>

ነፍስ እንዳላወቀ ሕፃን የሚያደርጋቸው የኦሮሞ ፅንፈኞችና ግብረ-በላው መንግስት!!! (ጌታቸው ሽፈራው)

ነፍስ እንዳላወቀ ሕፃን የሚያደርጋቸው የኦሮሞ ፅንፈኞችና ግብረ-በላው መንግስት!!!

ጌታቸው ሽፈራው
 
የኦሮሞ ፅንፈኞች ችግር የሀገረ መንግስቱን ያለመቀበል ብቻ አይደለም። መንግስትነትንም አለማወቅ፣ አለመልመድ ችግር  ጭምር ነው። የኦሮሞ ፖለቲከኞች ፖለቲካው ላይ እንደህፃን ነው የሚያደርጋቸው። ነፍስ ያላወቀ ሕፃንን ቤት ውስጥ ጥለኸው ብትሄድ የሚያጠፋው ነገር ብዙ ነው። አመዱን ከዱቄት፣ ውሃውን እሳት ላይ ሲጨምር ቤቱንም ራሱንም ያጠፋል!
ለሌላ ብቻ ሳይሆን  ለራሱም ሕይወት የሚጎዳነውን ሲያደርግ ይደረስበታል። በርበሬ ቢያገኝ ሌላው አይን ላይ እንደሚረጨው ሁሉ ራሱንም የሚነካውን አያውቅም። ቤንዚን  እሳት ላይ፣ መርዝ ቢያገኝ ውሃ ላይ  እየደባለቀ ሊጫወት ይችላል።  የቤቱን ሕግ በሚገባ አይረዳውም። ለመረዳትም ግዴታ የለበትም።  ደስ ያለውን ሁሉ ጠቅልሎ ለራሱ ለማድረግ ይሞክራል። ሌሎች ቢከፉና ሁሉንም ቢወስድባቸው ግድ የለውም። ተቃጠለ፣ ተደፋ፣ ሁሉም እንዳልነበረ ሆነ ችግር የለበትም!
የኦሮሞ ፅንፈኞች ፖለቲካ በቅጡ የማያውቅ ሕፃን አይነት ነው። ኦሮሞ ስልጣን ያዘ ሲባል ፈነደቁ። ወደ ቤተ መንግስት አብዝተው  ተመላለሱ። ስልጣን ላይ ያለው ሁሉ የእኛ ነው አሉ። ሁሉንም ስጡን አሉ። መንግስት ውስጥ በነበሩ መሰሎቻቸው አማካኝነት ህይወት ያላወቀ ህፃን የሚያደርገውን ያህል የሌላውን አጋበሱ፣ ሰበሰቡ።  እቃ እቃ  እንደሚጫወቱት በተጓዳኝ “እኔም መንግስት ነኝ” እስከማለት ደርሰዋል፣ ለዛም ሰርተዋል። ማዶ ሆኖ የሚጫወተውን ጭቃ ቀብተዋል። መጀመርያ ፈንድቀው የገቡበትን ቤት አተረማምሰው ፍላጎታቸውን ለማርካት ጥረዋል። የሰው ሕይወት፣ ንብረት፣ ሀገር ምናቸውም አልነበረም። የያዙትን ሁሉ ይዘው፣ ያጠፉትን አጥፍተው፣ ሌላው የያዘውን ካልያዝኩ ብለው ያዙኝ ልቀቁኝ ብለዋል። ሰሞኑን ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ “ኦሮሞ ስልጣን አይዝም ብለው ኖረው፣ ዛሬ ኦሮሞ ስልጣን ያዘ ሲባል፣ ኦሮሞ ስልጣን መያዝ ከቻለማ እኔ እያለሁ እሱ  ሊይዝ አይችልም የሚል ቅናት አለባቸው” ብለዋል። ይህ ነፍስ ያላወቁ ህፃናት ትክክለኛ ባሕሪ ነው። የኦሮሞ አክራሪ ኃይል የተጠናወተው ይህ የህፃንነት ፖለቲካ ነው።
እነዚህ የመንግስትነትን ባሕሪና ክብር ያልተረዱ ፅንፈኞች ለሚጠይቁትና ለሚያደርጉት ልክ አልነበራቸውም። ስልጣን ላይ የነበሩት እኩዮቻቸው ለዚህ ፀባያቸው አስተዋፅኦ አድርገዋል።  ባለፉት ሁለት አመታት የታየው ትርምስ ከእነዚህ ፖለቲካን ስርዓት ካሳጡት ሰዎች ክፉ የፖለቲካ ባሕል የመጣ ነው። ለኦሮሞ ብሔርተኝነት ትልቅ አስተዋፅኦ አደረጉ የሚባሉ ሰዎች ለኦሮሚያ ክልል  ከተሞች ያላቸው ጥላቻ ልዩ ነው። ከተሞቹን የአጤ ምኒልክና የአጤ ኃይለስላሴ ሰፈራዎች የነበሩ ናቸው ብለው በዓድ አድርገው ሲስሏቸው ኖረዋል። ለእነዚህ ከተሞች መመስረት የሚጠሏቸው ሰዎች እጅ አለበት ስለሚሉ ብቻ ይጠሏቸዋል። ከተሜነት ለእድገት መሰረት ሆኖ፣ ሕዝብ መሰረተ ልማት አልተሟላለትም እያሉ እየወቀሱ፣ ፈረንጅ በሰራው ከተማ ተደንደላቅቀው እየኖሩ የራሳቸው ሕዝብ የሚኖርባቸውም ከተሞች “የእነ ምኒልክ ሰፈራዎች ነበሩ” ብለው አምርረው ይጠሏቸዋል። እነ መሃመድ ሀሰንና ሌሎችም ቃል በቃል ይህን ፅፈውታል። ትውልዱ ይህን የከተሞች ባይተዋርነት ትርክት  እንደ እውነት ወስዶታል። ታዲያ የዛሬው ትውልድ የሚያወድመው የብሔርተኝነቱ መስራቾች የሚጠሉትን ከተማ ነው። የብሔርተኝነቱ ዋና አቀንቃኞች መሰረተ ልማትን “ከአቢሲኒያ ቅኝ ግዛት፣ አማራ ሲጨቁን ያደረገው” አስመስለው ያቀርቡላቸዋል። ሀገረ መንግስት ግንባታን ወንጀል፣ መንግስትነትን  ለኦሮሞ የማይበጅ አድርገው ሲያቀርቡላቸው ኖረዋል። ኦሮሞ መንግስት የማይሆን አስመስለው፣ ዛሬ በእጃቸው ሲገባ የራሳቸው ወንድሞች የያዙትንም “አምጣው እስኪ እኔም ልጫወትበት” ብለው እቃ እቃ ካልተጫወትንበት በማለታቸው ነው ከዚህ የተደረሰው። ብዙዎቹ የያዙትን ስልጣን “እንካ ተጫወትበት” ብለው ስለፈቀዱላቸው ነው ከዚህ የተደረሰው። የኦሮሞ አክራሪ ኃይል ሀገረ መንግስቱ ላይ ያለውን ጥላቻ፣ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያሉትን ከተሞች እንደ በዓድ አድርጎ የመቁጠር ክፋ አመል ካልቆመ፣ የመንግስትነትን ባሕል እንዲለምዱ ካልተደረገ ነገም ዱቄትና አመድ እየጨመሩ፣ ቤንዚንን እሳት ላይ እየጨመሩ፣ ያገኙትን እየገበጡ፣ የሌላውን ሁሉ እየሰበሰቡ እንቀጥል ካሉ  የሰሞኑ ውድመት ምልክት እንጅ መጨረሻው አይሆንም። ይህ ያልተገራ ባሕል መጨረሻው የባሰ ክፉ ነው። ኦሮሚያ ክልል የሚገኙትን ብቻ ሳይሆን አዲስ አበባንም ካላወደምን የሚለው ትውልድ  ባለፉት አመታት ብሔርተኝነቱን ገነቡት ከሚባሉት የወሰዱት ፀረ ከተማ፣ ፀረ ስልጣኔ የሆነ የተዛባ አቋም ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀር “ቅናት ነው” ብለው የሚገልፁት የኦሮሞ ፅንፈኞች እኔ ካልተጫወትኩበት የሚሉትን የስልጣንና መንግስትነት ባሕልን አለመልመድ፣ ልክ ነፍስ ያላወቀ ሕፃን የቤቱን ሕግና ጥቅም ሳያውቅ እንደሚያተረማምሰው አይነት አላዋቂነት ነው። ይህ አላዋቂነት የሚታገሰው መንግስትነትን የያዙትና የሚያውቁት በሚያደርጉት ማስተካከያ ነው። መንግስት ውስጥ ያሉ የፅንፈኞቹ እኩያዎችንም አደብ በማስገዛት ጭምር ነው።
ነፍስ ያላወቀ ህፃን እጅግ ውድ የሆነው ነገርን ይዞ ካልፈጠፈጥኩት ብሎ ካዋቂዎቹ ጋር ይታገላል። ሰብሮት ይስቃል።  የሆነ ነገር ካላሟላህ እከሰክሰዋለሁ ብሎ ይገለገላል።  የኦሮሞ ፅንፈኞች ደስ ሲላቸው ኦሮሚያ ውስጥ ያለውን ውድ የሰው ህይወትና ንብረት በቅጡ ያላወቀ ህፃን እየሳቀ እንደሚሰብረው ማስያዢያ ሲያደርጉት ኖረዋል።  በትንሽ ነገር ሲያኮርፉና ተያያዥነት ነገር የለለው ነገር ሲፈፀም በቅርባቸው ያገኙትን ውድ ነገር እንዲወድም የሚያደርጉት  ነፍስ ያላወቀ ህፃን ባሕሪን የፖለቲካ ባሕል በማድረጋቸው ነው።  ነፍስ ያላወቀ ሕፃን ሲያጠፋ ከፍ ያለው እስከሳቀለት ድረስ ይቀጥላል። የኦሮሞ ፅንፈኞች ለዚህ  ውድመት ያደረሱን መንግስት ውስጥ ያሉ እኩዮቻቸው ስለሚስቁላቸውና ስለሚያግዙዋቸው ጭምር ነው።  ይህ ውድመት የሚቆመው ኃላፊነት የሚገባው ቦታ ላይ ተቀምጠውም እንደ ጨቅላ የሚያደርጉትን አደብ በማስገዛትና የሚመጥን አካል በማምጣት ብቻ ነው።
Filed in: Amharic