>

ፓርቲን የምትሸጡ ሰዎች እባካችሁን ለጤነኛ ሰው ሽጡ! አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ)

ፓርቲን የምትሸጡ ሰዎች እባካችሁን ለጤነኛ ሰው ሽጡ!

አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ)


ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና በጣም ከሚያሳዝኑኝ ሰዎች የስም ዝርዝሬ ውስጥ ከገባ ሰነበተ፡፡ የዘረኝነት ልክፍት መጥፎ ነው፤ እግዜር ይይለት ይህን በሽታ፡፡ እንዴት እንዴት ያሉ ሰዎችን እየቀማ በቁም እየገደለብን በመሆኑ ዘረኝነትን ጌታ ይንቀልልን፡፡ አሜን ነው – አሜን!

ለማንኛውም እባካችሁን የፖለቲካ ፓርቲዎች ሆይ! ፓርቲያችሁን ስትሸጡ ወይም ሰዎችን በአባልነት ስታስገቡ በገንዘብና በዝና ፍቅር ናውዛችሁ አይሁን፡፡ መርኅ ይኑራችሁ፡፡ ገና ለገና ፓርቲያችሁንና ኪሳችሁን በገንዘብ ያወፈራችሁ መስሏችሁ የሀገርና የሕዝብ ነቀርሣ ሸምታችሁ ራሳችሁንም ፓርቲያችሁንም አታውድሙ፡፡ ለዚህ እኮ ነው በአንዲት ድሃ አገር ውስጥ 100 ምናምን ፓርቲ ያቆማችሁት! የቤተሰብ አባላቱን ብቻ ያቀፈ ፓርቲም እንዳለ ለቀልድም ይሁን ከምር ይወራል፡፡ አሣፋሪ ማኅበረሰብኣዊ ቅርጽና ይዘት ላይ እንገኛለን፡፡ እንዴት እንደምንስተካከል እንጃ፡፡

ኦፌኮ የሞተው ጃዋርን በተቀበለ ወቅት ነው፡፡ መራራ የሞተው በስንት ልፋትና ድካም እንዲሁም መስዋዕትነት በክፉ ቀን መሥርቶ ያቆየውን ኦፌኮን ለማይረባ ምድራዊ ሀብት የሸጠ ዕለት ነው፡፡ ሴትዮዋ “እንዲህ ልጠግብ በሬየን አረድኩ” አለች ይባላል፡፡ ሰው ጠባቂና ጦም ጧሚ አንድ መሆናቸው የሚነገረውም ከዚሁ ጋር ይመሳሰላል፡፡ መራራ በሕዝብ ተወዳጅ ነበር፡፡ ነገር ግን በጊዜ ሂደት ምን እንደነካው አይታወቅም ይሄ የዐረብ የነዳጅ ገንዘብ በጃዋር ተመስሎ አማለለው መሰለኝ ክብሩንም ዝናውንም መሬት ደፍቶ ለአንድ የመናዊ የዐረብ ጀማላ ተንበረከከና የነበረውን ማኅበራዊ ከበሬታና ግርማ ሞገስ (ሶሻል ካፒታል) ለገንዘብ ሲል ጎማምዶ ጣለው፡፡ አሁን በሚያሳዝን ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ይመስላል፡፡ አዎ፣ “ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ …” በሚል ነባር ብሂል ሊገለጽ የሚችል  ሣንካ ሳይገጥመው አልቀረም – መራራን፡፡ ወደሽ ከተደፋሽ ነው ….ነገሩ፡፡

