው ሰዎች አኮ የሰጡት ምላሽ ” በዚያ ቀን ብዙዎች፦ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል።” የሚል ነው። ጌታ ግን አላውቃችሁም የሚል ምላሽ ነበር የሰጣቸው። እነዚህ ሰዎች አኮ ትንቢት ተናግረዋል፤ አጋንንት አውጥተዋል፤ ፈውሰዋል። ግን እውነተኛነታቸውን አልተመሰከረላቸውም።
3.  መናፍስትን ምስክር ማድረግ
በብዙ ማስል ወድምጽ(ቪዲዮ) ላይ እንደምናየው መናፍስቱን ስንት ናችሁ? እንማን ናችሁ፤ ማነው የስመተተብህ፤ምን ትሰሩ ነበር፡ ማን ታስደርጉት ነበር? …..ወዘተ። እስቲ ይህንን ያደረገው ማን ነው? የሚል ጥያቄ ያቀርቡለታል እሱም ይመልሳል። ቡዳ ነኝ እገሊት በላችኝ፤ እገሌ በላኝ  ይላል። ይህንን ምስክር ተቀብሎ ሌላው በልቶኛል፤ በልታኛለች ባለው ላይ ቂም ይይዛል። ጠቡ ይቀጥላል፡፤ ሰይጣን መቼ ነው የእውነት ምስክር የሆነው።    “የሐሰት አባት” ተባለ እንጂ። ጌታችንም “አንተ እርኩስ መንፈስ ውጣ” ነበር ያለው። ገድለ ጊዮርጊስን  ገድለ ተከላ ሃይማኖትን እንመልከት “በጌታዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ውጣ” ነው ያለው ቅዱስ ጊዮርጊስ። ሰይታንን ምስክርነት አልጠየቀውም።
4. ዝና 
ዛሬ አጥማቂ ተብየዎቹ ዝናቸው በዓለም ናኝቷል። ይምጡልን በዝቷል። ቅዱሳን ገድላትን ስናነብ ግን ከዚህ በተገላቢጦሽ አናነባላን። አባ ተክለ ሐይማኖት ጻድቁ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማለትም ከጻድቁ አባ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም የሔዱት በሚያደርጉት ተአምር ምክንያት ስማቸው ከፍ በማለቱ፤ ብዙ ሰዎች በመሰብሰባቸው ምክንያት ነው። በማለት ዲ/ን ዳናኤል ክብረት በጽኁፉ ገልጦታል።፡ዛሬ በተቃራኒው ገባሬ መንክራት ፤ መላከ መንክራት፤ ፋዋሴ ዱያን እየተባሉ ስም እያስለጠፉ፤ መጻፍ እየጻፉ ሲዲ እየሸጡ ፓስተር እየስለጠፉ ያኖራሉ። ሲዲ ለመግዛት እና የመናፍስትን ጫጫታ ለመስማት ብዙ ብር ሲያወጡ፡ ገድል እና ድርሳን ገዝተው ለማንበብ ለመጸለይ ግን አይመጣላችውም። ምክንያቱም ሰው እና ተአምር ላይ እንጂ መሰረታዊው ትምህርት ላይ  ግድ የላቸውም።
5. ባላ መናፍስቱ :- የሥላሴን፤ የድንግል ማርያምን የመላእክቱን፤ ስም ሲጠራ ምንም ችግር የለበትም።
ጥራ ሲባል ይጠራል። አጥማቂውን ሰውዬ ግርማ ለማለት፤  ስም ለመጥራት ግን “እንቃጠላለን፡ ስምህን መጥራት አንችልም” ይላል፡፤ ጉድ ሳይሰማ….. ይሉሃል ይህ ነው። ከዚሕ የሚከፋው ደግሞ አንዳንዴ የሥላሴን ፡ የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ይጠራና የድንግል ማርያምን ስም  አንጠራም እርሷ ታቃጥለናለች ይላል። ሕዝቡ በእልልታ ይደግፋል። ይሕ ከቤተ ክርስቲያን ትምሕርት ጋር ይጣረሳል። የማን ክብር በልጦ ነው። የሥላሴ ወይስ የድንግል ማርያም። ፈጣሪና ፍጡር። ሰይጣን ምን እየስተማረ እንዳለ እንኳን በውል ያስተዋልን አይመስለንም። በራስ መድረክ በሰይጣን ግብ ማስቆጠር ማለት አይደል።
