>

ጄኖሳይድና መከላከያ መንገዶቹ ...!!! (ሉሉ ከበደ)

ጄኖሳይድና መከላከያ መንገዶቹ …!!!

 ሉሉ ከበደ

አድሎ፤(Discrimination) የዘር ፤ የሀይማኖት ፤ የቆዳ ፤ የቀለም ፤ የቋንቋ ልዩነትን መሰረት ያደረገ አሰራርን ህያው ለማድረግ  ፤ የህግ መስመርን መፍጠር ፤ ወይም ክልል፤  አጥር፤ ግንብ፤ መገንባት የጄኖሳይድ ደረጃ አንዱ እርከን ነው ብለናል ፡፡ ቀደም ሲል « ጄኖሳይድ ዋች »  የሚከተለውን መርህ ለማስረዳት ስሞክር ፡፡
ባለጊዜ የሆነ ወገን ፤ « በበላይነት ያለሁት እኔነኝ » ብሎ የሚያምን ቡድን ፤ ህግ እያጣመመ እያወጣም ሊያስወግደው የፈለገውን ወገን ይጎዳል ፡፡ ሰብአዊ መብቱን ፤ የፖለቲካ የሲቢል የኢኮኖሚ መብቱንም ይረግጣል ፡፡ ለምሳሌ በ1935 በናዚዋ ጀርመን ውስጥ « የኑረምበርግ ህግ » ተብሎ የሚታወቅ ህግ ወጥቶ ፤ አይሁዳውያን የዜግነት መብታቸው እንዲገፈፍ እና ከመንግስት ስራዎች ሁሉ እንዲወጡ፥ ከዩንቨርስቲዎች መምህራንና አይሁድ የሆኑ ሰራተኞች ተጠራርገው እንዲባረሩ ተደርጓል ፡፡ ባገራችን የትላንት ትዝታ ነው ወያኔ ኢህ አደግ 42 ከፍተኛ የዩኒቨርስቲ መምህራንን ፤ ፕሮፌሰሮችን በአማራነታቸው ምክንያት «ዩኒቨርስቲውን ከትምክተኛ ሀይሎች ማጽዳት » ብሎ እንዳባረረ ፡፡ በአሁኑ ሰአትም ቢሆን የፈለጉትን መቅጠር እና አለመቅጠር በሀገራችን የክልሎች መብት ነው ፡፡ በዜግነት ተኩራርቶ ፤ ወደፈለጉበት ጥግ ሄዶ ፤  በችሎታ ተወዳድሮ ፤ አሸንፎ ፤ ስራ መያዝ ኢትዮጵያ ውስጥ የለም ፡፡
የሆነው ሁኗልና  ለእንደዚህ አይነቱ የጄኖሳድ ደረጃ « ጄኖሳይድ ዋች »  ወደሌላው እርከን እንዳያድግ መፍትሄ ብሎ ያስቀመጠውን ነገር ስናየው መፍትሄው በኢትዮጵያ በአሁኗ ሰአትም ስራ ላይ ቢውል እየሄድን ካለንበት የጥፋት መንገድ ሊመልሰን ይችላል ፡፡
«. … Prevention against discrimination means full political empowerment and citizenship rights for all groups in a society . Discrimination on the basis of nationality, ethnicity, race, or religion should be out lawed… »
 መድሎን ለመከላከል ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሀላፊነት በተሞላው ሁኔታ የሚጠቀሙበት ሙሉ የፖለቲካ ና የዜግነት ስልጣን  ፤ መብት መስጠት ፡፡  በራሳቸው ጉዳይ የመወሰን ሀይል እንዲኖራቸው ማድረግ ፡፡ በብሄር ፤ በጎሳ ፤ በዘር ፤ እንዲሁም በሀይማኖት  ልዩነት ላይ ተመስረተው ስራ ላይ የዋሉ ህጎች ፤ አሰራሮች  በህግ እንዲታገዱ ማድረግ ያስፈልጋል።
የሰውን ክብር ዝቅ የሚያደርጉ ንግግሮች ፤ ቅጽል ስሞች ፤ ምልክቶች ሊያጠፉት በፈለጉት ወገን ላይ መለጠፍ አራተኛው የጄኖሳይድ እርከን ነው ብያለሁ ዶክተር ግሬጎሪ እንዳስቀመጡት ፡፡ ነፍጠኛ ፤ ትምክተኛ ፤ አሀዳውያን ፤  ወዘተ.… በነገራችን ላይ እነዚህ ቃላት« ነፍጠኛና አሀዳውያን  » በራሳቸው መጥፎ ትርጉም ያላቸው አይደሉም ፡፡ ለጥቃት እንዲጋለጥ ለተፈለገው አማራ በቀጥታ የተሰጡ መለያዎች መሆናቸው እንጂ ፡፡ የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮች ሰውን ከሰውነት ክብር የሚያወርዱ ናቸው ወደ መፍትሄው ስንሄድ የሀገር ውስጥም ሆኑ የመላው አለም መሪዎች የጥላቻ ንግግሮችን አጥብቀው ማውገዝ ይጠበቅባቸውል ፡፡ በባህልም ተቀባይነት እንዳይኖራቸው መስራት ይገባቸዋል ፡፡ የዘር ፍጅትን የሚያነሳሱ የቡድንም ሆነ የዘር እንዲሁም የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ፤ በብሄራዊ የፍትህ ተቋማት  በከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ክስ ሊመሰረትባቸው ይገባል ፡፡ ከሀገር ውጭ በረራ መታገድ አለባቸው ፡፡ በውጭ ባንኮች ያስቀመጡት ገንዘብ እንዲያዝ ማድረግ ይገባል ፡፡ ጥላቻን እና አመጽን የሚነዙበት ሬዲዮና ቴሌቪዢን መገናኛ ብዙሀን እንዲታፈን እንዲዘጋ መስራት ግድ ይላል ፡፡ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ የሚነዙባቸው ማህበራዊ መገናኛ ብዙሀን ኢንተርኔት ፌስቡክ ዩቱብ ወዘተ…  እንዲያግዷቸው  አካውንታቸውን እንዲዘጉባቸው ማድረግ ያስፈልጋል ፡፡ በጥላቻ ተነሳስተው ወንጀል የሰሩ ፤ ህዝብ የፈጁ ፤ ንብረት ያወደሙ ፤ ጥብቅ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ማድረግ ያሻል ..…
ይቀጥላል
Filed in: Amharic