>

ፖለቲካ እውነትም ሸር…ጣ  ነው! (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

ፖለቲካ እውነትም ሸር…ጣ  ነው!

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ


ሐሙስ ሰኔ 25 ቀን 2012 ዓ.ም (በሀጫሉ ግድያ ሰበብ የተዘጋው ኢንተርኔት እንደተለቀቀ የሚላክ)

ይህችን ወረቀት በመዝገብ ስሜ ብጽፋት ደስ ባለኝ፡፡ ግን ለዚያ አልታደልኩም፡፡ ትንሸ ይቀረኛል፡፡ የዕድሜ ሣይሆን የአጋጣሚ ነገር ሆኖ “በወጣትነቴ ካልተቀጨሁ” በስተቀር ያንን ወርቃማ ጊዜ እደርስበት ይሆናል፡፡ ለማንኛውም “SAF” በሚል የደሞዝ የስም ዝርዝር ይያዝልኝ፡፡ ጭላንጭል ይታየኛል፡፡…

በሰው ሞት የሚደሰት ሰው፣ ሰው መሆኑ ያጠራጥራል፡፡ ጠላቴ የምለው ሰው ቢሞት በባህላችን ምሥጥ ሆኜ እንደማልበላው መገለጡ ትልቅ ቁም ነገር ያለው መሆኑ እንዳለ ሆኖ በሃይማኖቴ “ጠላትህን ውደድ” መባሉ ራሱ እንደሰውኛ ስሜት በማልወደው ሰው ሞት እንዳልደሰት ገደብ ይጥልብኛል፡፡ ስለዚህ የሚገድለኝን ሰው ራሱ ከአግባብ ውጪ በዘፈቀደና አለፍትህ እንዲሞት በፍጹም አልፈልግም፡፡

ስለሆነም የሀጫሉ ሁንዴሳ ያልጠተበቀ ሞት እጅግ ያሳዝነኛል፤ ያመኛልም፡፡ ሀጫሉ ኦሮሞነቱን ማስቀደሙ መብቱ ነው፡፡ እኔም ኢትዮጵያዊነቴን ማስቀደሜ መብቴ ነው፡፡ ሀጫሉ የኔን መብት ከተጋፋ፣ እኔም የርሱን መብት ከተጋፋሁ ችግር መፈጠሩ አይቀርም፡፡ ሀጫሉ የኔን መብት መጋፋቱ በገሃድ የተመሰከረ ቢሆንም እኔ ግን የርሱን መብት በመጋፋት ለመስዋዕትነት እንደማልዳርገው ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል፡፡ እኔ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ሀጫሉ “እንዲህ አለ፤ እንዲያ አለ” በሚል ሰበብ ልገድለው ይቅርና ዝምቡን እሽ እንደማልለው ሰማይም ምድርም ሊያውቁ ይገባል፤ ጠንቅቀው ያውቁማል፡፡ እርሱን በመግደል ሃሳቡን መግደል እንደማይቻል ስለምገነዘብ ብቻ ሣይሆን ሀጫሉ በሕይወት ኖሮ ከስህተቱ እንዲማርና ሰው እንዲሆን ከመመኘት ባለፈ ይህን መሰል የጭካኔ ተግባር በርሱ ላይ እንዲፈጸም በጭራሽ አልፈልግም፡፡ ይህን ዕኩይ ተግባር ሊፈጽም የሚችል ትልቅ ዓላማና ተልእኮ ያነገበ አካል ብቻ ነው፡፡ 

የሆነ ሆኖ የሆነው ሆነ፡፡ ለምን የሆነው እንደሆነ ትልቅ ሰው ይቅርና ጡት ያልጣለ ሕጻንም ያውቃል፡፡ ጡት ያልጣለ ሕጻን ስል እነሕዝቅኤል ጋቢሳንና ፀጋየ አራርሳን አይጨምርም፡፡ምክንያቱም እነሱ ገና አልተወለዱምና፡፡ ባይወለዱም በተሻላቸው፡፡ የይሁዳ ዕጣ የነሱም ነውና አለመወለዳቸው ይበልጥ እንደሚጠቅማቸው የፊታችን ጊዜ ታላቅ ምሥክር ነው፡፡ ከነሱ ይልቅ የሂትለር መጨረሻ በስንት ጣሙ!