6. ቅዱሳን አባቶች:-  ታሪካቸውን የሚያስረዳን በጸሎት የተጠቀሙበት መስቀላቸው ልብሳቸው ጥላቸው ሲፈውስ አንብበናል። ቅድስናቸው ለመቋሚያቸው፤ ለመቁጠሪያቸው ለልብሳቸው ሲተርፍ። ዛሬ የፈውሱ ምንጭ መቁጠሪያ ሆኖ መቁጠሪያ ሽያጭ ዋና የገቢ ምንጭ ሆኗል።    “ቅብዓ ቅዱስ” እየተባለ ከመርካቶ የተገዛ ዘይት ሲቸበቸብ እያየን ነው። መቁጠሪያ አእምሮ ሰብስቦ እየቆጠሩ ለመጸለይ በመቁጠር ኅሊና እንዳይበተን ስግደትን ለመቀጠር ያገለግላል እንጂ ስሪቱ ለፈውስ የሚውል አይደለም።
7. በነባር ወይም በተፈጥሮ በፈለቀ ጠበል አለመጠቀም። 
አብዛኞቹ “አጥማቂያን” በአካባቢው አልያ በቤተ ክርስቲያን የፈለቀ ጠበል ካለ በርሱ አያጠምቁም። ራሳቸው ባስቀዱት ጠበል ብቻ ያጠምቃሉ። በጠበሉ ውስጥ ሎሚ የሚጨምቁ አሉ። ዓይን ይውሳል እያሉ ዓይን ውስጥ ይጨምቃሉ።
8. መዕመናን :- እኒህ ሰዎች በእግዚአብሔር ስም በእመቤታችን ስም በመላዕክት ስም ነው የሚፈውሱት ችግሩ ምንድን ነው የሚል የየዋህ ሰው ጥያቄ ያቀርባሉ። ስመ እግዚአብሔርን የጠራ ሁሉ ማነው ትክክል ነው ያለው? በመጽሐፍ ቅዱስ ጌታችንን ስሙን ሲጠሩ ይታያል። እንደውም ጌታ ሆይ፤ የእግዚአብሔር ቅዱስ ብለውታል። ትክክል መስክራችኋል አላላቸውም። ውጣ አለው እንጂ። ” የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ፥ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ።”   ማር. 1፡24 ። ቅዱስ ጳውሎስም በጠንቋያዋ ሴት ላይ ያደረውን መንፈስ ይህንን አይነት የአጋንንት ምስክርነት ቃል ነቅፎታል። ”   የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው ብላ ትጮኽ ነበር።”  ብላ ነበር። ልክ ነሽ አላላትም። ሐዋ.16:17
9. ፈውስና ጥቅም:-
የዚህ ዘመን ፈውስ በሁለት መንገድ ገንዘብ መስብሰቢያ ሆኗል። ለዚህ ምስክር መቁተር ያለብኝ አይመስለኝም። በቅዱሳት መጻሕፍት በቤተክርስቲያን የቆየው ትውፊት ክብር ሁሉ ለእግዚአብሔር ነው። ዛሬ ግን ሁሉንም አጥማቂዎች ምን ሚሊየነር አደረጋቸው?  መቁጠሪያ፡ ሎሚ ፤ ቅባት፤ ሲዲ ምን አስቸበቸባቸው?። ጸጋ እኮ መንጋን ለመጥቀም ነበር። አሁን ግን ጸጋን ለጥቅም ማዋል። መንጋውን መንገጃ አደረጉት።  “ያለ ጸጋ በተለያየ መልኩ መፈወስም ሆነ ጸጋው ኖሮት አላግባብ መጠቀም እኩል ህገ ወጥ ናቸው”።  ……….
ርእሰ ባሕታውያን ቆሞስ አባ ዮሐንስ ተስፋ ማርያም”
ይህ ደግሞ ፊታውራሪ ጆቢራ ነው። “ባሕታዊ” የሚለው ተለመደ ቃል ሆነበት መሰለኝ  “ርዕሰ ባሕታውያን” ብሎ ብቅ አለ። የደቡብ ጎንደር ደራ ወረዳ ገዳማትንና አድባራትን እያወከና እያደናገረ የሚገኘው፣ ዮሐንስ ተስፋ ማርያም፥ በአጥማቂነት፣ በሰባኪነትና በልማት ስም ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጭ በመንቀሳቀስ፣ ሕገ ወጥ ሀብት እያካበቱ ከሚገኙ መሳይ ባሕታውያንና ለምንኵስና ከማይበቁት አንዱ ነው፡፡
