>
5:13 pm - Tuesday April 18, 6209

‹እሪ በይ ሀገሬ፣ በይ እርምሽን አውጪ...!!!" (አሰፋ ሃይሉ)

‹እሪ በይ ሀገሬ፣ በይ እርምሽን አውጪ…!!!

አሰፋ ሃይሉ
 
“ያንኑ የቀደመውን ነገር ደጋግመው እያደረጉ የተለየ ለውጥን ለማግኘት መከጀል እብደት ይሰኛል፡፡” 
                       — ሳይንቲስት አልበርት አንስታይን
 
“በስምንተኛው ሺ … ሲመሽ ተወልጄ፣
ጅቡን ጋሼ እላለሁ … ተኩላውን ወዳጄ” 
በለውጥ ተብዬው ዋዜማ ላይ ሰው ሁሉ መናገር በፈራበት ሰዓት ልደቱ አያሌው ከወያኔው አይነደረቅ ካድሬ ከዛዲግ አብርሃ ጋር በቴሌቪዥን ቀርቦ ባደረገው ክርክር ሽንጡን ገትሮ የሥርዓቱን የኢኮኖሚ ክሽፈትና አይቀሬ ውድቀት ያለ አንዳች ፍርሃት ሲናገር ነበረ፡፡ ዛዲግ አብርሃ ደግሞ የኢህአዴግ የቁርጥ ቀን ልጅ ሆኖ ወያኔ የሰላምና የገነት ምድር ስላደረጋት ኢትዮጵያ ሲመሰክር ነበር፡፡ ዛሬ ለውጥ የተባለው መጥቶ ልደቱን እስር ቤት ጨምሮት፣ ዛዲግ አብርሃን ሚኒስትር አድርጎታል፡፡ ለውጡ የእነማን ለውጥ፣ እና ለነማን የመጣ ለውጥ እንደሆነ ለማወቅ ይሄ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ የያኔው ወያኔ እስክንድር ነጋን ከነባለቤቱ እስር ቤት ወርውሮ በግፍ መጫወቻ ሲያደርገው የጮኸው ሕዝብ፣ አሁንም ደግሞ እስክንድር ነጋን መልሶ እስር ቤት በጨመረው ለውጥ ላይ እየጮኸ ነው፡፡ ወደፊትም ገና ይጮሃል፡፡
ይሄ በፀረ-አማራው ብአዴን የተደገፈ የቄሮ ሥርዓት ታከለ ኡማን ምክትል ከንቲባ የሚል ማዕረግ ፈጥሮ የአዲሳባ ገዢ ያደረገ ሥርዓት ነው፡፡ (ብአዴንን ፀረ-አማራ ያልኩበትን ምክንያት ከታች አስረዳለሁ፡፡) ይሄ ራሱን ‹‹የለውጡ መሪ›› አድርጎ ራሱን በራሱ ለሹመት የቀባው ሥርዓት ነው ታከለ ኡማን በህዝብ ሳይመረጥ ለሥልጣን ያበቃው፡፡ ለውጡ የተከለው ሥርዓት ነው ታከለ ኡማ የሥልጣን ዘመኑ አክትሞም እስከማይታወቅ መጪ ጊዜ ድረስ የአዲሳባን ህዝብ እንዲገዛ የሾመው፡፡ ይሄ ሥርዓት የጠቅላይ ሚኒስትሩንና ቀድመውም ኮሮጆ ገልብጠው ፓርላማ የገቡትን አባላት ሥልጣን በኮሮና አሳቦ ከህግ ውጭ ያራዘመ ከወያኔ የባሰ በሥልጣን ጠኔ የተለከፈ ሥርዓት ነው፡፡
ሥርዓቱ ጃዋር መሀመድን የአማራና የሌሎች ኢትዮጵያውያን ደም በቄሮ ነፍሰገዳዮች እንዲፈስ በተደጋጋሚ ባደረገው የአሸባሪነት ተግባር አይደለም ያሰረው፡፡ ጃዋር ያን ሁሉ ደም ሲያፈስ፣ ህዝብ ካለም ጫፍ እስከ ጫፍ ሲጮህ፣ ያ ሁሉ ግድ ያልሰጣቸው የለውጡ መሪ ተብዬዎች – ጃዋር የፈጸመውና ያስፈጸመው ወንጀል በግልጽ እየቀረበላቸው – ጃዋር የዓይን ብሌናችን ነው እያሉ ሲምሉ ሲገዘቱ፣ ደሙ በፈሰሰው ህዝብ ሲሳለቁ ነበር፡፡ ጃዋር የታሰረውና መታሰር ያስፈለገው አሁን በስተመጨረሻ የለውጡን የስልጣን ጥመኞች ለሥልጣናቸው ስላሰጋ ብቻ ነው፡፡ በአደባባይ የለውጥ ተብዬዎቹን ድራማና ሸፍጥ ማጋለጥ ስለጀመረ ብቻ ነው፡፡ እንጂ በትክክል ጃዋር ስለሠራው ወንጀልና ስለ ፍትህ ቁጭት ያደረበት አካል አይደለም ጃዋርን ያሰረው፡፡ ያኛውና ይሄኛው ምንስ ለይቶት… እና ማንስ ነው ለማን ፍትህ ሰጪ የሆነው?
በወያኔ ጊዜ እነ ታምራት ላይኔ የአማራ ህዝብ እየታረደ የሥልጣን ፍርፋሪ እንዳይቀርባቸው ጆሮ ዳባ ልበስ ሲሉ፣ ነፍጠኛ ከሚሉት ብሰው ነፍጠኛን በለው ሲሉ – መጨረሻ ወያኔ ሱሪውን አስወልቆ ገርፎ ከርቸሌ አወረደው፣ ሞራሉንና ጤንነቱን ሰልቦት የጴንጤ ሰባኪ ጌታ እየሱስ እያለ እንዲወጣ አድርጎት አረፈ፡፡ የፈሰሰው የአማራ ደም – እንደ ውሻ ደም ተረስቶ ቀረ፡፡ ተጠያቂ የለም፡፡ ፍትህ የለም፡፡ ለውጥ የለም፡፡
አሁንም በታምራት እግር ያንኑ የሥልጣን ፍርፋሪ ለቃሚ ድርጅት የአማራ ወኪል ብለው የተቀመጡት እነ ገዱና እነ ደመቀ – የስልጣን ፍርፋሪ እንዳይቀርባቸው ወያኔንና ሰማዕታቶቿን ጧትና ማታ እያወደሱ ኖረው – ስንቱን አማራ አስጨፈጨፉት፣ ስንቱን አኮላሹት፣ የስንቱን ቅስም አሰበሩት፡፡ ዛሬም አይናቸውን አጥበው ለውጥ የሚሉትን እያወደሱ፣ ግድብ እያወደሱ፣ እየተወዳደሱ ሥልጣን ላይ እንደ እባብ ተጠምጥመው ጥቅማቸውን ሲልሱ፣ የታረዱ አማራ ልጆች ደም ግድብ ሆኖ ሀገር ምድሩን አጥለቅልቆታል፡፡ ለውጥ የለም፡፡ ተረኝነት ግን አለ፡፡ የትናንቱን ግፍ አዳዲስ ተዋናዮች ቢደግሙት ጥሩ ነበር፡፡ አሁንም ግን በለውጥ ስም ሕዝብን የሚያርዱት የሚያሳርዱት፣ የሚገድሉት የሚያስሩት፣ እነዚያው የቀደሙት የቀደመው ሥርዓት ቋሚ ዘቦች፣ የቀደመው ሥርዓት የህዝብ ደም መጣጮች ናቸው፡፡
ወያኔ ላይ ጣት መቀሰር ራሳቸውን የለውጥ ሀዋርያ አድርገው የህዝብን ጩኸትና ትግል ነጥቀው ሥልጣን ላይ ፊጥ ያሉትን የወያኔ የኖሩ ጋሻጃግሬዎችና የቀደመው ደም መጣጭ ሥርዓት የጥቅምና የሥልጣን ተጋሪዎችን ከተጠያቂነት አያድንም፡፡ በፍፁም፡፡ ወያኔ ደደቢት ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የአማራን ሕዝብ ጠላቴ ብሎ ፈርጆ ማኒፌስቶ አውጥቶ የአማራን ደም ሲያፈስ በኖረባቸው ዓመታት ሁሉ – ከወያኔ ጎን ተሰልፈው የገዛ ወገናቸውን የአማራን ደም ሲያፈሱ የኖሩት ማን ናቸውና? የኢህዴን/ብአዴን ተብዬዎቹ ባንዳዎች አይደሉም ወይ? ከዚህ በላይ ፀረ-አማራነት ምንድነው? ከብአዴን በላይ ፀረ-አማራነቱን በተግባር ያስመሰከረ ባንዳ የለም! ከባንዳም የሚጠበቅ ለውጥ የለም!