ሀጫሉን አማራ አይገድለውም፤ 99.9 በመቶ እርግጠኛ መሆን እችላለሁ፡፡ 0.09 በመቶ የተውኩት የእግዚአብሔርን ቦታ ላለመሻማት ነው፤ እርሱ ብቻ ነውና ፍጹም፡፡ “ሀጫሉን አማራ ወይም ነፍጠኛ ገደለው” የሚለው ድራማ ከወንዙ በላይ በኩል ሆኖ እየጠጣ እያለ ከወንዙ ታች ሆና እየጠጣች የነበረችውን አህያ “ውኃውን አታደፍርሽብኝ!” ብሎ የተቆጣውን የአያ ጅቦን ታሪክ ያስታውሰኛል፡፡

አማራ እንኳንስ እስከመፈጠሩ የማያውቀውን ሀጫሉን በተቀነባበረ ሁኔታ ሊገድል ይቅርና በጉያው አቅፎ የሚያኖራቸውን ብአዴን ተብዬዎቹን በፊት የወያኔና አሁን የኦህዲድ አሽከሮች ከነመፈጠራቸውም አያስታውሳቸውም፡፡ አትታዘቡኝና አማራ ልክ እንደማንኛውም ‹ቤርቤረሰብ› ሁሉ መግደል የማይችል ሆኖ አይደለም – ግን ገና “አልተፈቀደለትም”፡፡ እስኪፈቀድለት መጠበቅ ግን ጅልነት ነው፡፡ አማራ ሁሉን ነገር ለፈጣሪው ሰጥቶ ፍርዱን ከላይ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡ እነአጅሬ ጃዋር ግን ከጥምር አለቆቻቸው በወረደላቸው ትዕዛዝ መሠረት በተጠና መልክ ድራማቸውን ካቀነባበሩና ካከናወኑ በኋላ “የነፃነት ታጋያችንን ነፍጠኛ ገደለብን” በማለት እሪታቸውን አቀለጡት፡፡ በሰበቡም የፌዴራል መንግሥቱን ገልብጠው በሮማንያው የቻውቼክስኮ ወንበር አወዳደቅ ሥልት በሀጫሉ የቀብር ሥነ ሥርዓት ሰበብ በአክራሪ ቄሮ የጦዘ የስሜት ግለት አራት ኪሎን በመቆጣጠር ሥልጣን ለመያዝ ቋመጡ፤ በእግረ መንገድም ሁለቱን ታላላቅ ሕዝቦች ለማጨራረስ የሲዖል በሮችን ሁሉ ከፋፈቱ፤ ግን በብዙ መስዋዕትነት ከሸፈ፡፡ መማር ለሚፈልግ ማንኛውም ወገን ይህ ጊዜ ከምንምና ከማንም በላይ አስተማሪ ነው፡፡ ቢያንስ አሁንና ለጊዜው እነጃዋር የፈለጉት አልተሳካም፡፡ ነገ ደግሞ ማንን የአብርሃም በግ እንደሚያደርጉ አድረን የምናየው ይሆናል፡፡ የመቀሌ፣ ካይሮና ኦኤምኤን(ኦነግና ግብረ አበሮቹ) የሦስትዮሽ ውል ግን እንዲህ በቀላሉ እንደማይተወን ልብ ማለት ይገባል፡፡ ፈጣሪ ይሁነን፡፡

ወደ ዋናው ሃሳቤ ልግባ፡፡ ፖለቲካ ሸርሙጣ ነው የሚባለው በጣም አውነት ነው፡፡ ሸርሙጣ እንዲያውም ከፖለቲካ እጅግ ትሻላለች፡፡ ያለፍኩበት ስለሆነ እኔም ምስክሯ ነኝ፡፡ ገንዘብ ከፍያት አብሬያት ላድር ከተስማማሁ “ተይዣለሁ” ትላለች እንጂ የፈለገውን ያህል ልክፈልሽ ቢላት ለገንዘብ ብላ በሌላ ሰው አትለውጠኝም ነበር፤ የዛሬዋን አላውቅም፡፡ ስለዚህ ሴተኛ አዳሪን ከፖለቲካ ሸርሙጦች ጋር አናወዳድር፡፡