ጃዋርም ፍየል ከመድረሷ እንዲሉ በአባልነት የተመዘገበበት ፓርቲ ውስጥ ገና የፊርማ ወረቀቱ ሳይደርቅ ፓርቲውን በአንድ ጀምበር ወደ አሸባሪነት ለውጦ በሽዎች የሚቆጠሩ አማሮችን አስፈጀ፤ በቢሊዮን የሚገመት ብር የሚያወጣ ሀብት ንብረትም አወደመ፤ በሽዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን ከሥራና ከኑሮ አውጥቶ ለስቃይ ዳረገ፡፡ ከዚህ በላይ ዕብደትና መንግሥት አልባነት የለም፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በብዙ አቅጣጫ እንዲሰቃዩና የደም ዕንባ እንዲያነቡ ሰማይና ምድር አንዳች ውል ሳይፈራረሙ አልቀሩም፡፡ አጥብቀን እንጸልይ! በድርብርብ ኮረናዎች ተወርረናል፡፡

የፌዴራል ተብዬው መንግሥትም ቅኝት በሌለው አስተዳደሩ እርጥቡን ከደረቅ፣ በጎውን ከክፉ እያዛነቀ ማሰር ማንገላታቱን ቀጥሏል፡፡ የበደለው ሌላ – የሚያስርና የሚገርፈው ሌላ፡፡ በአንድ ጎሣ አመራር የሚሽከረከረው መንግሥት በቀላሉ ወደማይወጣው ቀውስ እየገባ ነው፡፡

የማንም ፓርቲ አባል አይደለሁም፡፡ አጋነንክ አትበለኝና ራሴን ከእውነት ውጪ የማንም እስረኛ ማድረግ አልፈልግም፡፡ የየትኛውም ፓርቲ ወይ ድርጅት አባል መሆንን ያልፈለግሁትም ምናልባት – ከፍርሀቴ በመለስ – ለዚህ ይሆናል፡፡ ከዝንጀሮ ቆንጆ … ዓይነት ነው ዙሪያ ገባው ሲታይ፡፡

የእስክንድር ነጋ የወያኔና የነጃዋር ተባባሪነት በፍጹም ግራ አጋቢ ነው፡፡ እስክንድር እኔ የማላውቀው ሥውር ስብዕና ከሌለው በስተቀር ከጃዋርና ከግብጽ ጋር በመተባበር የንጹሓን ዜጎችን ደም የሚያስፈበት፣ የድሆችን አለኝታ ሀብትና ንብረት የሚያወድምበት የሞራል መደላድል አለው ብሎ ማመን አስቸጋሪ ነው፡፡ የሥልጣን ሱስ የፈለገውን ያህል ቢያሰቃየው እንኳን (ሥልጣን ወዳድ ነው አላልኩም!) እስክንድር ከቄሮ ጋር ተባብሮ ህዝብን በገጀራና በቆንጨራ ፍጁ ብሎ የሚያዝበትና ወጣቱን የሚያደራጅበት  ሞራል ይኖረዋል ብዬ በጭራሽ አላምንም፡፡ ይህ ክስተት የመንግሥትን ምንነት ከማሳየት የዘለለ ትርጉም የለውም፡፡ ዐይን አይቶ ልብ ይፈርዳል፡፡ ሕዝብን እስከዚህ መናቅም ተገቢ አልነበረም ከመነሻው፡፡ በከንቱ ደከሙ፡፡