ጠቅላዩ ሥልጣን የተቆናጠጠው ልክ እንደ ብአዴን ደግሞ የኦሮሞው ባንዳ ኦህዴድ የለውጥ ሃዋርያ አድርጎ ሰማይ የሰቀለው ለማ መገርሳ በገዛ ፍቃዱ የኦህዴድ ወንበሩን ለቆለት ነው፡፡ ጠቅላዩ ሥልጣኑን የተቆናጠጠው በሟቹ መለስና በሰማዕታት ስም ሀገሪቱን አንድ አድርጎ ለመምራት ያደረገው የህልም ሩጫ ያልተሳካለት ሃይድሮሎጂስቱ የይስሙላ ጠቅላይ ኃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣኑን በገዛ ፈቃዱ ለቆለት ነው፡፡ ጠቅላዩ ግን ይቺን በብዙ ሰዎች መልካም ፈቃድ የተቆናጠጣትን ስልጣን ላለማስነካት እየተጋደለ ነው፡፡ በወያኔ ጊዜ ወያኔን በሥልጣኑ አትምጣበት እንጂ በሌላ የፈለከውን ብትሠራ ዞር ብሎም አያይህም ይባል እንዳልነበር – አሁንም ለውጡ ወደ ሥልጣን ያመጣው የጠቅላዩ ነገር ያንኑ የወያኔን ነገር ሳንወድ በግድ እንድናስታውስ ያደርገናል፡፡
ራሱን የለውጥ ሃዋርያ አድርጎ ያቀረበው ጠቅላዩ ማርያም ንግሥት አድርጋ ቀብታኛለች ብላ በሥልጣኑ የመጣችበትን እህተማርያምን አልቀረውም ወደ እስርቤት ሲያጉር፡፡ እስክንድር፡፡ ልደቱ፡፡ ይልቃል፡፡ ጃዋር፡፡ አሳምነው፡፡ የሰባተኛው ንጉስ የለውጥ ጅማሮ እስርቤት ያጎራቸው የሩቅ ተፎካካሪዎች አይቆጠሩም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ሾርት ሜሞሪ ስላለው ይረሳዋል እንዳለው ጠቅላዩ እየተረሳ እንጂ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ጠቅላዩን የነቀፉ ሁሉ ዛሬ እስርቤት ናቸው፡፡ ትናንት ከጠቅላዩ በላይ ልታይ ልታይ አሉ የተባሉ ሁሉ ተመተዋል፡፡ አንድም ተገድለዋል፡፡ ታስረዋል፡፡ አሊያም በሥልጣናቸው ላይ የሉም፡፡ ዛሬም እንደ ትናንቱ ሰላማዊ ሰልፍ መውጣት ክልክል ነው፡፡ መሰብሰብ ክልክል ነው፡፡ መንግሥት ተብዬውን ባደባባይ ማውገዝ ክልክል ነው፡፡ ሌላ ቀርቶ ለጠቅላዩ አላጎበድድም ያለ ሐይማኖት ምዕመን ሆኖ መገኘት ራሱ ክልክል ነው፡፡ ለከፋ ቅጣት ከፍ ሲልም ለሞት ይዳርጋል፡፡ ሩቅ መሄድ አያስፈልግም፡፡ በአዲሳባ 22 በታቦቱ ፊት የተገደሉትን እነ ሚኪን ማሰብ ብቻ በቂ ነው፡፡
