>
5:13 pm - Tuesday April 18, 9037

የትግራይ ቴሌቪዝን ስርጭት በመንግስት ተዘጋ (ዘ አዲስ)

የትግራይ ቴሌቪዝን ስርጭት በመንግስት ተዘጋ

ዘ አዲስ
ፋና ብሮድካስቲንግም የመቀሌ ኤፍ ኤም ስርጭቱን አቋረጠ
የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ መልዕክቶችን በሚያስተላልፉ መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚወሰደው እርምጃ እንደሚቀጥል የብሮድካስት ባለሥልጣን አስታወቀ
*******************
የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ መልዕክቶችን በሚያስተላልፉ መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚወሰደው እርምጃ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን አስታወቀ።
ባለሥልጣኑ የአገርን ሠላምና የሕዝብን አንድነት የሚሸረሽሩ መገናኛ ብዙኃን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስቧል።
በቅርቡ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ሕልፈት ተከትሎ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች በተነሳ ሁከት ዜጎች ለሞትና ለአካል ጉዳት ሲዳረጉ በርካታ ንብረትም ወድሟል።
ክስተቱን ሁሉም የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን በሚባል ደረጃ በስፋት ሲዘግቡትም ተስተውሏል።
የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን አንዱዓለም ለኢዜአ እንደገለጹት መገናኛ ብዙኃኑ ለዓመታት ከነበሩበት ጫና ወጥተው በነጻነት እንዲዘግቡና የሕዝቡን ሐሳብ እንዲያስተላልፉ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።
ይሁን እንጂ ይህን ነጻነት በአግባቡ የማይጠቀሙና የጋዜጠኝነትን ስነ-ምግባር የሚጥሱ መገናኛ ብዙኃን መፈጠራቸውን ጠቁመዋል።
የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ሞት ሽፋን በማድረግ የዜጎችን ሠላምና አብሮነት የሚሸረሽሩ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ የነበሩ ኦ.ኤም.ኤን እና ድምፀ ወያኔ ጣቢያዎች መታገዳቸውን ገልጸዋል።
የትግራይ ቴሌቪዥን ጣቢያም ስርጭቱ እንዲቋረጥ በመንግስት እርምጃ እንደተወሰደበት አስታውሰዋል።
ሰላም ለማስከበር ከወሰደው እርምጃ ጎን ለጎን መገናኛ ብዙኃኑን ተጠያቂ በማድረግ ረገድ ባለሥልጣኑ አዋጁ በሚፈቅድለት ሕግና ደንብ መሠረት ኃላፊነቱን የሚወጣበትና የማይታገስበት ጊዜ መሆኑን አቶ ወንድወሰን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
መገናኛ ብዙኃን ድንጋይ መወራወሪያ ሳይሆን ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦች የሚፋጩባቸውና ሃሳብ የሚያሸንፍባቸው ሊሆኑ ይገባልም ብለዋል።
ሕዝቡ እውነተኛና ትክክለኛ መረጃ እንዲኖረው ከማድረግ ይልቅ መቃቃርን የሚሰብኩ የመገናኛ ብዙኃን አሁንም መኖራቸውን ባለሥልጣኑ መታዘቡን አቶ ወንድወሰን አንስተዋል።
የአንድ ወገንና ቡድንን ፍላጎት በሚያንጸባርቁና የተቋቋሙበትን ዓላማ በሚዘነጉ መገናኛ ብዙኃን ላይ አሁንም የእርምት እርምጃ የመውሰድ ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የችግራቸው መጠን ቢለያይም የመፍትሄ አካል ከመሆን ይልቅ የችግሩ አካል የመሆን አዝማሚያ በመገናኛ ብዙኃኑ እንደሚስተዋልም ጠቁመዋል።
ይህንን ከመሠረቱ ለማስቀረት ባለሥልጣኑ ሕግን በማስከበር መገናኛ ብዙኃኑ በትክክለኛ መንገድ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ያደርጋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ በአጠቃላይ 72 የማኅበረሰብ፣ የግል /የንግድ/ እና የሕዝብ ራዴዮ ጣቢያዎች እንዲሁም 37 የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አሉ።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከዛሬ ማለዳ ጀምሮ ከትግራይ ክልል መቀለ ከተማ በኤፍኤም አማካይነት ሲያደርገው የነበረውን ስርጭቱን ማቋረጡ ተረጋግጧል።
የብሮድካስት ባለስልጣን ለጣብያው የጻፈውን ደብዳቤ ከድርጅቱ ጋዜጠኞች በማየት ማረጋገጥ እንደተቻለው ስርጭቱ ከትናንት አመሻሹን ጀምሮ እንደተቋረጠ የተገለፀ ሲሆን ቢሮውም መዘጋቱን ለማወቅ ተችሏል።
Filed in: Amharic