>
5:13 pm - Thursday April 20, 8169

ከጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ ለኢትዮጵያ ህዝብ መግለጫ

ከጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ ለኢትዮጵያ ህዝብ መግለጫ

 

የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች፣
 
ክቡራትና ክቡራን
ባለፈው ሰሞን የአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ ግጭት ጠማቂዎች ባስነሡት ሑከት አያሌ ወገኖቻችን ሕይወታቸው አልፏል፤ የጸጥታ አካላት ተገድለዋል፡፡ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የግለሰቦች፣ የሕዝብና የመንግሥት ንብረት ወድሟል፡፡
በቅድሚያ በሑከቱ ሕይወታቸው ላለፈው ወገኖቼ የተሰማኝን ኀዘን መግለት እወዳለሁ፡፡ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን እመኛለሁ፡፡ መንግሥት ከማኅበረሰቡ ጋር በመሆን የተጎዱትን ለማቋቋም እንደሚሠራ፤ ወንጀለኞቹንም ለፍርድ የማቅረቡን ሂደትና የሕግ የበላይነትን ማስከበሩን እንደሚቀጥል በዚሁ አጋጣሚ በድጋሚ ላረጋግጥላቸው እወዳለሁ፡፡
ሁላችንም እንደምናውቀው የፖለቲካ መዝገበ ቃላችን የተሞላው ‹ምታው፣ ደምስሰው፣ ቁረጠውና ፍለጠው› በሚሉ የሞት ቃላት ሲሆን በመሳደድና ማሳደድ ዙሪያ መሽከርከር ከጀመረ ዘመናት ተቆጥረዋል። “ድርጊት ሲደጋገም ልማድ ይሆናል” እንዲሉ አሁን ያለው የፖለቲካ ባህላችን የተቀዳው ባንድ ወቅት እንደቀልድ በጀመርናቸው የሴራ፣ የመገዳደልና በጎራ ተከፋፍሎ ድንጋይ የመወራወር አጉል ልማዳችን ነው። በያጋጣሚው ሲነገር፣ ሲጻፍና ሲዜም የኖረው ይሄ የተበላሸ ፖለቲካችን በትውልድ ጅረት ተንከባልሎ እነሆ ዛሬ ላይ ደርሷል።
ይሄው እኛም እንደ መልካም ውርስ የመጠላለፍና የመገዳደል ባህልን ተቀብለን የየዕለት ኑሯችን በቆምንበት መርገጥ፣ ዛሬም ነገም አንድ ቦታ መሽከርከር ሆኗል። ሀገራችንን ወደፊት ለማራመድ የምንሻ ከሆነ ይሄንን ክፉ ውርስ አሽቀንጥረን መጣል ይኖርብናል፤ በመጥፎ ባህል ያደፈ ካባችንን አውልቀን በምትኩ በጋራ የምንበለጽግበትን ካባ ልንደርብ ይገባል። ለውጥ ሰዎችን በሰዎች፣ መሪዎችን በመሪዎች የመቀየር ሂደት ብቻ አይደለም። የተበላሸውን የፖለቲካ ሥነ ልቡና፣ የፖለቲካ ባህልና የፖለቲካ ሥርዓት ጭምር በአዲስ የመቀየር ጉዞ ነው። ተቋሞቻችንን፣ የእርስ በርስ ግንኙነታችንና የፖለቲካ ቋንቋችንን ጭምር መለወጥ ይገባናል። ይሄን ማድረግ ከቻልን እንደሀገርና እንደ ሕዝብ ወደ ምናስበው የብልጽግና ሠገነት እንሻገራለን። ካልሆነም የኋቀርነት አዘቅት ውስጥ ስንደፋደፍ ዘላለም መኖራችን ነው።