የዘንድሮው  ፖለቲካ በተለይ ዐይን ያወጣ ሸርዳጅና አሽሙረኛ፣ አስመሳይና ቀጣፊ ነው፡፡

ከጠ/ሚኒስትር እስከ ቀበሌ መስተዳድር አንዱ የሌላውን፣ የታችኛው የላይኛውን የስሜት ፍሰት እየተከተለ ማስመሰሉንና መመሳሰሉን ተያይዞታል – ላንዲት እንጀራ ሲባል፡፡ አክራሪ ኦሮሞን ለማስደስት በሚመስል ሁኔታ አንድን ተራ ግለሰብ ከንጉሠ ነገሥት በላይ በመሾም ሰይጣን ራሱ እስኪታዘብና በሣቅ እስኪፈርስ ድረስ አዳሜ ማሽቃበጡን ተያይዞታል፡፡ ሀጫሉም ትልቅ ሰው ሆኖ በርሱ ሞት ሀገር ምድሩ “በፍቅሩ እየተቃጠለ” ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነትን የሚያስጠላ ትዕይንት እየታዘብኩ እኔም በመቃጠል ላይ ነኝ፡፡

ቲቪውና ራዲዮው ሁሉ ሌላ ሥራ የለውም፡፡ ፕሮግራሙን ሁሉ አጥፎ ሁሉም ሚዲያ በመኮራረጅ የሀዘን ማቅ ለብሷል፤ ሙዚቃውም ሁሉ የሀዘን ነው፡፡ የአማራው ቲቪ ሳይቀር ምን ይሉኝን እርግፍ አድርጎ ትቶ ከል ለብሶ እያለቀሰ ነው፡፡ ላለውና ለባለጊዜ ማሸርገድ ማለት እንዲህ ነው፡፡ የስንት ውድ ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት ደመ ከልብ ሆኖ ለማስታወሻነት አንዲትም ሰባራ ሣንቲም ሳይወጣላቸው ለዚህ ልጅ ግን ከመንገድ እስከ ትምህርት ቤት፣ ከመናፈሻ እስከ ሀውልት … ምኑ ቅጡ … “ለኢትዮጵያ አንድነት እስከኅልፈተ ሕይወቱ” ለታገለው ለዚህ ልጅ ዝክረ ሰማዕት ሊሠራለት የመሠረት ድንጋዩ በየቦታው እየተጣለ ነው፡፡ እውነት ከኢትዮጵያ ኮበለለች፤ ማስመሰልና ማጎብደድ በምትኳ ደረታቸውን ነፍተው እየተንጎማለሉ ነው፡፡ ይብላኝ ለታሪክ – ይህን ሁሉ ጉድ ለሚታዘብ፡፡

ለማንኛውም ሀጫሉ በሞቱ ከበረ፤ በመገደሉ ነገሠ፡፡ ይህን የምለው የሀጫሉ ሬሣ ሥራ ማስፈታቱና ለበርካታዎች ሞትና የንብረት ውድመት ምክንያት መሆን አስቀንቶኝ አይደለም – በጭራሽ፡፡ ሞት አያስቀናም፡፡ ግን ለአንድ ሕዝብን ከፋፋይ ዜጋ ይህን ያህል ማሸርገዱና ለበርካታ ቀናት ብሔራዊ ሀዘን ማወጁ የሥሙኒ ዶሮ የብር ገመድ ይዛ እንደጠፋቸው ዓይነት ምሣሌ በመሆኑ ከዛሬ ይልቅ ነገን ይበልጥ እንድንፈራው ያደርጋልና ሀዘናችንን በቅጡ እንድናደርገው የሀጫሉ አስተዛዛቢ ክስተት ሊያስተምረን ይገባል፡፡ ይሄኔ በኮሮና ወይም በመኪና አደጋ ቢሞት ኖሮ ከአሥር ደቂቃ ያላለፈ የሚዲያ ሽፋን ባላገኘ ነበር፡፡ ግን ግን እንዴት ያለ አስመሳይ ወጥቶናል እባካችሁ! ሁሉም የሆዱን በሆዱ ይዞ “ሀጫሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋልታና ማገር፤ ኢትዮጵያ በጭንቋ ጊዜ ያጣችው ብቸኛ አንጡራ ሀብት… ቲሪሪም ቲሪሪም…” ሲባል እኔ በውነቱ በሀፍረት ተሸማቀቅሁ፡፡ ሁሉም ከል ለብሶ ስመለከት የመለስንና የኪም ኢል ሱንግ ልቅሶ አስታወሰኝ፡፡ እንዲያውም የርሱ ከነሱ በለጠ፡፡

ተመልከት! “ሀጫሉ ለብሔር ብሔረ ሰቦች እኩልነት የታገለ ድንቅ አርቲስትና የሰብኣዊ መብት ተሟጋች ነበር! ሀጫሉ ለኦሮሞ ብቻ አልነበረም የታገለው – ለሁሉም እንጂ” ሲል ይቀደዳል አንዱ፡፡

