>

ትእግስቱ የማያልቅበት ጨዋ ሕዝብ (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም)

ትእግስቱ የማያልቅበት ጨዋ ሕዝብ

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም

የሚሰሙኝ ከሆነ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዶር. ዓቢይ አሕመድ፣ ለአዲስ አበባ ከንቲባም፣ ለወይዘሮ ሙፈሪያት የሰላም ሚኒስትር፣ ምናልባት ሌሎች መኖሪያ ቤት መፍረስ የተጠናወታቸው ባለሥልጣኖች ካሉ ለነሱም የኅሊናዬን ጩኸት አስሰማለሁ፤
የሚያዩኝና የሚያዝኑልኝ ከሆነም ተንበርክኬ እለምናቸዋለሁ!
በዚህ የክረምት ወቅት፣ በዚህ የማትታይ ጉድ ዓለምን በሙሉ አንበርክካ በየዕለቱ ሰዎችን በምትጨርስበት ዘመን፣ በዚህ ዘመን እጃችሁን ቶሎ-ቶሎ ታጠቡ፤ አፍና አፍንጫችሁን ሸፍኑ፣ ስትገናኙ ተራራቁ በተባለበት ዘመን፣ በዚህ ሰው ሁሉ ሥራ ፈትቶ በቦዘነበት ዘመን፣ በዓባይ ጉዳይ ከግብጽ ጋር በተፋጠጥንበት ዘመን፣ የድሆችን ቤት በጉልበት ማፍረስና ድሆችን ማስለቀስ አቤቱታቸው የላይኛው ጌታ ዘንድ እንደሚደርስ ባለማወቅ ነው? ወይስ ኮሮና በቂ አልሆነምና ነው? እግዚአብሔር እንደሆነ ከኮሮና የባሰ ለመልቀቅ ችግር የለበትም፡፡
ዶር. ዓቢይ ስለይቅርታ የሚናገረው ስለነዚህ ደሀዎች አይሠራም? ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ትልልቅ ዓላማዎች አንዱም እነዚህን እንባቸው የእግዚአብሔርን ደጃፍ የሚያጨቀይ ደሀዎችን አይነካም?
በመጨረሻም እነዚህን ደሀዎቸ እግዚአብሔር አያያቸውም ብላችሁ ታስባላችሁ? ወይስ አይቶ መልስ ሳይሰጥ ይቀራል ብላችሁ ታምናላችሁ?
እግዚአብሔር ነገን ይግለጥላችሁ!
Filed in: Amharic