በአማራው ስም ፖለቲካ ይሰራበታል፡፡ በአባይ ስም ፖለቲካ ይተወንበታል፡፡ ሁሉም የሥርዓቱ ወንጀሎችና ግፎች በአንድ ለናቱ በወያኔና በወያኔ ላይ ብቻ ተሳቦ ጣት መጠነቋቆሉ፣ መወነጃጀሉና ግፋ ሲልም ማስፈራራቱ ቀጥሏል፡፡ የመደመር ወሬው ቀርቶ የጦርነት ወሬው ደርቷል፡፡ ከግብጽ ጋር፡፡ ከወያኔ ጋር፡፡ ከሱዳን ጋር፡፡ ከኦነግ ሸኔ ጋር፡፡ ከአሜሪካ ጋር፡፡ ከባንዳዎች ጋር፡፡ ከብዙ ባለስሞች ጋር፡፡ ነገር ግን በለውጡ የታየው ብቸኛ ውጊያ ቢኖር በአማራው ህዝብ ላይ የታወጀው ውጊያ ብቻ ነው፡፡ ለውጡ ያመጣው ነገር የአማራውን ሕዝብ በዘሩ በሐይማኖቱ እየተለየ በአደባባይ መታረድን ነው፡፡ ከተማ ዘግቶ መቀጥቀጥን፣ መታረድን፣ መሰቀልን፣ መቃጠልን ነው፡፡
ዛሬም እንደ ትናንት – እንዲያውም ከትናንቱም ብሶ በየጣራው ሥር – የንፁሃን እንባ እንደ አባይ በዝምታ መፍሰሱን ቀጥሏል፡፡ የአማራው ደምና የሌሎችን ኢትዮጵያውያን ደም እንደ ጅረት መፍሰሳቸውን የሚያስቆም ከቶም አልተገኘም፡፡ ደም አፍሳሹን የሚጠብቅ እንጂ ህዝብን የሚጠብቅ የለውጥ ሃዋርያ ከለውጥ ተብዬው ደጃፍ ሊፈልቅ አልቻለም፡፡ ለሕዝብ የቆመውን የሚያስር እንጂ – ዛሬም እንደቀድሞው – አሳሪውን ራሱን የሚያስር ፍትህ ፈጽሞ ዝር አላለም፡፡ ለውጡ ያመጣው ለውጥ-አልባ ለውጥ ይሄ ብቻ ሆኗል፡፡ ሌላ አንዳች ጠብ ያለ ነገር የለም፡፡ ከቀደመው የተለየ ምንም ነገር የለም፡፡ ለውጥ የለም፡፡ ቂም ያረገዘ ተረኝነት ግን አለ፡፡
‹‹ “ሐዘንሽ ቅጥ አጣ፣
ከቤትሽ አልወጣ፣
የገደለው ባልሽ፣
የሞተው ወንድምሽ፣”
‹‹እንዲል ባለቅኔው፣ ዕጣ ክፍልሽ ሆኖ፣ ይዞሽ እንደ ሲቃ፣
እንባሽ ወደ ውስጥሽ፣ መፍሰስ መንቆርቆሩ፣ ዛሬም አላበቃ፡፡
ከልጅሽ ገዳይ ጋር፣ ድንኳን ተጋርታችሁ፣ ደረት እያዳቃሽ፣
ማን ያባብልሻል፣ አንቺም እሱም አልቃሽ፡፡
‹‹እሪ በይ ሀገሬ፣ በይ እርምሽን አውጪ፣
ዕድርተኛም የለሽ፣ ከማን ትቀመጪ፡፡ ››
ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ፈጣሪ ዘረጋች፡፡ ፈጣሪ ኢትዮጵያችንን ይቅር ይበልልን፡፡ ኢትዮጵያ ትቅደም
Filed in: Amharic