ሁላችንም ልብ ካልን ምንጊዜም ከመከራ የሚያተርፉ አካላት በዙሪያችን እንዳሉ እንረዳለን። የከብት እልቂት ለገበሬ መከራ ቢያመጣም ለጅብ ግን ሠርግና ምላሽ ነው። የዶሮ እልቂት ለባለቤቱ ኪሳራ ለሸለምጥማጥ ደግሞ ትርፍ ነው። የሁለት በጎች ጠብ ጥቅም ካስገኘ የሚጠቀመው ተኩላውን ነው። የሁለት ርግቦች ግብግብ አንጋጦ ለሚጠብቃቸው ድመት በረከት ነው፡፡ ምንም መልፋት ሳይጠበቅባቸው ድመቱና ተኩላው በርግቦቹና በበጎቹ ጸብ ምክንያት በቀላሉ ሆዳቸውን ይሞላሉ፡፡ በተመሳሳይ በሰዎች ጸብም የሚያተርፉ ሞልተዋል። በእኛም ሀገር አሉ። አሁንም እርስ በእርሳችን እያጋጩን ከፍተኛ ጥቅም የሚያገኙት እነዚሁ ከቅርብም ከሩቅም ሆነው የሚጠብቁ የግጭት ነጋዴዎች ናቸው።
ለለውጥ ስንታገል ዋነኛው ዱላ የሚሠነዘርብን ከመከራችን ሲያተርፉ ከነበሩ አካላት እንደሆነ ግልጽ ነው። በሁላችንም ቤት ለዘመናት የተዘራ የልዩነት መርዝ አለ፡፡ አሁን እዚህም እዚያም ሲፈነዳ የምናየው እሱን ነው። ፈንጂው ዛሬ ቢፈነዳም ከተቀበረ ግን ቆይቷል። የግጭት ፈንጁ ምን እንደሆነ፣ የት የት እንደተቀበረ፣ በማን እንደተቀበረ ማወቅ ለአንድ አካል የሚተው የቤት ሥራ ሳይሆን የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ነው። ማወቅም ብቻውን በቂ አይደለም፤ አንድ በአንድ እየተቀለቀመ መክሸፍ ይኖርበታል። ሕዝብ እንዲበጣበጥ፣ አንዱ ብሔር በሌላው ላይ እንዲነሣ፣ አንዱ ሌላውን እንዲገድል፣ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያውያንን ንብረት እንዲያወድሙ፤ የጥላቻና የሞት ድግስ ቅስቀሳዎች በየሚዲያው እንዲካሄዱ የሚያደርጉት ፈንጅ ቀባሪዎቹ የግጭት ነጋዴዎች ናቸው። አንዳንዶች ከእነሱ ጋር ተባብረው በሕዝብ ላይ ፈንጅዎቹን ያፈነዳሉ። ሳያውቁ ቆመውበት የሚፈነዳባቸውም ይኖራሉ። አንዳቸውም ጉዳትን እንጂ ጥቅም አያስገኙልም፡፡ ከእንግዲህ ይበቃል፤ በጉያችን ይዘን ዘወትር መሰቃየት የለብንም፡፡
የሀገሬ ልጆች፣
አንገትን እንደ ሰጎን አሸዋ ውስጥ በመቅበር መፍትሔ የምናገኝበት ጊዜ ላይ አይደለንም። አጥፊዎቹን ፊት ለፊት እስካልተጋፈጥናቸው ድረስ የሚያደርሱትን ችግር በመሸሽ ብቻ አናመልጠውም። ላለማየት ጭንቅላትን ጎሬ ውስጥ በመቅበር ዘላቂ መፍትሔ ይገኛል ማለት ዘበት ነው። ዛሬ ጎረቤታችንን የጎበኘ እሳት ነገ ቤታችንን ማንኳኳቱ አይቀርም። ተነጣጥሎ አንድ ባንድ ማገዶ ከመሆን ይልቅ ተባብሮ የተለኮሰውን እሳት እስከወዲያኛው ማሰናበት ይበጃል። ለዚያም ነገሮችን በጥንቃቄ መመልከት፣ ትዕግሥትና አርቆ አስተዋይነት በተሞላበት መልኩ መገምገምና ጥበብ ባለው ሁኔታ ተንቀሳቅሶ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል።
ማን ነው በየአካባቢያችን ሰላም እየነሣን ያለው? ከነማን ጋር ሆኖ ነው የሚበጠብጠን? ለምንድን ነው የሚበጠብጠን? ጥቂት ነውጠኞች የጫሩት እሳት ብዙኃኑን ሲለበልብ ለምንድን ነው እኛስ ማስቆም ያልቻልነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ከያንዳንዳችን ይጠበቃል። እሳት ለኳሾቹ እነማን እንደሆኑ፣ ማገዶ እያቀበሉ እሳቱን የሚያባብሱት እነማን እንደሆኑ፣ ዳር ቆመው የሚያዩትና አብረው የሚሞቁት ጭምር እነማን እንደሆኑ ልናውቅ ይገባል። በመንግሥት በኩል እነዚህን ጥያቄዎች በየደረጃው ለመመርመርና አስፈላጊውን ሕግ የማስከበር ርምጃ ለመውሰድ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ቁርጠኞች ነን።