ባሕታዊው የነበረው ወንቅእሸት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ሲኾን፣ ወደ ገዳሙ የገባው ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ እንደኾነ ተገልጿል፡፡ በዐውደ ምሕረት ምሥጢራትንና ክብረ ቅዱሳንን እያቃለለ፣ ስለ ራሱ ግን መልክእ እስከማጻፍ ደርሷል፤ ምስሉን በአልበም አድርጎ በ120 ብር ይቸበችባል፡፡ “እኔ የመረቅኹት የተመረቀ፣ እኔ የተረገምኹት የተረገመ ነው” ከማለት አልፎ፣ እኵይ ድርጊቱን የሚቃወሙትን ሊቃውንትና ምእመናን መሣርያ ታጥቀው በሚጠብቁት ዘቦቹ ያስደበድባል፤ ያስፈራራል፤ በገዳሙ የግል እስር ቤት እንዳለውም ይነገራል፤ ያለቁጥጥር በሚሰበስበው ገንዘብም፣ ከአንዳንድ የሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች ጀምሮ አማሳኝ ባለሥልጣናትንና የጸጥታ አባላትን ይደልልበታል፡ሲል ሐራ ተዋህዶ ዘገበችልን።  ጉድ በል ጎንደር ይልሃል ይህ ነው። እጅግ በርካታ በርካታ ነገሮችን መጥቀስ ይቻላል ይህንን በጥቂቱ ለማሳያ ያክል እንጂ።
+++ ሁሉንም “ባሕታውያን አጥማቂዎች” ምን ያመሳስላቸዋል+++
1. ሁሉም ግላሰቦች ከመሰረታዊው የቤተክርስቲያን አስተምኅሮ ጋር የሚጋጭ ትምህርትም ተግባርም አለባቸው።
2. ሁሉም ለእውነተኛነታቸው ማረጋገጫ  የሚጠቅሙበት ከለላ አላቸው። ተአምራት ማድረግ። ተአምር ከሆነማ ሰይጣንም ተአምር ያደርጋል።
3.  ሁሉም የቤተ ክርስቲያን አባቶችን መንቀፍ ላይ አንድ አቋም አላቸው። መልካም ስላደረግን፤ ስለፈውስን ፤በለጡን ብለው ቀኑብን፤ አሳደዱን፤ አገዱን በማለት ምሬታቸውን ወደ ቀናኢው ሕዝብ ያቀርባሉ። ቤተ ክህነቱ አገደን ምዕመናን  ይህንንተከትለው ኡአኡአ ይላሉ። በዚሁ መረጃ መረብ ይድረስ ለ ዱስ ፓትርያርኩ የሚል ደብዳቤ ሁሉ አይቻለሁ።
4. ሁሉም የመንፈሳዊነት፤ የገዳም የቅድስና ታሪክ የላቸውም። እንደውም ብዙዎቹ ከውትድርና ቤት ነው መነሻቸው። ጀማነሽ ገመና ድራማ እንዳለቀ ነው  ከመድረክ  ቀጥታ ወደ ሐዋርያነት የተቀላቀለችው። ታዲያ ከ አራት ኪሎ ተነስቶ በአንድ ጀንበር ፈዋሽ፤ ባህታዊ?
5.   ሁሉም ታላቅ የገንዘብ አቅም አፍርተዋል።መኪና፤ ታላላቅ ፎቆች ፤ ገዝተዋል ገንብተዋል? ጀማነሽ ብቻ ትመስላለች እንደ ኤልያስ ለመሆን አምሯት ስንት የምታተርፍበትን ሙያ ትታ በረሃ ለበረሃ የምትንከራተተው። እስቲ በዚህ ጽኁፍ ላይ የእርሷን ወይም የተከታዮአችዋን ምላሿን እንጠብቃለን።
6. ሁሉም “ባሕታውያን አጥማቂ” ነን ባዮች  ሥልጣነ ክሕነት አልነበራቸውም። መነቀፍ ሲጀምሩ በዚያም በዚህም ብለው ካህን ሆኑ ወይም ክህነት ተቀበሉ። ለምን እና እንዴት እንደሆነም ዝርዝሩን እናውቀዋልን። ያለ በስመ አብ ክህነት። ያለ ኪዳን ጸሎት ክህነት።
7. ቤተ ከርስቲያን እነዚህን ሕገ ወጥ አጥማቂዎች በቅዱስ ሲኖዶስ ምንም አገልግሎት እንዳይሰጡ አግዷል። አልሞት ባይ ተጋዳይ ምዕመናን ስላሉ ጆቢራዎቹ በአይዞህ ባይ ተግባራቸውን ቀጥለዋል።
የተወደዳችሁ አንባብያን ይህንን ጽኁፍ ብዙ ጊዜ ለመጻፍ አስብ ነበር። ያለፈውን ጊዜ ችላ በማለታችን ይህው ርዕሰ ባህታዊው ተነስቶ ገዳማትን ማወክ ጀመረ። አሁንም ዝም ስንል አይናችን እያየ ምን ሊሆን እንደሚችል ማሳያ ነው። እናንተም ትቆጣላችሁ ተብሎ በይሉኝታ ጉዳዩን መስታመም ምንደኝነት ነው። ይህው የምምነውን ጻፍኩላችሁ። በአሁኑ ወቅት መናፍቃንን ስንዋጋ ውስጣችን ያሉትን ችግሮች ግን እንደ መልካም ነገር አቅፈን መያዛችን ትልቅ ችግር ነው።
 ” ሁሌም ከውሸት ጋር ከመኖር ከእውነት ጋር ብትቸገሩ ይሻላል” ብዬም ምልከታዬን አሰፋርኩ።
ናሽቪል ቴነሲ
Filed in: Amharic