>

ሳይለካ የተቆረጠው የኦነግ ፖለቲካና መጨረሻው፡፡ (አሰፋ ታረቀኝ)

ሳይለካ የተቆረጠው የኦነግ ፖለቲካና መጨረሻው፡፡

አሰፋ ታረቀኝ


የ 1966ቱን የአብዮት ፍንዳታ ተከትሎ ምስቅልቅል ዉስጥ የገባው የኢትዮጵያ ፖሊቲካ የሰከነ ባለቤት ሳያገኝ ሃምሳ አመቱን ሊደፍን ነው፡፡ ህዝባዊ አብዮቱን መርቸ ከግብ አደርሰዋለሁ ያለው ደርግ፤ ሥልጣን ከተቆናጠጠበት ጊዜ ጀምሮ የረባ እረፍት ሳያገኝ 17 ዐመት ሙሉ ራሱንም ሀገሪቱንም ሲያዋክብ ኖሮ፤ በሥነ ምግባር ድህነት ለተራቆቱ ህዋህቶች አስረክቦ ተበታተነ፤ ታዲያ መዘንጋት የለለበት ጦርነቱ ተገዶ የገባበት እንጂ ደርግ ፈልጎት የመጣ ወይም በተንኳሺነት የቀሰቀሰው አልነበረም፡፡  

ከ 1950ወቹ መገባደጃ ጀምሮ ‘መሬት ላራሹ የብሄረሰቦች እኩልነት ይከበር’ እያለ ይታገል የነበረው ትውልድ በፖለቲካ ድርጅቶች ተቧድኖ በሥልጣን አያያዝና በርእዮተ ዓለም አተገባበር ላይ መግባባት ተሣነው፡፡ ያ አለመግባባት ባስከተለው ጦሥ  በሁለት ክፍለ ዘመን ሊተካ የማይችል ምርጥ ትውልድ እንደ ቅጠል ረገፈ፤ ስንትና ስንት እውቀት የታጨቀበትን አእምሮ በጥይት በርቅሶ በቴሌቪዢን መስኮት ማሳየትና በጸረ አብዮተኞች ጥይት የወደቁ ጓዶች እያሉ ሥም ዝርዝር ማንበብ ተዘወተረ፡፡ ሀገሪቱን ትውልድ አልባ ያደረገው ጭፍጨፋ ቀይና ነጭ በሚል ብቻ ሳይወሰን ስልጣን የያዘው ክፍል ፋሺስት የሚል ስም ሲወጣለት፡ እሱም ለተቃዋሚው አምስተኛ ረድፋኛ/ግልገል ፋሺስት/ የሚል የክርስትና ስም ሰጠው፡፡ ያ በሃገር ፍቅር የነደደና የለውጡን ፍሬ ቶሎ ለማየት የጓጓ ትውልድ፤ ቁጭ ብሎ ለመነጋገርና መፍትሄ ለመፈለግ የባህል እሴቱ ስላልፈቀደለት፤ ፍላጎቱን በአፈሙዝ ለማሳካት ሲል በጠላትነት የፈረጀውን ሁሉ በተገኘበት መረሸኑን ተያያዘው፡፡ ኢትዮጵያ እንደሀገርና ኢትዮጵያውያን እንደ ህዝብ የሃዘን ማቅ ለበሱ፡፡ በጣም አጭር በሆነ የጊዜ ክልል ውስጥ ያንን የመሰለ ትውልድ ማጣት፡ ኢትዮጵያን ትህነግን ለመሰለ የማፊያ ቡዲንና የሰውን ልጅ እንደሸንኮራ አገዳ በስለት እያስጨፈጨፈ የሚደሰት ኦነግ የሚባል ድርጅት መፈንጫ አደረጋት፡፡ ከፍጂት የተረፈውም ተሸማቅቆ እንድኖር በመገደዱ፤ ውሸቱ እንደእውነት፤ ተረቱ እንደታሪክ ሲሰበክ ጸጥ ብሎ ማዳምጥን መረጠ፤ 