ሀጬኮ ደግሞ እንዲህ ይልልሃል፡- “የኦሮሞ ጠላት ዱሮም ሆነ አሁን፣ ወደፊትም ሆነ ወደኋላ አማራና አማራ ብቻ ነው! ምኒሊክ በአህያ መጥቶ የሲዳ ደበሌን ፈረስ ቀምቶ ባለፈረስ ሆነ…፡፡”

ምን ማለት ነው?  ሚዲያዎች ምን እያሉ ነው?  ባለሥልጣናት ምን እያሉ ነው? አቢይ ምን እያለ ነው? አሸርጋጁ ደመቀ መኮንንስ ምን እያለን ነው? ስንት ሽህ ዓመት ሊኖር ነው እንደዚህና እስከዚህ ለማስመሰል መሞከሩ? ኅሊናችን ምን ይታዘበን? ለውሸት ለምን ለከት አይኖረውም? በስመ አብ!!

አቢይ በውሸት ቆርቦ በውሸት ይህችን ምድር ለመሰናበት የቆረጠ ይመስለኛልና ግዴለም፤ እሱን አንቀየመውም – ተፈጥሮን ደግሞ ተመክሮ አይለውጠውም፤ እሱም እኛም አልታደልንም በዚህ ረገድ፡፡ እንጂ ለምሣሌ ከየትኛው ጊዜው ቀንጭቦ ነው የሀጫሉ የረጂም ጊዜ ጓደኛ ሊሆን የሚችለው? – እርሱ እንደተናገረው ማለቴ ነው፡፡ አቢይና ሀጫሉ የረጂም ዘመን ጓደኛሞች ሊሆኑ የሚችሉበት ሁኔታ ከፖለቲካ ፍጆታ ባለፈ ሊታየኝ አልቻለም፡፡ የዕድሜ መበላለጡን አስቡት፤ የሙያ አለመመሳሰሉን ጨምሩበት፤ የፖለቲካ ጎራ ልዩነትን አትርሱ፤ የአቢይን ከዱሮ ጀምሮ በሥራና በትምህርት መወጣጠር አትዘንጉ፤ እናሳ! ጓደኝነታቸው በስልክና በኢሜል ይሆን? ታውቃለህ – ግነት ለከት ሲኖረው ያምራል፡፡ ወይ አቢይሻ!

ሀጫሉ የኢትዮጵያ ነፃነት ታጋይ እንዳልሆነና እንዳልነበረም የቀብሩ ሥነ ሥርዓት ራሱ በግልጽ ነግሮናል፡፡ አስከሬኑ የለበሰው ባንዲራ የግብጽን እንጂ የኢትዮጵያን አልነበረም፡፡ ለሀጫሉ ፀረ-ኢትዮጵያዊነት ይህ ብቻውን በቂ ምስክር ነው – እንዲህ መናገሬ መረር እንደሚል አውቃለሁ፡፡ በቀብሩም ወቅት ልቅሶው ሁሉ ኦሮሞ ኦሮሞ የሚል ቅኝት ይበዛበት ነበር፡፡ ያም ከንቱነት ነው፡፡ ሲጀመር ሀጫሉ ሰው እንጂ ኦሮሞ አይደለም ወይም አልነበረም፡፡ ከሰውነትም ሲያንስ ኢትዮጵያዊ ነበር – ቢያድለው፡፡ ከዚያ አንሶ ኦሮሞ ኦሮሞ ማለት ግን ከእንስሳም ማነስ ነው፡፡ አንድ ሰው ወደ ነገድ ደረጃ ወርዶ ከዘቀጠ ኅሊናው ይታወራል፡፡ ከዘሩ ውጪም አያስብም፡፡ ከዘሩ ውጪ ያለው ሁሉ ሰው አይመስለውም፡፡ ይህን በአክራሪ ኦሮሞዎች የሚስተዋል የዘረኝነት አዝማሚያ ከአክራሪ ትግሬዎች ውጪ በሌሎች ብዙም አናይም፡፡ ለምሣሌ አያርግበትና አቶ እርገጤ ቢሞት “አማራው እርገጤ፣ አማራው እርገጤ፣ ውይ ዋይ ዋይ አማራው እርገጤ” እየተባለ አይለቀስም – አልተለመደም፡፡ “ጅግናው አማራ አቶ እርገጤን በዛሬው ዕለት ተነጠቀ! ወይ የአማራ አለመታደል! ዕድለቢሱ አማራ፣ አቶ እርገጤን በዛሬዋ ዕለት ኦነግ/ኦህዲድ ቀጠፈው…!” እየተባለ ቢለቀስ ልቅሶው እንዴት ወደሳቅ እንደሚለወጥ ይታያችሁ፡፡ 