እሳቱን ማጥፋት ሲገባቸው በቸልታ የሚያልፉት ሰዎች በአንድም በሌላም መንገድ መከራችንን የሚያበዙብን መሆናቸው አያጠያይቅም። የሚወድመው የሀገር ሀብት፣ የሚሞተው የሁላችንም ወገን ነውና ሕጋዊና ሞራላዊ ኃላፊነት እያለባቸው አይተው እንዳላዩ የሚያልፉ አካላት ፈጽሞ ከተጠያቂነት አያመልጡም።
የተጋረጠብን ችግር እስከወዲያኛው እንዲወገድ ወላጆች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የየአካባቢው የባህልና የሐሳብ መሪዎች አስተዋጽኦችሁ ከፍተኛ ከመሆኑ አኳያ ያለማመንታት ሚናችሁን እንድትወጡ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ። ከምንም በላይ ሕዝባችን አስፈላጊውን ሁሉ ከማድረግ መቆጠብ እንደሌለበት ሊታወቅ ይገባል። እያንዳንዱ ዜጋ ጥፋተኞቹ በማስረጃ ለፍርድ እንዲቀርቡ የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት አለበት፤ ከሕግ አስከባሪዎች ጋር ተባብሮ መሥራት፣ የመንደሩንና የከተማውን ሰላምና ልማት ተደራጅቶ መጠበቅ አለበት። በየአካባቢው የተለየ እንቅስቃሴ ስናይ ለምን? ብለን ልንጠይቅ፤ እነማን እንደሆኑ ልናውቅ፤ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን አጥፊዎችን ለሕግ ልናቀርብ ይገባል። ጎረቤቶቻችንን፣ የልማት ተቋማትን፣ የንግድ ድርጅቶችን፣ ሕዝባዊ ንብረቶችን፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን፣ የእምነት ተቋማትን፣ የትምህርትና የጤና ተቋማትን በጋራ እስካልጠበቅናቸው ድረስ ነገ የጉዳቱ የመጀመሪያ ሰለባዎች እኛው ስለመሆናችን ነጋሪ አያሻንም።
ለሚያልፍ ጊዜ የማያልፍ ጠባሳ እንዲቀመጥብን መፍቀድ የለብንም። የትላንቶቹ ጠበሳ ስላቆዩልን እኛ የዛሬዎቹ ምን ያህል አበሳ እያጨድን እንደሆነ ሁላችንም የሚገባን ይመስለኛል፤ ስለሆነም ከዚህ ስሕተት ተምረን ዳግም አበሳው ወደ ልጆቻችን እንዳይሻገር ማድረግ የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ነው። በጉያችን ታቅፈናቸው የሚዘርፉን፣ የሚያቃጥሉን፣ የሚያበጣብጡንና የሚያገዳድሉን ሰዎች የጊዜ ጉዳይ እንጂ የእጃቸውን ማግኘታቸው፤ ከእነሱ አልፎ በልጆቻቸው በኩል ብድሩን መክፈላቸው አይቀሬ ነው።
ውድ ኢትዮጵያውያን፣
ሀገሩንና ሕዝቡን እንደሚወድ ዜጋ ከእያንዳንዳችን ሁለት ነገሮች ይጠበቁብናል። ከተጎዱ ወገኖቻችን ጎን መቆምና አለኝታነታችንን ማሳየት አለብን። የቦታ መቀያየር ይሆናል እንጂ እኛም አንድ ቀን በተጎጂዎች ቦታ የማንቆምበት ምንም ምክንያት የለም። ስለሆነም በሞራል፣ በኢኮኖሚና በባህላዊ መንገድ ደግፈን ተጎጂዎችን ወደነበሩበት እንመልሳቸው። የተቃጠለና የወደመ ንብረታቸውን ለመተካት አጋርነታችን እናሳያቸው፤ ቁስላቸው ጠገግ እስኪል እናክማቸው፤ የፈረሰ ቤታቸውን እንገንባላቸው። የማይተካ ሕይወታቸውን ለተነጠቁ ዜጎቻችን ጸሎት፣ ለሟች ቤተሰቦች መጽናናት እንዲያገኙ እናድርግ። በሁሉም ዘርፍ ያሉ መሪዎች ለዚህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ግንባር ቀደም ሆነው መልካም አርአያነታቸውን እንደሚያስመሰክሩ እተማመናለሁ።