ጸረ ኢትዮጵያዊነትን ከቀደምት አያቶቻቸው የወረሱት መለሰ ዜናዊ የኢትዮጵያን ታሪክ ወደ አንድ መቶ አመት ሲያወርዱት፤ የዛሬው አዛውንትና የያኔው ጎልማሳ አቶ ሌንጮ ለታ ደግሞ በ 1985 ዓ. ም በወቅቱ  የ ‘ነጻው ፐሬስ’ አባል ከነበረው ሳሌም መጽሄት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ‘ We are Abyssinian subjects. We need to negotiate to live together’. “እኛ የአቢሲኒያውያን  ተገዥወች ነን፤ አብረን ለመኖር መድራደር ይኖርብናል” ነበር ያሉት፡፡ አቶ መለስ የመቶ አመቷ ወጣት ኢትዮጵያ ከየት ጀምራ የት እንደምትደርስ ሳይነግሩንና እንዳፌዙብን  ሞት ቀደማቸው፤ አቶ ሌንጮም ‘ቅኝ ገዧ’ አቢሲኒያ የጂኦግራፊ ክልሏ ከየት እስክየት እንደሆነ ሳይነግሩን የአቋም ለውጥ አደረግሁ አሉና አዳፈኑት፡፡ ለነገሩ ሁለቱም እየተሸዋወዱ ያስቁን ነበር፡፡ አቶ መለስ የኢትዮጵያን ዕድሜ ወደ መቶ አመት ዝቅ ሲያደርጉ ‘የምኒሊክ ወረራ’ የሚለውን የኦነግን የጃጀ ፖሊቲካ ውሀ እያጠጡ አባላቱን ማስፈንጠዛቸው ሲሆን፤ ለአቶ ሌንጮ  ለታ አቢሲኒያ አማራና ትግሬ ማለት ነው፤ በሌላ አባባል አቶ መለስን “ቅኝ ገዥ’ ነህ እያሏቸው ነበር፡፡ የሚገርመው አቶ መለስ ዕሞትለታለሁ ይሉት የነበረውን ድርጅታቸውን ‘ሰው አልባ’ አድርገውት ወደ እማይቀረው አለም ከሄዱ ከስድስት ኣመት በኋላ ድርጅታቸው ጓዙን ጠቅልሎ ወደ መንደሩ ወደትግራይ የተመለሰ ሲሆን፤ የአቶ ሌንጮ ለታ ኦነግ ግን እንደ አሜባ ራሱን እያራባ ሀገር ማመሱን ተያይዞታል፡፡ የአሁኗን ኢትዮጵያ በመገንባቱ ሂደት ውስጥ ኦሮሞወች ድርሻ እንዳልነበራቸው፤ እንዲያውም ኦሮሞ ቅኝ እንደተገዛ ተደርጎ የተዘራው የኦነግ ተረት እውነተኛ ታሪክ እስኪመስል ድረስ ተሰበከ፤ ኦነግ በትግል ጓዱ በህዋህት ታግዞ በቀረጸው የትምህርት ፖሊሲ አማካይነት ባባቶቹ ታሪክ ላይ የሸፈተ ብቻ ሳይሆን ኦነግ ከቀባለት ቀለም ውጭ ሌላ ማየት የማይችል ትውልድ ተፈለፈል፡፡