የአቢይና የአዳነች አቤቤ የኦሮሙማ መንግሥት በካፈርኩ አይመልሰኝ እያደረገ ያለው ነገር እጅግ አስገራሚ ነው – አንዱን ለማስደሰት ሲል ሌላውን ለማስከፋት የሚጓዝበት ቅጥ የለሽ ርቀት በሌላ ዘመን እጅግ አስተዛዛቢ መሆኑ ከአሁኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ አንድ ሰው ወይም አንድ አካል ሶበር ከማለት ይልቅ በዚህ መልክ አጋጣሚዎችን እየጠበቀ ጠላቴ ነው ብሎ የፈረጀውን ሰው የሚያጠቃ ከሆነ ከድጥ ወደ ማጥ ለመሄዳችን ትልቅ ማሳያ ነው – ትምህርት የሚገኘው በግድ ከትምህርት ቤት ብቻ መሆን የለበትም – ከግል ገጠመኞችና ከአስከፊ ማኅበራዊ ተሞክሮዎችም መማር ይቻላል፡፡ በግላጭ ባገኙት ሥልጣን ሰክረው  የሚያደርጉትን ያጡት ነብራራዎቹ አዲሶቹ ወያኔዎች ግን ካለፈና ከአሁን ተሞክሮ ግንዘቤ ወስደው ከውድቀት ለመዳን የሚያስችላቸውን አሁን የሚገኙበትን የገደል አፋፍን በአስተማሪነቱ የመጠቀም ሣይሆን ከገቡ በኋላ የማይወጡበትን እንጦርጦስን እየጠበቁ ይመስላሉ – ያ ደግሞ ለማንም አልበጀ – ለደርግም፣ ለሕወሓትም ይሄኛው የዕብሪትና የትምክህት መንገድ አልጠቀመም፡፡ እነአቢይ ከሁኔታዎችና በሁኔታዎች ሊማሩ የማይችሉ ግብዞችና ሥልጣን ወዳዶች መሆናቸውን ከተገነዘብኩባቸው ነገሮች አንዱ ይሄው “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” ዓይነት የነእስክንድርና የነኢንጂኔር ይልቃል እሥራትና ወከባ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለፖለቲካቸው ይጠቅመናል ብለው እስካሰቡ ድረስ የማይጠቀሙት የፕሮፓጋንዳ ዘዴ የሌላቸው መሆኑ ራሱ እጅግ አደገኛና መሠሪነትን የተላበሰ ነው – ለአብነት ሀብታሙ አያሌው እንደገለጸው አቡዬ የተባለ የቡና ይሁን የሻይ ክለብ ደጋፊ የእግር ኳስ አፍቃሪ ሀጫሉን እንደገደለ አድርገው የቀድሞዋን የኢትዮጵያ ባንዲራ አልብሰው በሚዲያ ማቅረባቸውና በኋላ ደግሞ እውነተኛ ገዳዮች ተገኙ ብለው ማወጃቸው ሰዎቹ በ“የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጭው” ዓይነት የሥልጣን ማቆያ ሥልት የተጠመዱ ለመሆናቸው ወቅቱን የጠበቀ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ ሰዎቹ ለውሸታቸው አንዳች ልጓም ካልተፈለገላቸው ጉድ ሳያደርጉን አይቀሩም፡፡ እነዚህ ውሪ ባለሥልጣናት የፈለጉትን ያህል ዘረኞችና ሥልጣን ወዳዶች ቢሆኑም ይህን መሰል ቅሌት ውስጥ መግባት አልነበረባቸውም፡፡ አሣፋሪ ነው፡፡ የነበረቻቸውን ጭልጭል የምትል ሕዝባዊ አመኔታ ከናካቴው የሚያደበዝዝና የሚያጠፋም ነው፡፡ አመኔታ ደግሞ ትልቅ አሤት ነው፤ ከጠፋ በቀላሉ አይመለስም፡፡ በአጭሩ ዘረኞቹ እየተምቦዣቦዡ ናቸው፡፡ ምክርና ተግሣፅ የሚቀበሉ አይደሉም፡፡ የራስ ፍቅርና የሥልጣን አራራ አነሁልለዋቸዋል፡፡