ትንሽ ሰው ምን ጊዜም ትንሽ ነው፡፡ የርሱ ትንሽነት ብቻውን ምንም አይደለም፡፡ ግን አንሶ ያሳንሳል፡፡ ለምሣሌ እኔን፡፡ እንጂ በዘረኝነት ልክፍት አብደው እንደነዚህ ያሉት ራሳቸው አንሰው ሌላውን የሚያሳንሱት እነ “ፕሮፌሰር” ሣጥናኤል ማነው ሕዝቅኤል ከድንችና ከካሮትም አንሰው በአሁኑ ሰዓት አማራንና ኦሮሞን ለማፋጀት ምን እያደረጉ እንደሆነ እያየንና እየሰማን ነው፡፡ ሤራቸው ለጊዜው በመክሸፉ ወፈፌ ሆነዋል፡፡ ፈረንጆቹ እንደሆኑ ዋና ዓላማቸው ኢትዮጵያን ማጥፋት በመሆኑ ከ“አይዟችሁ፣ ግፉበት” በስተቀር፤ በገንዘብ፣ በሃሳብና በሞራል ከመደገፍ ባለፈ ምንም አይሏቸውም፡፡ ዓላማቸው ምን ሆነና!

እነአቢይ ግን በጀመሩት ቢገፉበት ቢያንስ ራሳቸውን ከጭዳነት ይታደጋሉ – ለውጥም እያሳዩ ነው፡፡ እነእስክንድርን በመናጆነት ማሰራቸው ግን አግባብነቱ በፍጹም አልታየኝም፡፡ ስለምንም አይደለም – ግን “ከአክራሪ የኦሮሞ ቄሮዎች ተጠበቁ” ብለው እንወክለዋለን የሚሉትን ማኅበረሰብ ማስጠንቀቃቸውና በቀላሉ ለጥቃት እንዳይዳረጉ ማደራጀታቸው ከማስመስገን አልፎ  እንደወንጀል ሊቆጠር እንደማይገባ እንኳንስ እኔ አሳሪዎቹ ራሳቸውም የሚረዱት ይመስለኛል፡፡ ግን ይሄ “ከዘር ልጓም ይስባል” የሚባል ነገር እየማረካቸው በስህተት ጎዳና መትመምን መርጠዋል – እንደወያኔ እስኪንኮታኮቱ፡፡ ይህ አካሄዳቸው በሌላ በኩል ሊያስደስቱት የሚፈልጉት ወገን መኖሩን ይጠቁማል፡፡ በስንቱ አርረንና ተክነን እንዘልቀዋለን ግን ጎበዝ! 

ትልቁ ነጥብ አሁን በተያያዝነው የዘር መሥፈርትና የዘረኝነት ፖለቲካ የትም አንደርስም፡፡ ኢትዮጵያ ከሙታን መንደር እንድትነሣ ከፈለግን የትምህርት ደረጃ፣ የሙያ ብቃትና ልምድና ችሎታ ዋና መሥፈርት ሊሆኑ ይገባል፡፡ የ8ኛ ክፍል ምሩቅ ሚልኬሣ ሥራ አስኪያጅ ሆኖ የማስትርስ ዲግሪ ምሩቅ ዘበርጋ ዘበኛ ከሆነ፣ አሥር አለቃ ሐጎስ በሚመራው የሻምበል ጦር ሻለቃ ዘበርጋ የግምጃ ቤት ኃላፊ ከሆነ፣ የዲፕሎማ ምሩቁ ስንሻው በርዕሰ መምህርነት በሚመራው ኮሌጅ የፒኤችዲ ምሩቁ ኡጁሉ ምክትል ዲን ከሆነ … አደጋ አለው! ዕውቀት በዘር ተረገጠ፤ እውነት በዕብለት ዕድገትም በውድቀት ተሸነፈ፡፡ በሀገራችን እየሆነ ያለው ይሄው ነው፡፡ Meritocracy should be reinstated, ASAP

Email: ma74085@gmail.com.

Filed in: Amharic