በሃሣብ ገበያ ላይ ወጥቶ የሚሸጥ ቁምነገር ማመንጨት የተሣነው ኦነግ በውስጥም ምውጭም ተቀባይነት ሲያጣ፤ ሀገራችን ነው ብለው በኦሮሞ ወገኖቻቸው መካከል ኑሮ የመሰረቱትን ሌሎች ጎሣወች በተለይም አማራውን ማስጨፍጭፍና ማሳረድን ሥራየ በሎ ይዞታል፡፡ እዚህ ላይ ስደርስ የአንድ ምሁር ማስታወሻ ላካፍላችሁ፡፡  ወሎየው ዶ/ር አሰፋ እንደሻው “ለሃገር የተመደበ ህይወት” በተሰኘውና ባልታተመው መጽሀፉ ገጽ 15 ላይ “ የደርግ መንግሥት እንደወደቀ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር(ኦነግ) ወደ ቦረና ጎራ ብለው የኔን ቤተሰቦች ለመስበክና ወደ ዱሮው ክትክት እንዲመለሱ ለመጎትጎት ሞክረው ነበር፡፡ አጎቴ አሊ እንደነገርኝ “ እናንተ ቀጣፊ ሌቦች የማታውቁትን ስትፈተፍቱ አንድ ነገር ሳይደርስባችሁና ሰው ሳይሰማ ሹልክ ብላችሁ ጥፉ” ብሎ እንዳባረራቸው ነገረኝ” ይላል፡ ያልተቀደሰው የህዋህትና የኦነግ ጋብቻ ቶሎ ባይፈርስ ኖሮ፡ ወሎም የኦነግ የጦርነት ቀጠና መሆኗ የማይቀር ነበር፡፡ ለነገሩ ሁለቱ ጸረ ኢትዮጵያ ድርጅቶች ደም ተቃብተው ያፈረሱትን የፖለቲካ ጋብቻ በዕርቅ አድሰው በዶ/አብይ መንግሥት ላይ ጦርነት ካወጁ ወድህ፤ ሰውን ሰው በመሆኑ ብቻ በማክበር በሚታወቀው የወሎ ሕዝብ መሀል፤ ኦነግ እኩይ አላማውን ተግባራዋ ለማድረግ ሁለት ጊዜ ሙከራ አድርጎ በውርደት ተመልሷል፡፡ኦነግ ኢትዮጵያን የሚያይበትን መነጽር ከየት እንደተዋሰው ማመን ያስቸግራል፡፡  በእምየ ምንልክ ዘመን ታላላቆቹ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ኦሮሞወች ነበሩ፤ ንጉሥ ኀይለሥላሴም ሆኑ ባለቤታቸው ዕቴጌ መነን አስፈው ኦሮሞወች ነበሩ፡፡ ባልቻ አባነፍሶን፤ አባመላ ሀብቴን፤ ጃገማ ኬሎን፤ ራስ አበበ አረጋይን፤ ሙሉገታ ቡሊን፤ ጀኔራል አበበ ገመዳን፤ ሀገር ብቻዋን እንድትቆም ተፈርዶባት በነበረበት  ወቅት (1967 1973)፤ በምሥራቅም በሰሜንም የኢትዮጵያን ሰራዊት የመሩት ጀግኞች ማለትም፤ ጀኔራል ረጋሣ ጂማ፤ ጀኔራል መርዕድ ንጉሤ፤ ጀኔራል ደምሴ ቡልቶ የኦሮሞ ልጆች እንደነበሩ ለኦነግ ትውልድ ማስረዳት ፈጽሞ አይቻልም፤ የመሰማት ዕድል ካገኘሕም በቁምሕ የምትቃዥ እንጅ ትናንት የተፈጸመን ድርጊት እያብራራህ መሆኑን ፈጽሞ አይቀበሉም፡፡

የኦነግ ጂማሮ የተሣሣተ ስለነበረ 47 አመት ሙሉ ቢንገታገትም የሰውን ልጅ እንደ እንጨት በገጀራ ከማስጨፍጨፍ በስተቀር ለኦሮሞ ህዝብ አንዳች የፈየደው ነገር የለም፤  ኦነግ ደርግ እንደወደቀ በህዋህት ጀርባ ታዝሎ አዲስ አበባ ገባ፡፡ መሪውቹ ተጣላን አሉና ክመቀለጃው የኢህደግ ምክርቤት ለቀቅን ብለው በማወጅ፤ የታጠቀውን ጦር ለህዋህት እሥር ቤት አስረክበውና ትግሉን ተሰናብተው በቦሌ ወደ ውጭ ወጡ፤ አፈናና ሥቃይ በጨመረ ቁጥር  የተቃውሞ መባባስ የተፈጥሮ ህግ ነውና ኦነግ አጋልጦት ቢሸሺም የኦሮሞ ወጣት ጸረ ህዋህት ትግሉን አጠናክሮ ቀጠለ፡፡