ፓርቲ የምትሸጡ ሆይ! ወደ እናንተ ተመለስኩ፡፡ እባካችሁን ስትሸጡ ትርፍን ብቻ ሳይሆን የሽያጩን የጎንዮሽ ጉዳትም ለማጤን ሞክሩ፡፡ ጉዳቱ ዛሬ ላይደርስ ይችል ይሆናል፡፡ ጉዳቱ በእናንተ ላይ (ብቻም) ላይደርስ ይችል ይሆናል፡፡ ጉዳቱ በገንዘብ ሲ(ቢ)ተመን ምንም ላይሆን ይችላል፡፡ ግን ግን በሀገርና በሕዝብ ታሪክ ላይ የማይፋቅ የታሪክ ጠባሳ ሊያስከትል ይችላልና ተቻኩላችሁ ለማይሆን ወፈፌ አትሽጡ፡፡ ከኦፌኮም ተማሩ፡፡ መልካም ማድረግ ወጪ የለውም፤ ቀላል ነው፡፡ ክፉ ማድረግ ግን ምንም እንኳን በወጪ ደረጃ ከባድ ባይሆንም የዞረ ድምሩ ለራስም ይከፋልና እንጠንቀቅ፡፡ አይነጋ እየመሰለን የምንሠራው ክፋት ሁሉ ነገ ዞሮ እኛኑ ማሳደዱ አይቀርም፡፡ የዘራነውን ማጨድ ያለ ነውና የምንወረውረው ጦር ወደኛም እንደሚመለስ እንወቅ፡፡ ኮረብታው ላይ ቤት ሲቃጠል በደስታ ትቧርቅ የነበረችዋንና በኋላ ግን በባልዲ ተጨልፋ እሳቱን ማጥፊያ የተደገረችውን ነፈዝ ዕንቁራሪት እናስታውስ፡፡ በአያት ቅድመ አያቶቹ ኃጢኣት ሰበብ በአልሞት ባይ ተጋዳይ ፍየል ቀንድ ሆዱን ተዘርግፎ የሞተውን ነብርም አንርሣ፡፡

እግዚአብሔር ከኢትዮጵያ የጠፋውን ልብና አስተውሎት ይመልስን፡፡ የሀጫሉንና በርሱ ምክንያት እንዲሁም በነጃዋር ሤራ ሳቢያ የሞቱና ደብዛቸው የጠፋ ዜጎችን ፈጣሪ ያስብልን፡፡ በቃችሁ ይበለን፡፡ ካበዱ ቄሮዎችና እነሱን ከሚያዝዙ ኅሊናቢስ የግብጽ፣ የኦሮሞና የወያኔ የጥፋት አምባሣደሮች ሀገራችንን ፈጣሪ ይጠብቅ፡፡ አእምሮ ስንኩላን ባለሥልጣኖቻችንን ወደመስመር ያስገባልን፡፡ (ለምሣሌ አቶ አሰፋ አደፍርስ የተባሉ ዲያስፖራ በቅርቡ በደረጀ ኃይሌ “በነገራችን ላይ…” ዝግጅቱ የተናገሩት ቅስምን ይሰብራል፡፡ እንደዚያ ያለ ሚኒስትር ባለባት ሀገር እንደዜጋ ከመኖር ጭራሽ አለመወለድ ብዙ ዋጋ አለው፡ – ከጽድቅም ይቆጠራል … ወጣቱ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አሜሪካንን በጎበኘበት ወቅት ስልኩን ለሰውዬው ይሰጣል፡፡ ሰውዬው ሀገሬ ከሞት ተነሳች ብለው ወዳገር ይመለሱና ለሚኒስትር ተብዬው ይደውላሉ፤ ቢሮው እንዲመጡ ይነግራቸውና ይገናኛሉ፡፡ “አሁን ሥራ ይበዛብኛል” ብሎ ሌላ ጊዜ እንዲደውሉለት ይነግርና ያሰናብታቸዋል፡፡ በወሩ ገደማ ይደውሉለታል፡፡ ያኔ “ከአሜሪካ መጣህ ማለት ከስፔስ መጣህ ማለት እኮ አይደለም፤ በል ሁለተኛ እንዳትደውል” ብሎ  ስልኩን ጆሯቸው ላይ ይጠረቅምባቸዋል፡፡ በቢሊዮን የሚገመት ኢንቬስትመንትም ሀገራችን አጣች፡፡… እንዲህ ነን ኢትዮጵያውያን! ታዲያ ኮራ ብለን እናጨብጭባ! የዚህ ዓይነት ሹማምንት ጌቶች ያልኮራን ማን ይኩራ፡፡ ከገመናዎቻችን አንዱ ልክ አሁን ትዝ ብሎኝ ነው … ከዚህም የባሱ ጉዶች ባለቤቶች ነን፡፡) 

Filed in: Amharic