ሰላማችንን ለማስጠበቅ ደፋ ቀና ሲሉ የተሰዉት ፖሊሶችና የጸጥታ አስከባሪዎች ያለእነሱ ትጋትና መሥዕዋትነት የሚደርሰውን አደጋ በቀላሉ መቆጣጠር ባልቻልን ነበር፡፡ ለሀገርና ለሕዝብ ደኅንነት ሲሉ የቆሰሉና የሞቱ የሕግ አስከባሪዎች የከፈሉት የሕይወት ዋጋ በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ በክብር የሚታተም ስለመሆኑ አልጠራጠርም። ለሟች ቤተሰቦቻቸው፣ ለወላጅና ለልጆቻቸው ጭምር ተገቢውን ክብር እንሰጣለን።
በመንግሥት በኩል ዐቅም በፈቀደ መጠን የተጎዱትን ንጹሐን ዜጎችና የሕግ አስከባሪዎች ለመደገፍና ለማቋቋም ይሠራል። በሌላ በኩል የችግሩን ነዳፊዎች፣ ጠንሳሾች፣ ተልዕኮ ተቀባዮችና ፈጻሚዎችን በየደረጃው መርምሮና አጣርቶ ለሕግ ያቀርባል። ይሄን መሰል ክሥተት ዳግም እንዳይፈጠርም ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የጸጥታ አካላት ሥምሪትን አጠናክሮ ይቀጥላል።
ከዚህ በተረፈ ሁላችንም ውድመትና ጥፋት ከእንግዲህ በሀገራችን ላይ እንዳይደገም አምርረን እምቢ ማለት ይኖርብናል። ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ለፖለቲካ ትርፋቸው ሲሉ በየሚዲያው ‹በለው፣ በለው› የሚሉ አካላትን አሁን በግልጽ ነቅሰናቸዋል። በየአካባቢያችን የሚገኙትን የግጭት ነጋዴዎች በሚገባ ዐውቀናቸዋል። መረባቸውን እየበጣጠስነው ነው፡፡ ለጊዜው የተደበቁ የሚመስላቸውም በቅርቡ አደባባይ ይወጣሉ። እሳቱን ለኩሰው ጢሱ እንዳይሸታቸው መሸሽ፤ ፈንጂውን ወርውረው ፍንጣሪ ሳይነካቸው እስከመጨረሻው ማምለጥ አይችሉም። ሰላም ወዳዱ ሕዝባችን በእሳት እየተቃጠለና ሕይወቱን እየተነጠቀ ከእንግዲህ ይቀጥላል ማለት ዘበት ነው። አብሮነትን የሚፈልገው ዜጋችን፣ ለማደግና ለመበልጸግ ሌት ተቀን ደፋ ቀና የሚለው ሕዝባችን እየተጎዳ የግጭት ነጋዴዎቹ በምቾት አይቆዩም።
በሕዝብ መከራ ካላተረፍን ለሚሉ፤ በምስኪን ዜጎች ሞት ሥልጣን ለመያዝ ለሚቋምጡ ራስ ወዳዶች ‹አሻንጉሊት› መሆን ከእንግዲህ ይበቃል። ሰላማችንና ልማታችን፣ ዕድገታችንና ብልጽግናችን ደንታቸው ከሆኑ አካላት ጋር አበሳን እንጂ መልካም ነገርን ስለማናጭድ ከጉያችን ፈልቅቀን ብቻቸውን ይቆማሉ። ምክር ካልመለሳቸው መከራውን ፈልገዋልና በሚገባቸው መንገድ እንዲጓዙ እንተዋቸዋለን።
ክቡራትና ክቡራን፣