እብሪት የወጠረው ህዋህት በኦሮሞ ወጣቶች ትግል መዋከቡ ሣያንሰው፤ ጎንደር ዘልቆ ኮሮኔል ደመቀ ዘውዱን አፍኖ ለመውሰድ ያደረገው ሙከራ በአስደንጋጭ ሁኔታ ከመክሸፉ በተጨማሪ  ‘የኦሮሞ ደም የኔም ደም ነው’ ብሎ ጎንደሬው ከዳር ዳር  በመንቀሣቅሥ፡ የህዋህትን መተንፈሻ እያጠበበው መጣ፡፡ የነ ዶ/ር አብይ ወደ ሥልጣን መምጣት የህዋህትን ዕድሜ ማጠር አመላካች ነበር፡፡ ዶ/ር አብይ ወደ ሥልጣን አንደመጡ፤ በህዋህት እየተወነጀሉ የታሰሩትን ፈቱ፡ በስደት ያሉትን ወደ ሀገራቸወ እንድገቡና በሀገር ግንባታው ላይ እንድሳትፉ ጋበዙ መድረኩንም አመቻቹ፡፡የሀገራቸውን ሰማይ እንዳያዩ ከተፈርደባቸው የፖለቲካ ድርጅቶ መካከል አንዱ ኦነግ ነበር፡፡  ኦነግ ከኤርትራ ተንቀሣቅሶ መቀሌ ላይ በህዋህት ግብዣ ተንበሺብሾ አዲስ አበባ እንደደረሰ  የአመጽ እጁን ዘረጋ፡፡ በቡራዩና በሰበታ ጋሞወችን እንደቅጠል አረገፋቸው፡፡ከ 1983 ጀምሮ ብቻውን ይረሸን፤ ይታረድ የነበረው አማራ፤ በኦነግ የእልቂት ኢላማ የሆነ የጋሞን ብሄረሰብ የሞት አጋር አገኘ፡፡ ሰሞኑን በተከፈተው የእልቂት ምዕራፍ ደግሞ ኦሮሞ መሆንም ከሞት አላስመለጠም፡፡ በ 47 አመት “የትግል” ዕድሜ አንድት ቀበሌ ንጻ አውጥቶ የማያውቀው ኦነግ፤ በሰላም የተቸረለትን መድረክ ወደ አመጽ ቀየረው፡፡ ያደረገው ሙከራ ሁሉ አላዛልቅ ሲለው፤ ከወንድሞቹ ከነ ዶ/ር አብይ ጋር ከመነጋገር ይልቅ ህዋህትን መረጠና ትውልድን የማጥፋት፡ ሀገርን የመበተን ሥራውን ተያያዘው፤ ተደግሶ ለነበረው እልቂት እንደነዳጅ ሆኖ እንዲያገለግል የተፈረደበት ደግሞ ወጣቱና ታዋቂው የጥበብ ሰው ሀጫሉ ነበር፡፡ የመጨረሻ ግቡ ደግሞ የዶ/ር አብይን መንግሥት ማስወገድ ነው፡፡ ግን ለምን?

ከኮሎኔል መንግሥቱ ሐይለማርያም በኋላ ኢትዮጵያን በሙሉ ስሟ ጠርተው ታሪኳን ወደ ሀዲዱ የመለሱት ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ ናቸው፤ ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ደግሞ ህዋህቶችና ኦነጎች ከምንም ነገር በላይ ይጠሉታል፡፡ በሰሞኑ የ”Down Down Amhara and down down Ethiopia”. “ኢትዮጵያ ትውደም አማራ ይውደም” መፈክራቸው፤ እንደ ሀገር በኢትዮጵያ ላይ፤ እንደ ሕዝብ በአማራ ላይ ያላቸውን ሥር የሰደደ ጥላቻ በግልጽ ለአለም አሣይተዋል፡፡ 

 የጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ራዕይ ሁሉም ብሄረሰቦች የሚኮሩባት፤ መታወቂዋ ብልጽናና፤ ሰላም የሆነ፤ ዘመናዊ ዕውቀትን የተካነ ሀገር ወዳድ ትውልድ የምታስተናግድ ኢትዮጵያን መፍጠር ሲሆን፤ የፖለቲካውን ሸማ ሳይለካ የቆረጠው ኦነግ ደግሞ ከደረሰበት የፖለቲካ ኪሣራ የተነሳ፤ ህጻን ሺማግሌ፤ ነፍሰጡር አራስ ሳይለይ የሰውን ልጅ በስለት መዘልዘል፤ ሰውን ቤት ውስጥ ዘግቶ በሳት ማጋየት፤ የልማት ተቋማትን ማውደም፡ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር መተባበርና ዕድገቷን ማደናቀፍ፤ ሰላሟን ማናጋት ነው፡፡ ኦንግ ዕድገቷ በቀጨጨ፤ ሰላሟ በደፈረሰ ኢትዮጵያ ውስጥ ምን አይነት ኦሮሚያን ሊገነባ እንደፈለገ፤ ገጀራ አሸክሞ ለጭፍጨፋ የሚያሰማራቸው ቀርቶ፤ ቀና ነገር አበርክቶ ለማለፍ ያልታደሉት ጎሰኛ  ዶክተሮች ማለትም የአውስትራሊያው ጸጋየ አራርሳና የአሜሪካው ሕዝቃኤል ጋቢሳም የሚያውቁት አይመስልም፡፡ አንድን የፖለቲካ ድርጅት ለዘላቂና ለተራዘመ ድል የሚያበቃው እወክለዋለሁ የሚለው ህዝብ ብዛትና በፈጠራ የታጀበ ታሪክ መሰል ተረት ሳይሆን፤ መነሻውን በእውነት ላይ፤ መዳረሻውን በህዝብ ሰላምና በሀገር ዕድገት ላይ ሲያደርግ ነው፡፡ ብልሁ የሀገሬ ገበሬ “ ሦሥት ጊዜ ለካ አንድ ጊዜ ቁረጥ” ይላል፡፡ ህዋህቶች ደደቢት በረሀ ላይ ሳይልኩ የቆረጡትን የፖለቲካ ሸማ አንጠልጥለው መጥትው በኢትዮጵያ ልክ ግጠም ቢሉት አልሆን ሲላቸው፤ 27 አመት ሙሉ ከሌብነትና ከውንብድና ወጥተው መንግሥት የመሆን ባህርይ ሳይላበሱ ወደመጡበት ተመለሱ፡ 

ህዋህት ከመፈጠሯ በፊት አመታትን ያስቆጠረው ኦነግ የኦሮሞን ልጆች ደም ለማፍሰስ የህዋህት ታዛዥና ጉዳይ አስፈጻሚ ሆኖ ሲመጣ፤ ነገሩን ለታሪክ ፍርድ ከመተው በስተቀር በቃላት መግልጽ ያስቸግራል፡፡ እሱ ብቻም አይደለም፤ ዘመኑን ሁሉ የኢትዮጵያን ፖልቲካ ወደመኅል መምጣት አለበት እያለ ሲታገል የኖረው ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እሱ ራሱ ወደዳር ወጥቶ እራሱን እንደ አማራጭ መንግሥት ከሚቆጥረውና የዘር ፍጅት ማስተጋቢያ ሜዳ ባለቤት ከሆነው ጁሀር ሙሃመድ ጋር ሸርጉድ ሲል ማየት ያሳዝናል፡፡ ምክንቱም ለኦሮሞ ብቻ ሣይሆን፤ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላምና ብልጽግና ሲታግል እንደሁላችንም ወርቃማ የወጣትነት ዘመኑ በእሥር ቤት ባክኖበታል፡፡ 

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ የሚመኟትን ኢትዮጵያን ሳያዩ ምንም አይሆኑም፤ ምክንቱም ዕቅዳቸው እንኳን ለሰው ልጅ ለዱር ነፍሳትም የሚመች ነውና፡፡ ኦነጎች እባካችሁ ታላቁን የኦሮሞ ህዝብ በአለም ፊት በነፍሰ ገዳይነት አታስፈርጁት፤ ያለንበት አለም የተሠራ ቀርቶ የታሰበ የሚጋለጥበት ነውና፡፡ ‘መሸጥ የለመደ እናቱን ያስማማል’ እንድሉ ጀግኖች የኦሮሞ ልጆች ከሌሎቹ ኢትዮጵያዊያን ጋር ሆነው በደም በአጥንታቸው የገነቧትን ሐገር፤ መርዳት ቢያቅታችሁ ለጠላቶቿ ገበያ ላይ አታውጧት፡፡ ተመልሳችሁ የፖለቲካውን ውሐልክ ለክታችሁ ክቀድዳችሁት ታሪካችሁን አድሳችሁ ልታልፉ ትችላላችሁ፤ መቃብር አፋፍ ላይ ቆማ ከምትቆዝም ሕዋሕት ጋር እንደ አድስ የተጀመረው ጋብቻ ብዙ ደም ሊያፈስ ይችል ይሆናል፤ የ ዶ/ር አብይ አላማ ከመፈጸሙ አይቆምም፡፡ በግፍ ስለሚፈሰውም ደም እግዚአብሔር ዝም አይልም፡፡

Filed in: Amharic