የሐሳብ ልዩነት ጌጥ እንጂ እርግማን አይደለም። የተሰማንን መግለጽና ጥያቄዎቻችንን ያለ ሥጋት ማንሣት እስካዛሬ የታገልንለት ወሳኙ መብታችን ነው። የዚያኑ ያህል በሀገራችን ነገሮች በሥርዓት እንዲከናወኑ፣ የአንዱ ጥቅም የሌሎችን መብት እንዳይጋፋ እና ዜጎች ሰላምና ደኅንነታቸው ተጠብቆላቸው በሀገራችን እንዲኖሩ ማስቻል የሁሉም ኢትዮጵያዊ ምኞት ነው። ኃይል እስካልተቀላቀለበት ድረስ የሐሳብ ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ ማስተናገድ ለዘመናት የታገንለትን መብት ከማጎናጸፍ ባለፈ የሌሎች ዜጎችን ሰላምና ደኅንነት እንዲጠበቅ ያደርጋል። ሐሳብ የሚሞገተውም የሚሸነፈውም በሌላ ሐሳብ እንጂ በጉልበት፣ በነውጥና በዐመጽ አይሸነፍም፤ ተሸንፎም አያውቅም። መነጋገር፣ መከራከርና መወያየት እንጂ መጠፋፋት ሥልጣኔን አምጥቶ እንደማያውቅ ማገናዘቢያ አዕምሮ ያለው ሰው ሁሉ በቀላሉ የሚረዳው ሐቅ ነው። ወገኖቼ፣ ሌላው መታወቅ ያለበት ጉዳይ የምንገኝበት ወቅት ብዙ ጊዜ የማይሰጡ ፈተናዎች ከፊታችን የተደቀኑበትና ወሳኝ ድሎችን የምናሳካበት ወቅት እንሆነ ሊረሳ አይገባም። የግብርና ሥራችንን ሳይስተጓጎል መከናወን አለበት። ምርታማነትን በመጨመር ከውጭ የምናስመጣውን የምግብ እህል ጭምር ሊተካ በሚቻልበት አኳኋን ሥራችንን መቀጠል ይኖርብናል። ከገጠር ግብርናችን በተጨማሪ የከተማ ግብርና ላይ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ። አምራች ኢንዱስትሪው የኮሮናን ሁለንተናዊ ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚያስችሉ ምርቶችን ለማምረት ሌት ተቀን መድከም አለበት። ከዚሁ ጎን ለጎን እየተባባሰ የመጣውን የኮሮና ወረርሽኝ ተቋቁመን ለመዝለቅ የጥንቃቄ፣ የምርመራና የሕክምና ተግባሮቻችንን ሳንዘናጋ እንፈጽማለን። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታችንን እያጠናቀቅን በዕቅዱ መሠረት የመጀመሪያውን የውኃ ሙሌት ሥራችንን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እናከናውናለን። በዚህ ክረምት ለመትከል ያቀድነው የአራት ቢሊዮን ችግኞች “የአረንጓዴ አሻራ” መርሐ ግብርም ጥንቃቄ ባልተለየው መልኩ ተግባራዊ እናደርጋለን።
ምንም እንኳን ዛሬ የደረሰብን ፈተና ቢያሳምመንም የምንሠራው ለሀገር ነውና የነገውን ማየት አለብን። ሕዝብና ሀገር ይቀጥላሉ። ትውልድ ይቀጥላል። የተሻለ ትውልድ ፈጥረን የተሻለች ሀገር ማስረከብ ደግሞ ከኛ የሚጠበቅ የቤት ሥራ ነው። ነገሮች ወደ በጎ እልህና ቁጭት እንጂ ወደ መጥፎ ቁዘማና ትካዜ ሊወስዱን አይገባም። ችግሮች ትምህርት እንጂ እሥር ቤት ሊሆኑብን አይገባም። ሕዝብ መሥራት ያለበትን ባግባቡ ከሠራ፤ መንግሥትም ያለበትን ኃላፊነት በብቃት ይወጣል። ከከባድ ክረምት ማዶ መልካም አዲስ ዘመን ቆሞ እንደሚጠብቀን ሁሉ የሌሊቱን ግርማ የሚያሸንፍና ጽልመቱን የሚደመስስ የብርሃን ጸዳል ማልዶ ወደኛ እንደሚገሠግሥ ሁላችንም እናውቃለን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ 
ለዘላለም ትኑር! 
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ! 
ሐምሌ 10 ቀን 2012 ዓ.ም
Filed in: Amharic